በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ ጤንነቴ ያን ያህል ማሰብ ይኖርብኛል?

ስለ ጤንነቴ ያን ያህል ማሰብ ይኖርብኛል?

የወጣቶች ጥያቄ

ስለ ጤንነቴ ያን ያህል ማሰብ ይኖርብኛል?

ከታች ከተዘረዘሩት መካከል ቢሳካልህ ደስ በሚልህ ላይ ✔ ምልክት አድርግ።

○ ክብደት መቀነስ

○ የቆዳህን ጥራት ማሻሻል

○ ተጨማሪ ጉልበት ማግኘት

○ ይበልጥ ንቁ መሆን

○ ጭንቀትን መቀነስ

○ ቁጣን መቆጣጠር

○ በራስ የመተማመን ስሜትን ማሳደግ

ወላጆችህን እንዲሁም ወንድሞችህንና እህቶችህን ብሎም የምትኖርበትን ቦታ መምረጥን ጨምሮ በሕይወትህ ውስጥ በአንተ ምርጫ የማይሆኑ አንዳንድ ነገሮች አሉ። የጤንነትህን ሁኔታ በተመለከተ ግን ማድረግ የምትችለው ነገር አለ። ጥሩ ቁመና ያለህ መሆን አለመሆንህ የተመካው በዘር ውርስና በምትከተለው የአኗኗር ዘይቤ ላይ ነው። *

‘ስለ ጤንነቴ የምጨነቅበት ዕድሜ ላይ አይደለሁም!’ ትል ይሆናል። አይምሰልህ! እስቲ ከላይ የተዘረዘሩትን ነገሮች ተመልከት። በስንቶቹ ላይ ምልክት አደረግህ? ብታምንም ባታምንም፣ የተዘረዘሩት ነገሮች በሙሉ እንዲሳኩልህ ከፈለግህ ቁልፉ ጥሩ ጤንነት ነው።

እርግጥ ነው፣ “ካልተፈተገ ስንዴ የተዘጋጀ ዳቦና ቅባት ያልበዛበት ወይም ስኳር የሌለው ምግብ ብቻ እየበላሁ የምኖርበት ምንም ምክንያት የለም!” በማለት የተናገረችውን የ17 ዓመቷን የአምበርን * ስሜት ትጋራ ይሆናል። ከሆነ አይዞህ፤ ጥሩ ቁመና ካልኖረኝ ብለህ መከራህን መብላት፣ ጣፋጭ ነገሮችን እርግፍ አድርገህ መተው ወይም በየሳምንቱ ረጅም ርቀት መሮጥ አያስፈልግህም። በእርግጥም የተሻለ ቁመና እንዲኖርህ፣ ጥሩ ስሜት እንዲሰማህና ቀልጣፋ እንድትሆን ከፈለግህ የሚጠበቅብህ ጥቂት ማስተካከያዎችን ብቻ ማድረግ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ እኩዮችህ እንዴት ሊሳካላቸው እንደቻለ እስቲ እንመልከት።

ያማረ ቁመና እንዲኖርህ ጥሩ አመጋገብ ይኑርህ!

መጽሐፍ ቅዱስ በልማዶቻችን ረገድ ልከኞች እንድንሆን ይመክራል። ምሳሌ 23:20 [የ1980 ትርጉም] ‘ብዙ ምግብ መብላትን’ ያወግዛል። እርግጥ ነው፣ ይህን ምክር መከተል ሁልጊዜ ቀላል አይደለም።

“እንደ አብዛኞቹ ወጣቶች ሁሉ እኔም ቶሎ ቶሎ ይርበኛል። በዚህም የተነሳ ወላጆቼ ጎተራ ሆድ እንዳለኝ ይናገራሉ!”—የ15 ዓመቱ አንድሩ

“አንዳንድ ምግቦች የሚያስከትሉት ጉዳት ለጊዜው ስለማይታየኝ ያን ያህል ይጎዱኛል ብዬ አላስብም።”—የ19 ዓመቷ ዳንዬል

ከአመጋገብ ጋር በተያያዘ ራስን የመግዛት ባሕርይ ማዳበር ያስፈልግህ ይሆን? አንዳንድ እኩዮችህ በዚህ ረገድ ምን እንደረዳቸው የተናገሩት ሐሳብ ከዚህ በታች ቀርቧል።

ሆድህን አዳምጠው። የ19 ዓመቷ ጁሊያ እንዲህ ብላለች፦ “የምበላውን ምግብ መጠን በካሎሪ እየለካሁ የመመገብ ልማድ ነበረኝ፤ አሁን ግን ሆዴ እንደሞላ ሲሰማኝ መብላት አቆማለሁ።”

ለጤና ተስማሚ ያልሆኑ ምግቦችን አትመገብ። የ21 ዓመቱ ፒተር እንዲህ ብሏል፦ “ለስላሳ መጠጣት ሳቆም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ አምስት ኪሎ ቀነስኩ!”

መጥፎ የአመጋገብ ልማድህን አስተካክል። “የሚያስፈልገኝን ያህል ከበላሁ በኋላ ሁለተኛ ዙር ላለመጀመር ጥረት አደርጋለሁ” በማለት የ19 ዓመቷ ኤሪን ተናግራለች።

የስኬት ሚስጥር፦ ቁርስህንም ሆነ ምሳህን አሊያም እራትህን አትዝለል! እንዲህ ማድረግ በጣም እንዲርብህ ስለሚያደርግ ብዙ ልትበላ ትችላለህ።

ጥሩ ስሜት እንዲሰማህ ስፖርት ሥራ!

መጽሐፍ ቅዱስ “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በጥቂቱ ይጠቅማል” ይላል። (1 ጢሞቴዎስ 4:8) ብዙ ወጣቶች ግን ስፖርት ለመሥራት ፍላጎት ያላቸው አይመስሉም።

“በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለሁ ምን ያህል ብዙ ልጆች በስፖርት ፈተና እንደወደቁ ብነግራችሁ አታምኑም። የስፖርት ክፍለ ጊዜ ምሳ የመብላትን ያህል ቀላል ነበር!”—የ21 ዓመቱ ሪቻርድ

“አንዳንዶች ‘የቪዲዮ ጨዋታ በመጫወት ስፖርት የሠራህ ሆኖ እንዲሰማህ ማድረግ እየቻልክ ላብ በላብ እስክትሆን ድረስ በጠራራ ፀሐይ ምን አሯሯጠህ?’ ብለው ያስባሉ።”—የ22 ዓመቷ ሩት

ስፖርት መሥራት የሚለውን ነገር ገና ስታስበው ድክም ይልሃል? ከሆነ ጥሩ የስፖርት ልማድ ማዳበር የሚያስገኛቸው ሦስት ግሩም ሽልማቶች ቀጥሎ ተገልጸዋል።

ሽልማት 1፦ ስፖርት መሥራት በሽታ የመከላከል አቅምህን ያጠናክረዋል። የ19 ዓመቷ ራሄል እንደሚከተለው ስትል ተናግራለች፦ “አባቴ ሁልጊዜ እንዲህ ይል ነበር፦ ‘ስፖርት ለመሥራት ጊዜ ማግኘት ካልቻልሽ ታመሽ ለመተኛት ጊዜ ብትፈልጊ ይሻልሻል።’”

ሽልማት 2፦ ስፖርት መሥራት አንጎልህ ስሜትህን የሚያረጋጉ ኬሚካሎችን እንዲያመነጭ ያደርጋል። የ16 ዓመቷ ኤሚሊ “አእምሮዬ በብዙ ነገር በሚወጠርበት ጊዜ እፎይታ ለማግኘት ጥሩው ዘዴ መሮጥ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ሰውነቴ የሚታደስ ከመሆኑም በላይ ስሜቴ ይረጋጋል” በማለት ተናግራለች።

ሽልማት 3፦ ስፖርት መሥራት ደስታ ይጨምርልሃል። የ22 ዓመቷ ሩት እንዲህ ብላለች፦ “ውጪውን በጣም እወደዋለሁ። በእግር እንደ መንሸራሸር፣ እንደ መዋኘት፣ በበረዶ ላይ እንደ መንሸራተትና ብስክሌት እንደ መንዳት ያሉ ስፖርቶችን የምመርጠውም ለዚህ ነው።”

የስኬት ሚስጥር፦ የምትወደውን ሆኖም በደንብ የሚያሠራህን ስፖርት በመምረጥ በሳምንት ሦስት ቀን ቢያንስ ለ20 ደቂቃ ለመሥራት ጊዜ መድብ።

ቀልጣፋ እንድትሆን ጥሩ እንቅልፍ ተኛ!

