በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የወጣቶች ጥያቄ

ቅርርባችን ከተራ ጓደኝነት ያለፈ ነው? ክፍል 2

ቅርርባችን ከተራ ጓደኝነት ያለፈ ነው? ክፍል 2

ባለፈው ርዕስ ላይ ሁለት እውነታዎችን ተመልክተናል።

● የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት ዝግጁ ሳትሆን ከተቃራኒ ፆታ ጋር በጣም ብትቀራረብ ስሜትህ መጎዳቱ አይቀርም።​—ምሳሌ 6:27

● የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት ዝግጁ ሳትሆን ከተቃራኒ ፆታ ጋር በጣም ብትቀራረብ ጥሩ ጓደኛህን ታጣለህ። *​—ምሳሌ 18:24 የ1980 ትርጉም

በዚህ እትም ላይ ደግሞ

● ከተቃራኒ ፆታ ጋር በጣም መቀራረብ ስለሚያስከትለው ሌላ ችግር እንመለከታለን።

● እንዲሁም ከተቃራኒ ፆታ ጋር ያለህ ጓደኝነት ገደቡን አልፎ እንደሆነ እንዴት ማወቅ እንደምትችል እንመረምራለን።

የሕይወት እውነታ፦ የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት ዝግጁ ሳትሆን ከተቃራኒ ፆታ ጋር በጣም ብትቀራረብ መጥፎ ስም ልታተርፍ ትችላለህ። ሚያ * እንዲህ ትላለች፦ “ከብዙ ሴቶች ጋር ጓደኛ የሆኑ ወንዶች አውቃለሁ። በመሠረቱ እንዲህ የሚያደርጉ ወንዶች ከበርካታ ሴቶች ጋር የፍቅር ጓደኝነት የመሠረቱ ያህል ነው። ሴቶቹ የተወደዱ ይመስላቸዋል፤ ወንዶቹ ግን እንዲህ የሚያደርጉት የሴቶቹን ትኩረት ማግኘት ስለሚያስደስታቸው ብቻ ነው።”

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦

● ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ከተቃራኒ ፆታ ጋር በጣም መቀራረባቸው ስማቸውን ሊያጎድፍባቸው የሚችለው እንዴት ነው?

“ከተቃራኒ ፆታ ጋር በስልክ የጽሑፍ መልእክት መለዋወጥ ትልቅ አደጋ አለው። መጀመሪያ ላይ አንዲት ወጣት ለአንድ ልጅ አጭር መልእክት ትልክ ይሆናል፤ ብዙም ሳይቆይ ግን ከብዙ ወጣቶች ጋር አዘውትራ መልእክት መለዋወጥ ትጀምራለች። ለእሷ ባይታወቃትም ከሦስት ወንዶች ጋር የፍቅር ጓደኝነት የጀመረች ያህል ነው፤ እያንዳንዱ ልጅ እሱን ‘በተለየ ዓይን’ እንደምታየውና ስለ እሱ ይበልጥ ለማወቅ እየሞከረች እንደሆነ አድርጎ ያስባል። በመጨረሻ ሁሉም እውነቱን ሲደርሱበት ግን ስሜታቸው የሚጎዳ ከመሆኑም ሌላ እሷ መጥፎ ስም ታተርፋለች።”​ላራ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ሕፃን እንኳ ጠባዩ ንጹሕና ቅን መሆኑ፣ ከአድራጎቱ ይታወቃል።”​—ምሳሌ 20:11

ዋናው ነጥብ፦ ተቃራኒ ፆታ ካላቸው ወጣቶች ጋር መቀራረብ ስህተት አይደለም። ይሁን እንጂ ለቅርርባችሁ ገደብ ካላበጃችሁለት ስሜታችሁ ሊጎዳ፣ ጥሩ ጓደኛችሁን ልታጡ እንዲሁም መጥፎ ስም ልታተርፉ ትችላላችሁ።

ታዲያ ቅርርባችሁ ገደቡን አልፎ እንደሆነ እንዴት ማወቅ ትችላላችሁ? ይህን ለማወቅ የሚረዳችሁ አንዱ መንገድ ‘ተቃራኒ ፆታ ያለው ጓደኛዬ ሚስጥረኛዬ ሆኗል?’ ብላችሁ ራሳችሁን መጠየቅ ነው። ኤሪን የምትባል አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ወጣት እንዲሁ ተራ ጓደኛሽ ብቻ ከሆነ ከማንም በላይ በየቀኑ ልታነጋግሪው የምትጓጊው ወይም አንድ አዲስ ነገር ሲፈጠር መጀመሪያ ልትነግሪው የምትፈልጊው ሰው እሱ አይሆንም። እንዲሁም የሚያጽናናሽ ሰው በምትፈልጊበት ጊዜ ወደ እሱ አትሄጂም።”

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦

● ወጣቶች ተቃራኒ ፆታ ያለውን ሰው ሚስጥረኛ ማድረግ የሚፈልጉት ለምን ሊሆን ይችላል? እንዲህ ማድረግ ምን አደጋዎች አሉት?

