በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አምላክ ዲያብሎስን ያላጠፋው ለምንድን ነው?

አምላክ ዲያብሎስን ያላጠፋው ለምንድን ነው?

የአንድን ሰው ችግር ለማስወገድ የሚያስችል ኃይል ቢኖርህ ኖሮ ምን ታደርግ ነበር? ችግሩን አታስወግድለትም? ብዙውን ጊዜ የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት የእርዳታ ሠራተኞች ፈጽሞ የማያውቋቸውን ሰዎች ከሥቃይና ከሞት ለመታደግ ሲሯሯጡ ይታያሉ። ከዚህ በመነሳት አንድ ሰው ‘አምላክ በሰው ልጆች ላይ እየደረሱ ላሉት ፈርጀ ብዙ ችግሮች ተጠያቂ የሆነውን ዲያብሎስን ያላጠፋው ለምንድን ነው?’ የሚል ጥያቄ ያነሳ ይሆናል።

የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት አንድን የከፍተኛ ፍርድ ቤት ችሎት በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። አንድ ነፍሰ ገዳይ፣ የፍርድ ሂደቱን ለማስተጓጎል ካለው ፍላጎት የተነሳ ዳኛው የእሱን ጉዳይ የያዘበት መንገድ ትክክል እንዳልሆነ አልፎ ተርፎም ለእማኝ ዳኞች ጉቦ እንደሰጠ በመናገር ዳኛውን ይወነጅለዋል። በዚህ ምክንያት በርካታ ምሥክሮች የምሥክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተደረገ።

ዳኛው የፍርዱ ሂደት መጓተቱ ብዙ ችግሮችን ሊያስከትል እንደሚችል ስለሚያውቅ ጉዳዩ ቶሎ እልባት እንዲያገኝ ይፈልጋል። ይሁንና ዳኛው፣ ወደፊት ለሚነሱ ተመሳሳይ ጉዳዮች እንደ ምሳሌ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል ውሳኔ ላይ መድረስ እንዲቻል ሁለቱም ወገኖች አሳማኝ ማስረጃ ለማቅረብ የሚያስችላቸውን በቂ ጊዜ ማግኘት እንዳለባቸው ተገንዝቧል።

እንደ ምሳሌ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል ውሳኔ ላይ መድረስ እንዲቻል ሁለቱም ወገኖች አሳማኝ ማስረጃ ለማቅረብ የሚያስችላቸውን በቂ ጊዜ ማግኘት አለባቸው

ታዲያ ይህ ምሳሌ “ዘንዶ፣” “እባብ” እና “ሰይጣን” ተብሎ የሚጠራው ዲያብሎስ “በምድር ሁሉ ላይ ልዑል” በሆነው በይሖዋ ላይ ከሰነዘረው ክስ ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው? (ራእይ 12:9፤ መዝሙር 83:18) ለመሆኑ ዲያብሎስ ማን ነው? በይሖዋ አምላክ ላይ ምን ክስ ሰንዝሯል? አምላክ ዲያብሎስን የሚያጠፋውስ መቼ ነው?

እንደ ምሳሌ የሚታይ የፍርድ ሂደት

ከጊዜ በኋላ ዲያብሎስ የሆነው መልአክ በመጀመሪያ ፍጹም መንፈሳዊ አካል የነበረ ሲሆን ከአምላክ መላእክት  መካከል አንዱ ነበር። (ኢዮብ 1:6, 7) ሆኖም ይህ መልአክ የሰው ልጆች እንዲያመልኩት ከፍተኛ ምኞት ባደረበት ጊዜ ራሱን ዲያብሎስ አደረገ። በዚህም ምክንያት የአምላክን የመግዛት መብት ተገዳደረ። አልፎ ተርፎም አምላክ ታዛዥነት የሚገባው እንዳልሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ገልጿል። በተጨማሪም ሰዎች አምላክን የሚያገለግሉት ከእሱ በረከት ለማግኘት ሲሉ ብቻ እንደሆነ የሚገልጽ ክስ ሰንዝሯል። ሰይጣን እያንዳንዱ ሰው አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥመው ፈጣሪውን ‘ይረግማል’ በማለት ተናግሯል።—ኢዮብ 1:8-11፤ 2:4, 5

