በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሎሚ—ሁለገቡ ፍሬ

ሎሚ—ሁለገቡ ፍሬ

ለመድኃኒትነት፣ ለጽዳት አገልግሎት፣ ጀርሞችን ለመግደልና ውበትን ለመጠበቅ ያገለግላል። ልትበላው፣ ጨምቀህ ልትጠጣው እንዲሁም ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት ለማውጣት ልትጠቀምበት ትችላለህ። ሲያዩት የሚያምር ከመሆኑም በላይ በሁሉም የዓለም ክፍሎች ይገኛል፤ ዋጋውም ቢሆን ርካሽ ነው። አሁን ራሱ ቤትህ ውስጥ ሊኖር ይችላል። ይህ ነገር ምን ይሆን? ሎሚ ነዋ!

ሎሚ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በደቡብ ምሥራቅ እስያ እንደሆነ ይገመታል። ከዚያም ቀስ በቀስ ወደ ምዕራብ እስከ ሜድትራንያን አካባቢዎች ተሰራጨ። የሎሚ ዛፍ መካከለኛ ሙቀት ያለው የአየር ንብረት ይስማማዋል፤ እንደ አርጀንቲና፣ ጣሊያን፣ ሜክሲኮና ስፔን ባሉ አገሮች ሌላው ቀርቶ በአንዳንድ የአፍሪካና የእስያ አገሮች በጥሩ ሁኔታ የሚያድገው በዚህ ምክንያት ነው። ፍሬ ለመስጠት የደረሰ አንድ ዛፍ እንደ ዘሩ ዓይነትና እንዳደገበት አካባቢ በዓመት ከ200 እስከ 1,500 የሚደርስ ፍሬ ሊያፈራ ይችላል። በማሳ ላይ የሚለሙ የሎሚ ዛፎች በዓመት ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ስለሚያብቡ ዓመቱን ሙሉ ምርት መሰብሰብ ይቻላል።

በጣሊያን ምድር ተሰራጨ

በጥንቷ ሮም የነበሩ ሰዎች ሎሚ ያመርቱ ነበር የሚለው ጉዳይ አወዛጋቢ ነው። ይሁንና ሮማውያን ሲትረን ስለተባለው መጠኑ ትልቅ የሆነ የሎሚ ዝርያ ያውቁ እንደነበር የሚጠቁም ሰነድ አለ። ሮማዊ የታሪክ ምሁር የሆነው ትልቁ ፕሊኒ ናቹራል ሂስትሪ በተባለው መጽሐፉ ላይ ስለ ሲትረን ዛፍና ስለዚህ ዛፍ ፍሬ በቀጥታ ጠቅሷል። ይሁን እንጂ እውቅ የሆኑ ሊቃውንት፣ ሮማውያን ስለ ሎሚ ጭምር ያውቁ እንደነበረ ያምናሉ። ለምን? ምክንያቱም በጠጠር በተሠሩ ወይም ግድግዳ ላይ በተቀረጹ በርካታ ምስሎች ላይ የሚታዩት የሎሚ እንጂ የሲትረን ፍሬዎች አይደሉም። በፖምፔ በተደረገ ቁፋሮ የተገኘን አንድ ቪላ እንደ ምሳሌ መጥቀስ እንችላለን፤ የተክሎች ቤት (ኦርቸርድ ሃውስ) የሚል ተስማሚ ስያሜ የተሰጠው ይህ ቤት ግድግዳዎቹ የሎሚ ዛፍን ጨምሮ በተለያዩ የዕፅዋት ሥዕሎች አጊጠዋል። እርግጥ ነው፣ በዚያ ዘመን ሎሚ በደንብ ስለማይታወቅ የሚጠቀሙበት ለመድኃኒትነት ብቻ ሊሆን ይችላል። በዚያን ዘመን የሎሚ ዛፎችን የማሳደጉ ሥራ ቀላል ወይም ከባድ እንደነበር ማወቅ አዳጋች ነው፤ በተጨማሪም ይህ ፍሬ ምን ያህል ተስፋፍቶ እንደነበር በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም።

ረዘም ያለ በጋና ከባድ ያልሆነ ክረምት ያላት የሲሲሊ ደሴት እንደ ሎሚ፣ ብርቱካንና ኮምጣጤ የመሳሰሉ ፍራፍሬዎች ዋነኛ አምራች ናት። ይሁን እንጂ በሌሎች ቦታዎች በተለይም በባሕር ዳርቻዎች አካባቢ ጥራት ያለው ሎሚ ይመረታል።

