በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታዲያ ምን ልልበስ?

ታዲያ ምን ልልበስ?

 የወጣቶች ጥያቄ

ታዲያ ምን ልልበስ?

ሄዘር ከቤት ወጣ ለማለት ተዘጋጅታለች፤ ነገር ግን ወላጆቿ ሲያዩዋት ዓይናቸው ማመን አቅቷቸዋል።

“ይህን ለብሰሽ ልትሄጂ ነው?” በማለት አባቷ በጩኸት ተናገራት።

ሄዘር በጥያቄው በመገረም “ምናለበት? የምሄደውኮ ከጓደኞቼ ጋር ዕቃ ለመግዛት ነው” ብላ መለሰች።

እናቷ “እሱን ለብሰሽማ አትሄጂም!” አለቻት።

“እንዴ እማዬ! ሁሉም ልጆች የሚለብሱት እኮ እንዲህ ነው” በማለት ሄዘር ተነጫነጨች። “በዚህ ላይ ልብሱ ‘ይናገራል!’” አለች።

“ልክ ነሽ ልብሱ ‘ይናገራል፣’ እኛ ግን የሚያስተላልፈውን መልእክት አልወደድነውም!” አለ አባቷ ኮስተር ብሎ። ከዚያም “በይ የኔ እመቤት፣ ወደ ውስጥ ገብተሽ ሌላ ልብስ ቀይሪ። አለዚያ ይህን ለብሰሽ የትም አትሄጃትም!” አላት።

በልብስ ጉዳይ መጨቃጨቅ አዲስ ነገር አይደለም። ወላጆቻችሁ በእናንተ ዕድሜ ላይ ሳሉ እነሱም በተመሳሳይ ከወላጆቻቸው ጋር ሙግት ገጥመው ሊሆን ይችላል። ምናልባት ወላጆቻችሁ በዚያን ጊዜ የነበራቸው ስሜት ዛሬ እናንተ ካላችሁ ስሜት ጋር ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል! አሁን ግን ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኗል፤ የምትለብሱትን ልብስ በተመለከተ በተደጋጋሚ ጊዜ በመካከላችሁ ጭቅጭቅ ይነሳ ይሆናል።

ልጅ፦ ልብሱ ይመቻል።

ወላጅ፦ ቅጥ ያጣ ነው።

ልጅ፦ በጣም ያምራል!

ወላጅ፦ ወንዶችን ለመሳብ ነው።

ልጅ፦ ዋጋው በግማሽ ይቀንሳል።

ወላጅ፦ ታዲያ ቢረክስ ምን ይገርማል። . . . ብጣቂ ጨርቅ እኮ ነው!

እንዲህ ዓይነቱን ንትርክ ማስቀረት የሚቻልበት መንገድ ይኖር ይሆን? አዎን! አሁን 23 ዓመት የሆናት ሜጋን ለዚህ ሚስጥሩ ምን እንደሆነ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “መጀመሪያውኑ መጨቃጨቅ አያስፈልግም። ከስምምነት ላይ መድረስ ይቻላል።” የአንቺና የወላጆችሽ አመለካከት የተለያየ ሆኖ ሳለ እንዴት መስማማት ይቻላል? ወይስ እንደ ትልቅ ሰው መልበስ አለብሽ ማለት ነው? ቆይ፣ ተረጋጊ! መስማማት ሲባል አንቺና ወላጆችሽ በልዩነቶቻችሁ ላይ መወያየትና ሁለታችሁም የምትቀበሏቸውን ሌሎች አማራጮች መፈለግ ማለት ነው። እንዲህ ማድረጉ ምን ጥቅም ያስገኛል?

