አልባራሲን—እንደ “ንስር ጎጆ” ያለች ከተማ
አልባራሲን—እንደ “ንስር ጎጆ” ያለች ከተማ
“በስፔን ካሉት እጅግ ውብ ከተሞች አንዷ የሆነችውን አልባራሲንን ጎብኙ።”—ሆሴ ማርቲኔዝ ሩዪዝ (አዞሪን በመባልም ይታወቃሉ) የተባሉት ስፔናዊ ጸሐፊ፣ 1873-1967
አልባራሲን በጣም ልዩ የሆነች ከተማ ናት። ከተማዋን ልዩ የሚያደርጋት ምንድን ነው? መልክዓ ምድራዊ አቀማመጧ፣ ታሪኳ እንዲሁም አስደሳች የሆነው አካባቢዋ ልዩ ያደርጓታል። በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ በ1961 የስፔን መንግሥት በቴሩኤል ግዛት የምትገኘውን ይህችን ትንሽ ከተማ ብሔራዊ ቅርስ ብሎ ሰየማት። በ2005 ደግሞ የተወሰኑ ባለሙያዎች አልባራሲንን “በስፔን ከሚገኙት ሁሉ እጅግ ውብ የሆነች ከተማ” በማለት መርጠዋታል።
በማዕከላዊ ስፔን ባሉት ተራሮች ላይ የምትገኘው አልባራሲን 1,000 የሚያህሉ ነዋሪዎች ያሏት ጥንታዊ ከተማ ናት። በአካባቢው የሚፈሱት አያሌ ወንዞች በከተማዋ ዙሪያ የሚገኙትን አረንጓዴ መስኮች ያጠጧቸዋል፤ ሲየራ ዴ አልባራሲን የሚባለው የከተማዋን ስም የሚጋራ የተራራ ሰንሰለት ከተማዋን ከብቧታል።
የከተማዋ የምግብና የውኃ ምንጭ
በጥንት ዘመን በአልባራሲን አካባቢ ለምግብነት ሊውሉ የሚችሉ ብዛት ያላቸው የአደን እንስሳት መኖራቸው ብዙዎች በዚህ አካባቢ እንዲሰፍሩ ምክንያት ሆኗል፤ እነዚህ ሰዎች በዋሻዎች ውስጥ ከሳሏቸው ሥዕሎች መመልከት እንደሚቻለው ጥሩ የሥዕል ችሎታ የነበራቸው ከመሆኑም ሌላ ተፈጥሮን የሚያደንቁ ነበሩ። ሠፋሪዎቹ በዚህ አካባቢ ብቻ የተገኘ ነጭ ቀለም በመጠቀም በርካታ ትልልቅ ኮርማዎችንና ሌሎችንም እንስሳት ስለዋል። የሰዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በሥዕል የተገለጸባቸው እነዚህ ዋሻዎች ለሃይማኖታዊ ወይም ለማህበራዊ ጉዳዮች መሰብሰቢያ ሥፍራዎች ሆነው ያገለግሉ እንደነበር ምሑራን ይገምታሉ።
በዛሬው ጊዜም እንኳ በከተማዋ አቅራቢያ ባለው ሞንቴስ ዩኒቨርሳሌስ የተባለ ለዱር አራዊት የተከለለ ቦታ ውስጥ አጋዘን፣ ከርከሮና ትንንሽ የአደን እንስሳት በብዛት ይገኛሉ። ከዚህም በተጨማሪ ጉዋታላቢያር (በአረብኛ “ነጭ ወንዝ” ማለት ነው) የሚባለው ወንዝ በስፔን ካሉት ትራውት የሚባለው ዓሣ የሚገኝባቸው ወንዞች ውስጥ አንዱ ነው።
በ133 ዓ.ዓ. ሮማውያን የአካባቢው ነዋሪዎች የነበሩትን ኬልቲቤሪያን የሚባሉ ጎሣዎች ድል ካደረጉ በኋላ በአልባራሲን አካባቢ በርካታ መንደሮች ቆረቆሩ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. ሮማውያን መሐንዲሶች ርዝመቱ 18 ኪሎ ሜትር የሆነ ቦይ (1) ሠሩ። ይህ ግንባታ ሮማውያን በስፔን ውስጥ ካከናወኗቸው ሕዝቡን የሚጠቅሙ ፕሮጀክቶች መካከል እጅግ ውስብስብ እንደሆነ ይታመናል። የሮማውያን ሃይማኖትም ቢሆን የራሱን አሻራ ትቶ አልፏል።
በአልባራሲን ከተማ ውስጥ በአንድ የሮማውያን መቃብር ላይ ተቀርጾ የተገኘ አንድ ጽሑፍ በከተማዋ የንጉሠ ነገሥት አምልኮ ይከናወን እንደነበር ያመለክታል።በሙስሊሞች አገዛዝ ሥር የነበረው ብልጽግና
በዘጠነኛው መቶ ዘመን ሙር የሚባሉት ሕዝቦች ይህን ክልል ተቆጣጥረውት ነበር፤ አልባራሲን የሚለው ስም ወደዚህ ቦታ ከመጡት ባኑ ራዚን የሚባሉ የበርበር ጉሳ አባላት የሆኑ ሙስሊም ሠፋሪዎች እንደተወሰደ ይታመናል። በመካከለኛው ዘመን የሙር ሕዝቦች፣ አይሁዶችና ስመ ክርስቲያኖች እርስ በርስ በመከባበርና በመቻቻል አብረው ይኖሩ ነበር። በዚህም የተነሳ በአልባራሲን ታሪክ ውስጥ ይህ ወቅት የብልጽግና ዘመን ሆኖ ነበር።