ከኔፕልስ በስተደቡብ ውቧ የሶሬንቶ ከተማ የምትገኝ ሲሆን ከዚህች ከተማ በስተደቡብ ደግሞ የአማልፊ የባሕር ጠረፍ ተንጣሎ ይታያል። ይህ የባሕር ጠረፍ ከ40 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት አለው። አማልፊ፣ ፖዚታኖ እና ቪዬትሪ ሱል ማሬ በዚህ የባሕር ጠረፍ ላይ ከሚገኙ ውብ ከተሞች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። በሶሬንቶና በአማልፊ የባሕር ጠረፍ አካባቢ ሎሚ የሚመረት ሲሆን በሎሚዎቹ ላይ በአካባቢው መመረታቸውን የሚጠቁም ምልክት ይደረግባቸዋል። በዚያ አካባቢ ያሉ የሎሚ ዛፎች በደንብ ፀሐይ እንዲያገኙ ተደርገው በተራራው ላይ ባለ እርከን ስለሚተከሉ ፍሬዎቹ ጥሩ መዓዛና ብዙ ፈሳሽ አላቸው። በመሆኑም የአካባቢው ነዋሪዎች ምርታቸው በሌሎች ቦታዎች ከሚመረቱ ሎሚዎች እንዲለይ ማድረጋቸው ምንም አያስገርምም።

የሎሚ ዛፍ ለማሳደግ የግድ ሰፊ ቦታ አያስፈልግም። ድንክ የሎሚ ዛፎችን በዕቃ ውስጥ መትከል ስለሚቻል ፀሐይ እንደልብ በሚገኝበት በረንዳ ላይ በማስቀመጥ ለቤት ማሳመሪያነት መጠቀም ይቻላል። ዛፉ የፀሐይ ሙቀት እንደልብ በሚያገኝበትና ነፋስ በሌለበት ቦታ በተለይ ደግሞ ግድግዳ ተጠግቶ ቢቀመጥ የበለጠ ይስማማዋል። በክረምት ወራት ከባድ ቅዝቃዜ የሚኖር ከሆነ ግን ቤት ውስጥ መግባት ወይም መሸፈን ይኖርበታል።

ከምግብነት ያለፈ ጥቅም

ብዙ ጊዜ ሎሚ ትጠቀማለህ? አንዳንዶች ሻይ ውስጥ የተቆረጠ ሎሚ ያደርጋሉ። ሌሎች ደግሞ ኬክ ሲሠሩ የሎሚውን ፍቅፋቂ ወይም ጭማቂ ይጠቀማሉ። አንተ ደግሞ ሎሚ ጨምቀህ ከውኃ ጋር ደባልቀህ ትጠጣ ይሆናል። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የወጥ ቤት ሠራተኞች ሎሚን ለብዙ ነገር ስለሚጠቀሙበት ምንጊዜም ይህ ፍሬ ከአጠገባቸው አይጠፋም። ይሁን እንጂ ጀርሞችን ለመግደል ወይም ቆሻሻን ለማስለቀቅ የሎሚ ጭማቂ ተጠቅመህ ታውቃለህ?

አንዳንድ ሰዎች መክተፊያቸውን ለማጽዳትና ከጀርም ነፃ ለማድረግ መክተፊያውን በሎሚ ያሹታል። ሌሎች ደግሞ ቆሻሻ ለማስለቀቅ ወይም የዕቃ ማጠቢያቸውን ለማጽዳት ከበረኪና ይልቅ የሎሚ ጭማቂና ቤኪንግ ሶዳን አዋህደው መጠቀም ይመርጣሉ። በማቀዝቀዣ ወይም በዕቃ ማጠቢያ ማሽን ውስጥ የሚፈጠርን መጥፎ ጠረን ለማጥፋት የተቆረጠ ሎሚ ማስቀመጥ ብቻ ይበቃል።

ሎሚ፣ አንድ ምግብ ወይም መጠጥ ኮምጠጥ ያለ ጣዕም እንዲኖረውና ሳይበላሽ እንዲቆይ በሚያደርገው ሲትሪክ አሲድ የበለጸገ ነው። ፔክቲን የሚባለው ንጥረ ነገር በሎሚ ልጣጭና በውስጡ ባለው ነጭ ሽፋን ላይ የሚገኝ ሲሆን ይህ ንጥረ ነገር በምግብ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሚመረቱ ነገሮችን ለማለድለድና መቀላቀል የማይችሉ ነገሮችን ለማዋሃድ ያገለግላል። በተጨማሪም ለምግብነት፣ ለመድኃኒትነትና የመዋቢያ ቅባቶችን ለመሥራት የሚያገለግል ዘይት ከሎሚ ልጣጭ ይገኛል። በአጠቃላይ የሎሚን ጥቅም ዘርዝረን አንጨርሰውም። በእርግጥም ሎሚ የሚያምር፣ ጥሩ ጣዕም ያለውና ሁለገብ የሆነ ፍሬ ነው።