ልዩ የሚያደርጉን ባሕርያት
ልዩ የሚያደርጉን ባሕርያት
የግንባታ ሠራተኛ የሆነ አንድ የ50 ዓመት ሰው በኒው ዮርክ ከተማ ባቡር ጣቢያ ባቡር እየጠበቀ ነበር። ባቡሩ እየመጣ ሳለ በአጠገቡ የነበረ አንድ ወጣት ተደናቅፎ ሐዲዱ ላይ ወደቀ። የግንባታ ሠራተኛው በዚያች ቅጽበት ዘልሎ ሐዲዱ ውስጥ በመግባት ባቡሩ እስኪያልፍ ድረስ ወጣቱ ላይ ተኛበት፤ ይህ ሰው ወጣቱን እንዳይንቀሳቀስ አድርጎ ይዞት ስለቆየ ባቡሩ ሁለቱንም ሳይጎዳቸው በላያቸው አለፈ።
በናዚ የግዛት ዘመን በአውሮፓ የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች “ሃይል ሂትለር!” ለማለት ፈቃደኞች አልነበሩም፤ ምክንያቱም ሃይል የሚለው የጀርመንኛ ቃል “አዳኝ” ማለት ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛቸው እንደሆነና ከእሱ ውጪ “መዳን በሌላ በማንም [እንደማይገኝ]” አጥብቀው ያምናሉ። (የሐዋርያት ሥራ 4:12) ሂትለርን ለማምለክ ፈቃደኞች ባለመሆናቸው የተነሳ ብዙዎቹ ከቤታቸው በኃይል ተወስደው ወደ ማጎሪያ ካምፖች ተልከዋል፤ በእርግጥ እዚያም ቢሆን የሚመሩበትን ክርስቲያናዊ አቋም አላላሉም።
አንድ ሰው ከራሱ ደኅንነት ይልቅ ለሌላ ሰው ምናልባትም ጨርሶ ለማያውቀው ሰው ደኅንነት ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚችል እንዲሁም የሚመራባቸውን ሥርዓቶች ከመጣስ ይልቅ ነፃነቱን መሥዋዕት እንደሚያደርግ ከላይ የተጠቀሱት ምሳሌዎች ማስረጃ ይሆናሉ። ታዲያ እንደነዚህ ያሉት ባሕርያት፣ የሰው ልጆች በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ እንስሳት መሆናቸውን ያሳያሉ? ወይስ ከእንስሳት የላቅን ፍጥረታት መሆናችንን ያመለክታሉ? ይህን በአእምሮህ ይዘህ እስቲ ቀጥሎ የቀረቡትን ጥያቄዎች አስብባቸው፦
● እኛ የሰው ልጆች፣ ሕሊና ማለትም ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ነገር የመለየት ውስጣዊ ችሎታ ያለን ለምንድን ነው?
● አስደናቂ ስለሆኑት የፍጥረት ሥራዎች ስናስብ በከፍተኛ የአድናቆት ስሜት የምንዋጠው ለምንድን ነው?
● ሙዚቃ፣ ሥዕል፣ ግጥምና ሌሎች የሥነ ጥበብ ሥራዎች በሕይወት ለመኖር የግድ ባያስፈልጉንም በእነዚህ ነገሮች የምንደሰተው ለምንድን ነው?
● በማንኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ ሰዎች ማለት ይቻላል መንፈሳዊ ፍላጎት ያላቸው ለምንድን ነው?
● ‘የተፈጠርኩት ለምንድን ነው?’ እንዲሁም ‘የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው?’ እያልን የምንጠይቀው ለምንድን ነው?
● አንድ ሰው ሲሞት የተለያዩ የቀብር ሥነ ሥርዓቶችን የምናከናውነው ለምንድን ነው?
● በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኙ ብዙ ሰዎች ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለ የሚያምኑት ለምንድን ነው? በውስጣችን ያለው ለዘላለም የመኖር ፍላጎት በዝግመተ ለውጥ የወረስነውና ፈጽሞ እውን ሊሆን የማይችል ምኞት ነው?
ለጥያቄዎቻችን መልስ የምናገኘው ከየት ነው?
