በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የቤተሰብህን አባላት ከኢንፍሉዌንዛ ጠብቅ

የቤተሰብህን አባላት ከኢንፍሉዌንዛ ጠብቅ

የቤተሰብህን አባላት ከኢንፍሉዌንዛ ጠብቅ

ኢየሱስ የዚህን ሥርዓት ፍጻሜ አስመልክቶ “በየቦታው . . . ወረርሽኝ ይሆናል” የሚል ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ሉቃስ 21:11 የታረመው የ1980 ትርጉም) እንዲህ ካሉት ወረርሽኞች መካከል አንዱ ኢንፍሉዌንዛ ነው።

ኢንፍሉዌንዛ የሚከሰተው በአጉሊ መነፅር ብቻ በሚታይ ቫይረስ አማካኝነት ነው፤ ይህ ቫይረስ ሕይወት ወዳላቸው ሴሎች ውስጥ በመግባት ማባዣዎቻቸውን ተቆጣጥሮ ተጨማሪ ቫይረሶችን እንዲያራቡ የማስገደድ ባሕርይ አለው። የመተንፈሻ አካልን የሚያጠቃው የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ በዋነኝነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው የታመመው ሰው ሲያስነጥስ፣ ሲያስል ወይም ሲያወራ ከሰውነት ውስጥ በሚወጡ የፈሳሽ ብናኞች አማካኝነት ነው። አንድ በሽታ ወረርሽኝ የሚባለው በሰፊው ተሰራጭቶ ብዙ ሰዎችን ሲያጠቃ ነው።

ቫይረሶች ሰዎችን ብቻ ሳይሆን እንስሳትንና ወፎችንም ያጠቃሉ። የኢንፍሉዌንዛ ቫይረሶች ዓይነታቸው የተለያየ ስለሆነ ኤ፣ ቢ ወይም ሲ ተብለው ይከፈላሉ። በጣም ለተለመደው ኢንፍሉዌንዛ መንስኤ የሚሆነው ኤ የሚባለው የቫይረስ ዓይነት ነው። ቫይረሶች በዓይነት በዓይነት የሚመደቡት በቫይረሱ ሽፋን ላይ የሚገኙትን ሁለት የፕሮቲን ዓይነቶች መሠረት በማድረግ ሲሆን እነሱም ሄማግሉትኒን (ኤች) እና ኑውረሚኒዴዝ (ኤን) ናቸው።

የኢንፍሉዌንዛን ቫይረሶች አስጊ የሚያደርጓቸው ዋነኞቹ ነገሮች፣ ያለማቋረጥ ባሕርያቸውን እየለዋወጡ በከፍተኛ ፍጥነት ሊራቡ የሚችሉ መሆናቸውና የተለያዩ ቫይረሶች ተዋሕደው የተለየ ባሕርይ ያለው አዲስ የቫይረስ ዓይነት ሊፈጥሩ መቻላቸው ነው። አዲስ የተፈጠረው ቫይረስ ሙሉ በሙሉ የተለየ ከሆነ ሰውነታችን ይህን ቫይረስ የመከላከል አቅም ላይኖረው ይችላል።

አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች በኢንፍሉዌንዛ የሚጠቁት በቅዝቃዜ ወቅት ነው። በቅርቡ የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው በቅዝቃዜ ወቅት ቫይረሱ ሽፋኑን በዝልግልግ ፈሳሽ ስለሚሸፍን በአየር ውስጥ ረጅም ጊዜ መቆየት ይችላል፤ በሰው የመተንፈሻ አካል ውስጥ ሲገባ ግን እዚያ ባለው ሙቀት አማካኝነት ስለሚሟሟ ኢንፌክሽን ይፈጠራል። ሰዎች በቫይረስ የሚጠቁት በቀዝቃዛ አየር ምክንያት ባይሆንም እንዲህ ያለው አየር ቫይረሶቹ ለመዛመት የሚያስችላቸውን አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል።

የመከላከያ እርምጃዎች

ብዙ መንግሥታት ዝግጁ የመሆንን አስፈላጊነት በመገንዘብ ቀደም ብለው የድርጊት መርሐ ግብሮችን አዘጋጅተዋል። ይሁንና እናንተ ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ? ልትወስዷቸው የሚገቡ ሦስት መሠረታዊ እርምጃዎችን እንመልከት፦

