በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥቃት ተሰነዘረ

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥቃት ተሰነዘረ

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥቃት ተሰነዘረ

መጽሐፍ ቅዱስን ወይም ቅዱሳን መጻሕፍት እያልን የምንጠራቸውን የመጻሕፍት ስብስብ ለማዘጋጀት ከ1,600 ዓመታት በላይ ወስዷል። ከእነዚህ መጻሕፍት ውስጥ የመጀመሪያዎቹን የጻፈው ሙሴ ነው፤ የመጨረሻው መጽሐፍ ደግሞ የተጻፈው ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወለደ ከመቶ ዓመት ገደማ በኋላ ሲሆን ጸሐፊው ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዱ ነው።

ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዳያነቡ ለማገድ የሚደረገው ጥረት ረጅም ዘመን አስቆጥሯል፤ ክርስቶስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከብዙ ዓመታት በፊት የጀመረው ይህ ሙከራ በመካከለኛው ዘመንም የቀጠለ ሲሆን እስከ ዘመናችን ድረስ ዘልቋል። እንዲህ ያለውን ጥረት በተመለከተ ተመዝግቦ የምናገኘው ጥንታዊ ታሪክ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመወለዱ ከ600 ዓመት በፊት ይኖር በነበረው ኤርምያስ የተባለ የአምላክ ነቢይ ዘመን የተፈጸመ ነው።

ተወዳጅ ባልሆነው መልእክት ላይ ጥቃት ተሰነዘረ

ነቢዩ ኤርምያስ፣ የጥንቷን ይሁዳ ኃጢአተኛ የሆኑ ነዋሪዎች የሚያወግዝና አካሄዳቸውን ካልለወጡ ዋና ከተማቸው ኢየሩሳሌም እንደምትጠፋ የሚያስጠነቅቅ መልእክት በመጽሐፍ ጥቅልል ላይ እንዲጽፍ በአምላክ ታዝዞ ነበር። የኤርምያስ ጸሐፊ የነበረው ባሮክ መልእክቱን በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ሕዝብ በተሰበሰበበት ጮክ ብሎ አነበበው። ይህንኑ መልእክት ለይሁዳ መሳፍንትም አነበበላቸው፤ እነሱም ጥቅልሉን ወደ ንጉሥ ኢዮአቄም ወሰዱት። ንጉሡ የአምላክ ቃል ሲነበብለት መልእክቱ አላስደሰተውም። በመሆኑም ጥቅልሉን ቆራርጦ አቃጠለው።​—ኤርምያስ 36:1-23

ከዚያ በኋላ አምላክ ኤርምያስን እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “ሌላ ብራና ወስደህ፣ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም ባቃጠለው በመጀመሪያው ብራና ላይ የነበረውን ቃል ሁሉ ጻፍበት።” (ኤርምያስ 36:28) ይህ ከሆነ ከ17 ዓመታት ገደማ በኋላ አምላክ በኤርምያስ በኩል እንደተነበየው ኢየሩሳሌም ጠፋች፣ ከገዥዎቿ ብዙዎቹ ተገደሉ እንዲሁም ነዋሪዎቿ በግዞት ወደ ባቢሎን ተወሰዱ። ኤርምያስ ባስጻፈው ጥቅልል ላይ ስለነበረው መልእክት እንዲሁም ጥቅልሉን ለማጥፋት ከተደረገው ጥረት ጋር ስለተያያዙት ሁኔታዎች የሚገልጸው ታሪክ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በኤርምያስ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ እስከ ዘመናችን ድረስ ተጠብቆ ቆይቷል።

መጽሐፍ ቅዱስን ማቃጠሉ ቀጠለ

በቅድመ ክርስትና ዘመን የአምላክን ቃል ለማቃጠል የሞከረው ኢዮአቄም ብቻ አልነበረም። የግሪክ ግዛት መከፋፈሉን ተከትሎ እስራኤል በሰሉሲድ ሥርወ መንግሥት ሥር ወደቀች። ከ175 እስከ 164 ዓ.ዓ. የገዛው አንቲኦከስ ኤጲፋኔስ የተባለ የሰሉሲድ ሥርወ መንግሥት ንጉሥ፣ በግዛቱ በሙሉ የግሪክ ባሕል እንዲሰርጽ ለማድረግ ፈልጎ ነበር። ይህን ዓላማውን ለማሳካት ሲል አይሁዳውያን የግሪካውያንን አኗኗር፣ ባሕልና ሃይማኖት እንዲቀበሉ ለማስገደድ ሞከረ።

በ168 ዓ.ዓ. ገደማ አንቲኦከስ በኢየሩሳሌም የነበረውን የይሖዋ ቤተ መቅደስ መዘበረ። ለይሖዋ አምልኮ በተዘጋጀው መሠዊያ ላይ ዙስ ለተባለው የግሪካውያን አምላክ ሌላ መሠዊያ ሠራ። በተጨማሪም ሰንበት እንዳይከበርና አይሁዳውያን ወንዶች ልጆቻቸውን እንዳይገርዙ ከለከለ። ይህን ትእዛዝ መጣስ በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል ነበር።