መጽሐፍ ቅዱስ “በድካምና ነፋስን በመከተል ከሚገኝ ሁለት ዕፍኝ ይልቅ፣ በርጋታ [“በዕረፍት፣” የ1954 ትርጉም] የሚገኝ አንድ ዕፍኝ ይሻላል” ይላል። (መክብብ 4:6) በቂ እንቅልፍ ካላገኘህ ነገሮችን በብቃት ማከናወን ዳገት ይሆንብሃል!

“በቂ እንቅልፍ ካላገኘሁ ምንም ነገር በሥነ ሥርዓት ማከናወን አልችልም። በአንድ ነገር ላይ ትኩረት ማድረግ እቸገራለሁ!”—የ19 ዓመቷ ራሄል

“ከቀኑ ስምንት ሰዓት ገደማ ሲሆን በጣም ስለሚደክመኝ ከሌሎች ጋር እየተጨዋወትኩ እንኳ እንቅልፌ ይመጣል!”—የ19 ዓመቷ ክሪስቲን

የእንቅልፍ ሰዓትህን መጨመር ያስፈልግህ ይሆን? አንዳንድ እኩዮችህ ምን እንዳደረጉ እስቲ እንመልከት።

በጊዜ ተኛ። “በጊዜ ለመተኛት ጥረት እያደረግሁ ነው” በማለት የ18 ዓመቷ ካትሪን ተናግራለች።

በጣም ከመሸ በኋላ ወሬ አቁም። የ21 ዓመቱ ሪቻርድ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “አንዳንድ ጊዜ ጓደኞቼ በጣም ከመሸ በኋላ ይደውሉልኛል ወይም በሞባይል መልእክት ይልኩልኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ወሬዬን በማቆም ቶሎ መተኛት እንዳለብኝ ተምሬያለሁ።”

ጥሩ ልማድ አዳብር። የ20 ዓመት ዕድሜ ያላት ጄኒፈር “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየቀኑ በተወሰነ ሰዓት ለመተኛትና ለመነሳት እየጣርኩ ነው” ብላለች።

የስኬት ሚስጥር፦ በየቀኑ ከስምንት እስከ አሥር ሰዓት ለመተኛት ጥረት አድርግ።

እስከ አሁን ካየናቸው ሦስት ነጥቦች ውስጥ አንተ ይበልጥ ልትሠራበት የሚባው የትኛው ነው?

አመጋገብ ስፖርት እንቅልፍ

በዚህ ረገድ ማሻሻያ ለማድረግ ምን ዕቅድ ልታወጣ እንደምትችል ከዚህ በታች ጻፍ።

․․․․․

ራስህን ለመንከባከብ ቀላል የሆኑ ጥቂት እርምጃዎችን ብቻ በመውሰድ የምትፈልገውን ነገር ማግኘት ትችላለህ። ጥሩ ጤንነት የተሻለ ቁመና እንዲኖርህ፣ ጥሩ ስሜት እንዲሰማህና ቀልጣፋ እንድትሆን የሚረዳህ መሆኑን አትዘንጋ። በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙህን አንዳንድ ነገሮች መለወጥ ባትችልም ጥሩ ቁመና እንዲኖርህ የማድረጉ ጉዳይ ግን በተወሰነ መጠንም ቢሆን በአንተ ላይ የተመካ ነው። የ19 ዓመቷ ኤሪን እንደተናገረችው “ዞሮ ዞሮ ጤንነትህ የተመካው በአንድ ሰው ላይ ብቻ ነው፤ ያም ሰው አንተ ነህ።”

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.11 ከቁጥጥራቸው ውጪ በሆነ ምክንያት ለጤና ችግር ወይም ለአካል ጉዳት የተዳረጉ ብዙ ሰዎች እንዳሉ እንገነዘባለን። ይህ ርዕስ እንደነዚህ ያሉ ሰዎችም ቢሆኑ አቅማቸው በሚፈቅድላቸው መጠን የተሻለ ጤንነት ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ይጠቁማል።

^ አን.13 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

ጤንነትህን መንከባከብ በራስ የመተማመን ስሜትህ ላይ ለውጥ የሚያመጣው እንዴት ነው?

