በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በ2011 በጃፓን የደረሰው ሱናሚ—ከአደጋው ከተረፉ ሰዎች አንደበት

በ2011 በጃፓን የደረሰው ሱናሚ—ከአደጋው ከተረፉ ሰዎች አንደበት

በ2011 በጃፓን የደረሰው ሱናሚ—ከአደጋው ከተረፉ ሰዎች አንደበት

በጃፓን ከደረሰው ርዕደ መሬትና ያንን ተከትሎ ከመጣው ሱናሚ የተረፉ ሰዎች ያጋጠማቸውን ሁኔታ አስመልክተው የተናገሩትን ሐሳብ እንድታነብ እንጋብዝሃለን።

ዓርብ፣ መጋቢት 11 ቀን 2011 ከሰዓት በኋላ 8:46 ላይ ጃፓን በዓለም ላይ ከደረሱት ኃይለኛ ርዕደ መሬቶች አራተኛውን ደረጃ በያዘ ነውጥ ተመታች። ይህ ርዕደ መሬት ኃይለኛ ሱናሚ ያስከተለ ከመሆኑም በላይ ከዋናው የመሬት መንቀጥቀጥ በኋላ የአካባቢውን ሕዝብ ለብዙ ሳምንታት ያሸበሩ ኃይለኛ ነውጦች በተደጋጋሚ እንዲከሰቱ አድርጓል። በዚህም ሳቢያ 20,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል ወይም የደረሱበት አልታወቀም። የሚያስደስተው ግን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በሕይወት ተርፈዋል። በሕይወት ከተረፉት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ እንደሚከተለው በማለት ያጋጠማቸውን ሁኔታ ተናግረዋል።

ኢሺኖማኪ ሚያጊ በሚባል ክፍለ ግዛት የሚኖሩት ታዳዩኪ እና ባለቤቱ ሀሩሚ ቤታቸው ሳሉ ኃይለኛ የጉርምርምታ ድምፅ ሰሙ፤ ከዚያም ቤታቸው በኃይል ተናወጠ። ታዳዩኪ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ተሯሩጠን ወደ ውጭ ስንወጣ መሬቱ ተሰነጣጥቆ ስናይ ደነገጥን። ቤታችን ወዲያና ወዲህ ሲወዛወዝና ከግድግዳው ላይ አቧራው እንደ ጭስ እየተትጎለጎለ ሲወጣ ተመለከትን።”

መናወጡ የጀመረው ከሚያጊ የባሕር ዳርቻ 129 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ባሕር ውስጥ ነበር። በዚህ ነውጥ ምክንያት የተፈጠረው ሱናሚ በጃፓን የፓስፊክ ውቅያኖስ ዳርቻ ላይ እስከ 670 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ ጥፋት አስከትሏል። በአንዳንድ የባሕር ዳርቻዎች ማዕበሉ 15 ሜትር ከፍታ ስለነበረው የማዕበል መከላከያ ግንቦችንና የወንዝ ዳርቻዎችን ጥሶ 40 ኪሎ ሜትር ያህል ወደ የብሱ ገብቷል።

የኤሌክትሪክ ማመንጫዎች፣ የጋዝና የንጹሕ ውኃ አቅርቦት የሚሰጡ ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወደሙ። ወደ 160,000 የሚያህሉ ቤቶች፣ ሱቆችና ፋብሪካዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል አሊያም በማዕበሉ ተጠርገው ተወስደዋል። በአንድ ወቅት 440,000 የሚያህሉ ሰዎች እንደ ትምህርት ቤቶችና ማኅበራዊ ተቋማት በመሳሰሉ 2,500 ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ተጠልለው ነበር። ሌሎች በርካታ ሰዎች ደግሞ ወደ ዘመዶቻቸው ወይም ጓደኞቻቸው ቤት ሸሽተው ነበር። በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የአደጋው ሰለባ ሲሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም።