ሰውነታችሁን አጠናክሩ፦ ቤተሰባችሁ በቂ እንቅልፍ እንዲያገኝና ሰውነት በሽታ የመከላከል ኃይሉን እንዲያጠናክር የሚረዱ ምግቦችን እንዲመገብ አድርጉ። ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን፣ ያልተፈተጉ ጥራጥሬዎችን እንዲሁም በሽታ የመከላከል አቅማችንን ለማጠናከር አስፈላጊ የሆኑትን አሚኖ አሲዶች የያዙ ስብ ያልበዛባቸው ፕሮቲኖችን በየዕለቱ ተመገቡ።

ቤታችሁን ለጀርሞች መራባት የማይመች እንዲሆን አድርጉ፦ በተቻለ መጠን ወጥ ቤታችሁንና የመመገቢያ ጠረጴዛችሁን በየዕለቱ በደንብ አጽዱ። ምግብ ማብሰያና መመገቢያ ዕቃዎቻችሁን ከተጠቀማችሁ በኋላ እጠቧቸው፤ እንዲሁም እንደ አንሶላ ያሉ ሌሊት የምትጠቀሙባቸውን የመኝታ ልብሶቻችሁን ቶሎ ቶሎ እጠቧቸው። ብዙ ጊዜ በእጅ የሚነካኩ ነገሮችን ለምሳሌ የበር እጀታዎችን፣ ስልኮችንና የቴሌቪዥን የርቀት መቆጣጠሪያዎችን (ሪሞት ኮንትሮል) ጀርም በሚገድሉ ኬሚካሎች ጠራርጓቸው። ከተቻለ ቤታችሁ ውስጥ ንጹሕ አየር እንዲንሸራሸር አድርጉ።

ጥሩ የግል ንጽሕና አጠባበቅ ልማድ ይኑራችሁ፦ እጃችሁን በሳሙናና በውኃ ለመታጠብ ወይም አልኮልነት ባለው የእጅ ማጽጃ ለማጽዳት አትታክቱ። (የሚቻል ከሆነ ጀርም ለመግደል የሚያገለግል የእጅ ማጽጃ ፈሳሽ አይለያችሁ።) እጅ ወይም ፊት ለማድረቅ የሚያገለግሉ ፎጣዎችን ከማንም ሰው ጋር ሌላው ቀርቶ ከቤተሰብ አባሎቻችሁ ጋር በጋራ አትጠቀሙ።

ባልታጠበ እጃችሁ ዓይናችሁን፣ አፍንጫችሁን ወይም አፋችሁን አትነካኩ። የሚቻል ከሆነ ስታስሉ ወይም ስታስነጥሱ አፋችሁንና አፍንጫችሁን ለአንድ ጊዜ ብቻ በሚያገለግል ናፕኪን ሸፍኑ፤ ከዚያም ናፕኪኑን ወዲያውኑ ጣሉት። ጀርምን በቀላሉ እንዲሠራጭ የሚያደርጉ እንደ ስልክ ያሉ ነገሮችን በጋራ ከመጠቀም ተቆጠቡ። ልጆች በዚህ ረገድ በደንብ ሊሠለጥኑ ይገባቸዋል። ይህ ልማድ ምንጊዜም ጥሩ ቢሆንም በተለይ ኢንፍሉዌንዛ በሚበዛበት ወቅት በጣም አስፈላጊ ነው።

ለሌሎች አሳቢነት አሳዩ

ኢንፍሉዌንዛ እንደያዛችሁ የሚያሳይ ምልክት ከመታየቱ ከአንድ ቀን በፊት አንስቶ በበሽታው ከተያዛችሁ በኋላ እስከ አምስት ቀናት ድረስ በሽታው ወደ ሌሎች ሊተላለፍ ይችላል። የኢንፍሉዌንዛ ምልክት ከጉንፋን ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም የኢንፍሉዌንዛ ሕመም ግን ያይላል። ከምልክቶቹም መካከል ትኩሳት (አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ የሆነ)፣ ራስ ምታት፣ ከፍተኛ የድካም ስሜት፣ ደረቅ ሳልና የጡንቻዎች መጓጎል ይገኙበታል። ንፍጥ እንዲሁም እንደ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክና ተቅማጥ ያሉ የሆድ ሕመም ምልክቶች ከአዋቂዎች ይልቅ በልጆች ላይ ያይላሉ። እነዚህን ምልክቶች ካየህ የሚቻል ከሆነ ከቤት ባለመውጣት ወደ ሌሎች ከማስተላለፍ ተቆጠብ።