“የማውቃቸው ወንዶች የቅርብ ጓደኞቼ አይደሉም። ከሴት ጓደኛዬ ጋር እንደማደርገው ከእነሱ ጋር በስልክ ለሰዓታት አላወራም። እንዲሁም ከእነሱ ጋር ፈጽሞ የማላወራቸው ጉዳዮች አሉ።”​ሪአን

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ተጠንቅቀህ [ተናገር]፤ . . . ያለ ጥንቃቄ በሚናገር ሰው ላይ ጥፋት ይደርስበታል።”​—ምሳሌ 13:3 የ1980 ትርጉም

እስቲ ይህን አስብ፦ ተቃራኒ ፆታ ላለው ሰው ስለ ግል ጉዳይህ ብዙ ማውራት አደጋ አለው? ውሎ አድሮ ጓደኝነታችሁ ቢቋረጥስ? ለዚያ ሰው ስለ ራስህ ብዙ በማውራትህ ትቆጫለህ?

አሌክሲስ የምትባል በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ ወጣት እንደሚከተለው በማለት ጉዳዩን ጥሩ አድርጋ ገልጻዋለች፦ “አንድ ሰው ተቃራኒ ፆታ ስለሆነ ብቻ ልትርቁት አይገባም። በሌላ በኩል ደግሞ ‘ቅርርባችን ከተራ ጓደኝነት ያለፈ አይደለም’ እያላችሁ ራሳችሁን አታሞኙ። ስሜታችሁ እንዳይለወጥ ተጠንቀቁ፤ እንዲህ ያለው ጥንቃቄ ከብዙ ሥቃይ ያድናችኋል።”

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚለው ዓምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን በእንግሊዝኛ ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የሰኔ 2012 ንቁ! ከገጽ 15-17 ተመልከት።

^ አን.9 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

እውነተኛ ታሪክ፦ “ከአንድ ልጅ ጋር ጓደኛሞች ነበርን፤ ደግሞም በጣም እንግባባ ነበር። እያደር ግን ለረጅም ሰዓት ማውራት እንደጀመርንና የግል ጉዳያችንን አንስተን እንደምንጨዋወት አስተዋልኩ። የሚያሳስቡትን ነገሮች ሁሉ ይነግረኝ ስለነበረ በጣም እየተቀራረብን እንደሆነ ተሰማኝ። አንድ ቀን፣ እንደሚወደኝ በኢ-ሜይል ነገረኝ። ምን ብዬ እንደምመልስለት ግራ ገባኝ። ልጁ ለእኔ ልዩ አመለካከት እንዳለው በማወቄ በአንድ በኩል ደስ ቢለኝም በሌላ በኩል ግን ነገሩ አሳስቦኝ ነበር። እሱ ቅርርባችን ከተራ ጓደኝነት ያለፈ እንደሆነ ስለተሰማው እንደቀድሞው ጓደኛሞች ሆነን መቀጠል እንደማንችል ገባኝ። ሆኖም የፍቅር ጓደኝነት ለመጀመር ዕድሜያችን እንዳልደረሰ ብነግረው ስሜቱ ይጎዳል ብዬ ፈራሁ። በመሆኑም ሁሉንም ነገር ለወላጆቼ ነገርኳቸው፤ እነሱም በቅርርባችን ረገድ ገደብ ማበጀታችን በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ገለጹልኝ። ከዚህ አጋጣሚ እንደተማርኩት መጀመሪያ ላይ ቅርርባችን ከተራ ጓደኝነት ያለፈ እንዳልሆነ ቢሰማንም እንኳ ሳናስበው ነገሮች መልካቸውን ሊቀይሩ ይችላሉ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ከተቃራኒ ፆታ ጋር ባለኝ ቅርርብ ረገድ፣ በተለይም በስልክ የጽሑፍ መልእክት በምለዋወጥበት ጊዜ ገደቤን ላለማለፍ እጠነቀቃለሁ። በተጨማሪም ተቃራኒ ፆታ ካለው ሰው ጋር ነጠል ብሎ ከመጨዋወት ይልቅ በቡድን ሆኖ ጊዜ ማሳለፉ የተሻለ ነው። እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ ተቃራኒ ፆታ ካለው ሰው ጋር ሚስጥረኞች አትሆኑም፤ እንዲሁም ልዩ ቅርርብ አይኖራችሁም።”​—ኤሌና

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ወላጆችህን ለምን አትጠይቃቸውም?

“ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች” በሚሉት ንዑስ ርዕሶች ሥር ለቀረቡት ጥያቄዎች ምን ምላሽ እንደሚሰጡ ወላጆችህን ጠይቃቸው። እነሱ የሰጡህ አስተያየት ከአንተ የተለየ ነው? ከሆነ እንዴት? እነሱ የሰጡት አስተያየት ምን ጥቅም ያለው ይመስልሃል?​—ምሳሌ 1:8

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

እኩዮችህ ምን ይላሉ?

አንድሬ​—ከአንዲት ልጅ ጋር ብዙ ጊዜ ባሳለፍክ መጠን በቀላሉ የፍቅር ስሜት ሊፈጠር የሚችል ሲሆን እሷም ለፍቅር ጓደኝነት እንደምታስባት ሊሰማት ይችላል። የፍቅር ጓደኝነት ከመጀመርህ በፊት ልትደርስባቸው የምትፈልጋቸው ግቦች ካሉህ ልጅቷን እንደወደድካት የሚያስመስል ነገር ከማድረግ ተቆጠብ።

ካሲዲ​—በተፈጥሮዬ ተግባቢ ነኝ፤ ያደግሁት ከወንዶች ጋር ስለሆነ ከእነሱ ጋር መሆን አይከብደኝም፤ ሆኖም ይህ ዓይነቱ ባሕርይ አደጋ ሊኖረው ይችላል። ከሴቶች ጓደኞቼ ጋር እንደምቀራረበው ከአንድ ልጅ ጋር ከተቀራረብኩ የተሳሳተ መልእክት ላስተላልፍ እችላለሁ። የተሻለው ነገር አንድን ልጅ እንደ ወንድሜ አድርጎ መመልከት ነው!

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለወላጆች የቀረበ ሐሳብ

በተገቢው መንገድ ከሆነ ወጣቶች ከተቃራኒ ፆታ ጋር መቀራረባቸው ስህተት አይደለም። ይሁን እንጂ ትዳር ለመመሥረት ዝግጁ ያልሆኑ ወጣቶች በቅርርባቸው ረገድ ገደብ ማበጀት ያስፈልጋቸዋል። * ከተቃራኒ ፆታ ጋር የሚኖራቸው ቅርርብ ከጓደኝነት ማለፍ አይኖርበትም።

ሁለት ወጣቶች የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት ዝግጁ ሳይሆኑ ከተቃራኒ ፆታ ጋር በጣም ቢቀራረቡ ውጤቱ ምን ይሆናል? መጀመሪያ ላይ የነበራቸው የደስታ ስሜት ብዙም ሳይቆይ ወደ ብስጭት ይቀየራል። ሁኔታው ጎማ በሌለው መኪና ለመጓዝ ከመሞከር ጋር ይመሳሰላል። ይዋል ይደር እንጂ እነዚህ ወጣቶች የጀመሩት ጓደኝነት የትም እንደማያደርሳቸው ይገነዘባሉ። አንዳንዶች በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት ይጀምሩ ይሆናል፤ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ግን አደጋዎች አሉት። ሌሎች ደግሞ ጓደኝነታቸውን የሚያቋርጡ ሲሆን ይህም ሁለቱም እንደተታለሉ እንዲሰማቸው፣ ስሜታቸው እንዲጎዳ አልፎ ተርፎም የመንፈስ ጭንቀት እንዲይዛቸው ሊያደርግ ይችላል። ታዲያ በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያለውን ልጃችሁን አለጊዜው የፍቅር ጓደኝነት መመሥረት ለሚያስከትለው አደጋ እንዳይጋለጥ ልትረዱት የምትችሉት እንዴት ነው?​—መክብብ 11:10

ይህን ለማድረግ ቁልፉ፣ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ ከተቃራኒ ፆታ ጋር ስለሚኖረው ጓደኝነት በግልጽ መነጋገር ነው። እንዲህ ካደረጋችሁ፣ ልጃችሁ ከተቃራኒ ፆታ ጋር ያለው ጓደኝነት ገደቡን ማለፍ ከጀመረ ይህን ማስተዋል እንዲሁም እሱን መርዳት ትችላላችሁ።

አንዳንድ ወላጆች በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃቸው ከተቃራኒ ፆታ ጋር ስላለው ጓደኝነት በግልጽ እንዳይነግራቸው ሳይታወቃቸው በሩን ይዘጉታል። አንዳንድ ወጣቶች ለንቁ! የተናገሩትን እስቲ እንመልከት፦

