በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ምን ታውቃለህ?

ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ምን ታውቃለህ?

“ስለ ይሖዋ ምሥክሮች በኢንተርኔት ላይ ብዙ አንብቤያለሁ፤ እንዲሁም አሉባልታና ጭፍን ጥላቻ የሚንጸባረቅበት ብዙ ነገር ሰምቻለሁ” በማለት በዴንማርክ የምትኖር በሥልጠና ላይ ያለች አንዲት ዜና ዘጋቢ ጽፋለች። “በዚህም የተነሳ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች በጣም አፍራሽ የሆነ አመለካከት አደረብኝ።”

ጊዜ በኋላ ይህች ዜና ዘጋቢ የይሖዋ ምሥክር ለሆነ አንድ ቤተሰብ ቃለ ምልልስ አደረገች። ውጤቱስ ምን ሆነ? እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “ገና ቤታቸው ከመግባቴ ስለ እነሱ የነበረኝ አመለካከት ተለወጠ። ምናልባት ሰዎች በደንብ አያውቋቸውም አሊያም ደግሞ ሁላችንም ለመፍረድ እንቸኩላለን። እኔም ለመፍረድ ችኩል እንደነበርኩ ተሰማኝ፤ ትክክል እንዳልነበርኩም ተረዳሁ።”—ሴሲሊየ ፌሊንግ፣ ለዩዌስከ ቬስትኩዌስተን

በአውሮፓ በሚገኝ ብዙ ቅርንጫፎች ባሉት መደብር ውስጥ የሠራተኞች አማካሪ ሆኖ የሚሠራ አንድ ባለሙያ፣ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ባለው የሥራ ግንኙነት ላይ ተመርኩዞ ስለ እነሱ አስተያየት ሲሰጥ ሐቀኛ ሠራተኞች እንደሆኑ ገልጿል። በዚህም ምክንያት መቅጠር የሚፈልገው የይሖዋ ምሥክሮችን ነው።

እርግጥ ነው፣ የይሖዋ ምሥክሮች በዋነኝነት የሚታወቁት በስብከት ሥራቸው ነው። የይሖዋ ምሥክሮች የስብከት ሥራቸውን ሲያከናውኑ አንዳንዶች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለመወያየት ፈቃደኞች እንደማይሆኑ ሌሎች ግን መወያየት እንደሚያስደስታቸው ያስተውላሉ። እንዲያውም በሁሉም አገሮች ማለት ይቻላል ከሰባት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር አዘውትረው የሚያጠኑ ሲሆን ከእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መካከል አንዳንዶቹ ከጊዜ በኋላ እነሱ ራሳቸው አስተማሪዎች ይሆናሉ። ለምሳሌ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ አንድ የአብያተ ክርስቲያናት ብሔራዊ ምክር ቤት፣ ከ25ቱ ትልልቅ ሃይማኖቶች ውስጥ የቁጥር ጭማሪ ያሳዩት አራት ብቻ እንደሆኑና ከእነዚህም መካከል አንዱ የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖት እንደሆነ ሪፖርት አድርጓል።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑት ለምንድን ነው? ጥናቱ የሚካሄደው እንዴት ነው? ደግሞስ የሚያጠኑት ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች እንዲሆኑ ይጠበቅባቸዋል? የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ባትፈልግም እንኳ ለእነዚህ ጥያቄዎች ትክክለኛውን መልስ ማግኘት ትችላለህ። ስለዚህ ጎጂ አሉባልታዎችን ወይም ወሬዎችን ከመስማት ይልቅ እውነቱን ብትመረምር የተሻለ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 14:15 ላይ እንዲህ ይላል፦ “የዋህ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል።”—የ1954 ትርጉም

ይህ የንቁ! እትም የይሖዋ ምሥክሮችን በደንብ እንድታውቃቸውና ስለ እነሱ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖርህ እንደሚረዳህ ተስፋ እናደርጋለን። በእርግጥም ይህን መጽሔት እያነበብክ መሆንህ በራሱ ጭፍን አመለካከት እንደሌለህ ይጠቁማል። ታዲያ ለምን እንዲህ አታደርግም? የሚቀጥሉትን አራት ርዕሶችና ሣጥኖቻቸውን በምታነብበት ጊዜ ጥቅሶቹን ከራስህ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እያወጣህ ተመልከት። * ይህን ማድረግህ ብልህ መሆንህን አልፎ ተርፎም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “ልበ ቀና” መሆንህን ያሳያል።—የሐዋርያት ሥራ 17:11

^ စာပိုဒ်၊ 7 ኢንተርኔት መጠቀም የምትችል ከሆነ www.watchtower.org ከሚለው ድረ ገጻችን ላይ መጽሐፍ ቅዱስን በተለያዩ ቋንቋዎች ማግኘት ትችላለህ። (ለጊዜው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ድረ ገጽ ውስጥ አይገኝም።) በተጨማሪም በዚህ ድረ ገጽ ውስጥ ከ380 በሚበልጡ ቋንቋዎች የተዘጋጁ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ሌሎች ጽሑፎች ይገኛሉ።