የአልባራሲን የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች ውብ የሆኑ ዕቃዎችን ይሠሩ የነበረ ሲሆን በሕክምና መስክም ከፍተኛ እድገት አድርገው እንደነበር መመልከት ይቻላል። በቁፋሮ ከተገኙት የቀዶ ሕክምና መሣሪያዎች መመልከት እንደሚቻለው በአካባቢው የነበሩ የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች የዓይን ሞራ እንደመግፈፍ ያሉ ቀዶ ሕክምናዎችን እንኳ ያከናውኑ ነበር። አልባራሲን በሮም ካቶሊክ እጅ እስከገባችበት እስከ 12ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ድረስ በሙስሊሞች አገዛዝ ሥር ቆይታለች። ይህ በስፔን ታሪክ ውስጥ እንዲህ ያለው ፖለቲካዊ ለውጥ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የተከናወነበት ብቸኛ ወቅት መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው።
አልባራሲን በዛሬው ጊዜ ምን ትመስላለች? በከተማዋ ውስጥ አዳዲስ ግንባታዎች ስላልተከናወኑ አንድ ጎብኚ በአልባራሲን ውስጥ ሲዘዋወር አሁንም ድረስ በመካከለኛው ዘመን የተሠሩ ነገሮችን መመልከት ይችላል።
አስደናቂ ውበት
ስፔናዊው ፈላስፋ ሆሴ ኦርቴጋ ኢ ጋሴት (1883-1955) አልባራሲንን “በቋጥኞች አናት ላይ ጉብ ያለች አስደናቂ ውበት ያላት ከተማ” በማለት ገልጿታል። ከተማዋ ከባሕር ወለል በላይ 1,200 ሜትር ገደማ ከፍታ ላይ በሚገኝ ቋጥኝ አናት ላይ ጉብ ያለች ከመሆኗም ሌላ ጥልቅ በሆነ ሸለቆ የተከበበች ከመሆኗ አንጻር በዚህ መንገድ መገለጿ ተገቢ ነው፤ በዙሪያዋ የሚገኘው ሸለቆ ለከተማዋ ከጥቃት እንደመከላከያ ሆኖ ያገለግላል። ይህ ተፈጥሯዊ ምሽግ ከተማዋን በመቶ ለሚቆጠሩ ዘመናት ከጠላት ሲከላከልላት የኖረ ሲሆን ለአልባራሲን የንስር ጎጆ የሚል ቅጽል ስም አትርፎላታል።
አንድ ጎብኚ ክብ ድንጋዮች የተነጠፈባቸው ጠባብ የሆኑ ጎዳናዎች ባሏት በዚህች ከተማ ውስጥ ሲዘዋወር አስደናቂ የሆነውን ጥንታዊ የሥነ ሕንፃ ጥበብ ይመለከታል። አስደናቂ አሠራር ካላቸው ግንባታዎች መካከል ኮርነር ባልኮኒ፣ ብሉ ሀውስ (2) እና ሁሊያኔታ ሀውስ (3) የሚባሉት ይገኙበታል። በሁለት ጎዳናዎች መገናኛ ሥፍራ ላይ የሚገኘው ሁሊያኔታ ሀውስ ሚዛኑን ለመጠበቅ የሚሞክር ሕንፃ ይመስላል።
በዚያ ዘመን የተገነቡት ቤቶች በእንጨት ከተሠሩ በኋላ የተለሰኑ ናቸው፤ ከተማዋ የተገነባችው በተራራ አናት ላይ ከመሆኑ አንጻር ቤቶቹ ከድንጋይ በእጅጉ ያነሰ ክብደት ባላቸው በእነዚህ የግንባታ ቁሳቁሶች መሠራታቸው ተገቢ ነው። የብረት መከላከያ (4) የተገጠመላቸውና የዳንቴል መጋረጃዎች የተሰቀሉባቸው ትንንሽ መስኮቶችም የጎብኚዎችን ትኩረት ይስባሉ። በከተማዋ ውስጥ የሚገኙት ቤቶች የጣሪያ ክፈፍ የተጠጋጋ መሆኑ እንዲሁም ከተቀረጸ እንጨት የተሠሩት ሰገነቶችና ብዙውን ጊዜ በእንስሳት ቅርጽ ተዘጋጅተው በር ለማንኳኳት እንዲያገለግሉ መዝጊያው ላይ የሚንጠለጠሉት ነገሮች ከተማዋን ልዩ የሚያደርጓት ተጨማሪ ነገሮች ናቸው።