ለእነዚህ ጥያቄዎች ከሁሉ በላይ ምክንያታዊ የሆኑ መልሶችን በዓለም ላይ በሰፊው ተሰራጭቶ በሚገኘው ቅዱስ መጽሐፍ ይኸውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማግኘት ይቻላል።
ይህ መጽሐፍ ከዚህ በታች ስለቀረቡት ጉዳዮች ምን እንደሚል እንመልከት፦የሰው አፈጣጠር። የሰው ዘር የተፈጠረው በአምላክ “መልክ” ነው፤ ይህም ሲባል የፈጣሪያችንን ባሕርያት የማንጸባረቅ ችሎታ አለን ማለት ነው። (ዘፍጥረት 1:27) በመሆኑም የመጀመሪያው ሰው “የአምላክ ልጅ” ተብሏል።—ሉቃስ 3:38
የመውደድና የመወደድ ፍላጎታችን። “አምላክ ፍቅር ነው” በማለት 1 ዮሐንስ 4:8 ይናገራል። በአምላክ መልክ የተፈጠርን በመሆናችን ከተወለድንበት ጊዜ ጀምሮ እስከምንሞትበት ጊዜ ድረስ ፍቅር ማግኘት እንፈልጋለን። ክርስቲያን የሆነው ሐዋርያው ጳውሎስ “ፍቅር . . . ከሌለኝ ከንቱ ነኝ” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 13:2) በተጨማሪም “የተወደዳችሁ ልጆች በመሆን አምላክን የምትኮርጁ ሁኑ” ብሏል።—ኤፌሶን 5:1
መንፈሳዊ ፍላጎታችን። “ሰው ከይሖዋ አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ ሊኖር አይችልም።” (ማቴዎስ 4:4) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት አምላክ የተናገራቸው ቃላት ስለ እሱ ባሕርያትና ለእኛ ስላለው ዓላማ ይገልጻሉ። መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ሳናረካ እውነተኛ ትርጉም ያለው ሕይወት መኖር አንችልም።
የምንሞትበት ምክንያት። “ኃጢአት የሚከፍለው ደሞዝ ሞት ነው፤ አምላክ የሚሰጠው ስጦታ ግን . . . የዘላለም ሕይወት ነው።” (ሮም 6:23) ኃጢአት ማለት አምላክ ከሥነ ምግባርና ከአምልኮ ጋር በተያያዘ ካወጣቸው መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር አለመቻል ማለት ነው። ይሁን እንጂ አምላክ፣ ኃጢአትን አስወግዶ እሱን የሚወዱትንና የሚታዘዙትን ሁሉ መጀመሪያ ወዳሰበው ሁኔታ በመመለስ ገነት በሆነች ምድር ላይ ዘላለማዊ ሕይወት የመስጠት ዓላማ አለው።—መዝሙር 37:10, 11, 29፤ ሉቃስ 23:43
አንተስ ይኖሩኛል ብለህ አስበሃቸው እንኳ የማታውቅ ክህሎቶችን በማዳበር ሕይወትን በተሟላ መልኩ ማጣጣም ትፈልጋለህ? ስለ ፈጣሪህና ለአንተ ስላለው አስደናቂ ዓላማ ይበልጥ ለማወቅ ትፈልጋለህ? ከሆነ የመንፈሳዊ እውነት ምንጭ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን እንድትመረምር እንጋብዝሃለን። አሁንም ሆነ ወደፊት፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለማወቅ የምታደርገውን ጥረት ያህል ከፍተኛ ደስታ ሊሰጥህ የሚችል ሌላ ነገር የለም።—ማቴዎስ 5:3፤ ዮሐንስ 17:3
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ከጨቅላነታችን ጀምሮ ፍቅር እንሻለን
ጄራልድ ሽሮደር የተባሉት የሳይንስ ተመራማሪ “የሕፃናት አእምሮ ማበረታቻና ፍቅር ይሻል” በማለት ተናግረዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እናቶች “ልጆቻቸውን የሚወዱ” መሆን እንዳለባቸው ይናገራል፤ ይህ መመሪያ የተሰጠው በተለይ ለእናቶች ቢሆንም ሁሉም ወላጆች ይህን ተግባራዊ ማድረጋቸው ምንኛ አስፈላጊ ነው!—ቲቶ 2:4
[በገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለመኖር የግድ አስፈላጊ ባይሆኑም እንኳ ደስታ የሚሰጡን በርካታ ውብና አስደሳች ነገሮች አሉ
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሰዎች ከምግብና ከውኃ በተጨማሪ የፈጣሪያቸውን መመሪያ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል