በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክን ስም በዴንማርክ ይመልከቱ

የአምላክን ስም በዴንማርክ ይመልከቱ

 የአምላክን ስም በዴንማርክ ይመልከቱ

በየዓመቱ ኮፐንሃገንን ከሚጎበኙ በሺህ የሚቆጠሩ ቱሪስቶች መካከል ብዙዎቹ ይሖዋ ወይም በዕብራይስጥ አጻጻፉ יהוה የሚለውን የአምላክ ስም በዋና ከተማይቱ ውስጥም ሆነ በዙሪያዋ በሚገኙ ጥንታዊ ግንብ ቤቶችናና ሌሎች ሕንጻዎች ላይ ተቀርጾ ማየታቸው በጣም አስገርሟቸዋል። * ለምሳሌ ያህል፣ በከተማይቱ እምብርት ላይ የሚገኘው ዶክያርድ ቤተ ክርስቲያን የአምላክ ስም በወርቃማ ቀለም የተቀረጸበት ትልቅ በር አለው። በተጨማሪም ስሙ በበሩ በውስጥ በኩል በሚገኝ በ1661 በተቀረጸ የመታሰቢያ ሰሌዳ ላይ ይገኛል።

በዶክያርድ ቤተ ክርስቲያን አቅራቢያ ራውንድ ታወር የሚባል ሕንጻ ይገኛል። በዚህ ሕንጻ የውጪ ግድግዳ ላይ ተለጥፎ በሚገኝ በላቲን ቋንቋ የተዘጋጀ አርማ ላይ የአምላክ ስም በትልልቅ የዕብራይስጥ ፊደላት ተጽፎ ይታያል። አርማው ላይ ያለው ሐሳብ ሲተረጎም “ይሖዋ የንጉሡን የክርስቲያን አራተኛን ልብ ወደ ትክክለኛ መሠረተ ትምህርትና ወደ ፍትሕ ይምራ” ይላል። የአምላክ ስም ዴንማርክ ውስጥ ይህን ያህል በስፋት ሊታወቅ የቻለው እንዴት ነው?

የፕሮቴስታንት ተሃድሶና የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም

የአምላክ ስም በስፋት እንዲታወቅ ከፍተኛውን አስተዋጽዖ ያበረከተው የፕሮቴስታንት ተሃድሶ ነው። እንደ ማርቲን ሉተር፣ ጆን ካልቪንና ሁልድሪክ ዝዊንግሊ ያሉ አውሮፓውያን የተሃድሶ አራማጆች መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ የተጻፈባቸውን ቋንቋዎች ይኸውም ዕብራይስጥን፣ አረማይክንና ኮይኔ ተብሎ የሚጠራውን ተራው ሕዝብ የሚጠቀምበት ግሪክኛ በጥልቀት አጠኑ። በዚህም ምክንያት የአምላክን የተጸውኦ ስም በሚገባ ሊያውቁ ቻሉ። ማርቲን ሉተር በአንድ ወቅት በስብከቱ ላይ “ይሖዋ የሚለው ይህ ስም . . . እውነተኛው አምላክ ብቻ የሚጠራበት ስም ነው” ብሎ ነበር።

ይሁንና ሉተር መለኮታዊውን ስም “ጌታ” ወይም “አምላክ” በሚሉት የማዕረግ ስሞች ከመተካቱ የተሳሳተ ልማድ ስላልተላቀቀ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ጀርመንኛ በተረጎመ ጊዜ የአምላክን የተጸውኦ ስም ሳይሆን የማዕረግ ስሞቹን ተጠቅሟል። ከጊዜ በኋላ ሉተር እሱ የተረጎመውን መጽሐፍ ቅዱስ በሰሜናዊ ጀርመንና በደቡባዊ ዴንማርክ ይነገር በነበረው የጀርመን ቋንቋ ቀበሌኛ እንዲያዘጋጅ ዮሐነስ ቡገንሃገን  የተባለ ጓደኛውን ጠየቀው። ቡገንሃገን በ1541 እትሙ መቅድም ላይ (የመጀመሪያው እትም የወጣው 1533 ነው) “ይሖዋ የአምላክ ቅዱስ ስም ነው” የሚለውን ዓረፍተ ነገር ጨምሮ መለኮታዊውን ስም በተደጋጋሚ ጊዜያት ጠቅሶ ነበር።

በ1604 ሃንስ ፖልዘን ሬዘን የተባለ ወጣት የሥነ መለኮት ምሑር፣ በሉተር መጽሐፍ ቅዱስ የዴኒሽ ትርጉም ውስጥ አንዳንድ ስህተቶች እንደሚገኙ ለንጉሥ ክርስቲያን አራተኛ አሳወቀ። ከዚያም ሬዘን መጀመሪያ በተጻፉት የዕብራይስጥና የግሪክኛ መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ አዲስ ትርጉም ለማዘጋጀት ጥያቄ አቅርቦ ፈቃድ ተሰጠው። ሬዘን ዘፍጥረት 2:4ን አስመልክቶ ባሰፈረው ማስታወሻ ላይ “ይሖዋ ከሁሉ በላይ የሆነ ብቸኛው ጌታ ነው” ብሏል። *