1. በእኩዮችሽ ዘንድ እንኳን ሳይቀር በጣም አምረሽ እንድትታዪ ያደርግሻል።

2. የምትለብሽውን ልብስ በተመለከተ ከወላጆችሽ ጋር የመጨቃጨቁ አጋጣሚ እየቀነሰ ይሄዳል።

3. ወላጆችሽ በዚህ ረገድ ምን ያህል እምነት የሚጣልብሽ እንደሆንሽ ሲያዩ ተጨማሪ ነፃነት ሊሰጡሽ ይችላሉ።

እስቲ ምን ማድረግ እንዳለብሽ እየተወያየን እንሂድ። ሰው ላይ አሊያም ሱቅ ውስጥ ወይም ደግሞ በኢንተርኔት ያየሽውን አንድ “ሊኖረኝ ይገባል” ብለሽ የምታስቢውን ልብስ ወደ አእምሮሽ ለማምጣት ሞክሪ። በመጀመሪያ ልታደርጊው የሚገባው ነገር . . .

የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ግምት ውስጥ ማስገባት

የሚገርመው መጽሐፍ ቅዱስ አለባበስን በተመለከተ የሚናገረው ነገር በጣም ጥቂት ነው። እንዲያውም ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ  ጋር ቀጥታ ተያያዥነት ያላቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮች በሙሉ በደቂቃዎች ውስጥ አንብበሽ መጨረስ ትችያለሽ! ምክሮቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተነበው የሚያልቁ ቢሆኑም እንኳ አስተማማኝና ጠቃሚ መመሪያዎች ሊሆኑሽ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፦

▪ መጽሐፍ ቅዱስ ሴቶች ራሳቸውን “በልከኝነትና በማስተዋል” እንዲያስውቡ ይመክራቸዋል። *1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10

“ልከኝነት” የሚለው ቃል ያስጨንቅሽ ይሆናል። ‘ታዲያ የአሮጊት ልብስ መልበስ ይኖርብኛል ማለት ነው?’ ብለሽ ታስቢ ይሆናል። በጭራሽ! እንደዚያ ማለት አይደለም። በአለባበስ ረገድ ልከኛ መሆን ሲባል ለራሳችን አክብሮት እንዳለንና ለሌሎች ስሜት እንደምናስብ በሚያሳይ መንገድ መልበስ ማለት ነው። (2 ቆሮንቶስ 6:3) ይህን መሥፈርት የሚያሟሉ ብዙ ልብሶች ማግኘት ይቻላል። የ23 ዓመቷ ዳኒየል እንዲህ ትላለች፦ “መምረጡ ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል፤ ይሁን እንጂ በጣም ፋሽን ባትከተሉም ዘመናዊ አለባበስ ሊኖራችሁ ይችላል።”

▪ አለባበስን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ለተሰወረው የልብ ሰው’ ወይም እንደ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ‘ለውስጥ ሰውነት ውበት’ ትኩረት መስጠት እንዳለብሽ ይናገራል።—1 ጴጥሮስ 3:4

ልከኛ ያልሆነ ልብስ ለጊዜው የሰዎችን ትኩረት ይስብ ይሆናል፤ ውስጣዊ ውበት ግን በአዋቂዎችም ሆነ በእኩዮችሽ ዘንድ ዘላቂ አክብሮትን ያተርፍልሻል። ‘ደግሞ በእኩዮቼ ዘንድ የሚያስከብረኝ እንዴት ነው?’ ትዪ ይሆናል። እኩዮችሽም እንኳ ከመጠን ያለፈ ፋሽን መከተል ሞኝነት እንደሆነ ያስተውሉ ይሆናል። “ሴቶች በአለባበሳቸው የወንዶችን ትኩረት ለመሳብ ሲሞክሩ ማየት ያስጠላል!” በማለት የ16 ዓመቷ ብሪትኒ ትናገራለች። ኬይም በዚህ አባባል ትስማማለች። ኬይ፣ ስለ ቀድሞ ጓደኛዋ ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “የምትለብሳቸው ልብሶች በሙሉ ‘እዩኝ’ የሚል ጽሑፍ የተጻፈባቸው ያህል ነበር። ወንዶችን ለመማረክ ትፈልግ ስለነበር ትኩረት የሚስቡ ልብሶችን ለመልበስ የማታደርገው ጥረት አልነበረም።”