ሞት ያስከተለው ሐዘን

በሱናሚው የሞቱት ሰዎች ቁጥር በርዕደ መሬቱ ከሞቱት ሰዎች ቁጥር ይበልጣል። በሪኩዜንታካታ ኢዋቴ ክፍለ ግዛት ይኖር የነበረው ዮዪኪ፣ ርዕደ መሬቱ ሱናሚ እንደሚያስከትል ስለገባው ወላጆቹን በአቅራቢያው ወደሚገኝ መጠለያ ወሰዳቸው። ከዚያም ጎረቤቶቹን ለማየት ተመልሶ ወደ ሰፈሩ ሄደ። ያም ሆኖ ዮዪኪ የወላጆቹ ነገር ስላሳሰበው ከባለቤቱ ከታትሱኮ ጋር ወደ ወላጆቹ ለመሄድ አሰበ፤ በዚህ ጊዜ ሱናሚው እየተቃረበ መሆኑን የሚገልጽ ዜና ሰማ።

በመሆኑም ወደ ሌላ መጠለያ በፍጥነት ሄዱ፤ ይሁን እንጂ በሩ በፍርስራሽ ተዘግቶ ስለነበረ ወደ ሕንፃው መግባት አልቻሉም። ከዚያም ጥላሸት የሚመስለው በአቅራቢያው የነበረ የእንጨት መሰንጠቂያ ሕንፃ በጎርፉ እየተነዳ እነሱ ወዳሉበት አቅጣጫ ሲመጣ አዩ። በዚህ ጊዜ ታትሱኮ “እንሩጥ!” ብላ ጮኸች።

በመጨረሻም ከፍ ባለ አካባቢ ወደሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ግቢ ደረሱ። በዚያም ሱናሚው አካባቢውን በሙሉ ጠራርጎ ሲወስደው ተመለከቱ። አንዲት ሴት “ቤቴን ጎርፍ ወሰደው” አለች። ሦስት አራተኛ የሚሆነው የሪኩዜንታካታ ክፍል የወደመ ሲሆን የዮዪኪ ወላጆችም በጎርፍ ተወሰዱ። የአባቱ አስከሬን ጨርሶ ባይገኝም የእናቱ አስከሬን ከጊዜ በኋላ ተገኝቷል።

ቶሩ አደጋው በደረሰ ጊዜ በኢሺኖማኪ የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ፋብሪካ ውስጥ እየሠራ ነበር። አነስተኛ መጠን የነበረው የመጀመሪያው ነውጥ ጋብ ሲል ከአደጋው ለማምለጥ ሮጦ ወደ መኪናው ሄደ። ከነውጡ በኋላ ሱናሚ እንደሚከሰት ስለጠረጠረ ሰዎች አካባቢውን ጥለው እንዲሸሹ ለማስጠንቀቅ መጮኽ ጀመረ።

ቶሩ እንዲህ ብሏል፦ “መጀመሪያ ላይ ከፍታ ቦታ ላይ ወደሚገኘው ቤቴ ለመሄድ ሞከርኩ፤ ሆኖም በመኪና መጨናነቅ ምክንያት መንገድ ተዘጋጋብኝ። መኪና ውስጥ እያለሁ ሱናሚው በአቅራቢያችን ወዳለች ከተማ እንደደረሰ በሬዲዮ ሰማሁ። ሱናሚው እኔ ወዳለሁበት አካባቢ ከደረሰ ማምለጥ እንድችል የመኪናዬን መስኮት ከፈትኩ። ወዲያውኑ 2 ሜትር ከፍታ ያለው ጥቁር ውኃ እያስገመገመ እኔ ወዳለሁበት አቅጣጫ መጣ። ሱናሚው ከፊቴ የነበሩትን መኪናዎች መኪናዬ ወዳለችበት አቅጣጫ አሽቀንጥሮ ከወረወራቸው በኋላ ሁላችንንም ጠራርጎ ወደ የብሱ የመሃል ክፍል ወሰደን።

“ከመኪና ውስጥ እንደምንም ብዬ በመስኮት ወጣሁ፤ ነገር ግን በዘይት የተበከለ መጥፎ ሽታ ያለው ጎርፍ ተቀበለኝ። ጎርፉም እያንከባለለ ወስዶ አንድ የመኪና ጋራዥ ውስጥ አስገባኝ፤ በዚህ ጊዜ ደረጃውን በመያዝ ወደ ሁለተኛ ፎቅ ወጣሁ። ሦስት ሰዎችን በብዙ ትግል ወደ ላይ ጎትቼ በማውጣት ማዳን ችያለሁ። በፎቁ ላይ ከነበርነው ሰዎች መካከል የተወሰንነው እየጨመረ ከመጣው ጎርፍና ሌሊት ላይ ይጥል የነበረው በረዶ ካስከተለው ቅዝቃዜ መትረፍ ቻልን። ይሁን እንጂ ለእርዳታ ሲጣሩ የነበሩ ሰዎችን ማዳን አልቻልንም።”