አንቲኦከስ፣ አይሁዳውያን ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ ለማድረግ ከተጠቀመባቸው ዘዴዎች አንዱ ሕጉ የተጻፈባቸውን የመጽሐፍ ጥቅልሎች በሙሉ ማጥፋት ነበር። አንቲኦከስ በመላው እስራኤል ዘመቻ ቢያደርግም የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን ቅጂዎች በሙሉ ማጥፋት አልቻለም። በእስራኤል የሚኖሩ አንዳንድ አይሁዳውያን ጥቅልሎቹን በጥንቃቄ በመደበቅ በእሳት ተቃጥለው ከመጥፋት እንዲተርፉ ሳያደርጉ አልቀሩም፤ በሌሎች አገሮች ይኖሩ የነበሩ አይሁዳውያንም የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ተጠብቀው እንዲቆዩ እንዳደረጉ ይታወቃል።

የዲዮቅላጢያን አዋጅ

ቅዱሳን መጻሕፍትን ለማጥፋት የተነሳው ሌላው እውቅ መሪ የሮም ንጉሠ ነገሥት የሆነው ዲዮቅላጢያን ነበር። በ303 ዓ.ም. ዲዮቅላጢያን በክርስቲያኖች ላይ እንግልት እንዲደርስ የሚያዝዙ ተከታታይ አዋጆችን አውጥቶ ነበር። ይህም አንዳንድ የታሪክ ምሁራን “ታላቁ ስደት” ብለው የጠሩትን መከራ አስከትሏል። የመጀመሪያው አዋጅ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች እንዲቃጠሉና የክርስቲያኖች መሰብሰቢያ ቦታዎች እንዲወድሙ የሚያዝዝ ነበር። በቨርጂኒያ ዩኒቨርስቲ የሃይማኖታዊ ጥናቶች ፕሮፌሰር የሆኑት ሃሪ ጋምብል እንዲህ ብለዋል፦ “ዲዮቅላጢያን፣ ማንኛውም የክርስቲያኖች ማኅበረሰብ የትም ይኑር የት፣ የመጻሕፍት ስብስብ እንደሚኖረውና እነዚህ መጻሕፍት ለማኅበረሰቡ ሕልውና ወሳኝ እንደሆኑ ያምን ነበር።” የፓለስቲና ተወላጅ የሆነ የቂሳርያው ዩሲቢየስ የተባለ የአብያተ ክርስቲያናት ታሪክ ጸሐፊ “የጸሎት ቤቶች ዶግ አመድ ሲሆኑና በመንፈስ መሪነት የተጻፉትና ቅዱስ የሆኑት መጻሕፍት በገበያ መሃል ወደ እሳት ሲጣሉ በገዛ ዓይናችን ተመልክተናል” ብሏል።

የዲዮቅላጢያን አዋጅ ከወጣ ከሦስት ወር በኋላ ሲርታ (የዛሬዋ ኮንስታንቲን) የምትባለው የሰሜን አፍሪካ ከተማ ከንቲባ፣ ክርስቲያኖች በእጃቸው ያሉትን “የሕጉን መጻሕፍት” እና “የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች” በሙሉ እንዲያስረክቡ አዝዞ እንደነበር ይነገራል። በወቅቱ የተጠናቀሩ የታሪክ ዘገባዎች እንደሚገልጹት የመጽሐፍ ቅዱስን ቅጂዎች እንዲቃጠሉ ከመስጠት ይልቅ መሠቃየትንና መሞትን የመረጡ ክርስቲያኖች ነበሩ።

የጥቃቶቹ ዓላማ

ኢዮአቄምም ሆነ አንቲኦከስና ዲዮቅላጢያን ዓላማቸው የአምላክን ቃል ጨርሶ ማጥፋት ነበር። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥፋት የተደረጉት ሙከራዎች በሙሉ ከሽፈዋል። ከዲዮቅላጢያን በኋላ የተነሱ የሮም ገዥዎች ደግሞ ወደ ክርስትና እንደተለወጡ መናገር ጀመሩ። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት አላባራም። ለምን?

ገዥዎቹም ሆነ የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች መጽሐፍ ቅዱሶች የተቃጠሉት ይህን መጽሐፍ ለማጥፋት ታስቦ ሳይሆን መጽሐፉ በተራው ሰው እጅ እንዳይገባ ለማድረግ እንደነበረ ገልጸዋል። ይሁንና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ይህን ማድረግ የፈለጉት ለምንድን ነው? ቤተ ክርስቲያኗስ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዳያነቡ ለማገድ ምን እስከ ማድረግ ደርሳለች? እስቲ እንመልከት።