በጤንነትህ ረገድ ምክንያታዊነትን ማንጸባረቅ የምትችለው እንዴት ነው?ፊልጵስዩስ 4:5

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

እኩዮችህ ምን ይላሉ?

“የሰው ሰውነት እንደ መኪና ነው፤ በመሆኑም ጥገና ማድረግ የባለቤቱ ፋንታ ነው። እኔም ስፖርት መሥራት የምፈልግበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው።”

“አብሯችሁ ስፖርት የሚሠራ ሰው መኖሩ ያበረታታችኋል፤ ምክንያቱም እሱን ቅር ማሰኘት አትፈልጉም።”

“ስፖርት ስሠራ ደስ የሚል ስሜት ይሰማኛል። ስፖርት መሥራት ጥሩ ቁመና እንዲኖረኝ ስላስቻለኝ በራስ የመተማመን ስሜቴን ጨምሮልኛል!”

[ሥዕሎች]

ኢታን

ብሪአነ

ኤሚሊ

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

‘የአኗኗር ለውጥ አደረግሁ’

“ስድስት ዓመት ሲሆነኝ ከዕድሜዬ አንጻር ወፈር ያልኩ ነበርኩ። ከዚያም እንደ ቀልድ የጀመርኩት በሄድኩበት ሁሉ የመብላት ልማድ ቀስ በቀስ ያለማቋረጥ ምግብ የማግበስበስ አባዜ እንዲጠናወተኝ አደረገኝ! በዚያ ላይ መንቀሳቀስ ስለማልወድ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አላደርግም ነበር። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ስገባ ከመጠን በላይ ወፈርኩ፤ ይህ ደግሞ ፈጽሞ የማልፈልገው ነገር ነበር። ቅርጼን በጣም የጠላሁት ከመሆኑም በላይ ጥሩ ስሜትም አይሰማኝም ነበር! ለየት ያለ የአመጋገብ ሥርዓት በመከተል አልፎ አልፎ ክብደት ለመቀነስ የሞከርኩባቸው ጊዜያት ቢኖሩም መልሼ እወፍር ነበር። ስለዚህ 15 ዓመት ሲሆነኝ ለውጥ ለማድረግ ቆርጬ ተነሳሁ። ትክክለኛውን መንገድ ማለትም በቀሪው ሕይወቴ ሁሉ ተግባራዊ ላደርገው የምችለውን አኗኗር በመከተል ክብደቴን ለመቀነስ ፈለግሁ። መሠረታዊ ስለሆነ የአመጋገብ ሥርዓትና የሰውነት እንቅስቃሴ የሚዳስስ መጽሐፍ ገዛሁና ያነበብኩትን ነገር ተግባራዊ ማድረግ ጀመርኩ። እንዲህ ማድረጌን ለጊዜው ባቋርጥም ወይም ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ቢያጋጥመኝም እንኳ ከነጭራሹ ላልተወው ቁርጥ ውሳኔ አድርጌ ነበር። የሆነውን ነገር መገመት ትችላላችሁ? ጥረቴ ሰመረልኝ! በአንድ ዓመት ውስጥ 25 ኪሎ ቀነስኩ። ለሁለት ዓመት ያህል ምንም ክብደት ሳልጨምር በዚያው መቀጠል ቻልኩ። ይህ ይሆናል ብዬ ፈጽሞ አላሰብኩም ነበር! ሊሳካልኝ የቻለው የአመጋገብ ለውጥ ስላደረግሁ ብቻ ሳይሆን የአኗኗር ለውጥ በማድረጌ የተገኘ ውጤት እንደሆነ ይሰማኛል። ለውጥ ማድረጌ እያንዳንዱን የሕይወቴን ክፍል እንደሚነካ ስረዳ አስፈላጊውን ማስተካከያ ለማድረግ ከልብ ተነሳሳሁ።—የ18 ዓመቷ ካተሪን

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጤንነትህ እንደ መኪና ነው፤ በተገቢው መንገድ ካልተንከባከብከው ሊጎዳ ይችላል