“ደስ ስለሚለኝ ልጅ ለእናቴ ለመናገር ሁልጊዜ እፈልግ ነበር፤ ሆኖም ጉዳዩን በጣም አክብዳ ታየዋለች ብዬ ስለፈራሁ አልነገርኳትም።”​ካራ

“ለእናቴ አንድ ልጅ ደስ እንዳለኝ ስነግራት ‘ሠርጌ ላይ ትገኛለች ብለሽ እንዳታስቢ!’ ትለኛለች፤ እንዲህ ከማለት ይልቅ ‘እስቲ ስለዚህ ጓደኛሽ ንገሪኝ። ምኑን ነው የወደድሽለት?’ ብትለኝ ኖሮ የምትሰጠኝን ምክር ለመቀበል ይቀለኝ ነበር።”​ናዲን

በአንጻሩ ደግሞ ወላጆች በትዕግሥት ካዳመጡ በኋላ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ምክር መስጠታቸው የሚያመጣውን ለውጥ እንመልከት።

“ወላጆቼ አንድን ልጅ እንደወደድኩት ስነግራቸው አልተደናገጡም። የሚያስፈልገኝን ምክር የሰጡኝ ቢሆንም ስሜቴን ተረድተውልኛል። በዚህ ምክንያት ምክራቸውን መስማትና ሌላ ጊዜም የማስበውንና የሚሰማኝን ነገር ለእነሱ በግልጽ መንገር ቀላል ሆኖልኛል።”​ኮሪና

“ወላጆቼ ወጣቶች ሳሉ ወደዋቸው ስለነበሩ ሰዎች አልፎ ተርፎም ከአንድ ሰው ጋር የነበራቸው የፍቅር ጓደኝነት ለምን እንደተቋረጠ በግልጽ ሲናገሩ መስማቴ እኔም ፍቅር ቢይዘኝ ለወላጆቼ መናገሬ ምንም ችግር እንደሌለው እንድገነዘብ ረድቶኛል።”​ሊኔት

በተጨማሪም አንዳንድ ጊዜ ወጣቶች አለጊዜው የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት የሚነሳሱት ከበስተጀርባ ሌላ ምክንያት ስላላቸው እንደሆነ ተገንዘቡ።

“ከአንድ ልጅ ጋር በድብቅ የፍቅር ጓደኝነት ጀምሬ ነበር፤ ይህን ያደረግሁት ልጁ ደስተኛ እንድሆን ስለሚያደርገኝና ስለሚያዳምጠኝ ነበር።​አኔት

“ሁልጊዜ አብሬው መሆን የምፈልገው አንድ ልጅ አለ። ይህ ልጅ ምንጊዜም ትኩረት ይሰጠኛል፤ ትልቁ ድክመቴ ይህ ነው። ከየትም ይምጣ ከየት ትኩረት ማግኘት ደስ ይለኛል።”​ኤሚ

“ወላጆቼ ቆንጆ እንደሆንኩ ወይም የለበስኩት ልብስ እንደሚያምርብኝ ከልባቸው ከነገሩኝ እንዲህ ያለውን አድናቆት ከአንድ ወንድ ማግኘት እንዳለብኝ አይሰማኝም።”​ካረን

ራሳችሁን እንዲህ እያላችሁ ጠይቁ፦

በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጄ ወደ እኔ መቅረብ እንዲቀልለው ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?​—ፊልጵስዩስ 4:5

‘ለመስማት የፈጠንኩና ለመናገር የዘገየሁ’ ነኝ?​—ያዕቆብ 1:19

በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጄ ፍቅርና አድናቆት ለማግኘት ሲል ወደ ሌሎች ለመሄድ እንዳይፈተን ምን ማድረግ እችላለሁ?​—ቆላስይስ 3:21

ዋናው ነጥብ፦ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ ከተቃራኒ ፆታ ጋር ያለው ጓደኝነት ገደቡን ያላለፈና ችግር የማያስከትል እንዲሆን የሚያደርግበትን መንገድ አሠልጥኑት። ይህ፣ ትልቅ ሰው ሲሆንም ሊጠቅመው የሚችል ችሎታ ነው።​—ቆላስይስ 3:5፤ 1 ተሰሎንቄ 4:3-6

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.37 ከዚህ ቀደም ያለውን ርዕስ እንዲሁም በሰኔ 2012 ንቁ! ላይ “የወጣቶች ጥያቄ” በሚለው ዓምድ ሥር የወጣውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ቻርት]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ገደቦች

ተገቢ

በቡድን ሆኖ ጊዜ ማሳለፍ

ይበልጥ መተዋወቅ

መጨዋወት

የማይገባ

X መነጠል

X ሚስጥረኛ መሆን

X ማሽኮርመም

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

መቀራረብ

ማሽኮርመም

መንካት

መያያዝ

መሳሳም