በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

 የወጣቶች ጥያቄ

ምንም ነገር የማይሳካልኝ ሰው ነኝ?

ምንም ነገር የማይሳካልኝ ሰው ነኝ?

“ራሴን ከጓደኛዬ ጋር ሳወዳድር የበታችነት ስሜት ይሰማኝ ነበር። እሷ ሁሉም ነገር በቀላሉ ይሳካላታል፤ ማለቴ እንዲሳካላት ለማድረግ ምንም የምትለፋ አትመስልም! ይህ ደግሞ ‘እኔ የማይሳካልኝ ምን ሆኜ ነው’ ብዬ እንዳስብ አደረገኝ። የራሴ ጠላት እኔው ሆንኩ።”​—አኔት *

ብቃት እንደሌለህ የሚሰማህ መሆኑ አዳዲስ ነገሮችን ከመሞከር ወደኋላ እንድትል አድርጎህ ይሆን? የምታከብራቸው ሰዎች በቅን ልቦና ተነሳስተው የሚሰጡህ አንዳንድ አስተያየቶች በራስህ እንዳትተማመን አድርጎሃል? ቀደም ሲል የፈጸምካቸው ስህተቶች ተስፋ እንድትቆርጥና ‘ከዚህ ሁሉ ቢቀርብኝስ’ እንድትል አድርገውሃል? ከሆነ ምንም የማይሳካለት ዓይነት ሰው ነኝ ብለህ ታስባለህ ማለት ነው። ታዲያ አይሳካልኝም የሚለው ፍርሃትህ እውነተኛም ይሁን በሐሳብህ የፈጠርከው እንዲህ ያለውን አፍራሽ ስሜት ማሸነፍ የምትችለው እንዴት ነው?

ለመጨረሻው ጥያቄ መልስ ማግኘትህ ይጠቅምሃል፤ ምክንያቱም ማንኛውም ሰው ይዋል ይደር እንጂ የማይሳካለት ጊዜ መኖሩ አይቀርም። (ሮም 3:23) ይሁን እንጂ ያሰቡት ሳይሳካ ሲቀር በጥረታቸው የሚገፉ ሰዎች መንፈሰ ጠንካራ ናቸው። በሌላ አባባል ስህተታቸውን ካጤኑ በኋላ ከወደቁበት ተነስተው እንደገና ይሞክራሉ ማለት ነው። በዚህ ጊዜ ስኬታማ የመሆናቸው አጋጣሚ ሰፊ ይሆናል! እንግዲያው ፈታኝ ሊሆኑብህ የሚችሉ ሦስት ሁኔታዎችን እንመልከት፦ ላይሳካ ይችላል ብሎ መፍራት፣ አልተሳካም ብሎ ማሰብ እና በእርግጥ ሳይሳካ ሲቀር የሚሰማህ ስሜት።

ባይሳካስ የሚል ፍርሃት → ወደፊት ሊያጋጥምህ የሚችለውን ነገር በማሰብ መጨነቅ።

መጥፎ መጥፎ ነገሮችን ስለምታስብ ሙከራህ ሁሉ ስኬታማ የመሆኑ አጋጣሚ በጣም የመነመነ እንደሆነ ይሰማሃል፤ ስለሆነም ምንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ ትላለህ።

ችግሩ የት ጋ እንዳለ ለይተህ እወቅ። ቢሳካልህ ደስ በሚልህ ሆኖም ብትሞክረው እንደማይሆንልህ እርግጠኛ እንደሆንክ ከሚሰማህ ነገር አጠገብ ✔ አድርግ።

  • በክፍል ጓደኞችህ ፊት ስለ እምነትህ መናገር

  • ሥራ ለመቀጠር ማመልከት

  • በሕዝብ ፊት መናገር

  • ስፖርት መጫወት

  • መዘመር ወይም የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት

  • ሌላ ․․․․․

በደንብ አስብበት። እስቲ ምልክት ስላደረግክበት ነገር ቆም ብለህ አስብ፤ ከዚያም ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ሊያጋጥሙህ የሚችሉት ነገሮች ምን እንደሆኑ ለማወቅ ሞክር።

‘ቢሆን ደስ የሚለኝ ነገር ምንድን ነው?’

․․․․․

‘ይደርስብኛል ብዬ የምፈራው ነገር ምንድን ነው?’

