በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የማር ጉንዳኖችና የሚሠሩት ጣፋጭ የበረሃ ምግብ

የማር ጉንዳኖችና የሚሠሩት ጣፋጭ የበረሃ ምግብ

የማር ጉንዳኖችና የሚሠሩት ጣፋጭ የበረሃ ምግብ

የሚኒየ የተባለችው አቦሪጂናዊት ወዳጃችን ከበረሃ ሚስጥሮቿ መካከል አንዱን ልታካፍለን ነው። በማዕከላዊ አውስትራሊያ ከአሊስ ስፕሪንግስ በስተሰሜን ወዳለው በጥሻ የተሸፈነ ደረቅ አካባቢ ወሰደችን፤ ከዚያም አሸዋማውን መሬት በጥንቃቄ መመርመር ጀመረች። የሚኒየ፣ ጣፋጭ ወደሆነ ምግብ የሚመሩንን ጥቃቅን ፍጥረታት የግራር ዝርያ ከሆኑት መልገ ከሚባሉት ዛፎች ሥር መፈለጓን ተያያዘችው። እነዚህ ፍጥረታት የማር ጉንዳኖች ናቸው።

የሚኒየ፣ ጉንዳኖቹ በአሸዋማው መሬት ውስጥ የሠሯቸውን እንደ ዋሻ ያሉ መተላለፊያዎች ተከትላ መሬቱን ባለ በሌለ ኃይሏ መቆፈር ጀመረች። ብዙም ሳይቆይ አንድ ሜትር ያህል ጥልቀት ያለውና ለመቀመጥ የሚያስችል ስፋት ያለው ጉድጓድ ቆፈረች። የሚኒየ “የማር ጉንዳኖችን ለማግኘት በዓመቱ ውስጥ በማንኛውም ጊዜ መቆፈር የሚቻል ቢሆንም በበጋ በጣም ስለሚሞቅ በቅዝቃዜው ወቅት ይሻላል” በማለት በጉድጓዱ ውስጥ ሆና ተናገረች። የጉንዳኖቹን መተላለፊያ የማግኘት ልምድ ያላት የሚኒየ መተላለፊያዎቹን በትኩረት ስትመለከት አየናት። “የትኛውን መተላለፊያ መከተል እንዳለባችሁ ማወቅ ያስፈልጋችኋል” አለችን።

የሚኒየ ብዙም ሳትቆይ መኖሪያቸውን አገኘችው። በውስጡ ቢያንስ 20 የሚያህሉ የማር ጉንዳኖች ነበሩ፤ ብርቱካንማ ቀለም ባለው ፈሳሽ የተሞላው የጉንዳኖቹ ሆድ በጣም ተወጥሮ የወይን ፍሬ ያክላል። ጉንዳኖቹ ሆዳቸው ከመቀብተቱ የተነሳ መንቀሳቀስ ስለማይችሉ ከአፈር የተሠራውን የዋሻውን ጣሪያ ቆንጥጠው በመያዝ ተንጠልጥለዋል። የሚኒየ በደቂቃዎች ውስጥ ከበርካታ የጉንዳን ዋሻዎች ከመቶ በላይ የማር ጉንዳኖችን ሰበሰበች። “የእነዚህ ጉንዳኖች ማር በዱር ከምናገኛቸው እጅግ ጣፋጭ ምግቦች አንዱ ነው” አለችን።

ሕያው የማር ማሰሮዎች

የማር ጉንዳኖች እስከ አሁን ከሚታወቁት ከ10,000 በላይ የጉንዳን ዝርያዎች መካከል በጣም ለየት ያሉ ናቸው። ማር ሠርተው በማር እንጀራ ውስጥ ከሚያከማቹት ከንቦች በተለየ መልኩ የማር ጉንዳኖች የአበባ ማሩን የሚያከማቹት ሪፕሊት ተብለው በሚጠሩት ሠራተኛ ጉንዳኖች ሆድ ውስጥ ነው። የጉንዳኑ መንጋ የምግብ እጥረት በሚያጋጥመው ጊዜ ምግብ የሚያገኘው ከእነዚህ ሕያው “የማር ማሰሮዎች” ነው።

