በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቴክኖሎጂን በአሳቢነትና በቁጠባ ተጠቀሙበት

ቴክኖሎጂን በአሳቢነትና በቁጠባ ተጠቀሙበት

 ቴክኖሎጂን በአሳቢነትና በቁጠባ ተጠቀሙበት

በ20ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኘው ካትሪን በሥራ ቦታዋ ኮምፒውተር ትጠቀማለች። ይሁን እንጂ ቤቷ በምትሆንበት ጊዜም ድረ ገጾችን በመቃኘት፣ በኢንተርኔት አማካኝነት በመገብየትና ለሚደርሷት ስፍር ቁጥር የሌላቸው የኢ-ሜይል መልእክቶች ምላሽ በመስጠት ረዘም ያለ ጊዜ ታሳልፋለች። ያም ሆኖ በዕድሜ ከእሷ ከሚያንሱ የሥራ ባልደረቦቿ ጋር ስትወዳደር በቴክኖሎጂ የምትጠቀምበት መንገድ መጠነኛ ነበር። “የማይረቡ የጽሑፍ መልእክቶች ሁልጊዜ እየላኩ የሚያስቸግሩኝ ለምንድን ነው?” በማለት ትጠይቃለች። “እኔ ሰው ነኝ! ስልክ ደውለው የማያናግሩኝ ለምንድን ነው?”

ካትሪን እዚህ ላይ ያነሳችው ሐሳብ እርሱ በርሱ የሚጋጭ ይመስላል፤ ምክንያቱም ስልክም ቢሆን ፊት ለፊት ለመነጋገር አያስችልም። ያም ቢሆን ካትሪን የተናገረችው ሐሳብ በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው ነው፦ ሰዎችን ለማገናኘት ተብለው የተሠሩ ብዙ የመገናኛ ዘዴዎች እንዲያውም ሰዎች ልብ ለልብ እንዳይቀራረቡ አድርገዋል። የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መጠቀም እንድትችል ቀጥሎ የቀረቡትን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተመልከት።

“እንግዲህ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም እንደዚሁ ልታደርጉላቸው ይገባል።” (ማቴዎስ 7:12) ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረውን ይህንን ሐሳብ በስልክና በኮምፒውተር አጠቃቀማችን ረገድ በሥራ ላይ ስናውለው ሌሎችን በአክብሮት ከመያዛችንም በላይ ጥሩ ሥነ ምግባር እናሳያለን። አን የተባለች ሴት እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “እኔና ባለቤቴ በአንድ ምግብ ቤት ተቀምጠን ነበር። አጠገባችን ባለው ጠረጴዛ ላይ ሁለት ሰዎች አብረው ምግብ እየበሉ ነበር። ይሁንና አንደኛው ሰው ምግቡን በልቶ እስኪጨርስ ድረስ በሞባይል ስልኩ እያወራ ነበር። ‘ብቻውን’ የበላው ጓደኛው አሳዘነን።” አንተ በሞባይል የሚያወራው ሰው ጓደኛ ብትሆን ኖሮ ምን ይሰማህ ነበር? በሁኔታው ቅር ይልህ ነበር? ትናደድ ነበር? በእርግጥም፣ በማንኛውም ቦታና ጊዜ በሞባይል ስልክ መጠቀም እንችላለን ሲባል እንዲህ ልናደርግ ይገባል ማለት አይደለም። ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ በዚህ ረገድ መመሪያ ሊሆነን ይገባል።

“የምትመላለሱት ጥበብ እንደጎደላቸው ሰዎች ሳይሆን እንደ ጥበበኛ ሰዎች መሆኑን ምንጊዜም በጥንቃቄ አስተውሉ፤ . . . ለራሳችሁ አመቺ የሆነውን ጊዜ ግዙ።” (ኤፌሶን 5:15, 16) ጊዜ ከአምላክ ያገኘነው ውድ ስጦታ ስለሆነ ልናባክነው አይገባም። በቴክኖሎጂ ውጤቶች መጠቀም ጊዜ ሊቆጥብልን እንደሚችል አያጠራጥርም። ለምሳሌ ምርምር ለማድረግ፣ ዕቃዎችን ለመግዛት እንዲሁም በባንክ የገንዘብ ዝውውር ለማድረግ በኢንተርኔት መጠቀም ጊዜ ሊቆጥብልን ይችላል። ይሁን እንጂ ያለ አንዳች ዓላማ ለረጅም ሰዓታት ድረ ገጾችን የምንቃኝ ከሆነ ኢንተርኔት ጊዜያችንን ሊያባክንብን ይችላል።