ፋሽንን አስመልክቶ የተሰጠ ጠቃሚ ምክር፦ የፆታ ስሜትን ከሚቀሰቅሱ አለባበሶች ተቆጠቢ። እንዲህ ዓይነቱ አለባበስ  ለፆታ ስሜት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለሽ እንዲሁም ለሌሎች ግድ የለሽ እንደሆንሽ ሊያስመስል ይችላል። በተጨማሪም ለፆታዊ ትንኮሳ ወይም ከዚያ ለከፋ ነገር ሊያጋልጥሽ ይችላል። በተቃራኒው ደግሞ ልከኛ አለባበስ ይበልጥ አምረሽ እንድትታዪ የሚያደርግሽ ከመሆኑም በላይ ጥሩ ምግባርሽ ጎልቶ እንዲታይ ሊያደርግ ይችላል።

የወላጆችን ሐሳብ መቀበል

ወላጆችሽ እንድትለብሺው የማይፈቅዱልሽን ልብስ በቦርሳሽ በመያዝ ትምህርት ቤት ስትደርሺ መቀየሩ ተገቢ አይደለም። ከወላጆችሽ መደበቅ በምትችያቸው ነገሮች ረገድም እንኳ ግልጽና ሐቀኛ መሆንሽ ይበልጥ የእነሱን አመኔታ እንድታተርፊ ይረዳሻል። እንዲያውም አንድን ልብስ ለመግዛት ስታስቢ የወላጆችሽን አስተያየት ብትጠይቂ መልካም ነው።—ምሳሌ 15:22 

ይሁን እንጂ የወላጆችሽን ምክር መጠየቅ ያለብሽ ለምንድን ነው? ‘ወላጆቼ እንደሆነ የእኔን የፋሽን ምርጫ ከማፈን ውጪ ሌላ ሥራ የላቸውምትዪ ይሆናል። ነገር ግን ሁልጊዜ እንደዚያ ነው ማለት አይደለም። እውነት ነው፣ ወላጆችሽ ነገሮችን የሚያዩት ከአንቺ በተለየ መንገድ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ያለ አስተያየት ማግኘትሽ አስፈላጊ አይደለም? የ17 ዓመቷ ናታሌይን እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ የሚሰጡኝን ምክር አደንቃለሁ። ምክንያቱም ከቤት በምወጣበት ጊዜ አለባበሴ የማፍርበት ወይም ሰዎች ስለ እኔ አሉታዊ ነገር እንዲናገሩ የሚያደርግ እንዲሆን አልፈልግም።”

ከዚህም ሌላ አንድ አምነሽ ልትቀበዪው የሚገባ ሐቅ አለ፦ ከወላጆችሽ ጋር በአንድ ጣራ ሥር እስከኖርሽ ድረስ በእነሱ ቁጥጥር ሥር ነሽ። (ቆላስይስ 3:20) ያም ሆኖ፣ አንዴ የእነሱ አመለካከት ከገባሽና እነሱም የአንቺን ስሜት ከተረዱ በኋላ በመካከላችሁ የነበረው ጭቅጭቅ ምን ያህል እንደቀነሰ ስታዪ ትገረሚ ይሆናል። እንዲያውም ውሎ አድሮ በልብስ ጉዳይ መነታረኩ ከናካቴው ሊቀር ይችላል!

