በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኪንግ ጄምስ ቨርዥን ተወዳጅነት ያተረፈው እንዴት ነው?

ኪንግ ጄምስ ቨርዥን ተወዳጅነት ያተረፈው እንዴት ነው?

ኪንግ ጄምስ ቨርዥን ተወዳጅነት ያተረፈው እንዴት ነው?

ኪንግ ጄምስ ቨርዥን ወይም ኦተራይዝድ ቨርዥን የተባለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም 400ኛ ዓመት ለማሰብ በዚህ ዓመት በእንግሊዝ ውስጥ ትልቅ ዝግጅት ተደርጎ ነበር። ከዚህ በዓል ጋር በተያያዘ ልዩ ጥናታዊ ዘገባዎች በቴሌቪዥንና በሬዲዮ የቀረቡ ሲሆን ስብሰባዎች፣ ንግግሮችና ትምህርታዊ ሴሚናሮችም ተደርገዋል።

በእንግሊዝ ንጉሥ በቀዳማዊ ጄምስ ስም የተሰየመውን ይህን ብሔራዊ ቅርስ ለማሰብ የተደረገውን ዝግጅት በበላይነት የመራው ልዑል ቻርለስ ነበር። ለመሆኑ፣ ግንቦት 1611 የታተመው ኪንግ ጄምስ ቨርዥን እንግሊዝኛ ተናጋሪ በሆኑ ሕዝቦች ልብ ውስጥ ትልቅ ቦታ ሊኖረው የቻለው እንዴት ነው?

የትርጉም ሥራው አስፈላጊነት እየጨመረ መጣ

በ16ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ መጽሐፍ ቅዱስን የማወቅ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ቁጥር በመላው አውሮፓ እየጨመረ መጣ። ይህ ከመሆኑ ሁለት መቶ የሚጠጉ ዓመታት ቀደም ብሎ ማለትም በ1382 ጆን ዊክሊፍ መጽሐፍ ቅዱስን ከላቲን ወደ እንግሊዝኛ በመተርጎሙ እንግሊዝኛ ተናጋሪ የሆነው ሕዝብ የአምላክን ቃል በራሱ ቋንቋ የማንበብ ፍላጎት አደረበት። በተጨማሪም በቀጣዮቹ ሁለት መቶ ዓመታት ውስጥ ሎላርድ የሚባሉት የእሱ ተከታዮች በእጅ የተጻፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በመላው አገሪቱ አሰራጭተው ነበር።

ሌላው ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ትርጉም ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የነበረው ዊሊያም ቲንደል ያዘጋጀው ኒው ቴስታመንት የተባለው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ይህ መጽሐፍ ከመጀመሪያው ግሪክኛ ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመው በ1525 ነበር። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በ1535 ማይልዝ ከቨርዴል ሙሉ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ አዘጋጀ። ይህ ከመሆኑ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ የእንግሊዙ ንጉሥ ሄንሪ 8ኛ ከሮም ካቶሊክ ጋር የነበረውን ግንኙነት ያቋረጠ ከመሆኑም በላይ አንድ ስልታዊ እርምጃ ወስዶ ነበር። ሄንሪ 8ኛ ራሱን የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ራስ አድርጎ ሾሞ ስለነበር ይህን ሥልጣኑን ለማጠናከር የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲዘጋጅ ፈቃድ ሰጠ፤ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ግሬት ባይብል በመባል ይታወቃል። በ1539 የታተመው ይህ ትርጉም በጎቲክ የአጻጻፍ ስልት ማለትም ደመቅ ተደርገው በተጻፉ ፊደላት የተዘጋጀ ትልቅ ጥራዝ ነበር።

ከመላው አውሮፓ ተሰደው የመጡ ፒዩሪታኖችና ሌሎች ፕሮቴስታንቶች በጄኔቫ፣ ስዊዘርላንድ ይኖሩ ነበር። በመሆኑም በ1560 ጄኔቫ ባይብል የሚባል ምዕራፎችና ቁጥሮች ያሉት ለመጀመሪያ ጊዜ ለማንበብ ቀላል በሆነ መልኩ የተዘጋጀ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ታተመ። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች የአውሮፓ አገሮች ወደ እንግሊዝ በመግባት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተወዳጅነትን አተረፈ። ከጊዜ በኋላ ማለትም በ1576 ጄኔቫ ባይብል በእንግሊዝ አገርም ታተመ። ይህ ትርጉም ጥቅሶችን ለማብራራት የሚረዱ ካርታዎችና የኅዳግ ማስታወሻዎች ነበሩት። ይሁን እንጂ ማስታወሻዎቹ የጳጳሳቱን ሥልጣን የሚቃረን ሐሳብ የያዙ ስለነበሩ አንዳንድ አንባቢያንን አበሳጩ።

