በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምትናገረው ነገር ለውጥ ያመጣል?

የምትናገረው ነገር ለውጥ ያመጣል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

የምትናገረው ነገር ለውጥ ያመጣል?

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንዲትን አረጋዊት ሴት በትሕትና አነጋግረዋት ከተለያዩ በኋላ ሴትየዋ ግትር እንደሆነችና መጀመሪያውኑም ወደ እሳቸው እንድትቀርብ መደረግ እንዳልነበረበት በመናገር አጉረመረሙ። ይህን ሲሉ ማይክራፎኑ እንዳልጠፋ አላወቁም ነበር። ሕዝቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ሴትየዋ የተናገሩትን ነገር ሲሰማ ደነገጠ። ከስምንት ቀን በኋላ በተደረገው ምርጫ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በድጋሚ ለመመረጥ ቢወዳደሩም አንዴ ስማቸው ስለጎደፈ ሳያሸንፉ ቀሩ።

ማንም ሰው ቢሆን አንደበቱን ፍጹም በሆነ መንገድ መቆጣጠር አይችልም። (ያዕቆብ 3:2) ያም ሆኖ ከላይ የተገለጸው ገጠመኝ የምትናገረው ነገር ለውጥ እንደሚያመጣ ያመለክታል። የምትናገረው ነገርም ሆነ የምትናገርበት መንገድ በስምህ፣ በሥራህ፣ አልፎ ተርፎም ከሰዎች ጋር ባለህ ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

ይሁን እንጂ የምትናገረው ነገር ሌላም የሚጠቁመው ነገር እንዳለ ታውቃለህ? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው አነጋገርህ ትክክለኛውን ማንነትህን የሚገልጥ በመሆኑ በልብህ ውስጥ ያለውን የሚያሳይ መስኮት ነው ሊባል ይችላል። ኢየሱስ “አንደበት የሚናገረው በልብ ውስጥ የሞላውን ነው” ብሏል። (ማቴዎስ 12:34) የምትናገራቸው ቃላት አንተነትህን ለይተው ስለሚያሳውቁ በሌላ አባባል ፍላጎትህን፣ አስተሳሰብህንና ስሜትህን ስለሚያንጸባርቁ የአነጋገር ልማድህን በጥሞና መመርመርህ በጣም አስፈላጊ ነው። በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው? እስቲ ቀጥሎ የቀረበውን ሐሳብ ተመልከት።

የአነጋገር ልማድህን ማሻሻል የምትችለው እንዴት ነው?

ከመናገር በፊት የሚቀድመው ሐሳብ ነው። ስለዚህ የምትናገረውን ነገር ለማሻሻል ከፈለግህ አስተሳሰብህን ማስተካከል ይኖርብሃል። የአምላክን ቃል በሥራ ላይ ማዋልህ አስተሳሰብህን እንዴት እንደሚለውጠውና ይህ ደግሞ በምላሹ በአነጋገርህ ላይ ምን ለውጥ እንደሚያስከትል ልብ በል።

ልብህን በጥሩ ነገሮች ሙላው። መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ ስለሚባሉት ነገሮች ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “እውነት የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ቁም ነገር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ በመልካም የሚነሳውን ነገር ሁሉ፣ በጎ የሆነውን ሁሉና ምስጋና የሚገባውን ነገር ሁሉ ማሰባችሁን አታቋርጡ።”​ፊልጵስዩስ 4:8

ይህን ጥሩ ምክር መከተልህ ተገቢ ያልሆኑ አስተሳሰቦችን እንድታስወግድ ይረዳሃል። የምታያቸውና የምታነባቸው ነገሮች በአስተሳሰብህ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ አስታውስ። ስለዚህ አፍራሽና ንጹሕ ያልሆኑ አስተሳሰቦችን ማስወገድ ከፈለግህ በመጀመሪያ በአስተሳሰብህ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ነገሮችን አስወግድ። በሌላ አማርኛ ዓመፅና ጸያፍ ነገሮች ከሞሉበት መዝናኛ መራቅ ይኖርብሃል ማለት ነው። (መዝሙር 11:5፤ ኤፌሶን 5:3, 4) ከዚህ ይልቅ አእምሮህ ንጹሕና ገንቢ በሆኑ ሐሳቦች ላይ እንዲያተኩር አድርግ። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን እንድታደርግ ሊረዳህ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ምሳሌ 4:20-27⁠ን፣ ኤፌሶን 4:20-32⁠ን እና ያዕቆብ 3:2-12⁠ን አንብብ። ከዚያም በእነዚህ ጥቅሶች ላይ የተገለጹትን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች በሥራ ላይ ማዋልህ አነጋገርህን ምን ያህል ሊያሻሽለው እንደሚችል ተመልከት። *

