በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የፆታ ግንኙነት መፈጸም ይበልጥ ያቀራርበን ይሆን?

የፆታ ግንኙነት መፈጸም ይበልጥ ያቀራርበን ይሆን?

 የወጣቶች ጥያቄ

የፆታ ግንኙነት መፈጸም ይበልጥ ያቀራርበን ይሆን?

ሣራ ከጆን ጋር የፍቅር ጓደኝነት ከጀመረች ገና ሁለት ወሯ ቢሆንም ለረዥም ጊዜ በጓደኝነት እንደቆዩ ሆኖ ይሰማታል። አዘውትረው በሞባይል መልእክት ይለዋወጣሉ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በስልክ ለሰዓታት ያወራሉ፣ እንዲሁም እርስ በርስ እስኪናበቡ ድረስ በጣም ይጣጣማሉ! ይሁንና አንድ ቀን በምሽት ጨረቃ መኪናቸውን አቁመው እየተጨዋወቱ ሳለ ጆን ከመጫወት ባለፈ ሌላ ነገር ማድረግ ፈለገ።

ባለፉት ሁለት ወራት ጆንና ሣራ እጅ ለእጅ ከመያያዝና ለሰላምታ ያህል ከመሳሳም ያለፈ ምንም ነገር አድርገው አያውቁም። ሣራም ቢሆን ከዚህ ያለፈ ነገር ማድረግ አትፈልግም። በሌላ በኩል ደግሞ ጆንን ማጣት አትፈልግም። ከጆን ጋር ስትሆን በጣም ቆንጆና ልዩ እንደሆነች ይሰማታል። በተጨማሪም ‘እኔና ጆን እንዋደዳለን፣ . . . አይደል?’ በማለት ከራሷ ጋር ትነጋገራለች።

የሣራና የጆን ሁኔታ ወዴት እያመራ እንዳለ መገመት አያቅትሽም። * ይሁን እንጂ ጆንና ሣራ የፆታ ግንኙነት ቢፈጽሙ ሕይወታቸው ምን ያህል በቅጽበት ሊለወጥ እንደሚችል አታስቢ ይሆናል፤ ለውጡ ግን መልካም ለውጥ አይደለም። እስቲ ቆም ብለሽ አስቢ፦

እንደ ስበት ሕግ ያሉ የተፈጥሮ ሕጎችን ብትጥሺ መዘዙን ማጨድሽ አይቀርም። ‘ከዝሙት ራቁ’ እንደሚለው ያለውን የሥነ ምግባር ሕግ ብትጥሺም ውጤቱ ተመሳሳይ ነው። * (1 ተሰሎንቄ 4:3) ይህን ትእዛዝ መጣስ ምን መዘዝ ያስከትላል? መጽሐፍ ቅዱስ “ዝሙት የመፈጸም ልማድ ያለው ግን በራሱ አካል ላይ ኃጢአት እየሠራ ነው” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 6:18) ይህ እውነት የሆነው እንዴት ነው? ከጋብቻ በፊት የፆታ  ግንኙነት በሚፈጽሙ ሰዎች ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ሦስት ጎጂ ውጤቶችን ቀጥሎ ባሉት ክፍት ቦታዎች ላይ ጻፊ።

1. ․․․․․

2. ․․․․․

3. ․․․․․

እስቲ የጻፍሽውን መለስ ብለሽ ተመልከቺ። ከጻፍሻቸው ነገሮች ውስጥ በፆታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች፣ ያልተፈለገ እርግዝና ወይም የአምላክን ሞገስ ማጣት የሚሉት ይገኙበታል? በእርግጥም እነዚህ አምላክ ዝሙትን አስመልክቶ የሰጠውን የሥነ ምግባር ሕግ በሚጥሱ ሰዎች ላይ የሚደርሱ አስከፊ መዘዞች ናቸው።