․․․․․

አሁን ደግሞ ላይሳካ ይችላል የሚለው ፍርሃት እንዳለ ሆኖ የመረጥከውን ነገር መሞከር የሚገባህ ለምን እንደሆነ አንድ ምክንያት ጻፍ።

․․․․․

 የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ። ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ እንዲመራ ይሖዋ ተልእኮ በሰጠው ጊዜ መጀመሪያ ላይ የታየው ሊያጋጥመው የሚችለው ችግር ነው። አምላክን “ቃሌን ባይቀበሉስ” አለው። ከዚያም ስላሉበት ጉድለቶች ማሰብ ጀመረ። “እኔ ኮልታፋና ንግግር የማልችል ሰው ነኝ” በማለት ተናገረ። ይሖዋ እንደሚረዳው ቃል ከገባለት በኋላም እንኳ ሙሴ “ጌታ ሆይ፣ እባክህ ሌላ ሰው ላክ” ሲል ተማጸነ። (ዘፀአት 4:1, 10, 13) ሙሴ በመጨረሻ የተሰጠውን ተልእኮ የተቀበለ ሲሆን ከዚያ በኋላ ምን እንዳደረገ ታሪኩን የምናውቀው ነው። ሙሴ አምላክ በሚሰጠው አመራር እየታገዘ የእስራኤልን ሕዝብ ለ40 ዓመታት መርቷል።

ምን ብታደርግ ይሻላል? ንጉሥ ሰለሞን “እጅህ የሚያገኘውን ሥራ ሁሉ በሙሉ ኀይልህ ሥራው” በማለት ጽፏል። (መክብብ 9:10) ስለዚህ ላይሳካልኝ ይችላል የሚለው ፍርሃት እንዲያሽመደምድህ ከመፍቀድ ይልቅ የምትመኘውን ነገር ለማከናወን የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ። ከጠበቅከው በላይ የተሻለ ውጤት ያገኘህባቸውን ጊዜያት ለምን አታስብም? በእነዚህ ወቅቶች ያገኘኸው ስኬት ለራስህ ከምትሰጠው ግምት ጋር በተያያዘ ምን አስተማረህ? ያገኘኸው ትምህርት አሁን የሚያስቸግርህን አይሳካልኝም የሚለውን ፍርሃት ለማሸነፍ ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?

ለጥቆማ ያህል፦ አስፈላጊ ከሆነ ወላጅህን ወይም በራስ የመተማመን መንፈስህን ከፍ እንድታደርግ ሊረዳህ የሚችል አንድ የጎለመሰ ወዳጅህን አስተያየት እንዲሰጡህ ጠይቅ። *

አልተሳካም የሚል ስሜት → አልሆነልኝም ብለህ እንድታስብ ባደረገህ ነገር ላይ ብቻ ማተኮር።

አንተ የምትመኘውን ነገር ሌላ ሰው በተሳካ ሁኔታ እንዳከናወነው ስትመለከት ራስህን ከእሱ ጋር በማወዳደር እንዳልተሳካልህ ይሰማሃል።

ችግሩ የት ጋ እንዳለ ለይተህ እወቅ። ራስህን የምታወዳድረው ከማን ጋር ነው? አንተ እንዳልተሳካልህ ሆኖ የተሰማህ ግለሰቡ ያደረጋቸውን የትኞቹን ነገሮች በማየትህ ነው?

․․․․․

በደንብ አስብበት። ያ ሰው ተሳካለት ማለት በእርግጥ አንተ አልተሳካልህም ማለት ነው? በቅርብ ያጋጠመህን አንድ ሁኔታ ከታች ባለው ክፍት ቦታ ላይ ጻፍ፤ ለምሳሌ ደህና ውጤት ብታገኝበትም ሌላ ልጅ ከአንተ የተሻለ ነጥብ ያመጣበትን ፈተና መጥቀስ ትችላለህ።

․․․․․

አሁን ደግሞ ያደረግከው ጥረት የማያስቆጭ ነው እንድትል የሚያደርግህን ምክንያት ጻፍ።

․․․․․

 የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ። ቃየን፣ አቤል ባደረገው ነገር ይሖዋ መደሰቱን በተመለከተ ጊዜ “ቁጣው ነደደ።” ይሖዋ ቃየንን የቅናት ስሜቱን እንዲያስወግድ አስጠንቅቆት ነበር፤ በሌላ በኩል ግን ከፈለገ ሊሳካለት እንደሚችል ያለውን እምነት ገልጾለታል። “መልካም ብታደርግ ተቀባይነትን አታገኝምን?” ብሎታል። *​—ዘፍጥረት 4:6, 7

ምን ብታደርግ ይሻላል? በልብህ ውስጥም እንኳ ቢሆን “የፉክክር መንፈስ” እንዲነሳሳ መፍቀድ የለብህም፤ ከዚህ ይልቅ ሌሎች ባገኙት ስኬት ደስተኛ ሁን። (ገላትያ 5:26፤ ሮም 12:15) በሌላ በኩል ደግሞ ጉረኛ መሆን ባያስፈልግህም የራስህን ልዩ ችሎታዎች ለይተህ እወቅ። መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዱ ሰው የራሱን ሥራ ምንነት ፈትኖ ያሳይ፤ ከዚያም . . . ከራሱ ጋር ብቻ በተያያዘ የሚመካበት ነገር ያገኛል” በማለት ይናገራል።​—ገላትያ 6:4