ችግሮችን ለመፍታት የተወሰዱ እርምጃዎች

ግሬት ባይብል በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት በማጣቱ፣ ጄኔቫ ባይብል ደግሞ አወዛጋቢ የሆኑ የግርጌ ማስታወሻዎች የያዘ በመሆኑ የታረመና የተሻሻለ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንዲዘጋጅ ተወሰነ። ይህን ትርጉም ለማዘጋጀት መሠረት እንዲሆን የተመረጠው ግሬት ባይብል ነበር። ኃላፊነቱ የተሰጠው ለእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ሲሆን እነሱም በ1568 ቢሾፕስ ባይብል የሚባል የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አዘጋጁ። ይህ ትርጉም ሥዕላዊ መግለጫዎች የሞሉበት ትልቅ ጥራዝ ነበር። ይሁን እንጂ ሃይማኖታዊ የማዕረግ ስሞችን የሚቃወሙት የካልቪን ተከታዮች “ጳጳሳት” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መግባቱን አልወደዱትም። በዚህም የተነሳ ቢሾፕስ ባይብል የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉምም በአብዛኞቹ እንግሊዛውያን ዘንድ ተቀባይነት ሊያገኝ አልቻለም።

ቀዳማዊ ጄምስ በ1603 * በእንግሊዝ ዙፋን ላይ ከወጣ በኋላ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንዲዘጋጅ ፈቃድ ሰጠ። ንጉሡ፣ የሚዘጋጀው ትርጉም በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ሰዎችን ቅር የሚያሰኙ ማስታወሻዎችና ሐሳቦች እንዳይኖሩበት ትእዛዝ ሰጠ።

ንጉሥ ጄምስ ለትርጉም ሥራው መሳካት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። በመሆኑም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ስድስት ቡድኖች ውስጥ የታቀፉ 47 ምሁራን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ተከፋፍለው ማዘጋጀት ችለዋል። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን የቲንደልንና የከቨርዴልን የትርጉም ሥራዎች የተጠቀሙ ቢሆንም አርመው ያወጡት ቢሾፕስ ባይብል የተሰኘውን መጽሐፍ ቅዱስ ነው ማለት ይቻላል። በተጨማሪም ጄኔቫ ባይብልን እና በ1582 የተዘጋጀውን ሮማን ካቶሊክ ሪምዝ ኒው ቴስታመንት የተባለ ትርጉም ተጠቅመዋል።

ንጉሥ ጄምስ ራሱም የተከበረ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የነበረ ሲሆን የትርጉሙ መታሰቢያነት “እጅግ ለተከበረውና ለታላቁ ልዑል ለጄምስ” መሆኑ ጄምስ ይህ ትርጉም እንዲዘጋጅ ላደረገው ጥረት እውቅና መሰጠቱን የሚያሳይ ነው። በብዙኃኑ ዘንድ እንደሚታሰበው ከሆነ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ራስ የሆነው ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲተረጎም ያደረገበት ምክንያት ሕዝቡን አንድ ለማድረግ ስለፈለገ ነው።

ድንቅ የትርጉም ሥራ

ቀሳውስቱ “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲነበብ የተመደበውን” መጽሐፍ ቅዱስ ከንጉሣቸው እጅ ሲቀበሉ ደስ ብሏቸው ነበር። ይሁን እንጂ ሕዝቡ ይህን አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንዴት ይቀበለው ይሆን? የሚለው ጥያቄ ገና መልስ አላገኘም።

ተርጓሚዎቹ በጣም ረጅም በሆነው በመጀመሪያው እትም መቅድም ላይ ይህ አዲስ ትርጉም ተቀባይነት የማግኘቱ ጉዳይ እንዳሳሰባቸው ገልጸው ነበር። ይሁን እንጂ ኪንግ ጄምስ ቨርዥን በሕዝቡ ዘንድ ተወዳጅነት በማትረፍ ረገድ የጄኔቫ ባይብልን ቦታ ለመውሰድ 30 ዓመታት ቢፈጅበትም የኋላ ኋላ ጥሩ ተቀባይነት አግኝቷል።

ዘ ባይብል ኤንድ ዚ አንግሎ ሳክሰን ፒፕል የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው ከሆነ “በወቅቱ ይህ ትርጉም [የቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሆን ተመርጦ] ነበር፤ ይሁንና ተመራጭ እንዲሆን ያደረገው ዋናው ነገር የትርጉም ሥራው ላቅ ያለ መሆኑ ነበር።” ዘ ካምብሪጅ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ባይብል ደግሞ እንደሚከተለው በማለት ገልጿል፦ “መጽሐፉ በቀጥታ ከአምላክ እንደመጣ ተቆጥሮ ትልቅ ክብር ተሰጥቶታል፤ እንግሊዝኛ ተናጋሪ የሆኑ በርካታ ክርስቲያኖች በኪንግ ጄምስ ቨርዥን ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ ማድረግን አምላክን ከመዳፈር ለይተው አያዩትም ነበር።”

