እጅግ አዝጋሚ የሆነው ስሎዝ
እጅግ አዝጋሚ የሆነው ስሎዝ
“ቶሎ ብለሽ ካሜራሽን አምጪው!” ይህን ያልኩት ከፊት ለፊቴ ባለው ጫካ ውስጥ አንድ አረንጓዴ ስሎዝ ስላየሁ ነበር። ይሁን እንጂ ስሎዝ በዓለም ላይ ካሉት በጣም አዝጋሚ የሆኑ እንስሳት አንዱ በመሆኑ ምንም የሚያስቸኩለን ነገር እንደሌለ ስንገነዘብ እኔና እህቴ ያደረግነው ነገር አሳቀን።
ስለዚህ እንስሳ የበለጠ ለማወቅ ስለፈለግሁ በኮስታ ሪካ ውስጥ ላ ጋሪታ ዴ አላህዌላ በሚባል ሥፍራ የሚገኘውን ትሶ አቬ የሚባል የአራዊት መጠበቂያ ጎበኘሁ። ይህ ሥፍራ የዱር እንስሳት መጠበቂያ ከመሆኑም ሌላ ማዕከሉ እንስሳትን ከአደገኛ ሁኔታ በመታደግ እንክብካቤ ያደርግላቸዋል፤ ከዚያም እንስሳቱ እንደገና ከሌሎቹ የዱር እንስሳት ጋር እንዲቀላቀሉ ይደረጋል። በትሶ አቬ የአራዊት መጠበቂያ ጣቢያ የሚደረገው ምርምር ዳይሬክተር የሆነችውን ሽርሊ ራሚሬስ የተባለች የባዮሎጂ ባለሙያ በዚህ ማዕከል ውስጥ አገኘሁ። እሷም ፔሎታ (በስፔን ቋንቋ “ኳስ” ማለት ነው) የተባለውን በዚህ ቦታ የሚገኝ ስሎዝ አሳየችኝ። እነዚህ እንስሳት ጥቅልል ብለው ሲተኙ በእርግጥም ኳስ ይመስላሉ። ፔሎታ፣ ባለ ሁለት ጣት ስሎዝ ሲሆን መጠኑ ትንሽ ውሻ ያክላል። ይህ እንስሳ ለስላሳ ፀጉር፣ ደፍጠጥ ብሎ ጫፉ ጋ ቀና ያለ አፍንጫና ቡናማ ቀለም ያላቸው ትልልቅ ዓይኖች አሉት፤ እንባ ያዘሉ የሚመስሉት የፔሎታ ዓይኖች ገራም እንስሳ እንደሆነ ይጠቁማሉ።
ካደረግሁት ምርምር ለመረዳት እንደቻልኩት እነዚህ እንስሳት ተነጣጥለው ለየብቻቸው መኖር የሚመርጡ ሲሆን በዓመት አንድ ጊዜ አንድ ልጅ ብቻ ይወልዳሉ። ግልገል የሆነው ስሎዝ ጡት እስኪጥል ድረስ ከአራት እስከ ስድስት ሳምንታት ከእናቱ ጉያ የማይወጣ ሲሆን ከዚያ በኋላ ከአምስት እስከ ስምንት ወራት ባለው ጊዜ ደግሞ ደረቷ ላይ ተለጥፎ አብሯት ይቆያል። በዚህ ወቅት እናቲቱ ልጇን ለጋ የሆኑና በቀላሉ ሊፈጩ የሚችሉ ቅጠሎችን በአፏ እያጎረሰች ትመግበዋለች። በኋላም ግልገሉ እናቱን ሳይለቅ ራሱ ቅጠሎችን እየቀጠፈ መብላት ይጀምራል። ልጁ ከእናቱ ጋር በሚቆይበት በዚህ ወቅት እናትየው የሚኖሩበትን አካባቢ እንዲያውቀው ትረዳዋለች።
ባለ ሁለትና ባለ ሦስት ጣት፣ አረንጓዴና ቀዝቃዛ ስሎዝ
ቀደም ሲል በጫካው ውስጥ ያየሁት ስሎዝ ባለ ሦስት ጣት እንደሆነ ተረዳሁ። በዓይኖቹ ዙሪያ ጥቁር ፀጉር ያለው መሆኑ ጭምብል ያጠለቀ ያስመስለዋል፤ በሰውነቱ ላይ የሚገኘው ፀጉር ጠንካራ ሲሆን ጅራቱ አጭርና ጥቅጥቅ ባለ ፀጉር የተሸፈነ ነው። የፊት እግሮቹ ከኋላ እግሮቹ ይልቅ በጣም ይረዝማሉ፤ በትከሻዎቹ መካከል ያለው ፀጉር ደግሞ ወርቃማ ቀለም አለው። ይህ ዓይነቱ ስሎዝ በአንገቱ ላይ ዘጠኝ የአከርካሪ አጥንቶች ስላሉት የሚወዳቸውን ቅጠሎች ለማግኘት አንገቱን 270 ዲግሪ ማዞር ይችላል። ይሁን እንጂ መልኩ አረንጓዴ የሆነው ለምንድን ነው? ሽርሊ እንደገለጸችልኝ “በዚህ ስሎዝ ሰውነት ላይ አረንጓዴ ቀለም ጣል ጣል ብሎበት የሚታየው ፀጉሩ ላይ በሚያድገው አልጌ ምክንያት ነው።”