ፋሽንን አስመልክቶ የተሰጠ ጠቃሚ ምክር፦ ገበያ ወጥተሽ አንድን ልብስ ስትሞክሪ በመስታወት ውስጥ ከምታዪው ባሻገር ያለውን ነገር ለማየት ሞክሪ። ልከኛ መስሎ የታየሽ ልብስ ስትቀመጪ ወይም አንድ ነገር ለማንሳት ጎንበስ ስትዪ እንዳሰብሽው ላይሆን ይችላል። ከተቻለ ወላጆችሽን አሊያም አንድ የጎለመሰ ጓደኛሽን አማክሪ።

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.23 እንዲህ ያሉት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክሮች በቀጥታ የተነገሩት ለሴቶች ቢሆንም መሠረታዊ ሥርዓቱ ለወንዶችም ይሠራል።  “ስለ ወንዶችስ ምን ማለት ይችላል?” የሚለውን ሣጥን ተመልከቱ።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

ልትገዢው ስለምትፈልጊው አንድ ልብስ ለማሰብ ሞክሪ። ከዚያም ራስሽን እንደሚከተለው በማለት ጠይቂ፦

▪ ይህ ልብስ ምን “መልእክት” ያስተላልፋል?

▪ በሌሎች ላይስ ምን ዓይነት ስሜት ሊያሳድር ይችላል?

▪ ሰዎች እንዲያዩኝ የምፈልገው በዚያ መንገድ ነው? በዚህስ ምክንያት የሚመጣውን ውጤት ለመቀበል ፈቃደኛ ነኝ?

 [በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ልብስ ለመምረጥ የሚረዳ ሣጥን

መመሪያ፦ ይህን ገጽ ፎቶ ኮፒ አድርጊ። አንቺ በስተግራ በኩል ያለውን ረድፍ ሙዪ፤ ወላጆችሽ ደግሞ በስተቀኝ ያለውን ረድፍ እንዲሞሉ አድርጊ። ከዚያም የሞላችኋቸውን ወረቀቶች ተለዋወጡና በመልሶቻችሁ ላይ ተወያዩ። ያልጠበቃችሁት መልስ አገኛችሁ? አንዳችሁ ስለ ሌላው ከዚህ በፊት የማታውቁት ምን ነገር አስተዋላችሁ?

አንቺ የምትሞዪው

ልትለብሽው ወይም ልትገዢው ስለፈለግሽው አንድ ልብስ አስቢ።

▪ ይህን ልብስ የወደድሽው ለምንድን ነው? ከዚህ በታች ያሉትን ምክንያቶች ከተመለከትሽ በኋላ ቅድሚያ የምትሰጫቸውን ነገሮች በማሰብ በቅደም ተከተል ቁጥር ስጪያቸው።

․․․․․․ ልብሱ ላይ ባለው የንግድ ምልክት ምክንያት

․․․․․․ ወንዶችን ለመሳብ

․․․․․․ በእኩዮችሽ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ለማግኘት

․․․․․․ የሚመች ስለሆነ

․․․․․․ ዋጋው

․․․․․․ ሌላ ․․․․․․

▪ ወላጆችሽ የመረጥሽውን ልብስ ገና እንዳዩት የሚሰጡት ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል ብለሽ ታስቢያለሽ?

“በጭራሽ አይሆንም!”

“እስኪ ይሁን።”

“ምንም ችግር የለውም።”

▪ ወላጆችሽ ልብሱን ያልፈለጉበት ዋነኛው ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል ብለሽ ታስቢያለሽ?

ወንዶችን የሚስብ ስለሆነ

ቅጥ ያጣ ስለሆነ

በጣም ፋሽን ስለሆነ

እንዲህ ያለ ልብስ ብትለብሺ ስማቸው እንደሚጠፋ ስለተሰማቸው

በጣም ውድ ስለሆነ

ሌላ ․․․․․․

በዚህ ጉዳይ ለመስማማት ምን ማድረግ እንችላለን?

▪ ወላጆቼ ከሰጡት አስተያየት ምን ጠቃሚ ነገር ማግኘት እችላለሁ?

․․․․․

▪ ልብሱ ሌሎችን ቅር እንዳያሰኝ ምን ማስተካከያ ሊደረግበት ይችላል?