ሰይጣን ያነሳቸው እነዚህ ክሶች የኃይል እርምጃ በመውሰድ ብቻ እልባት የሚያገኙ አይደሉም። እንደ እውነቱ ከሆነ አምላክ በኤደን ገነት ውስጥ ዲያብሎስን ወዲያውኑ አጥፍቶት ቢሆን ኖሮ ይህ እርምጃ አንዳንዶችን ዲያብሎስ ትክክል ነው ብለው እንዲያስቡ ሊያደርጋቸው ይችል ነበር። ስለሆነም አምላክ በሌሎች አእምሮ ውስጥ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ ሳይፈጠር ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ሲል ሕጋዊ አሠራር መከተል ጀመረ፤ ደግሞም ይህን ለማድረግ የሚያስችል ሙሉ መብት አለው።

ይሖዋ አምላክ እሱ ያወጣው መመሪያና ፍጹም የሆነው ፍትሑ በሚጠይቀው መሠረት ሁለቱም ወገኖች አወዛጋቢውን ጉዳይ በተመለከተ የየራሳቸውን ምሥክሮች ማቅረብ እንደሚችሉ ገልጿል። ምሥክር ለማቅረብ ጊዜ መፈቀዱ የአዳም ዘሮች በሕይወት መኖራቸውን እንዲቀጥሉ ያስቻላቸው ከመሆኑም በላይ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸው እንኳ በፍቅር ተነሳስተው ንጹሕ አቋማቸውን በመጠበቅ ለአምላክ ምሥክር ሆኖ የመቅረብ አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል።

ምን ያህል ጊዜ ይቆያል?

ይሖዋ አምላክ፣ ሕጋዊውን አሠራር ለመከተል ሲል በሚፈቅደው ጊዜ ውስጥ የሰው ልጆች ሥቃይና መከራ እንደሚደርስባቸው በሚገባ ያውቃል። በመሆኑም ጉዳዩን በተቻለ መጠን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቋጨት ወስኗል። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን “ከርኅራኄ የመነጨ ምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ” እንደሆነ አድርጎ ይገልጸዋል። (2 ቆሮንቶስ 1:3) “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” ዲያብሎስን አስፈላጊ ከሆነው ጊዜ በላይ እንዲኖርም ሆነ እሱ የሚያሳድረው መጥፎ ተጽዕኖ እንዲቀጥል የማይፈቅድ መሆኑ ግልጽ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አምላክ በአጽናፈ ዓለም ላይ የተነሳው ክርክር ሙሉ በሙሉ እልባት ሳያገኝ ዲያብሎስን አያጠፋውም።

ይህ ጉዳይ እልባት ሲያገኝ የይሖዋ የመግዛት መብት ሙሉ በሙሉ ይረጋገጣል። በሰይጣን ላይ የተላለፈው ፍርድ ለዘለዓለም እንደ ማስረጃ ሆኖ ያገለግላል። ወደፊት ተመሳሳይ የሆነ ግድድር ቢነሳ በሰይጣን ላይ የተወሰደው እርምጃ እንደ ምሳሌ ሆኖ ስለሚያገለግል የፍርድ ሂደቱን መድገም አስፈላጊ አይሆንም።

ይሖዋ አምላክ እሱ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ዲያብሎስን እንዲያጠፋና ዲያብሎስ ያስከተለውን ጉዳት እንዲያስወግድ መመሪያ ይሰጠዋል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ክርስቶስ በዚያ ጊዜ ስለሚያደርገው ነገር ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “መንግሥትን ሁሉ እንዲሁም ሥልጣንን ሁሉና ኃይልን አጥፍቶ መንግሥቱን ለአምላኩና ለአባቱ [ያስረክባል።] . . . አምላክ ጠላቶችን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግለት ድረስ ንጉሥ ሆኖ ሊገዛ ይገባዋልና። የመጨረሻው ጠላት የሆነው ሞት ይደመሰሳል።”—1 ቆሮንቶስ 15:24-26

ደስ የሚለው ነገር፣ መጽሐፍ ቅዱስ መላዋ ምድር ገነት እንደምትሆን ቃል ገብቷል። ሰዎች አምላክ መጀመሪያ ባወጣው ዓላማ መሠረት ሰላም በሚሰፍንባት ገነት ውስጥ ይኖራሉ! መጽሐፍ ቅዱስ “ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ” ይላል። አዎን “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:11, 29

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ አገልጋዮች ወደፊት የሚጠብቃቸውን ታላቅ ነገር አስመልክቶ ምን እንደሚል ልብ በል፦ “እነሆ፣ የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው፤ እሱም ከእነሱ ጋር ይኖራል፤ እነሱም ሕዝቦቹ ይሆናሉ። አምላክ ራሱም ከእነሱ ጋር ይሆናል። እሱም እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”—ራእይ 21:3, 4