መለኮታዊው ስም እየታወቀ በሄደ መጠን ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ መጻፍ ጀመረ። ለምሳሌ ያህል፣ በ1624 ሃንስ ፖልዘን ሬዘን ጳጳስ ሆኖ ከተሾመ በኋላ በብሮንስሆይ ቤተ ክርስቲያን አንድ የመታሰቢያ ሰሌዳ እንዲቆም አዝዞ ነበር። በሰሌዳው አናት ላይ ጀሆቫ የሚለው የአምላክ ስም በወርቃማ ቀለም በዴኒሽ ቋንቋ ተጽፏል። በተጨማሪም ሬዘን ጳጳስ በነበረባቸው ዓመታት በጻፋቸው በአብዛኞቹ ጽሑፎች ላይ ከፊርማው ጋር “ይሖዋ ያያል” የሚሉ ቃላትን ያሰፍር ነበር።

በ18ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ አካባቢ ዮሐን ዳቪድ ሚካኤሊስ ያዘጋጀው ጀርመንኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በዴኒሽ ቋንቋ ወጣ። በዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ላይም መለኮታዊው ስም በበርካታ ቦታዎች ላይ ይገኛል። በ19ኛው መቶ ዘመንም ክርስቲያን ካልካር እና ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች መለኮታዊው ስም በበኩረ ጽሑፉ ላይ በሚገኝባቸው በአብዛኞቹ ቦታዎች ላይ እንዲገባ አድርገዋል። በ1985 ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች አዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉምን በዴኒሽ ቋንቋ አወጡ። የመጽሐፍ ቅዱስ አፍቃሪዎች ይሖዋ የሚለው ስም ከ7,000 ጊዜ በላይ ተጠቅሶ በማግኘታቸው በጣም ተደስተዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ለአምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ “ስምህን ገልጬላቸዋለሁ” ብሎ ነበር። (ዮሐንስ 17:6) በተጨማሪም ኢየሱስ “አባታችን ሆይ” ተብሎ በሚጠራው የናሙና ጸሎት ላይ “ስምህ ይቀደስ” ብሏል። (ማቴዎስ 6:9) የዴንማርክ የሃይማኖት ታሪክ እንደሚያሳየው ብዙ ሰዎች ለእነዚህ ቃላት ትልቅ ቦታ ሰጥተዋል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 ቴትራግራማተን የሚባሉት እነዚህ አራት ፊደላት ተነባቢ (consonant) ሲሆኑ የሚነበቡትም ከቀኝ ወደ ግራ ነው። እነዚህ ፊደላት በአማርኛ የሚጻፉት የሐወሐ ተብለው ነው። በዛሬው ጊዜ ምኅጻረ ቃላት እንደሚነበቡት ሁሉ በጥንት ጊዜ ሰዎች ፊደላቱን አናባቢ እየጨመሩ ያነቧቸው ነበር።

^ አን.7 ዘፍጥረት 2:4 የአምላክ የተጸውኦ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ በኩረ ጽሑፍ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጽፎ የሚገኝበት ቦታ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ በኩረ ጽሑፍ ላይ 7,000 ጊዜ ያህል ተጠቅሶ የሚገኘው ይህ ስም “ይሆናል” የሚል ትርጉም ያለው መሆኑ ይሖዋ ምንጊዜም ዓላማውን ዳር የሚያደርስ አምላክ መሆኑን ያመለክታል። ይሖዋ የተናገረው ሁሉ ይፈጸማል።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ታይኮ ብራህ እና የአምላክ ስም

ታይኮ ብራህ የተባለው ዝነኛ የሥነ ፈለክ ተመራማሪ በ1597 ከዴንማርክ መኳንንትና ከንጉሥ ክርስቲያን አራተኛ ጋር ባለመግባባቱ የትውልድ አገሩን ጥሎ ተሰደደ። ብራህ ለዴንማርክ በተቀኘው የስንብት ግጥም ላይ በላቲንኛ “የይሖዋ ፈቃድ ስለሆነ የባዕድ አገር ሰዎች በደግነት ይቀበሉኛል” ሲል ጽፏል።

[በገጽ 24 እና 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የዶክያርድ ቤተ ክርስቲያን በር

[በገጽ 24 እና 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ራውንድ ታወር

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሃንስ ፖልዘን ሬዘን

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዮሐነስ ቡገንሃገን፣ በ1541 በጀርመን ቋንቋ ቀበሌኛ ባዘጋጀው የሉተር መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መቅድም ላይ የአምላክን ስም ተጠቅሟል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ሃንስ ፖልዘን ሬዘን እና ታይኮ ብራህ፦ Kobberstiksamlingen, Det Kongelige Bibliotek, København