በኢዋቴ ክፍለ ግዛት ካማኢሺ ውስጥ የምትኖረው ሚዶሪ ከርዕደ መሬቱ ቀደም ብሎ ከአያቶቿ ጋር ጥሩ ጊዜ አሳልፋ ነበር። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ገና ማጠናቀቋ ስለነበር ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ እንደ ልብ መንቀሳቀስ ለማይችሉት የወንድ አያቷ ዲፕሎማዋን ለማሳየት ሄዳ ነበር። አያቷም ዲፕሎማዋን ጮክ ብለው ካነበቡ በኋላ ለጉብዝናዋ ሚዶሪን አመሰገኗት። ርዕደ መሬቱ የተከሰተው እንዲህ ያለ አስደሳች ጊዜ ካሳለፉ ከአምስት ቀናት በኋላ ነበር።

ሚዶሪና እናቷ ዩኮ ርዕደ መሬቱ ሱናሚ እንደሚያስከትል ስለተገነዘቡ የሚዶሪን አያቶች አካባቢውን ለቅቀው እንዲሸሹ ጎተጎቷቸው። ይሁን እንጂ የወንድ አያትየው “አይ፣ አልሄድም። ሱናሚ እዚህ አካባቢ ድረስ መጥቶ አያውቅም” አሉ። የሚዶሪን አያት ተሸክመው ከቤት ለማውጣት የሞከሩ ቢሆንም መሸከም ስላቃታቸው የሚረዳቸው ሰው ፍለጋ ሄዱ። ይሁንና በዚህ ጊዜ ሱናሚው ወደ ባሕሩ ዳርቻ ደርሶ ነበር። በአቅራቢያው ባለ ኮረብታማ ቦታ ያሉ ሰዎች “ቶሎ በሉ! ሩጡ!” እያሉ ይጮኹ ነበር። ሱናሚው ደርሶ ቤቶቹን አንድ በአንድ እየጠራረገ ወሰዳቸው። ሚዶሪ በጭንቀት እየተራወጠች በሚርገበገብ ድምፅ “አያቴ! አያቴ!” እያለች ሁለቱንም አያቶቿን ትጣራ ነበር። የወንድ አያቷ አስከሬን ከጊዜ በኋላ ቢገኝም የሴት አያቷ አስከሬን ግን ፈጽሞ ሊገኝ አልቻለም።

እርዳታ ለማቅረብ የተደረገ ርብርብ

የጃፓን መንግሥት ከመላው ጃፓን የተውጣጡ የእሳት አደጋ ሠራተኞችን፣ ፖሊሶችንና የመከላከያ ኃይሎችን አደጋው ወደተከሰተበት ቦታ በፍጥነት ላከ። ከ130,000 የሚበልጡ ሰዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ሕይወት በማዳንና እርዳታ በማቅረቡ ተግባር ላይ ተሰማሩ። ከጊዜ በኋላም ሌሎች አገሮችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በዚህ ሥራ ላይ መሳተፍ ጀመሩ። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሕይወት አድን ቡድኖችና የሕክምና ሠራተኞች ፈጥነው ደረሱ። እነዚህ ሰዎች በሕይወት የተረፉ ሰዎችን መፈለግ፣ የሕክምና እርዳታ መስጠትና ፍርስራሾችን ማጽዳት ጀመሩ።

የተለያዩ ድርጅቶች አባሎቻቸውን ለመርዳት ጥረት አድርገዋል። እንዲህ ካደረጉት መካከል የይሖዋ ምሥክሮችም ይገኙበታል። ዓርብ ከሰዓት ከተከሰተው ርዕደ መሬትና ሱናሚ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ዘወትር አብረዋቸው ለአምልኮ የሚሰበሰቡትን ሰዎች ደኅንነት ማጠያየቅ ጀመሩ። ይሁን እንጂ በብዙ ቦታዎች መንገዶች በፍርስራሽ ተዘግተው የነበረ ሲሆን የኤሌክትሪክና የስልክ አገልግሎትም ተቋርጧል። አደጋው በጣም ሰፊ ክልሎችን የሚሸፍን ስለነበር ሰዎችን ፈልጎ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነበር።

