በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የፒኮክ ማንቲስ ሽሪምፕ ዓይን

የፒኮክ ማንቲስ ሽሪምፕ ዓይን

ንድፍ አውጪ አለው?

የፒኮክ ማንቲስ ሽሪምፕ ዓይን

በታላቁ የአውስትራሊያ ባሪየር ሪፍ የሚገኘው ፒኮክ ማንቲስ ሽሪምፕ፣ በእንስሳት ዓለም ተወዳዳሪ ያልተገኘለት እጅግ ውስብስብ የማየት ችሎታ አለው። ዶክተር ኒኮላስ ሮበርትስ “በእርግጥም በጣም ልዩ ነው፤ እኛ የሰው ልጆች እስከ ዛሬ መፍጠር ከቻልናቸው ነገሮች ሁሉ የላቀ ነው” ብለዋል።

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ፒኮክ ማንቲስ ሽሪምፕ ከሰው ልጆች በተቃራኒ ፖላራይዝድ የሆነ የብርሃን ጨረርን አይቶ መለወጥ ይችላል። ፖላራይዝድ የብርሃን ጨረር ቀጥተኛ ወይም ጠመዝማዛ በሆነ መንገድ ሊጓዝ ይችላል። ማንቲስ ሽሪምፕ ከሌሎች ፍጥረታት ሁሉ በተለየ ሁኔታ ቀጥተኛም ሆነ ጠመዝማዛ በሆነ መንገድ የሚጓዝን ፖላራይዝድ የብርሃን ጨረር ማየት ብቻ ሳይሆን የብርሃኑን ጨረር ከአንዱ ዓይነት ወደ ሌላው ዓይነት መለወጥ ይችላል። በዚህ ምክንያት ይህ ሽሪምፕ የላቀ የማየት ችሎታ ሊኖረው ችሏል።

የዲቪዲ ማጫወቻዎች የሚሠሩበት መንገድ የፒኮክ ማንቲስ ሽሪምፕ ካለው ችሎታ ጋር ተመሳሳይ ነው። የዲቪዲ ማጫወቻ፣ መረጃዎችን ማንበብ እንዲችል በዲስኩ ላይ ያለው ፖላራይዝድ የብርሃን ጨረር ጠመዝማዛ በሆነ መንገድ እንዲሄድ ማድረግና ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደ ቀጥታ መስመር መመለስ ይኖርበታል። ፒኮክ ማንቲስ ሽሪምፕ ግን ከዚህ የበለጠ ነገር ማድረግ ይችላል። መደበኛ የዲቪዲ ማጫወቻ የሚለውጠው ቀይ የብርሃን ጨረርን ብቻ ሲሆን ከፍተኛ ደረጃ ያለው ከሆነ ደግሞ ሰማያዊ የብርሃን ጨረርን መለወጥ ይችላል፤ የፒኮክ ሽሪምፕ ዓይን ግን ሁሉንም ዓይነት ቀለም ማለት ይቻላል ወደ ሌላ ዓይነት የመለወጥ ችሎታ አለው።

ተመራማሪዎች የፒኮክ ማንቲስ ሽሪምፕን ዓይን እንደ ናሙና በመጠቀም ዛሬ ካሉት ዲቪዲዎች እጅግ የላቀ መረጃ የያዙ ዲቪዲዎችን የሚያነቡ የዲቪዲ ማጫወቻዎች መሥራት እንደሚቻል ያምናሉ። የፒኮክ ማንቲስ ሽሪምፕ ዓይን “በጣም ውብና ያልተወሳሰበ መሆኑ እጅግ አጓጊ ያደርገዋል” በማለት ሮበርትስ ተናግረዋል። “እኛ ልንሠራ ከሞከርናቸው መሣሪያዎች በሙሉ በላቀ ሁኔታ ይሠራል።”

ታዲያ ምን ይመስልሃል? አስደናቂ የሆነው የፒኮክ ማንቲስ ሽሪምፕ ዓይን እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Courtesy Stephen Childs