ያም ሆኖ የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም ትፈተኚ ይሆናል። ‘ምንም አልሆንም’ ብለሽ ታስቢ ይሆናል። ደግሞስ የፆታ ግንኙነት የሚፈጽመው ሁሉም ሰው አይደል? በትምህርት ቤት ያሉት እኩዮችሽ ስለፈጸሙት የፆታ ግንኙነት በጉራ ሲናገሩ ትሰሚያለሽ፤ በዚያ ላይ ምንም ጉዳት የደረሰባቸው አይመስሉም። ምናልባትም በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰችው እንደ ሣራ የፆታ ግንኙነት መፈጸም አንቺንና ጓደኛሽን ይበልጥ እንደሚያቀራርባችሁ ይሰማሽ ይሆናል። ደግሞስ ድንግል በመሆኗ እንዲሾፍባት የምትፈልግ ማን አለች? ታዲያ የፆታ ግንኙነት እንድትፈጽሚ ስትጠየቂ እሺ ብትይ አይሻልም?

ተረጋጊ! ቆም ብለሽ ለማሰብ ሞክሪ! ከሁሉ በፊት ማወቅ ያለብሽ ነገር ቢኖር የፆታ ግንኙነት የሚፈጽመው ሁሉም ሰው አይደለም። እውነት ነው፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች የፆታ ግንኙነት እንደሚፈጽሙ የሚገልጽ አኃዛዊ መረጃ አንብበሽ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ በዩናይትድ ስቴትስ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው በአገሪቱ ከሚኖሩ ሦስት ወጣቶች መካከል ሁለቱ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከመጨረሳቸው በፊት የፆታ ግንኙነት ይፈጽማሉ። ይሁን እንጂ ይህ አኃዝ እንደሚያመለክተው ከሦስቱ ወጣቶች አንዱ የፆታ ግንኙነት አይፈጽምም፤ ይህ ደግሞ ቀላል ቁጥር አይደለም። ይሁንና የፆታ ግንኙነት ስለሚፈጽሙት ወጣቶች ምን ማለት ይቻላል? ከእነዚህ ወጣቶች አብዛኞቹ ቀጥሎ ከተዘረዘሩት ዱብ ዕዳዎች መካከል ቢያንስ አንዱ እንደሚያጋጥማቸው ተመራማሪዎች ደርሰውበታል።

ዱብ ዕዳ 1፦ የጥፋተኝነት ስሜት። ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት የፈጸሙ አብዛኞቹ ወጣቶች በኋላ ላይ እንደተቆጩ ተናግረዋል።

ዱብ ዕዳ 2፦ አለመተማመን። ወጣቶቹ የፆታ ግንኙነት ከፈጸሙ በኋላ ‘ከእኔ ሌላ ከማን ጋር ወጥታ ይሆን?’ ወይም ‘ከእኔ ሌላ ከማን ጋር ወጥቶ ይሆን?’ እያሉ ማሰብ ይጀምራሉ።

ዱብ ዕዳ 3፦ መከዳት። የፆታ ግንኙነት ከፈጸሙ በኋላ ወንዱ እሷን ትቶ ወደ ሌላ ሴት የመሄዱ አጋጣሚ በጣም ሰፊ ነው።

ዱብ ዕዳ 4፦ ቁጭት። ሴቷ የሚጠቀምባት ሳይሆን ከጉዳት የሚጠብቃት ወንድ መምረጥ እንደነበረባት ማሰብ ትጀምራለች።

ከላይ ከተገለጸው በተጨማሪ የሚከተለውን አስቢ፦ ብዙ ወጣት ወንዶች አብራቸው የፆታ ግንኙነት ከፈጸመች ሴት ጋር  በጋብቻ መኖር እንደማይፈልጉ ተናግረዋል። ለምን? ንጽሕናዋን የጠበቀች ወጣት ማግባት ስለሚመርጡ ነው!

