በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የገና ዛፍ በቅድመ ክርስትና ዘመን የነበረው ታሪክ

የገና ዛፍ በቅድመ ክርስትና ዘመን የነበረው ታሪክ

የገና ዛፍ በቅድመ ክርስትና ዘመን የነበረው ታሪክ

በብዙ የዓለም ክፍሎች፣ ቅጠሉ የማይረግፈው የገና ዛፍ በበዓላት ወቅት የተለመደ ከመሆኑም ሌላ በንግዱ ዓለም በጣም የታወቀ ነው። ይህ ዛፍ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከጥንት ጀምሮ ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ ጥቅም ላይ ይውል ነበር።

ይህ ሁኔታ በስዊድን ምዕራባዊ የባሕር ጠረፍ ላይ በሚገኘው ቡሁስላን የሚባል ግዛትና በአቅራቢያው ባለው የእስትፎል ግዛት (ኖርዌይ ውስጥ) በግልጽ ይታያል። በእነዚህ አካባቢዎች በ5,000 የተለያዩ ስፍራዎች በዐለት ላይ የተቀረጹ ከ75,000 በላይ ምስሎች የተገኙ ሲሆን የተወሰኑት ምስሎች ቅጠላቸው የማይረግፍ ዛፎችን የሚያሳዩ ናቸው። ከእነዚህ ምስሎች ውስጥ ብዙዎቹ የተቀረጹት ከ1,800 እስከ 500 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ አካባቢ እንደሆነ የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች ይናገራሉ። *

እነዚህ አስደናቂ ምስሎች የናዝሬቱ ኢየሱስ ከመወለዱ ከረጅም ጊዜ በፊት የኖሩ ሰዎች ስለነበራቸው እምነት የሚገልጹት ነገር አለ። ለምሳሌ ያህል፣ በዛሬዎቹ የስዊድንና የኖርዌይ አካባቢዎች ስፕሩስ የሚባሉ ቅጠላቸው የማይረግፍ ዛፎች በጥንት ዘመን ቅዱስ ምልክት ሆነው ያገለግሉ እንደነበር አንዳንድ ተመራማሪዎች ያምናሉ።

በስተ ሰሜን ርቀው በሚገኙት በእነዚያ የባሕር ዳርቻዎች አካባቢ የኖሩ ሰዎች የስፕሩስ ዛፎችን የሚያሳዩ ምስሎችን የቀረጹት ለምን ነበር? አንዳንድ ምሁራን፣ ይህ የሆነበት አንዱ ምክንያት ምስሎቹ በተሠሩበት የቅድመ ክርስትና ዘመን እነዚያ ዛፎች እንደ ልብ ስለማይገኙ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል። አብዛኛዎቹ ዛፎች ቅጠላቸው በመርገፉ ምክንያት የሞቱ በሚመስሉበት በቀዝቃዛው ወቅት ቅጠሉ ምንጊዜም አረንጓዴ ወይም “ሕያው” የሆነ ዛፍ መገኘቱ በጣም አስደናቂ እንደሚሆን ግልጽ ነው።

በመላው ዓለም በሚገኙ ብዙ ባሕሎች ውስጥ ዛፎች የሕይወት፣ ከጥፋት የመትረፍና ያለመሞት ተምሳሌት ተደርገው ይታያሉ። ይህ ሐቅ በቡሁስላንና በእስትፎል አካባቢዎች ቅጠላቸው የማይረግፈው የስፕሩስ ዛፎች የተለመዱ ከመሆናቸው ከብዙ ዘመናት በፊት ከእነዚህ ዛፎች ጋር በጣም የሚመሳሰሉ ምስሎች በዐለት ላይ የተቀረጹበትን ሌላውን ምክንያት ለመረዳት ያስችለናል።

ከስዊድን የብሔራዊ ቅርስ ቦርድ ጋር በመተባበር የተዘጋጀው ሮክ ካርቪንግስ ኢን ዘ ቦርደርላንድስ የተሰኘው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “በዐለት ላይ የተቀረጹት የዛፍ ምስሎች እንደሚያሳዩት የደቡባዊ ስካንዲኔቪያ ክፍል የነሐስ ዘመን ተብሎ በሚጠራው ወቅት እንኳ ከመላው አውሮፓና ከአብዛኛው የእስያ ክፍል ጋር በሃይማኖትና በባሕል ረገድ ትስስር ነበረው። ሃይማኖትና ኮስሞሎጂ (ስለ ጽንፈ ዓለም የሚደረግ ጥናት) የቀረበው በግብርናና እንስሳትን በማርባት ለሚተዳደሩ ሰዎች በሚስማማ መንገድ ነበር። እነዚህ ሰዎች የሚያመልኳቸው አማልክት በስም ቢለያዩም በአብዛኛው አንድ ዓይነት ነበሩ።”