ሌላው ጊዜያችንን ሊያባክንብን የሚችል ነገር ደግሞ በአንድ  ጊዜ በርካታ ሥራዎችን ደራርቦ መሥራት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ቴሌቪዥን እየተመለከቱና ስልክ እያወሩ ኮምፒውተር ላይ መሥራት ወይም ኢ-ሜይል እያደረጉ በሌሎች የኮምፒውተር ፕሮግራሞች መጠቀም ጊዜያችንን ያባክንብናል። በአንድ ጊዜ በርካታ ሥራዎችን ደራርቦ መሥራት ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝነው ለምንድን ነው?

“በአንድ ጊዜ በርካታ ሥራዎችን ደራርባችሁ የምትሠሩ ከሆነ በአብዛኛው ስለ አንዱም ሥራ ጥልቀት ያለው እውቀት ሊኖራችሁ አይችልም” በማለት በነርቭ ጥናት ሊቅ የሆኑት ዶክተር ጆርዳን ግራፍማን ይናገራሉ። በአንድ ጊዜ ለበርካታ ነገሮች ትኩረት መስጠት አንችልም፤ አንደኛው ሥራ መበደሉ አይቀርም። እንዲህ ማድረግ ሥራው የይድረስ ይድረስ እንዲሆን የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ ነገሮችን በደንብ ማስታወስ እንዳንችል ያደርጋል። በተጨማሪም ታይም መጽሔት ላይ የወጣ ዘገባ እንደሚገልጸው ሰዎች በአንድ ጊዜ በተለያዩ ነገሮች ላይ ትኩረት ለማድረግ መሞከራቸው ብዙ ስህተት እንዲፈጽሙና “ሥራዎቹን ተራ በተራ ቢሠሯቸው ኖሮ ከሚፈጅባቸው የበለጠ ረጅም ጊዜ እንዲያውም እጥፍ ወይም ከዚያ በላይ ጊዜ እንዲወስዱ” ያደርጋቸዋል። ስለዚህ በአንድ ጊዜ በርካታ ሥራዎችን ደራርባችሁ ለመሥራት ከመነሳታችሁ በፊት ቆም ብላችሁ አስቡ፤ ያሰባችሁትን ሁሉ ለማከናወን ቀኑ ላይበቃችሁ ይችላል!

“አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ሕይወቱ በንብረቱ ላይ የተመካ ስላልሆነ ተጠንቀቁ፤ ከመጎምጀትም ሁሉ ተጠበቁ።” (ሉቃስ 12:15) ቁሳዊ ንብረት የቱንም ያህል ውድ ወይም ዘመናዊ ቢሆን ሕይወትም ሆነ እውነተኛ ደስታ አያስገኝም። እነዚህን ነገሮች ሊሰጠን የሚችለው አምላክ ብቻ ነው። ኢየሱስ “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው” ብሏል። (ማቴዎስ 5:3) በሌላ በኩል ደግሞ የንግዱ ዓለም ደስታ የሚገኘው በቁሳዊ ነገሮች እንደሆነ ይገልጻል። ‘ግዙ፣ ግዙ፣ ግዙ” የሚል ፕሮፖጋንዳ ይነዛል። እንዲሁም ‘ከሆነ አይቀር ዘመናዊ የሆነው ዕቃ ሊኖራችሁ ይገባል’ ይላል። በዚህ ዓይነቱ ፕሮፖጋንዳ ከመታለል ይልቅ ጠቢብ መሆን አለባችሁ። ለፍታችሁ ያገኛችሁትን ገንዘብ ከማጥፋታችሁ በፊት አንድን ዕቃ የምትገዙበትን ምክንያትና ዕቃው በእርግጥ የሚያስፈልጋችሁ መሆኑን አጢኑ። እንዲሁም ብዙ ዘመናዊ ዕቃዎች ተፈላጊነታቸው በፍጥነት እንደሚቀንስ አስታውሱ። ስለዚህ አንድ ዘመናዊ ዕቃ መግዛት ቢያስፈልጋችሁ ‘የግድ በቅርብ የወጣውን መግዛት ይኖርብኛል? ደግሞስ ምናልባትም ጨርሶ የማልጠቀምባቸው በርካታ ተጨማሪ ገጽታዎች ያሉትን ውድ ዕቃ መግዛት ያስፈልገኛል?’ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ።