በፉኩሺማ ክፍለ ግዛት ሶማ ውስጥ ባለ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ የሚያገለግል ታካዩኪ የተባለ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ፣ አስፈሪ በነበረው በዚያ ዓርብ ከሰዓት በኋላ ማግኘት የቻለው ጥቂት ቤተሰቦችን ብቻ ነበር። እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ሌሎቹን በማግስቱ ለመፈለግ አሰብኩ። ጎህ ሲቀድ መጀመሪያ ላይ በመኪና ከዚያም በእግሬ እየተዘዋወርኩ እስከ ምሽት ድረስ ስፈልጋቸው ዋልኩ። የጉባኤያችንን አባላት ለማግኘት መጠለያዎችን ጨምሮ ወደ 20 የተለያዩ ቦታዎች ሄድኩ። ሳገኛቸው ጥቅሶችን የማነብላቸው ከመሆኑም ሌላ አብሬያቸው እጸልይ ነበር።”

በኢሺኖማኪ የሚኖረው ሹንጂ እንዲህ ብሏል፦ “የእምነት አጋሮቻችንን የሚፈልጉ ቡድኖችን አቋቋምን። አደጋው ወደተከሰተበት ስፍራ ስንደርስ ያየነውን ነገር ማመን አቃተን። መኪኖች በኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ላይ ተንጠልጥለው፣ ቤቶች አንዱ በአንዱ ላይ ተነባብረውና ፍርስራሹ ከቤቶቹ ቁመት በላይ እስኪሆን ድረስ ተከምሮ አየን። በአንድ መኪና ጣሪያ ላይ የሞተ ሰው ተመለከትን፤ ሰውየው የሞተው በሌሊቱ ቅዝቃዜ የተነሳ ሳይሆን አይቀርም። ሌላ መኪና ደግሞ ተገልብጦ በሁለት ቤቶች መካከል ተንጠልጥሏል። በውስጡም አንድ የሞተ ሰው ነበር።”

ሹንጂ የእምነት አጋሮቹን በመጠለያዎች ውስጥ ሲያገኛቸው ደስ አለው። “ከእነሱ ጋር ስገናኝ ለእኔ ምን ያህል ውድ እንደሆኑ ተገነዘብኩ” ብሏል።

‘ይህን ያህል ፈጥናችሁ ትመጣላችሁ ብለን አልጠበቅንም!’

ዩኢ እና ሚዙኪ የሚባሉ ሁለት ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች የሚኖሩት በሚያጊ፣ ሚናሚሳንሪኩ ሲሆን ጎረቤታሞች ነበሩ። የመጀመሪያው ነውጥ ጋብ ሲል ፈጥነው ከቤት ሲወጡ በአጋጣሚ ተገናኙ። ሁለቱም ወደ አንድ ከፍታ ቦታ ሮጡ። አሥር ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ቤቶቻቸውን ጨምሮ መላው ከተማ በማዕበል እየተጠራረገ ሲወሰድ ተመለከቱ።

ዩኢ እና ሚዙኪ በአንድ መጠለያ ውስጥ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮችን ሲያገኙ አብረው ጸለዩ። በማግሥቱ ጠዋት የጉባኤያቸው አባላትና በአቅራቢያቸው ያለ ጉባኤ ወንድሞች ተራራውን አቋርጠው ምግብና ሌሎች ነገሮችን አመጡላቸው። ዩኢ እና ሚዙኪ “እንደምትመጡ እናውቅ ነበር፤ ይህን ያህል ፈጥናችሁ ትመጣላችሁ ብለን ግን አልጠበቅንም!” በማለት በአድናቆት ተናገሩ።