እስከ ምድር ዳር ድረስ

ከእንግሊዝ ወደ ሰሜን አሜሪካ የሄዱት የቀድሞዎቹ ሰፋሪዎች ጄኔቫ ባይብል የተሰኘውን ትርጉም ይዘው ሄደው ነበር። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ኪንግ ጄምስ ቨርዥን በአሜሪካ ውስጥ የበለጠ ተቀባይነት አገኘ። የብሪትሽ ግዛት በመላው ዓለም እየተስፋፋ ሲሄድ የፕሮቴስታንት ሚስዮናውያንም ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በሰፊው ጥቅም ላይ እንዲውል አደረጉ። መጽሐፍ ቅዱስን በአካባቢያቸው በሚነገሩ ቋንቋዎች የሚተረጉሙ ብዙ ተርጓሚዎች መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ የተጻፈባቸውን የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቋንቋዎች ስለማያውቁ ኪንግ ጄምስ ቨርዥንን ለትርጉም ሥራቸው እንደ መሠረት አድርገው መጠቀም ጀመሩ።

የብሪቲሽ ቤተ መጻሕፍት እንደገለጸው ከሆነ በዛሬው ጊዜ “ኪንግ ጄምስ ቨርዥን ወይም ኦተራይዝድ ቨርዥን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ከተዘጋጁ ጽሑፎች ሁሉ በስፋት በመሰራጨት ረገድ እስከ አሁን ድረስ ተወዳዳሪ አልተገኘለትም።” አንዳንዶች በሰጡት ግምታዊ አኃዝ መሠረት በመላው ዓለም ታትሞ የተሠራጨው የኪንግ ጄምስ ቨርዥን ትርጉም ከአንድ ቢሊዮን በላይ ይሆናል!

ማሻሻያ ማድረግ አስፈለገ

ባለፉት መቶ ዘመናት ብዙ ሰዎች የኪንግ ጄምስ ቨርዥን ትርጉም ካልሆነ በስተቀር ሌላ “እውነተኛ” መጽሐፍ ቅዱስ ያለ አይመስላቸውም ነበር። ይህን ትርጉም ሙሉ በሙሉ የማረሙ ሥራ በ1870 በእንግሊዝ ተጀመረ። በኋላም ኢንግሊሽ ሪቫይዝድ ቨርዥን በመባል የሚጠራውን ይህን የታረመ ትርጉም መሠረት በማድረግ አሜሪካን ስታንዳርድ ቨርዥን የተባለው ጥቂት ማሻሻያ የተደረገበት የአሜሪካኖች እትም ተዘጋጀ። * በ1982 እንደገና ታርሞ የወጣው ይህ ትርጉም በመቅድሙ ላይ እንደገለጸው በ1611 የታተመው “ኦተራይዝድ ቨርዥን ከፍተኛ አክብሮት እንዲያተርፍ ያደረጉት ውበት ያላቸው አገላለጾች ከዚህኛው እትም ውስጥ እንዳይጠፉ” ለመጠበቅ ጥረት ተደርጓል።

መጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛውን ሽያጭ በመያዝ ረገድ በዓለም ላይ ተወዳዳሪ የሌለው መጽሐፍ ሲሆን ኪንግ ጄምስ ቨርዥን ደግሞ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈ ትርጉም ነው፤ ያም ቢሆን ፕሮፌሰር ሪቻርድ ጂ ሞልተን እንዲህ ሲሉ የታዘቡትን ተናግረዋል፦ “ከእነዚህ የዕብራይስጥና የግሪክኛ ጽሑፎች ጋር በተያያዘ የምንችለውን ሁሉ አድርገናል። . . . ተርጉመናቸዋል [እንዲሁም] ትርጉሞቹን እንደገና አርመን አሻሽለናቸዋል። . . . ይሁንና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በተያያዘ አንድ የሚቀር ነገር አለ፦ እሱም መጽሐፉን ማንበብ ነው።”

ኪንግ ጄምስ ቨርዥን ውብ በሆነው አገላለጹ አድናቆትን ያተረፈና ከፍ ተደርጎ የሚታይ ድንቅ የትርጉም ሥራ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ በውስጡ ስላለው መልእክት አስፈላጊነትስ ምን ሊባል ይችላል? በመንፈስ መሪነት የተጻፈው የአምላክ ቃል በዓይነቱ ልዩ በሆነው በዚህ ዘመን ውስጥ ላሉት ችግሮች ዘላቂው መፍትሔ ምን እንደሆነ ይገልጻል። ለማንበብ የምትመርጠው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ምንም ይሁን ምን፣ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንድትችል አንተን ለመርዳት ፈቃደኞች ናቸው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.10 ጄምስ የተወለደው በ1566 ሲሆን በ1567 ጄምስ 6ኛ በመባል የስኮትላንድ ንጉሥ እንዲሆን ዘውድ ተደፋለት። በ1603 የእንግሊዙ ቀዳማዊ ጄምስ ተብሎ ዘውድ ሲደፋለት የስኮትላንድ ብቻ ሳይሆን የእንግሊዝም ንጉሥ ሆነ። በ1604 ደግሞ “የታላቋ ብሪታንያ ንጉሥ” የሚል ማዕረግ ተሰጠው።