ዘ ሮክ ካርቪንግ ቱር የተሰኘ በቡሁስላን ቤተ መዘክር የተዘጋጀ አንድ ቡክሌት እንደሚከተለው በማለት ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጣል፦ “ዐለት ላይ የሚቀርጹት ሰዎች በሥራቸው ለመግለጽ የፈለጉት የየዕለቱን ሕይወት አልነበረም። የቀረጿቸው ምስሎች ለአማልክቶቻቸው የቀረበ ጸሎትንና ልመናን ሊያመለክቱ እንደሚችሉ እናምናለን።” ቡክሌቱ አክሎም “እምነታቸው በሕይወት፣ በመራባት፣ በሞትና ዳግም በመወለድ ዘላለማዊ ዑደት ዙሪያ የሚያጠነጥን ነበር” ብሏል።

በሰሜን አውሮፓ የጽሑፍ ጥበብ ከመጀመሩ ከረጅም ጊዜ በፊት በምልክት የተሠራውን ይህን ልዩ የኪነ ጥበብ ሥራ በተመለከተ የስዊድን ብሔራዊ የማመሳከሪያ ኢንሳይክሎፒዲያ (ናቾናልኤንስዩክሎፔዴን) እንዲህ ብሏል፦ “ከፆታ ግንኙነት ጋር የተያያዙ በርካታ ምስሎች መኖራቸው የነሐስ ዘመን ተብሎ በሚጠራው ወቅት፣ በስተ ሰሜን በነበሩ ሰዎች ሃይማኖት ውስጥ የመራባት አምልኮ ትልቅ ቦታ ይሰጠው እንደነበር ያመለክታል።”

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ቅጠላቸው ከማይረግፍ ዛፎች ጋር የተያያዙ ልማዶች በብዙ ቦታዎች ተስፋፍተውና ተቀባይነት አግኝተው ነበር። ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ስለ ገና ዛፍ ሲናገር “የዛፍ አምልኮ አረማውያን በሆኑ አውሮፓውያን ዘንድ የተለመደ ሲሆን ወደ ክርስትና ከተለወጡ በኋላም ቀጥሏል” ይላል። የዛፍ አምልኮ “በቀዝቃዛዎቹ ወራት አጋማሽ ላይ በሚከበሩ ዐውደ ዓመቶች ወቅት የገና ዛፍን በበር ላይ ወይም በቤት ውስጥ የማስቀመጥ ልማድን” ጨምሮ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችና ባሕሎች ውስጥ መንጸባረቁን ቀጥሏል።

በ1841 የብሪታኒያ ንጉሣዊ ቤተሰብ ስፕሩስ የሚባለውን ዛፍ አስጊጠው ገናን ለማክበር መጠቀማቸው ቅጠሉ የማይረግፍ ዛፍን የመጠቀም ጥንታዊ ልማድ በዘመናችን ሰፊ ተቀባይነት እንዲኖረው መንገድ ጠርጓል። በዛሬው ጊዜ የገና ዛፍ በመላው ዓለም እውቅና ያገኘ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ የገና ዛፎች ተፈላጊነት ማብቂያ የሚኖረው አይመስልም። ያም ሆነ ይህ በስካንዲኔቪያ የሚገኙት የዛፍ ምስሎች፣ የገና ዛፍ ክርስቲያናዊ መሠረት እንደሌለው በዐለት ላይ የሰፈረ ድምጽ አልባ ምሥክርነት ይሰጣሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 በቡሁስላን በዐለት ላይ የተቀረጹ ምስሎች ከተገኙባቸው ቦታዎች አንዳንዶቹን የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት በዓለም ቅርስነት መዝግቧቸዋል።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በዐለት ላይ የተቀረጹ ምስሎች አረማውያን ቅጠላቸው የማይረግፍ ዛፎችን ለአምልኮ መጠቀም የጀመሩት ከክርስቶስ ዘመን በፊት እንደሆነ ይጠቁማሉ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የዛፍ ምስል የተቀረጸባቸው ዐለቶች (1) ቶርስቦ፣ (2) ባካ እና (3) ሎኬበርግ፣ ስዊድን

[የሥዕል ምንጭ]

Courtesy Stiftelsen för dokumentation av Bohusläns hällristningar