ከመናገርህ በፊት አስብ። ምሳሌ 12:18 “ግድ የለሽ ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤ የጠቢብ አንደበት ግን ፈውስን ያመጣል” በማለት ይናገራል። ብዙውን ጊዜ በአነጋገርህ ሌሎችን ‘እንደምትወጋ’ ወይም ስሜታቸውን እንደምትጎዳ ከተገነዘብህ ከመናገርህ በፊት ለማሰብ ብትጥር ጥሩ ነው። በ⁠ምሳሌ 15:28 ላይ የሚገኘውን “የጻድቅ ሰው ልብ የሚሰጠውን መልስ ያመዛዝናል፤ የክፉ ሰው አፍ ግን ክፋትን ያጐርፋል” የሚለውን ግሩም ምክር በተግባር ለማዋል ጥረት አድርግ።

ግብ ለማውጣት ሞክር። እስቲ በሚቀጥለው ወር እንዲህ ለማድረግ ግብ አውጣ፦ በተለይ በተናደድክበት ሰዓት መጀመሪያ ወደ አእምሮህ የሚመጣውን ነገር ላለመናገር ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ከዚህ ይልቅ በዚህ ርዕሰ ትምህርት ውስጥ የተጠቀሱትን ጥቅሶች አሰላስልባቸው፤ እንዲሁም ጥበብ በተሞላበትና ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ብሎም በተረጋጋ ሁኔታ ለመናገር የታሰበበት ጥረት አድርግ። (ምሳሌ 15:1-4, 23) ይሁን እንጂ የአነጋገር ልማድህን ለማሻሻል ይህ ብቻ በቂ አይደለም።

አምላክ እንዲረዳህ ጸልይ። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ “መጠጊያዬና አዳኜ እግዚአብሔር ሆይ፤ የአፌ ቃልና የልቤ ሐሳብ፣ በፊትህ ያማረ ይሁን” በማለት ጸልዮ ነበር። (መዝሙር 19:14) አንተም ወደ ይሖዋ ስትጸልይ አንደበትህን እሱን በሚያስደስትና ሌሎች ከአንተ ጋር ሲሆኑ ደስ እንዲላቸው በሚያደርግ መንገድ መጠቀም እንደምትፈልግ ንገረው። ምሳሌ 18:20, 21 “መልካም ንግግርህ በሚያስከትለው ውጤት ተደስተህ ትኖራለህ። የምትናገረው ሕይወትህን ሊያድን ወይም ሊያጠፋ ይችላል” ይላል።​—የ1980 ትርጉም

የአምላክን ቃል እንደ መስታወት ተጠቀምበት። መጽሐፍ ቅዱስ እንደ መስታወት ነው፤ በመሆኑም በዚህ መስታወት ተጠቅመህ ራስህን በደንብ መመርመር ትችላለህ። (ያዕቆብ 1:23-25) ለምሳሌ በሚከተሉት ሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ላይ ስታሰላስል ‘አነጋገሬና ያተረፍኩት ስም ከጥቅሶቹ ጋር ይስማማል?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።

“የለዘበ መልስ ቍጣን ያበርዳል፤ ክፉ ቃል ግን ቍጣን ይጭራል።” (ምሳሌ 15:1) የምትናገረው በለዘበና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ነው?

“እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎችን የሚያንጽና ሰሚዎቹን ሊጠቅም የሚችል ማንኛውም መልካም ቃል እንጂ የበሰበሰ ቃል ከቶ ከአፋችሁ አይውጣ።” (ኤፌሶን 4:29) አነጋገርህ አብረውህ ያሉትን ሰዎች የሚያንጽ ነው?

“ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ምንጊዜም ለዛ ያለውና በጨው የተቀመመ ይሁን።” (ቆላስይስ 4:6) ተፈታታኝ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙህ ጊዜም እንኳ ንግግርህ ለዛ ያለውና ሌሎች ሲሰሙት የማይከብዳቸው ዓይነት እንዲሆን ትጥራለህ?

ራስህን በመስታወት አይተህ ማስተካከል የሚገባህን ነገር ካስተካከልክ ሌሎች ከአንተ ጋር መሆን ይበልጥ የሚያስደስታቸው ከመሆኑም በላይ ስለ ራስህ ጥሩ ስሜት ይኖርሃል። እንደዚሁም እንደ መስታወት በተቆጠረው የአምላክ ቃል ተጠቅመህ አነጋገርህን የምታሻሽል ከሆነ ተመሳሳይ ጥቅም ታገኛለህ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.9 www.watchtower.org በሚለው ድረ ገጽ ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ተጨማሪ ጽሑፎችን ማንበብ ትችላለህ።

ይህን አስተውለኸዋል?

● አነጋገርህ ምን ያሳያል?​—ሉቃስ 6:45

● ሌሎችን ማናገር ያለብህ እንዴት ነው?​—ኤፌሶን 4:29፤ ቆላስይስ 4:6

● አነጋገርህን ለማሻሻል የትኞቹን ተግባራዊ እርምጃዎች መውሰድ ትችላለህ?​—መዝሙር 19:14፤ ፊልጵስዩስ 4:8

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የምንናገረው ነገር ስማችንን እና ከሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት ይነካል