በረከት ወይስ እርግማን—ምርጫው የእናንተ ነው

ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ካትሪን፣ ቤቷ የምትጠቀምበት ኮምፒውተር በተበላሸ ጊዜ ነገሩ በጣም አሳስቧት ነበር። “መጀመሪያ ላይ ደንግጬ ነበር፤ ያም ሆኖ ወዲያው ሌላ ኮምፒውተር ላለመግዛት ወሰንኩ። ከወር በኋላ ግን ይበልጥ የተረጋጋሁ ከመሆኑም ሌላ ከበፊቱ የበለጠ ማንበብ ጀመርኩ። በሥራ ቦታ በኮምፒውተር ስለምጠቀም አሁንም ቢሆን ከሥራ ሰዓት ውጪ ከጓደኞቼ ጋር መልእክት መለዋወጥ እችላለሁ። ይሁን እንጂ እንደቀድሞው ረዘም ላለ ጊዜ በኮምፒውተር መጠቀም እንደሚያስፈልገኝ አይሰማኝም። ከእንግዲህ ቴክኖሎጂ ሕይወቴን አይቆጣጠረውም።”

በርካታ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች ጠቃሚ እንደሆኑና ብዙ ጊዜና ጉልበት ሊቆጥቡልን እንደሚችሉ የማይካድ ነው። ስለዚህ የሚያስፈልጓችሁ ከሆነ ከመጠቀም ወደ ኋላ አትበሉ፤ ይሁን እንጂ ኃላፊነት እንደሚሰማችሁ በሚያሳይና አሳቢነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ተጠቀሙባቸው። እንዲህ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? ከቴክኖሎጂ ውጤቶች ይበልጥ ለሰዎች ቅድሚያ ስጡ። ውድ ጊዜያችሁንና ገንዘባችሁን የማያስፈልጓችሁን ዘመናዊ ዕቃዎች ወይም የኮምፒውተር ፕሮግራሞች በመግዛት አታባክኑ። ኢንተርኔትንም ሆነ ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎችን በሥነ ምግባር ያዘቀጠና ዓመፅ የሚንጸባረቅበት ነገር ለማየት አትጠቀሙባቸው። እንዲሁም የቴክኖሎጂ “ሱሰኛ” አትሁኑ። በአጭር አነጋገር ጠቢብ ሁኑ፤ በጽሑፍ በሰፈረው የአምላክ ቃል ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን በመንፈስ መሪነት የተነገሩና ዘመን የማይሽራቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ አውሉ። በእርግጥም፣ “እግዚአብሔር ጥበብን [ይሰጣል]፤ ከአንደበቱም ዕውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ።”—ምሳሌ 2:6

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ሞባይል ስልኮች፣ ኮምፒውተሮችና ጥሩ ሥነ ምግባር

ሞባይል ስልክህንና ኮምፒውተርህን አሳቢነት በሚታይበት መንገድ ልትጠቀምባቸው የምትችለው እንዴት ነው? የሚከተሉትን ሐሳቦች ተመልከት።

▪ ሌሎችን ልትረብሽ በምትችልበት ሁኔታ ወይም ቦታ ላይ የስልክ ጥሪ አትቀበል ወይም አትደውል። አስፈላጊ ከሆነ ስልክህን አጥፋው።

▪ አስፈላጊ ስለሆነ ጉዳይ ከአንድ ሰው ጋር ፊት ለፊት እየተነጋገርክ ባለህበት ጊዜ አንገብጋቢ ጉዳይ ካልገጠመህ በቀር ስልክህን አትጠቀም።

▪ በስልክ በምታወራበት ጊዜ እያነጋገርከው ያለኸውን ሰው ከልብ አዳምጠው።

▪ በሞባይል ስልክህ ሌላ ሰውን ፎቶግራፍ ማንሳት ግለሰቡን የሚያሳፍረው ወይም እንዲህ ማድረግህ ጨዋነት የጎደለው ድርጊት እንደሆነ የሚሰማው ከሆነ እንዲህ አታድርግ።

▪ “አስደሳች” ነው ብለህ የምታስበውን የኢ-ሜይል መልእክት በሙሉ ለሌሎች ከማስተላለፍ ተቆጠብ። መልእክቱ የሚደርሳቸው ሰዎች እንዲህ ማድረግህን ላይወዱት ይችላሉ።