ይህ የሚገርም ነው አይደል? ምናልባትም ከማስገረም አልፎ ያናድድሽ ይሆናል። ያም ሆነ ይህ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች የሚከተለውን እውነታ ማስታወስ ይኖርባቸዋል፦ ከጋብቻ በፊት ስለሚፈጸም የፆታ ግንኙነት ያለው እውነታ በፊልምና በቴሌቪዥን ላይ ከሚቀርበው እጅግ የተለየ ነው። የመዝናኛው ኢንዱስትሪ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች የሚፈጽሙትን የፆታ ግንኙነት ማራኪ አድርጎ በማቅረብ በመካከላቸው እውነተኛ ፍቅር እንዳለ ያስመስላል። ይሁን እንጂ አትሞኚ! ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት እንድትፈጽሚ የሚያባብሉሽ ሁሉ ሊጠቀሙብሽ የሚፈልጉ ሰዎች ብቻ ናቸው። (1 ቆሮንቶስ 13:4, 5) ደግሞስ ለአንቺ እውነተኛ ፍቅር ያለው ሰው አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ደህንነትሽን አደጋ ላይ እንዲወድቅ ያደርጋል? (ምሳሌ 5:3, 4) በእርግጥ የሚያስብልሽ ሰው ከአምላክ ጋር ያለሽን ዝምድና የሚያበላሽ ድርጊት እንድትፈጽሚ ይገፋፋሻል?—ዕብራውያን 13:4

ሐቁ የሚከተለው ነው፦ ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት እንድትፈጽሚ ለሚቀርብልሽ ጥያቄ እሺ የምትዪ ከሆነ ያለሽን እጅግ ውድ ነገር አሳልፈሽ በመስጠት ራስሽን ታዋርጃለሽ። (ሮም 1:24) በመሆኑም ብዙዎች የፆታ ግንኙነት ከፈጸሙ በኋላ ከሰውነታቸው ላይ አንድ ውድ ነገር በገዛ እጃቸው ያሰረቁ ያህል የባዶነትና የዋጋ ቢስነት ስሜት የሚሰማቸው መሆኑ ምንም አያስደንቅም! ይህ ሁኔታ በአንቺ ላይ እንዲደርስ አትፍቀጂ! አንድ ሰው “ብትወጂኝ ኖሮ እሺ ትይኝ ነበር” እያለ የፆታ ግንኙነት እንድትፈጽሚ ሊያባብልሽ ሲሞክር አንቺም ፈርጠም ብለሽ “አንተም ብትወደኝ ኖሮ ይህን እንድፈጽም አትጠይቀኝም ነበር!” በማለት መልሽለት።

ሰውነትሽ፣ እንዲሁ እንደዋዛ አሳልፈሽ ልትሰጪው የማይገባ እጅግ ውድ ነገር ነው። አምላክ ከዝሙት እንድትርቂ የሰጠሽን ትእዛዝ ለመጠበቅ የሚያስችል ጥንካሬ እንዳለሽ በተግባር አሳዪ። ደግሞም የፆታ ግንኙነት መፈጸሙን ስታገቢ ትደርሺበታለሽ። ያኔ ብዙውን ጊዜ ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ከሚያስከትለው ጭንቀት፣ ጸጸትና ያለመረጋጋት ስሜት ነፃ ሆነሽ በፆታ ግንኙነት የሚገኘውን ደስታ ሙሉ በሙሉ ማጣጣም ትችያለሽ።—ምሳሌ 7:22, 23፤ 1 ቆሮንቶስ 7:3

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 በዚህ ርዕሰ ትምህርት ውስጥ የተጠቀሱት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።

^ አን.6 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ዝሙት” የሚለው ቃል ያልተጋቡ ሰዎች የሚፈጽሙትን የፆታ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን የሌላውን የፆታ ብልት ማሻሸትን አሊያም በአፍ ወይም በፊንጢጣ ወሲብ መፈጸምን የመሳሰሉ ድርጊቶችንም ያመለክታል። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2 የተሰኘውን መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 42 እስከ 47 ተመልከቺ።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

● ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ፍጽምና ለጎደለው ሥጋችን የሚማርክ ቢመስልም እንኳን ይህን ማድረግ ትክክል ያልሆነው ለምንድን ነው?

