“ግሩምና ድንቅ” ሆነህ ተፈጥረሃል!
“ግሩምና ድንቅ” ሆነህ ተፈጥረሃል!
የተለያዩ እንስሳት ያላቸውን አስደናቂ ችሎታ ስትመለከት አንዳንድ ጊዜ እንደ እነሱ መሆን በቻልኩ ብለህ አስበህ ታውቃለህ? ምናልባትም አልባትሮስ እንደተባለችው ወፍ ወደ ሰማይ ለመምጠቅ፣ እንደ ዶልፊን ለመዋኘት፣ እንደ ንስር ከርቀት ለማየት ወይም እንደ አቦ ሸማኔ በፍጥነት ለመሮጥ ትመኝ ይሆናል።
አዎን፣ እንስሳት አንዳንድ አስደናቂ ችሎታዎች አሏቸው። እኛም ብንሆን አስደናቂ ችሎታዎች አሉን! የሰው አካል አስደናቂ ችሎታ ካለው ማሽን ጋር ተመሳስሏል። እውነት ነው፣ እኛ ከማሽን በእጅጉ እንበልጣለን። የሰው ልጆች የፈጠራ ችሎታ፣ የማወቅ ጉጉት፣ ብልሃት እንዲሁም ነገሮችን በዓይነ ሕሊናችን የማየት ችሎታ አለን፤ እነዚህ ችሎታዎች ያሰብነውን ማንኛውንም ነገር ለመሥራት የሚያገለግሉንን ማሽኖች ለመፈልሰፍ ያስችሉናል። ከድምፅ ሞገድ በሚበልጥ ፍጥነት እንኳ መብረር እንዲሁም ሰፊ የሆኑ ውቅያኖሶችን በመርከብ ማቋረጥ አሊያም በሰርጓጅ መርከብ ውስጥ ለውስጥ መጓዝ እንችላለን፤ በሕዋ ውስጥ እስከ 14 ቢሊዮን የብርሃን ዓመት ርቀት ላይ ያሉ ነገሮችን ማየት እንዲሁም ሕያው የሆነ ሴልን በጥልቀት መመርመር እንችላለን፤ በተጨማሪም መድኃኒቶችን መሥራትና የተለያዩ ሕክምናዎችን መስጠት እንዲሁም በሽታዎችን መርምረን ለማግኘትና ለማከም የሚረዱ ቴክኖሎጂዎችን መፈልሰፍ እንችላለን።
ጤናማ የሆኑና ጥሩ ሥልጠና ያገኙ ሰዎች ከላይ በተገለጹት ቴክኖሎጂዎች ሳይታገዙም እንኳ አስደናቂ ነገሮችን ማከናወን ይችላሉ። የኦሎምፒክ ውድድሮችን እንደ ምሳሌ ብንወስድ የጂምናስቲክ ስፖርተኞች፣ ከከፍታ ቦታ ላይ ተወርውረው ውኃ ውስጥ የመግባት ትርዒት የሚያሳዩ ዋናተኞች፣ በበረዶ ላይ የሚንሸራተቱና ትርዒት የሚያሳዩ ተወዳዳሪዎች እንዲሁም ሌሎች ስፖርተኞች ከፍተኛ ቅልጥፍና፣ ክህሎትና የፈጠራ ችሎታ የሚንጸባረቅበት ብሎም ማራኪ የሆነ እንቅስቃሴ በማሳየት ተመልካቾችን ያስደምማሉ።
ታዲያ እኛ የሰው ልጆች ያሉንን ልዩ ስጦታዎች ታደንቃለህ? እርግጥ ነው፣ በኦሎምፒክ ውድድሮች ላይ የምትካፈል ስፖርተኛ ላትሆን ትችላለህ፤ ይሁን እንጂ አመስጋኝ እንድትሆን የሚያነሳሱህ ብዙ ስጦታዎች አሉህ። አንድ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ እንዲህ ዓይነት አድናቆት ነበረው፤ ለአምላክ ባቀረበው መዝሙር ላይ “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ” ብሎ ነበር። * (መዝሙር 139:14) ይህን የመዝሙራዊውን አባባል በአእምሮህ ይዘህ ከዚህ ቀጥሎ ያሉትን ርዕሶች እንድታነባቸው እንጋብዝሃለን። እነዚህ ርዕሶች አስደናቂ ከሆኑት የሰው የአካል ክፍሎች መካከል አንዳንዶቹን በዝርዝር የሚያብራሩ ከመሆኑም ሌላ የሰው ልጆችን ከሌሎች ፍጥረታት የተለየን ስለሚያደርጉን የላቁ ባሕርያት ያወሳሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.5 ከፍጥረትና ከዝግመተ ለውጥ ጋር በተያያዘ ስለሚነሱት ጥያቄዎች ማወቅ የሚፈልጉ አንባቢዎች፣ ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው? እና የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች የተሰኙትን ብሮሹሮች ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። እነዚህን ብሮሹሮች በአካባቢያችሁ ካሉ የይሖዋ ምሥክሮች ወይም ከዚህ መጽሔት አዘጋጆች ማግኘት ይቻላል።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ኃይል በሚቆጥብ መንገድ የተሠራ
በሁለት እግራችን ቀጥ ብለን የምንቆም መሆናችን በጣም ኃይል ይቆጥባል፤ ምክንያቱም ሰውነታችን ቀጥ ብሎ እንዲቆም ለማድረግ ጡንቻዎቻችን ብዙ መሥራት አያስፈልጋቸውም። የነርቭ ሕክምና ሳይንስ ተመራማሪ የሆኑት ጆን ስኮይልስ “ለመቆም የሚያስፈልገን ኃይል ስንተኛ ከሚያስፈልገን የሚበልጠው በ7 በመቶ ብቻ ነው” በማለት ተናግረዋል። እኚህ ምሑር አክለው እንደተናገሩት አንድ ውሻ (በአራቱም እግሮቹ) በሚቆምበት ጊዜ የሚጠቀመው ኃይል በሚተኛበት ጊዜ ከሚጠቀመው በ70 በመቶ ይበልጣል።