ባለ ሁለት ጣት የሆኑት የስሎዝ ዝርያዎች፣ ባለ ሦስት ጣት ከሆኑት ዝርያዎቻቸው በተቃራኒ የኋላና የፊት እግሮቻቸው ተመሳሳይ ርዝመት አላቸው። ለስላሳ የሆነው ፀጉራቸው ረዘም ያለ ሲሆን ወደ ቡናማ የሚያደላ ቢጫ ቀለም አለው።
ስሎዝ ቀኑን የሚያሳልፈው በዛፎች ጫፍ ላይ ሆኖ ፀሐይ በመሞቅ ነው። የሰውነቱ ሙቀት ቀን ላይ 33 ዲግሪ ሴልሲየስ የሚደርስ ሲሆን ምሽት ላይ ደግሞ 24 ዲግሪ ሴልሲየስ ይሆናል፤ በመሆኑም የሰውነቱ ሙቀት የሚለዋወጥበት መጠን ከሌሎች አጥቢ እንስሳት ሁሉ የበለጠ ነው። በስሎዝ ሰውነት ውስጥ ያለው ጡንቻ በጣም አነስተኛ በመሆኑ ሰውነቱን በማርገፍገፍ ሙቀቱን መጠበቅ አይችልም። በዚህም ምክንያት ብዙውን ጊዜ ሙቀቱን ጠብቆ ለማቆየት እንደ ኳስ ተጠቅልሎ ይተኛል። ሰውነቱን የሸፈኑት ፀጉሮች አጫጭርና ቀጫጭን በመሆናቸው ሙቀት ለማስተላለፍ ይረዱታል። ደግሞም ስሎዝ በቀን ውስጥ 20 ሰዓት መተኛት ይችላል!
ሲበሉም መንቀርፈፍ
ምግብ በሆድ ውስጥ እንዲፈጭ ባክቴሪያዎች ለሚያከናውኑት ሥራ የሰውነት ሙቀት ያስፈልጋል፤ የስሎዝ የሰውነት ሙቀት ዝቅተኛ በመሆኑ የተመገበው ምግብ ተፈጭቶ ጥቅም ላይ ለመዋል በጣም ረጅም ጊዜ ይወስድበታል። ስሎዝ የበላቸው ቅጠሎች ብዙ ክፍሎች ባሉት ጨጓራው ውስጥ የሚከናወነውን የመፍጨት ሂደት አልፈው ወደ ትንሹ አንጀት ለመድረስ እስከ አንድ ወር የሚጠጋ ጊዜ ሊፈጅባቸው ይችላል። ለተከታታይ ቀናት አየሩ ቀዝቃዛ በሚሆንበት ዝናባማ ወቅት ስሎዝ ሆዱ ሙሉ ቢሆንም በረሃብ ሊሞት ይችላል። ሽርሊ
እንዳለችው “ስሎዝ ምግቡ እንዲፈጭለት የፀሐይ ሙቀት በጣም ያስፈልገዋል።”ሽርሊ አክላም እንዲህ ብላለች፦ “በዱር እንስሳት መጠበቂያው ውስጥ እንስሶቹን እንከባከባለሁ እንዲሁም መኖሪያቸውን አጸዳለሁ፤ ከስሎዞች በጣም የምወደው ነገር እዳሪያቸውን የሚወጡትና የሚሸኑት በሳምንት አንድ ቀን ብቻ መሆኑ ነው! እዳሪያቸውን በሚወጡበትና በሚሸኑበት ጊዜ ደግሞ ከዛፍ ላይ ወርደው ጉድጓድ ከቆፈሩ በኋላ ተጸዳድተው ይቀብሩታል። ከዛፍ ወደ መሬት የሚወርዱት ይህን ለማድረግ ብቻ ነው።”
ተዘቅዝቀው እንዲኖሩ የተፈጠሩ እንስሳት