በቂ እረፍት አግኝ፤ እንዲሁም ብዙ ፈሳሽ ጠጣ። ፀረ ቫይረስ መድኃኒቶችም ሊረዱ ይችላሉ፤ ሆኖም ውጤታማ የሚሆኑት ምልክቶቹ እንደታዩ ከተወሰዱ ብቻ ነው። ኢንፍሉዌንዛ ለያዛቸው ልጆች አስፕሪን (አሲትልሳላሲሊክ አሲድ) መስጠት አይገባም። የሳንባ ምች ዓይነት ምልክቶች ለምሳሌ የመተንፈስ ችግር፣ የደረት ውጋት ወይም የማያቋርጥ ኃይለኛ ራስ ምታት ካለህ አፋጣኝ የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ጣር።

የኢንፍሉዌንዛ ሕመም ደስ የማይል ስሜት ሊፈጥር ይችላል። ተገቢውን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ግን በሽታውን እንድትቋቋመው ይረዳሃል። ከሁሉም በላይ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ እንደሚሰጠው ማንም ሰው “ታምሜአለሁ” የማይልበትን ጊዜ በጉጉት እንጠብቃለን።—ኢሳይያስ 33:24

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ኃይለኛ የኢንፍሉዌንዛ ዓይነት

ለመጀመሪያ ጊዜ በሜክሲኮ በ2009 የተከሰተው ኤች1ኤን1 (H1N1) የተባለው የኢንፍሉዌንዛ ዓይነት በ1918 ተከስቶ ከነበረውና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከገደለው ከስፓኒሽ ፍሉ ወይም ከኅዳር በሽታ ጋር ተመሳሳይ ነው። ይሁን እንጂ አሳማዎችንና ወፎችን በሚያጠቁ ቫይረሶች ውስጥ የሚገኙትን ንጥረ ነገሮችም ይዟል።

[በገጽ 28, 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ራስህንም ሆነ ሌሎችን ከኢንፍሉዌንዛ ለመጠበቅ የምትችልባቸው 6 መንገዶች

1. ስታስል አፍህን ሸፍን

2. እጅህን ታጠብ

3. ቤትህን አናፍስ

4. እጅ የሚበዛባቸውን ነገሮች አጽዳ

5. ከታመምክ ከቤት አትውጣ

6. ከሰው ጋር አትነካካ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ወረርሽኝ በሚከሰትበት ጊዜ

በአንደኛ ደረጃ የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን መመሪያ ተከተል። አትሸበር ወይም አትደንግጥ። በዚህ ርዕስ ውስጥ የተወያየንባቸውን ጥሩ ልማዶች አጠናክረህ ቀጥል። የሚቻል ከሆነ ብዙ ሕዝብ በሚሰበሰብበት ቦታ ከመገኘት ተቆጠብ። ከታመምክ አፍና አፍንጫህን ለዚህ ዓላማ በተዘጋጀ መሸፈኛ መሸፈንህ ተገቢ ነው። እጅህን ቶሎ ቶሎ ታጠብ። ምናልባት ቢያምህና ገበያ መውጣት ባትችል ለሁለት ሳምንት ያህል ሳይበላሹ መቆየት የሚችሉ የምግብ ዓይነቶችን እንዲሁም የጤናና የንጽሕና መጠበቂያ ዕቃዎችን አዘጋጅተህ አስቀምጥ።

በመሥሪያ ቤት፣ በአምልኮ ቦታ ወይም በማንኛውም ጊዜ ከብዙ ሰዎች ጋር በምትሆንበት ወቅት እዚህ ላይ የቀረቡትን ጠቃሚ ምክሮች ተከተል። በተጨማሪም ቤትህ ወይም የሥራ ቦታህ በጥሩ ሁኔታ የተናፈሰ እንዲሆን ለማድረግ ጣር።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኤች1ኤን1 ኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ በአጉሊ መነፅር ሲታይ

[ምንጭ]

CDC/Cynthia Goldsmith