በእርግጥ ሳይሳካ ሲቀር → በሆነው ነገር ተስፋ ቆርጠሃል።

ከዚህ በፊት ሞክረህ ያልተሳካልህን ነገር ማሰብህ ጥረትህን እርግፍ አድርገህ እንድትተው አድርጎሃል።

ችግሩ የት ጋ እንዳለ ለይተህ እወቅ። ሞክረኻቸው ካልተሳኩልህ ውስጥ ይበልጥ ተስፋ አስቆራጭ ሆኖ ያገኘኸው የትኛው ነው?

․․․․․

መንፈሰ ጠንካራ የሆነ ሰው ቢወድቅም ይነሳል፤ አስፈላጊ ከሆነም የሚሰጠውን እርዳታ ይቀበላል

በደንብ አስብበት። ከላይ የጠቀስከው ነገር በእርግጥ ምንም የማይሳካልህ ሰው እንደሆንክ የሚያስቆጥርህ ነው? ለምሳሌ በአንድ ዓይነት ድክመት ተሸንፈህ መጥፎ ድርጊት ፈጸምክ እንበል። ታዲያ ይህ ምንም ተስፋ እንደሌለህ የሚያሳይ ነው? ወይስ እርዳታ ማግኘት እንደሚያስፈልግህ የሚጠቁም ምልክት ነው? ስፖርት እየተጫወትክ ሳለ ብትወድቅና አንድ ሰው ወደ ጨዋታው እንድትመለስ ለማድረግ እጁን ቢዘረጋልህ እርዳታውን እንደምትቀበል ጥርጥር የለውም። ታዲያ አንድ ነገር ሳይሳካልህ ሲቀር ለምን ይህን ዘዴ አትጠቀምም? ስለ ችግርህ ልታወያየው የምትችል የአንድ ሰው ስም ከዚህ በታች ጻፍ። *

․․․․․

የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ። ሐዋርያው ጳውሎስ በነበሩበት ድክመቶች ተስፋ የቆረጠባቸው ጊዜያት ነበሩ። “እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ” በማለት ጽፏል። (ሮም 7:24) ይሁንና ከሁኔታው መረዳት እንደምንችለው ጳውሎስ ማንነቱ የሚለካው ባለበት አለፍጽምና አለመሆኑን ተገንዝቦ ነበር። “መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫውን እስከ መጨረሻ ሮጫለሁ፤ እምነትን ጠብቄያለሁ” በማለት ጽፏል።​—2 ጢሞቴዎስ 4:7

ምን ብታደርግ ይሻላል? በፈጸምካቸው ስህተቶች ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ ያሉህን መልካም ጎኖችም አስብ። ይሖዋ የሚያተኩረው በመልካም ጎኖችህ ላይ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ “[አምላክ] የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለም” በማለት ይናገራል።​—ዕብራውያን 6:10፤ መዝሙር 110:3

ይህን አስታውስ፦ ማንም ሰው ፍጹም አይደለም። ሁሉም ሰው በሆነ ጉዳይ ላይ የማይሳካለት ጊዜ መኖሩ አይቀርም። መንፈሰ ጠንካራነትን የምታዳብር ከሆነ ትልቅ ሰው ስትሆን በእጅጉ ሊጠቅምህ የሚችል አንድ ባሕርይ ይኖርሃል። ምሳሌ 24:16 “ጻድቅ ሰባት ጊዜ እንኳ ቢወድቅ ይነሣል” ይላል። አንተም እንዲህ ዓይነት ሰው መሆን ትችላለህ!

^ አን.3 ስሟ ተቀይሯል።

^ አን.23 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የግንቦት 2010 ንቁ! ከገጽ 26-28 ተመልከት።

^ አን.31 ቃየን የይሖዋን ምክር መስማት አልፈለገም። ቃየን ላይ የደረሰው ውድቀት አንተ በሌላ ሰው ስኬት ሊያድርብህ የሚችለውን የቅናት ስሜት መቆጣጠር እንደሚያስፈልግህ ጠንከር ያለ ትምህርት ይሰጣል።​—ፊልጵስዩስ 2:3

^ አን.36 ከባድ ስህተት የፈጸመ አንድ ክርስቲያን ጉዳዩን ለጉባኤ ሽማግሌ ቢናገር ይጠቀማል።​—ያዕቆብ 5:14, 16