․․․․․․․․․․․

ወላጆችሽ የሚሞሉት

በጉርምስና ዕድሜ ላይ የምትገኘው ልጃችሁ ልትለብሰው ወይም ልትገዛው ስለፈለገችው አንድ ልብስ አስቡ።

▪ ልጃችሁ ይህን ልብስ የወደደችው ለምን ይመስላችኋል? ከዚህ በታች ያሉትን ምክንያቶች ከተመለከታችሁ በኋላ ልጃችሁ ቅድሚያ ትሰጠዋለች ብላችሁ የምታስቡትን በቅደም ተከተል ቁጥር ስጧቸው።

․․․․․․ ልብሱ ላይ ባለው የንግድ ምልክት ምክንያት

․․․․․․ ወንዶችን ለመሳብ

․․․․․․ በእኩዮቿ ዘንድ ተቀባይነት

․․․․․․ የሚመች ስለሆነ

․․․․․․ ዋጋው

 ․․․․․․ ሌላ ․․․․․․

▪ ልጃችሁ የመረጠችውን ልብስ ገና እንዳያችሁት የምትሰጡት ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል ብላችሁ ታስባላችሁ?

“በጭራሽ አይሆንም!”

“እስኪ ይሁን።”

“ምንም ችግር የለውም።”

▪ ልብሱን ያልፈለግነው . . .

“ወንዶችን የሚስብ ስለሆነ ነው።”

“ቅጥ ያጣ ስለሆነ ነው።”

“በጣም ፋሽን ስለሆነ ነው።”

“እንዲህ ያለ ልብስ ብትለብስ ስማችንን ስለሚያጠፋ ነው።”

“በጣም ውድ ስለሆነ ነው።”

ሌላ ․․․․․․

በዚህ ጉዳይ ለመስማማት ምን ማድረግ እንችላለን?

▪ ይህን ልብስ ያልፈለግነው ከግል ምርጫችን ጋር ስላልተስማማ ብቻ ነው?

አዎን ሊሆን ይችላል አይደለም

▪ ልብሱ ሌሎችን ቅር እንዳያሰኝ ምን ማስተካከያ ሊደረግበት ይችላል?

․․․․․

ውሳኔው

․․․․․․

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

እኩዮችሽ ምን ይላሉ?

“ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር እስካልተጋጨ ድረስ አንድን ‘ፋሽን’ መከተል ምንም ችግር የለውም። ልትገዟቸው የምትችሏቸው የሚያምሩና ሌሎች ሲያዩአቸው ቅር የማያሰኙ ብዙ ነገሮች አሉ።”—ዴሪክ

“በአሥራዎቹ ዕድሜ ሳለሁ በራሴ መመራት እፈልግ ነበር። ምን መልበስ እንዳለብኝ ሰዎች እንዲነግሩኝ አልፈልግም ነበር። ይሁንና በዚህ ሁኔታ የምፈልገውን አክብሮት እንዳላገኘሁ ከጊዜ በኋላ ተገነዘብኩ፤ የወላጆቼንና የትልልቅ ሰዎችን ምክር መስማት ስጀምር ግን የሌሎችን አክብሮት ማግኘት ቻልኩ።”—ሜጋን

“ሴቶች ሰውነትን የሚያጋልጡ ልብሶችን ለብሰው ሳይ ለእነሱ ያለኝ አክብሮት ይቀንሳል። በሌላ በኩል ደግሞ ልከኛና የሚያምር ልብስ የለበሱ ሰዎችን ስመለከት ‘ሰዎች እኔንም እንዲመለከቱኝ የምፈልገው እንዲህ ነው’ ብዬ በልቤ አስባለሁ።”—ናታሌይን

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ስለ ወንዶችስ ምን ማለት ይችላል?