አንድ ጉንዳን ምግብ ለማስቀመጥ ወይም ለመውሰድ ሲፈልግ በአንቴናዎቹ የሪፕሊቱን አንቴናዎች ነካ ነካ በማድረግ ምልክት ይሰጠዋል። በዚህ ጊዜ ሪፕሊቱ አፉን በማላቀቅ “የማር ማሰሮውን” ክዳን ይከፍታል። ወደ ሪፕሊቱ ሆድ ፈሳሽ የሚገባበትንና ከሆዱ የሚወጣበትን መንገድ የሚቆጣጠር ልዩ የሆነ መክፈቻና መዝጊያ አለ። አንድ ሪፕሊት ለበርካታ ወራት የሚኖር ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ ሌሎቹ ጉንዳኖች በሆዱ ያለውን ማር በተደጋጋሚ ጊዜያት ሊወስዱና እንደገና ሊሞሉት ይችላሉ።

ሪፕሊቶች አብዛኛውን ሕይወታቸውን የሚያሳልፉት ከቦታ ቦታ ሳይንቀሳቀሱ ቢሆንም ከመሬት በታች ስለሚኖሩ ከሀሩርና ነፍሳትን አድነው ከሚበሉ ፍጥረታት ከለላ የሚያገኙ ከመሆኑም ሌላ በውኃ እጦት አይቸገሩም። በጨለማ በተዋጠው በዚህ ቦታ ከመሬት ሥር የሚኖሩት ሪፕሊቶች ራሳቸውን ከባክቴሪያና ከፈንገስ ለመከላከል ከአንድ ልዩ ዕጢ የሚመነጭ ፀረ ባክቴሪያ ፈሳሽ ሰውነታቸውን ይቀባሉ።

ታዲያ “ማሩ” የሚመጣው ከየት ነው? ማር የሚሆነው ምግብ የሚገኘው በግራር ዛፎች ላይ ካለው ፈሳሽና የአበባ ማር ነው። ኤፊድ የሚባሉ ጥቃቅን ነፍሳት ይህን የተፈጥሮ ጭማቂ ይመጡታል። ከዚያም ሠራተኛ ጉንዳኖች ኤፊዶች ከቀሰሙት ስኳር ላይ ትርፍ የሆነውን ይወስዳሉ፤ ይህ ጣፋጭ ፈሳሽ ሃኒዲው (የማር ጠብታ) ተብሎ ይጠራል። ሠራተኛ ጉንዳኖቹ በቀጥታ ከዛፎች ላይም የአበባ ማር ይሰበስባሉ። በመጨረሻም ሠራተኛ ጉንዳኖቹ የሰበሰቡትን ፈሳሽ ለሪፕሊቶቹ ያጎርሷቸዋል። ብዙም የማይንቀሳቀሱት ሪፕሊቶች የሚያስፈልጋቸው ምግብ ጥቂት ስለሆነ አብዛኛው የማር ጠብታ “በማር ባንኩ” ውስጥ ይከማቻል!

ታዲያ ኤፊዶቹ ባዷቸውን ይቀራሉ ማለት ነው? በጭራሽ። መጀመሪያ ነገር፣ ጉንዳኖቹ በቂ የአበባ ፈሳሽ ያስቀሩላቸዋል። እንዲሁም ጉንዳኖቹ ኤፊዶቹን ከጥገኛ ተውሳኮችና ሊበሏቸው ከሚችሉ ሌሎች ፍጥረታት ይጠብቋቸዋል። አዎን፣ ጉንዳኖቹም ሆኑ ኢፊዶቹ በዚህ መንገድ እርስ በርስ እየተረዳዱ ስለሚኖሩ ሁለቱም ተጠቃሚዎች ናቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ ጕንዳን ሂድ፤ ዘዴውን አስተውለህ ጠቢብ ሁን፤ አዛዥ የለውም፤ አለቃም ሆነ ገዥ የለውም፤ ሆኖም ግን በበጋ ምግቡን ያከማቻል፤ በመከርም ወቅት ቀለቡን ይሰበስባል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 6:6-8) በእርግጥም ጉንዳኖች ተባብረው የሚሠሩ፣ በጣም የተደራጁና ታታሪዎች በመሆናቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለው ሐሳብ ምንኛ እውነት ነው! እነዚህ ችግር የማይበግራቸው የበረሃ ነዋሪዎች እንዲህ ባለው የማይመች አካባቢ ይህን የመሰለ ጣፋጭ ምግብ ማምረት መቻላቸው እንዴት ያስደንቃል!

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የተወጠረው የማር ጉንዳኗ ሆድ በጣፋጭ የአበባ ማር ተሞልቷል

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል ምንጭ]

Pages 10, 11, top: M Gillam/photographersdirect.com; page 11: © Wayne Lynch/age fotostock