● አንድ ሰው የፆታ ግንኙነት እንድትፈጽሙ ቢጠይቅሽ ምን ታደርጊያለሽ?

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

እኩዮችሽ ምን ይላሉ?

እምቢ ማለትሽ ብቻ ግለሰቡን እንደገና እንዳይጠይቅ አያደርገውም። ደግሞ እንዳይጠይቅሽ የሚያደርገው እምቢታሽን የምትገልጪበት መንገድ ነው። እንቢታሽን የምትገልጪው ቀለስለስ እያልሽ በማቅማማት ከሆነ በቀላሉ እንደማይተውሽ ግልጽ ነው። ኮስተር ብለሽ መናገር ይኖርብሻል!

እምቢ ማለት ብቻውን የማይበቃበት ጊዜ አለ። ስለ እምነታችን መናገርም ብዙ ላይረዳ ይችላል። ክርስቲያኖችን ‘ማንበርከክ’ እንደቻሉ በጉራ የሚናገሩ አንዳንድ ሰዎች አጋጥመውኛል። አንዳንድ ጊዜ ጥሎ መሄዱ የተሻለ ነው። እንዲህ ማድረግ ከባድ ቢሆንም ጥሩ ውጤት ያስገኛል።

ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን በሌሎች ዘንድ ተወዳጅ እንድንሆን የሚያደርጉን ባሕርያት አሉን። ስለዚህ ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት እንድንፈጽም ስንጠየቅ ንቁ መሆንና መቃወም ይኖርብናል። ላፈራናቸው ባሕርያት አክብሮት ይኑረን። በማይረባ ነገር አንለውጣቸው!

[ሥዕሎች]

ዲያና

ጄምስ

ጆሹዋ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንድትተማመንብህ አድርጋት!

የሴት ጓደኛ ካለችህ በእርግጥ ታስብላታለህ? ከሆነ ቀጥሎ የተዘረዘሩት ባሕርያት እንዳሉህ በተግባር አሳይ።

● የአምላክን ሕጎች ለማክበር የሚያስችል ጥንካሬ እንዳለህ

● ፈታኝ የሆኑ ሁኔታዎችን ለማስወገድ ጥበቡ እንዳለህ

● ለእሷ የሚጠቅማትን ነገር እንድታስብ የሚያደርግ ፍቅር እንዳለህ

እንዲህ የምታደርግ ከሆነ የሴት ጓደኛህ “ውዴ የእኔ ነው፤ እኔም የእርሱ ነኝ” በማለት እንደተናገረችው ሱላማጢስ ልጃገረድ ዓይነት ስሜት ይኖራታል። (ማሕልየ መሓልይ 2:16) በአጭሩ፣ ትተማመንብሃለች!

ምሳሌ 22:3ን፤ 1 ቆሮንቶስ 6:18ን እና 13:4-8ን ተመልከት።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጠቃሚ ምክር

ከተቃራኒ ፆታ ጋር በተያያዘ ሊኖርሽ የሚገባውን ምግባር በተመለከተ ልትከተይው የሚገባ ጥሩ መመሪያ፦ ልትፈጽሚው ያሰብሽውን ነገር ወላጆችሽ እንዲያዩት የማትፈልጊ ከሆነ ልታደርጊው አይገባም።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም የአምላክን ስጦታ አላግባብ መጠቀም ነው። አንድ ሰው የሰጠሽን ውብ ሥዕል በር ላይ የጫማ መጥረጊያ እንዲሆን ከማድረግ ጋር የሚመሳሰል ነው