በዚህ ርዕሰ ውስጥ የተወያየንባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በወንዶችም ላይ ተፈጻሚነት አላቸው። ልከኛ ሁን። የተሰወረው የልብህ ሰው ማለትም የውስጥ ሰውነትህ ውበት ግልጽ ሆኖ እንዲታይ አድርግ። ልብስ ልትገዛ ስታስብ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ይህ ልብስ ስለ እኔ ምን ይናገራል? ልብሴ “የሚናገረው ነገር” የእኔን እውነተኛ ማንነት የሚያንጸባርቅ ነው?’ ልብስ፣ ማንነታችንን ልንገልጽ ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱ እንደሆነ አስታውስ። ልብስህ የማታምንባቸውን ነገሮች የሚያንጸባርቅ እንዳይሆን ጥንቃቄ አድርግ!

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለወላጆች የቀረበ ሐሳብ

እስቲ በዚህ ርዕሰ ትምህርት መግቢያ ላይ የተጠቀሰውን ምሳሌ እንመልከት፤ ሄዘር የእናንተ ልጅ እንደሆነች አድርጋችሁ አስቡ። የለበሰችው ልብስ በጣም ሰውነትን የሚያጋልጥ በመሆኑ ነገሩን እንዳላየ ሆናችሁ ማለፍ አልቻላችሁም። በመሆኑም “በይ የኔ እመቤት፣ ወደ ውስጥ ገብተሽ ሌላ ልብስ ቀይሪ። አለዚያ ይህን ለብሰሽ የትም አትሄጃትም!” በማለት ወዲያውኑ ምላሽ ሰጣችሁ እንበል። በዚህ መልኩ ምላሽ መስጠታችሁ ውጤት አስገኝቶላችሁ ይሆናል። ደግሞስ ልጃችሁ የተባለችውን ከመፈጸም ሌላ ምን ምርጫ አላት? ይሁን እንጂ ልጃችሁ ልብሷን ብቻ ሳይሆን አስተሳሰቧንም እንድትቀይር ልታስተምሯት የምትችሉት እንዴት ነው?

▪ አንደኛ፣ ልከኛ ያልሆነ ልብስ መልበስ የሚያስከትለው መዘዝ የእናንተን ያህል ምናልባትም ከዚያ በበለጠ ልጃችሁን እንደሚያስጨንቃት አስታውሱ። ልጃችሁ በውስጧ የሚሰማት ስሜት ሌላ ሊሆን ይችላል፤ ምናልባት በአለባበሷ የሌሎች መሳቂያ መሆን ወይም አላስፈላጊ ትኩረት ወደ ራሷ መሳብ አትፈልግም። ስለዚህ ልከኛ ያልሆነ ልብስ መልበስ አንድን ሰው አምሮ እንዲታይ እንደማያደርገው በትዕግሥት አስረዷት። * አማራጭ ሐሳቦችን አቅርቡላት።

▪ ሁለተኛ፣ ‘ምክንያታዊ ሁኑ።’ (ፊልጵስዩስ 4:5) ራሳችሁን እንደሚከተለው እያላችሁ ጠይቁ፦ ‘ልብሱን ያልወደድኩት ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ጋር የሚጋጭ ስለሆነ ነው? ወይስ ከግል ምርጫዬ ጋር ስላልተስማማ?’ (2 ቆሮንቶስ 1:24) ታዲያ የግል ምርጫ ጉዳይ ብቻ ከሆነ ልጃችሁ ልብሱን እንድትለብስ ልትፈቅዱላት ትችላላችሁ?

▪ ሦስተኛ፣ ልብሱን መልበሷ ተገቢ እንዳልሆነ በመናገር ብቻ አትወሰኑ። ተስማሚ የሆኑ ልብሶችን በማፈላለግ እርዷት። ጊዜ ወስዳችሁ ይህን ለማድረግ መጣራችሁ ይክሳችኋል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.107 በጉርምስና ዕድሜ ላይ የምትገኘው ልጃችሁ የውበቷ ነገር በጣም ሊያሳስባት ስለሚችል መልኳን በተመለከተ ምንም ዓይነት የሚያንቋሽሽ ነገር ላለመናገር ተጠንቀቁ።