በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጤንነትህን ማሻሻል ትችላለህ

ጤንነትህን ማሻሻል ትችላለህ

ጤንነትህን ማሻሻል ትችላለህ

በሩሲያ የሚኖረው ሩስታም ሕይወቱ በውጥረት የተሞላ ነው። ቀደም ባሉት ዓመታት የነበሩት መጥፎ ልማዶች አሁን ዋጋ እያስከፈሉት መሆኑን ተገንዝቧል። ማጨሱንና አልኮል ከልክ በላይ መጠጣቱን አቁሟል። ያም ሆኖ ቀኑን ሙሉ ቢሮ ውስጥ ተቀምጦ ሲሠራ መዋሉ ሰውነቱን እንዳልፈሰፈሰበት ይሰማዋል።

ሩስታም ሥራ የሚጀምረው ጧት ሁለት ሰዓት ላይ ሲሆን እስከ አራት ሰዓት ድረስ በንቃት መሥራት የሚችለው ከስንት አንዴ ነበር፤ ከዚህም በላይ በሽታ ያጠቃው ነበር። በዚህ ምክንያት በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ላይ ማስተካከያ አደረገ። ታዲያ ምን ውጤት አገኘ? “ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ በዓመት ከሁለት ቀን በላይ ታምሜ የተኛሁበትን ጊዜ አላስታውስም” በማለት ተናግሯል። “ጥሩ ስሜት ይሰማኛል ማለትም ንቁና ቀልጣፋ ሆኛለሁ፤ ከዚህም በላይ ደስተኛ ነኝ!”

ባለትዳርና የሁለት ትንንሽ ልጆች አባት የሆነው ራም የሚኖረው በኔፓል ነው። ሠፈራቸው ጽዳት የጎደለው ከመሆኑም በላይ የትንኝና የዝንብ መራቢያ ነው። ቀደም ሲል ራምና ቤተሰቡ የመተንፈሻ አካል ችግርና የዓይን ሕመም ያጠቃቸው ነበር። ራምና ቤተሰቡ ጤናቸው በእጅጉ እንዲሻሻል ያስቻለ ለውጥ አድርገዋል።

ጤናችን በእጃችን!

ሀብታምም ይሁኑ ድሃ፣ ብዙ ሰዎች የሚከተሉት ልማድ ከጤናቸው ጋር ተያያዥነት እንዳለው አይገነዘቡም። ጥሩ ጤንነት የዕድል ጉዳይ እንደሆነ ወይም ጤናቸውን ለመጠበቅ ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ይሰማቸዋል። እንዲህ ያለው አመለካከት ብዙዎች ጤናቸውን ለማሻሻልና ውጤታማ ሕይወት ለመምራት የሚያስችላቸውን ጥረት እንዳያደርጉ እንቅፋት ይሆንባቸዋል።

እንደ እውነቱ ከሆነ ግን፣ የገንዘብ አቅምህ ምንም ይሁን ምን የራስህንም ሆነ የቤተሰብህን ጤንነት ለመጠበቅና በእጅጉ ለማሻሻል ልትወስዳቸው የምትችላቸው መሠረታዊ እርምጃዎች አሉ። ታዲያ እንዲህ ማድረግ የሚክስ ነው? እንዴታ! ይበልጥ ደስተኛ መሆን ብሎም ሕይወትህ በአጭሩ እንዳይቀጭ ማድረግ ትችላለህ።

ወላጆች ትምህርት በመስጠትም ሆነ ምሳሌ በመሆን ልጆቻቸው ጥሩ ልማዶችን እንዲያዳብሩ መርዳት ይችላሉ፤ እንዲህ ማድረጋቸው ልጆቻቸው የተሻለ ጤንነት እንዲኖራቸው ይረዳል። ይህን ማድረግ የሚጠይቀው ጊዜና ወጪ ብንታመም ከሚደርስብን ሥቃይ፣ ብንተኛ ከምናባክነው ጊዜና ለሕክምና ከምናወጣው ገንዘብ አንጻር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ እንደሚባለው ነው።

በሚቀጥሉት ርዕሶች ላይ ሩስታምንና ራምን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ጤናቸው እንዲሻሻል የረዷቸውን አምስት ቁልፍ ነገሮች እንመለከታለን። እነዚህ ቁልፍ ነገሮች አንተንም ሊረዱህ ይችላሉ!

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሩስታም

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ራምና ቤተሰቡ ንጹሕ የመጠጥ ውኃ አገኙ