ከቶሜ ጉባኤ የበላይ ተመልካቾች መካከል አንዱ የሆነው ሂዴሃሩ ወደ መጠለያው ሄዶ ነበር። እንደሚከተለው ብሏል፦ “በባሕሩ ዳርቻ የሚኖሩ ጓደኞቻችንን ለማግኘት ሌሊቱን ሙሉ ስፈልግ ነበር። በመጨረሻም ከሌሊቱ በ10:00 አንዳንዶቹ በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ እንደተጠለሉ የሚገልጽ ወሬ ሰማሁ። ከጠዋቱ 1:00 ላይ አሥር የምንሆነው ተሰባስበን ሩዝ ካዘጋጀን በኋላ ሦስታችን ምግቡን ይዘን በመኪና ሄድን። አብዛኞቹ መንገዶች ተዘጋግተው ነበርከብዙ ልፋት በኋላ የተባለው ትምህርት ቤት ደረስን። ቤታቸውን በአደጋው ያጡ ሰዎችም እንኳ ሌሎችን ለመርዳት በሚደረገው ሥራ ተካፍለዋል።”

መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት

የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት አዘውትረው የሚሰበሰቡ ሲሆን አንዳንድ ጉባኤዎች ስብሰባቸውን የሚያካሂዱት ዓርብ ምሽት ላይ ነው። በሪኩዜንታካታ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችም ስብሰባቸውን የሚያካሂዱት በዚህ ዕለት ነበር፤ ይሁንና ለአምልኮ የሚሰበሰቡበት የመንግሥት አዳራሽ በሱናሚው ተወስዶ ነበር። አንድ የይሖዋ ምሥክር “ለማንኛውም ስብሰባችንን እናድርግ” በማለት ሐሳብ አቀረበ። ስለዚህ ብዙም ጉዳት ያልደረሰበት አንድ ቤት ተመረጠና ለስብሰባ ወደዚያ እንዲመጡ ለጉባኤው አባላት ተነገራቸው።

ኤሌክትሪክ ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም መብራት ለማግኘት ጀነሬተር ተጠቀሙ። በስብሰባው ላይ አሥራ ስድስት ሰዎች ተገኝተው ነበር። የሚኖርበት አፓርተማ በሱናሚው የተወሰደበት ያሱዩኪ የተባለ ወጣት “የደስታ እንባ አነባን። ለእኛ ይህ ከምንም የተሻለ መጠጊያ ሆኖልናል” ብሏል። ሂዴኮ እንደሚከተለው በማለት ገልጻለች፦ “በተደጋጋሚ በሚከሰቱ ከባድ ነውጦች ምክንያት ስብሰባችን ይረበሽ የነበረ ቢሆንም ስብሰባው የነበረብኝን ፍርሃትና ጭንቀት ለመርሳት አስችሎኛል።”

ከዚያን ጊዜ ወዲህ ጉባኤው ስብሰባ ሳያደርግ ቀርቶ አያውቅም። ከሁለት ቀን በኋላ እሁድ ዕለት ለወቅቱ የተመረጠው ንግግር ርዕስ “ከጥፋት የሚድን ዓለም አቀፍ የወንድማማችነት ማኅበር” የሚል ነበር።

በተደራጀ መንገድ የቀረበ እርዳታ

በቶኪዮ አቅራቢያ በኢቢና የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እንዳደረገው ሁሉ የተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማትም ወዲያውኑ የእርዳታ ሥራ ጀምረው ነበር። ርዕደ መሬቱ በተከሰተ ማግስት ማለትም ቅዳሜ ዕለት ቅርንጫፍ ቢሮው በነውጡ ጉዳት የደረሰበትን ሰፊ ክልል ለሦስት ከፈለው። ርዕደ መሬቱ ከተከሰተ ከሦስት ቀን በኋላ ይኸውም ሰኞ ዕለት ከቅርንጫፍ ቢሮው የተላኩ ወኪሎች አካባቢውን ጎበኙ።

የእርዳታ ሥራው በቀጣዮቹ ሳምንታትና ወራትም ቀጥሎ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች የለገሱት ብዙ ቶን የሚመዝን የእርዳታ ቁሳቁስ ተከፋፍሎ ነበር። በአንድ ወቅት 3 የእርዳታ ጣቢያዎች፣ 21 መጋዘኖችና ሌሎች ማዕከሎች የእርዳታ ቁሳቁሶቹን ለማከፋፈል አገልግለዋል። በመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት ውስጥ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ፈቃደኛ ሠራተኞች ከ250 ቶን በላይ ምግብ፣ ልብስና ሌሎች መሠረታዊ ነገሮችን አከፋፍለዋል። በርካታ የይሖዋ ምሥክሮችም እንዲህ ያሉትን አቅርቦቶች ለጎረቤቶቻቸው አካፍለዋል።