ስሎዞች ሁሉንም ነገር የሚያከናውኑት ማለትም የሚበሉት፣ የሚተኙት፣ ከተቃራኒ ጾታ ጋር የሚገናኙትና የሚወልዱትም ጭምር በዛፎች ላይ እንደተንጠለጠሉ ነው። ፈጣሪ እነዚህን ትናንሽ አጥቢ እንስሳት ወደታች ተዘቅዝቀው በዛፎች ላይ እንዲኖሩ አድርጎ በጥበብ ፈጥሯቸዋል። ይህ እንስሳ በእጆቹና በእግሮቹ ላይ ባሉት ሰባት ሳንቲ ሜትር ርዝመት ያላቸው ጥፍሮች አማካኝነት የዛፍ ቅርንጫፎችንና ሐረጎችን ጨምድዶ በመያዝ በዛፎቹ ላይ ይንጠለጠላል። ሞቃት በሆነው አካባቢ የሚጥለው ኃይለኛ ዝናብ ሰውነቱን እንዳያበሰብሰው ለመከላከል ፀጉሩ እንኳ የሚበቅለው ከተለመደው በተቃራኒው አቅጣጫ ነው! ፀጉሩ ከሆዱ ላይ ተከፍሎ ወደ ጀርባው አቅጣጫ ያድጋል፤ ይህም በየብስ ላይ ከሚኖሩ ሌሎች እንስሳት የፀጉር አበቃቀል ተቃራኒ ሲሆን ፀጉሩ በዚህ መንገድ ማደጉ ዝናብ በሰውነቱ ላይ ተንከባልሎ ወደ መሬት እንዲወርድ ያደርጋል። ስሎዝ መሬት ላይ ሲሆን ገልጃጃና ቀርፋፋ ቢሆንም በዛፎች ቅርንጫፎች ላይ ሲታይ ግን እንቅስቃሴው እርጋታና ሞገስ የተላበሰ ነው። የሚደንቀው ነገር ስሎዝ ድንቅ ዋናተኛም ጭምር ነው!
በዛፎች ጫፍ ላይ የሚኖረውንና ድምፁ የማይሰማውን ይህንን እንስሳ በተመለከተ ሌላ ምን ማወቅ ችያለሁ? ሁለት ዋና ዋና ነጥቦችን መጥቀስ እችላለሁ። አንደኛ፣ ስሎዝ ሰውነቱ ሲጎዳ ቁስሉ አስደናቂ በሆነ መንገድ ቶሎ የሚድን ሲሆን ለሌሎች አጥቢ እንስሳት ገዳይ ሊሆን የሚችል መጠን ያለው መርዝም እንኳን እሱን አይገድለውም። ከባድ ቁስሎች በቶሎ የሚድኑለት ከመሆኑም ሌላ ብዙውን ጊዜ ቁስሉ አያመረቅዝም። በመሆኑም የስሎዝ ሰውነት በሽታ የሚከላከልበትን መንገድ መረዳት በሕክምናው መስክ ለሚደረገው ምርምር ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ሁለተኛው ደግሞ፣ ዘወትር የሚጣደፉና ውጥረት የሚበዛባቸው ሰዎች የስሎዝን የተረጋጋ እንዲሁም ከጭንቀት ነፃ የሆነ አኗኗር በመጠኑም እንኳ መኮረጃቸው ሊጠቅማቸው እንደሚችል ተገንዝቤያለሁ።—ተጽፎ የተላከልን
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
“ጥሩ እንግዳ ተቀባይ” የሆነው ስሎዝ
የስሎዝ የተመሰቃቀለ ፀጉር አረንጓዴ ቀለም ጣል ጣል ብሎበት የሚታየው በላዩ ላይ ባደገው አልጌ የተነሳ ነው፤ አልጌው በስሎዙ ፀጉር ላይ ማደጉ ሁለቱንም ይጠቅማቸዋል። ስሎዙ ለአልጌው መኖሪያ ይሆነዋል፤ አልጌው ደግሞ አልሚ ንጥረ ነገሮችን በመሥራት ውለታውን ይመልሳል። ስሎዙ ፀጉሩን በምላሱ በመላስ ይህን ንጥረ ነገር ወደ ሰውነቱ ያስገባዋል፤ አለዚያም በቆዳው በኩል ወደ ውስጥ ይገባል። ስሎዙ ወደ ግራጫ ያደላ አረንጓዴ ቀለም ያለው መሆኑ ከቅርንጫፎች ላይ የተንጠለጠሉ በዛ ያሉ የደረቁ ቅጠሎች የሚያስመስለው ሲሆን ይህ ደግሞ ከጫካው ጋር እንዲመሳሰል ስለሚያደርገው ከጠላቶቹ ለመደበቅ ይረዳዋል! ስሎዙ ረዥም ዕድሜ በኖረ መጠን ፀጉሩ ይበልጥ አረንጓዴ ይሆናል!
[ምንጭ]
ከላይ በስተቀኝ፦ © Michael and Patricia Fogden; ከታች፦ © Jan Ševčík