በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሁላችንም አንድ ቤተሰብ ነን

ሁላችንም አንድ ቤተሰብ ነን

 ሁላችንም አንድ ቤተሰብ ነን

ከአንተ የተለየ ዘር ወይም የቆዳ ቀለም ስላላቸው ሰዎች ምን ይሰማሃል? ከአንተ እኩል እንደሆኑ አድርገህ ትመለከታቸዋለህ? የሚያሳዝነው በርካታ ሰዎች አንዳንድ ዘሮችን ከእነሱ ያነሱ እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸዋል። አንድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ዘረኝነት ለሚለው ቃል “ከቀለም ወይም ከዝርያ ልዩነት የተነሣ ራስን የተሻለ አድርጎ በመገመት ሌላውን መናቅ መጨቆን የበታች አድርጎ ማየት” የሚል ፍቺ ሰጥቶታል።

እንዲህ ያለው አመለካከት ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል። ወን-ሺንግ ጀንግ የተባሉ ፕሮፌሰር ሃንድቡክ ኦቭ ካልቸራል ሳይካትሪ በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ የዘር የበላይነት ስሜት “ለቅኝ ግዛትና ሌሎች ዘሮችን ባሪያ አድርጎ ለመግዛት ሰበብ ሆኗል” በማለት ጽፈዋል። አክለውም ዘር “በማኅበራዊ፣ በፓለቲካና በኢኮኖሚ ረገድ ለሚታየው መበላለጥ ማመካኛ ሆኖ ሲጠቀስ ቆይቷል” ብለዋል። ዘረኝነት በዛሬው ጊዜም እንኳ በብዙ የዓለም ክፍሎች ይታያል። ይሁን እንጂ ይህ ጎጂ አስተሳሰብ ትክክለኛ መሠረት አለው? መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ሳይንስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ?

ሳይንስ ምን ይላል?

የጄኔቲክ ሳይንስ ግኝቶች፣ ዘረኝነት የተሳሳተ አመለካከት እንደሆነ አረጋግጠዋል። ከተለያዩ አሕጉራት በተውጣጡ ግለሰቦች ላይ ጥናት ያደረጉ ተመራማሪዎች ከማንኛውም የዓለም ክፍል በተመረጡ በማናቸውም ሁለት ግለሰቦች መካከል ያለው የዲ ኤን ኤ ልዩነት ከ0.5 በመቶ እንደማይበልጥ አረጋግጠዋል። * ከዚህ ልዩነት ውስጥ ከ86 እስከ 90 በመቶ የሚሆነው በማንኛውም ዘር ውስጥም ይታያል። በመሆኑም በተለያዩ ዘሮች መካከል ያለው ልዩነት 14 በመቶ ብቻ ነው፤ በሌላ አባባል ከላይ ከተገለጸው ከ0.5 በመቶ ያነሰ ነው።

ኔቸር የተባለው ጥናታዊ መጽሔት “የሰው ልጆች የጂን አወቃቀር አንድ ዓይነት [በመሆኑ] የጄኔቲክ ሳይንስ ስለ ዘር ልዩነት ያለንን ግንዛቤ ማስፋት ብሎም ችግሩን ማስወገድ መቻል ይኖርበታል” ብሏል።

እንዲህ ያለው አስተሳሰብ አዲስ አይደለም። የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት ከ1950 ጀምሮ ዘረኝነትን ለመዋጋት መግለጫዎችን ሲያወጣ  ቆይቷል። መግለጫዎቹን ያዘጋጁት ስለ ሰው ዘር አመጣጥ፣ ስለ ጂን እንዲሁም ስለ ማኅበራዊ ጉዳዮች የሚያጠኑ ጠበብቶች ናቸው። ያም ሆኖ ግን ዘረኝነት ሊወገድ አልቻለም። ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሰዎች ስለ ጉዳዩ ያላቸውን ግንዛቤ ማስፋት ብቻውን በቂ አይደለም። የሰዎችን ልብ መንካትም ያስፈልጋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ክፉ ሐሳብ ከልብ ይወጣል’ ሲል ተናግሯል።—ማቴዎስ 15:19, 20

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው የሰዎችን ልብ ሊነካ በሚችል መንገድ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ “በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩም የሰውን ወገኖች በሙሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ” የሚለውን ሳይንሳዊ ሐቅ ከማስፈሩም በላይ “አምላክ [አያዳላም፤] ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና የጽድቅ ሥራ የሚሠራ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው” ይላል። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35፤ 17:26) ይህን ማወቅህ አምላክን እንድትወደው አይገፋፋም?—ዘዳግም 32:4

ይሖዋ አምላክ እሱን በመምሰል እንደምንወደው እንድናሳይ ይፈልጋል። ኤፌሶን 5:1, 2 “የተወደዳችሁ ልጆች በመሆን አምላክን የምትኮርጁ ሁኑ፤ . . . በፍቅር መመላለሳችሁን ቀጥሉ” ይላል። ‘በፍቅር መመላለስ’ ደግሞ እኛም እንደ አምላክ የቆዳ ቀለም ወይም ዘር ሳንለይ ሰዎችን መውደድን ይጨምራል።—ማርቆስ 12:31

አምላክ ጥላቻንና የዘር መድልዎን ጨምሮ ልባቸው በክፋት የተሞላ ሰዎችን አገልጋዮቹ አድርጎ አይቀበላቸውም። (1 ዮሐንስ 3:15) እንዲያውም አምላክ ክፉ የሆኑ ሰዎችን በሙሉ ከምድር ገጽ ጠራርጎ የሚያጠፋበት ጊዜ በጣም እየቀረበ ነው። ከጥፋቱ የሚተርፉት የእሱን ባሕርያት የሚከተሉ ሰዎች ብቻ ናቸው። ከዚያ በኋላ መላው የሰው ዘር በሥጋም ሆነ በመንፈስ አንድ ቤተሰብ ይሆናል።—መዝሙር 37:29, 34, 38

^ አን.5 አንዳንድ በሽታዎች ከጂን ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ስለሚታመን በሰዎች ጂኖች ላይ የሚታየው ጥቂት ልዩነት በሕክምና ረገድ ትልቅ ትርጉም ይኖረው ይሆናል።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

‘የሰው ልጆች የጂን አወቃቀር አንድ ዓይነት ነው’