የሪኩዜንታካታ እና በአቅራቢያው የሚገኘው የኦፉናቶ ጉባኤዎች አባላት እንደገና የተገነባውን የመንግሥት አዳራሽ ተጠቅመው ሰዎችን በመንፈሳዊ እያጠናከሩ ነው። ይህም የአካባቢው ሰዎች ኑሯቸውን መልሰው ለማቋቋም ሲጥሩ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመወጣት እንዲሁም አውዳሚ የሆነው ርዕደ መሬትና ሱናሚ ካስከተለባቸው የስሜት መቃወስ ለማገገም ይረዳቸዋል። አደጋው በደረሰበት አካባቢ ከነበሩት 14,000 የይሖዋ ምሥክሮች መካከል 12ቱ መሞታቸው የተረጋገጠ ሲሆን ሁለቱ ደግሞ እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም።

የዚህ አስከፊ አደጋ ሰለባ ከሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል ብዙዎቹ በፉኩሺማ ከተማ የሚገኝ አንድ ቤተሰብ ከተናገረው ሐሳብ ጋር የሚመሳሰል አስተያየት ሰጥተዋል። ቤተሰቡ እንዲህ ብሏል፦ “ከአደጋው በሸሸንበት ጊዜ ይዘን የሄድነው አንድ አንድ ሻንጣ ብቻ ነበር። ይሁን እንጂ የእምነት አጋሮቻችን የሚያስፈልገንን ነገር በሙሉ አሟልተውልናል።” የእውነተኛው አምላክ የይሖዋ አገልጋዮች፣ ኢየሱስና ሐዋርያቱ የተናገሩለት ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር አባላት በመሆናቸው ደስተኞች ናቸው! ይህ የወንድማማች ማኅበር በሱናሚም ሆነ በሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ሊጠፋ የሚችል አይደለም።​—ዮሐንስ 13:34, 35፤ ዕብራውያን 10:24, 25፤ 1 ጴጥሮስ 5:9

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ቀጥሎ የተከሰተው የኑክሌር አደጋ

ሱናሚ በፉኩሺማ ዳይቺ በሚገኘው የኑክሌር ማብለያ ጣቢያ ላይ ያደረሰው ጉዳት በመላው ዓለም ትልቅ የዜና ርዕስ ሆኖ ነበር። ከኃይል ማመንጫው የሚወጣው የሬዲዮአክቲቭ ጨረር በጃፓንና በሌሎች አገሮች ተሰራጨ። ገዳይ የሆነው ጨረር ሊያስከትል ከሚችለው አደጋ የተነሳ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አካባቢውን እንዲለቁ ተደርጎ ነበር።

ሜጉሚ እንዲህ ብላለች፦ “ቤታችን የሚገኘው በኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያው አቅራቢያ ነበር። ርዕደ መሬቱ በተከሰተ ማግስት በኃይል ማመንጫ ጣቢያው ላይ ጉዳት እንደደረሰና አካባቢውን ለቀን መሸሽ እንዳለብን ተነገረን።” የሜጉሚ እህት ናትሱሚ ደግሞ “ሄሊኮፕተሮች በሰማይ ላይ ያንዣብቡ፣ የአደጋ ማስጠንቀቂያ ደወሎች ይጮኹ እንዲሁም ሰዎች አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ የሚገልጽ ማስታወቂያ በተደጋጋሚ ይነገር ነበር” ብላለች። በቀጣዮቹ ሳምንታት ሕዝቡ ወደ ዘጠኝ የተለያዩ ስፍራዎች ሄደ። ሜጉሚና ናትሱሚ በሁለት ሰዓት ውስጥ ጥቂት ንብረቶቻቸውን ለመውሰድ ብቻ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ተፈቀደላቸው።

በ60ዎቹ ዓመታት ዕድሜ ላይ የሚገኙት ቺካኮ፣ በፉኩሺማ ክፍለ ግዛት በምትገኘው በናሚ ይኖሩ ነበር። እሳቸውም እንዲህ ብለዋል፦ “ርዕደ መሬቱ ሲከሰት ለመጠለያነት ወደተዘጋጀ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ስፍራ ሄድኩ። እዚያም እኔና ሁለቱ ልጆቼ ከዋናው ርዕደ መሬት በኋላ በተደጋጋሚ በተከሰቱት ኃይለኛ ነውጦች የተነሳ እንቅልፍ በዓይናችን ሳይዞር አነጋን። በማግስቱ ጠዋት 1:00 ላይ በሌላ ከተማ ወደሚገኝ መጠለያ በአፋጣኝ እንድንሄድ ተነገረን።

“መንገዶቹ በመኪና ተጨናንቀው ስለነበረ መጠለያው ወዳለበት ቦታ የደረስነው ከሰዓት በኋላ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ነበር። እዚያም በኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያው ላይ ፍንዳታ መከሰቱን ሰማን። ወደ ቤታችን ቶሎ እንመለሳለን ብዬ አስቤ ስለነበር ይዘን የሄድነው ነገር አልነበረም።” እሳቸውና ቤተሰባቸው ከአንዱ ስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ ሲንከራተቱ ከቆዩ በኋላ ከመኖሪያ ቤታቸው ርቆ በሚገኝ አካባቢ አፓርተማ አገኙ።

[የሥዕል ምንጭ]

Photo by DigitalGlobe via Getty Images

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ለሁላችንም የሚሆን ትምህርት

ቀደም ሲል የተጠቀሰው በሪኩዜንታካታ የሚኖረውና አብዛኛውን ንብረቱን ያጣው ዮዪኪ “ቁሳዊ ነገሮች ዋስትና ሊሆኑ እንደማይችሉ እኔ ራሴ ምሥክር ነኝ” ብሏል። እንዲህ ያለው አባባል ከረጅም ጊዜ በፊት ጀምሮ በአምላክ አገልጋዮች በተለይም ከኢየሱስ በተማሩ ሰዎች ሲነገር የነበረ ነው። ኢየሱስ ቁሳዊ ንብረቶች፣ የአምላክን ሞገስና በረከት ከማግኘት ጋር ሲወዳደሩ ያን ያህል ትልቅ ቦታ እንደሌላቸው አስተምሮ ነበር።​—ማቴዎስ 6:19, 20, 33, 34

ሌላው የምናገኘው ትምህርት ደግሞ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን ነው። የአደጋ ሰለባ መሆናችን ወይም በሕይወት መትረፋችን ይህን በማድረጋችን ላይ የተመካ ነው። በጃፓን ያላንዳች ማመንታት በፍጥነት ከፍ ወዳለ ቦታ የሸሹ ሰዎች ሕይወታቸው ተርፏል።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ካርታ/​ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ጃፓን

ቶኪዮ

ካማኢሺ

ሪኩዜንታካታ

ሚናሚሳንሪኩ

ኢሺኖማኪ

ሶማ

ፉኩሺማ የኑክሌር ማብለያ ጣቢያ

ኢቢና

የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ

[ሥዕሎች]

ሪኩዜንታካታ፣ ኢዋቴ

ሶማ፣ ፉኩሺማ

ኢሺኖማኪ፣ ሚያጊ

ካማኢሺ፣ ኢዋቴ

ሚናሚሳንሪኩ፣ ሚያጊ

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሀሩሚ እና ታዳዩኪ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዮዪኪ እና ታትሱኮ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዩኮ እና ሚዶሪ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቶሩ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቶሩ ሲነዳው የነበረው መኪና

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ታካዩኪ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሹንጂ

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሚዙኪ እና ዩኢ

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሂዴሃሩ

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የእርዳታ ሠራተኞች በሥራ ላይ

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሪኩዜንታካታ የመንግሥት አዳራሽ ከሱናሚው በኋላ

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከሦስት ወራት በኋላ እየተካሄደ ያለው የመልሶ ግንባታ ሥራ

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ተሠርቶ የተጠናቀቀ የመንግሥት አዳራሽ

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

JIJI PRESS/AFP/Getty Images