^ አን.21 “አሜሪካን ስታንዳርድ ቨርዥን” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

አሜሪካን ስታንዳርድ ቨርዥን

አሜሪካን ስታንዳርድ ቨርዥን የተባለው መጽሐፍ ቅዱስ የተዘጋጀው በ1901 ሲሆን መሠረት ያደረገውም የኪንግ ጄምስ ቨርዥን ትርጉምን ነው። አሜሪካን ስታንዳርድ ቨርዥን በመቅድሙ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ሰዎች በኦተራይዝድ [ኪንግ ጄምስ] ቨርዥን ውስጥ ለተንጸባረቀው ውበትና ኃይል ያለው አገላለጽ ከፍተኛ አድናቆት እንዳላቸው እናውቃለን።” ይሁንና ይህ ትርጉም አንድ ጉልህ ማስተካከያ አድርጓል።

መቅድሙ ስለዚህ ጉዳይ ማብራሪያ ሲሰጥ እንዲህ ብሏል፦ “የአሜሪካን ስታንዳርድ ቨርዥን አዘጋጆች ጉዳዩን በጥንቃቄ ካገናዘቡ በኋላ መለኮታዊው ስም በጣም ቅዱስ በመሆኑ መጠራት አይገባውም የሚለው የአይሁዳውያን አጉል እምነት በእንግሊዝኛውም ሆነ በሌላ በማንኛውም የብሉይ ኪዳን ትርጉም ላይ ተጽዕኖ ማሳደር እንደማይገባው በአንድ ድምፅ አጽድቀዋል፤ ይህ አጉል እምነት የዘመናችን ሚስዮናውያን ባዘጋጇቸው በርካታ ትርጉሞች ላይ ተጽዕኖ አለማድረጉ የሚያስደስት ነው።”

ይህ ሲባል ግን ይሖዋ የሚለው መለኮታዊ ስም በኪንግ ጄምስ ቨርዥን ትርጉም ውስጥ ፈጽሞ አይገኝም ማለት አይደለም። መለኮታዊው ስም በአራት ቦታዎች፣ ማለትም በ⁠ዘፀአት 6:3፣ በ⁠መዝሙር 83:18፣ በ⁠ኢሳይያስ 12:2 እና 26:4 ላይ ይገኛል። ይሁን እንጂ በ1901 የታተመው የአሜሪካን ስታንዳርድ ቨርዥን ይህን ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገቢ በሆኑ 7,000 የሚያህሉ ቦታዎች ላይ መልሶ አስገብቷል።

[ሥዕል]

1901

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

አዳዲስ ገጽታዎች እንዲኖሩት ተደረገ

ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ የተባለው ድርጅት በ1907 ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብሎ የተዘጋጀውን የኪንግ ጄምስ ቨርዥን ትርጉም በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ማሳተም ጀመረ። ይህ እትም “የቤርያ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች መመሪያ” ተብሎ የሚጠራ ሰፊ ተጨማሪ መረጃ አካቶ ነበር። በኋላም የይሖዋ ምሥክሮች በራሳቸው ማተሚያዎች የኪንግ ጄምስ ቨርዥን ትርጉምን ማተም ጀመሩ። እስከ 1992 ድረስ ባለው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች 1,858,368 ቅጂዎችን አትመው ነበር።

[ሥዕል]

1907

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ጠቃሚ የሆነ ዘመናዊ ትርጉም

ባለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት ውስጥ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች (አንዳንዶቹ በብዙ ቋንቋዎች የተተረጎሙ ናቸው) ተዘጋጅተዋል። በተለይም ብዙዎች በጣም ጠቃሚ እንደሆነ የመሠከሩለት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም የተባለው ነው። ይህ ትርጉም በሙሉም ሆነ በከፊል በ100 ቋንቋዎች እና ከ170 ሚሊዮን በሚበልጡ ቅጂዎች ተሰራጭቷል። በባለማጣቀሻው የዚህ መጽሐፍ እትም ውስጥ የቀረቡት ካርታዎች እንዲሁም በፊደል ቅደም ተከተል የተዘጋጀው ማውጫና ተጨማሪ መረጃ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ለዘመናችን የያዘውን መልእክት ይበልጥ ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲረዱ አስችለዋል።

[ሥዕል]

1961

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

1611

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Art Resource, NY