ከፍታ ቦታ ላይ ሲሆን የሚያዞረው ሰው በአፋፍ ጫፍ ላይ ወደተገነቡት ቤቶች ሲገባ ቁልቁል ላለመመልከት መጠንቀቅ ይኖርበታል። ከተማዋ የተቆረቆረችው በትልቅ ቋጥኝ አናት ላይ በመሆኑ ለግንባታ የሚሆን በቂ ቦታ የላትም፤ በዚህም የተነሳ አንዳንድ ነዋሪዎች ቤቶቻቸውን የሠሩት በገደሉ አፋፍ ላይ ነው።
ከከተማዋ በላይ በሚገኘው ኮረብታ አናት ላይ የሙሮች ግንብ የሚገኝ ሲሆን አልባራሲን መጀመሪያ የተቆረቆረችው በዚህ ቦታ ነበር። አረቦች በአሥረኛው መቶ ዘመን ከሠሯቸው ግንቦች መካከል ቶሬ ዴል አንዳዶር የሚባለው አሁንም ይገኛል። በ16ኛው መቶ ዘመን ከተከናወኑት ግንባታዎች መካከል ጎቲክ በሚባለው የሕንፃ አሠራር ንድፍ የተገነባው ካቴድራል እንዲሁም በፈረስ ኮቴ ቅርጽ የተሠራው የከተማው አዳራሽ ይገኙበታል።
በከተማዋ አቅራቢያ የሚገኘው የተፈጥሮ ሀብት
አልባራሲን፣ ተፈጥሮን የሚያደንቁ ሰዎች ሊወዷቸው የሚችሉ ብዙ ነገሮችም አሏት። በዙሪያዋ ባለው የተራራ ሰንሰለት ላይ ብዙ ዓይነት የእንስሳትና የዕፅዋት ዝርያዎች ይገኛሉ። ምንጮችና ፏፏቴዎች በዛፎች የተሸፈኑትን ተራሮች አስውበዋቸዋል። እንዲሁም እዚህ ቦታ ለመዝናናት መጥተው በድንኳን የሚያድሩ ሰዎች ሌሊት ላይ በጣም አስደናቂ የሆነውን በከዋክብት የተሞላ ሰማይ መመልከት ይችላሉ።
በአልባራሲን አያሌ የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰቦች ይኖራሉ። እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች የሚኖሩበት ውብ አካባቢ፣ በአምላክ መንግሥት ግዛት ሥር መላዋ ምድር ገነት ሆና ታዛዥ የሰው ልጆች እንደሚኖሩባት መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ተስፋ ያስታውሳቸዋል። በዚያ የሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች ይህንን የምሥራች ለሰዎች ለማካፈል ይጥራሉ።—መዝሙር 98:7-9፤ ማቴዎስ 24:14
በየዓመቱ ከመቶ ሺህ በላይ ቱሪስቶች በአልባራሲን ጠባብ ጎዳናዎች ላይ በመዘዋወር ከተማዋን ይጎበኛሉ። አንተም ወደ ስፔን ከመጣህ በተራሮች ላይ የተደበቀችውን ይህችን ልዩ የሆነች “የንስር ጎጆ” ለምን አትጎበኝም?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
በአልባራሲን የተገኙ የዕደ ጥበብ ሀብቶች
ከብር የተሠራ የቅባት ዕቃ። የሙር ሕዝቦች ንጉሥ የነበረው አብደልመሊክ፣ ዛሀር ለተባለችው ሚስቱ ያሠራው ሲሆን የስሟ ትርጉም በአረብኛ “አበባ” ማለት ነው። በዚህ ዕቃ ላይ “ማለቂያ የሌለው በረከት . . . ፣ ጥሩነትና ፍትሕ እንዲሰፍን መለኮታዊ እርዳታና አመራር” የሚል ጽሑፍ በወርቅ ተቀርጾበታል። ይህ የቅባት ዕቃ የስፔንና የአረቦች የዕደ ጥበብ ውጤት ከሆኑት ምርጥ የብር ዕቃዎች አንዱ እንደሆነ ይታመናል።
በክሪስታል የተሠራ ዓሣ። ዓሣው እውነተኛ እንዲመስል ድንጋዩ እየተቀረጸ ቅርፊት የተሠራለት ሲሆን አፉ ከብር እንዲሁም ክንፎቹ ደግሞ ከወርቅ የተሠሩ ናቸው። በተጨማሪም በዕንቁዎችና ሩቢ በሚባል የከበረ ድንጋይ አጊጧል። ዓሣው የተቀረጸበት መንገድ በጣም የረቀቀ ከመሆኑ የተነሳ በሙያው የተካኑ ሰዎች ይህን ቅርጽ አንድ የዕደ ጥበብ ሠራተኛ ብቻውን ዕድሜውን ሙሉ ቢሠራም ሊጨርሰው እንደማይችል ያምናሉ።
[ምንጭ]
Jar: Museo de Teruel. Foto Jorge Escudero; crystal: Sta. Ma de Albarracín Foundation
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ፖርቱጋል
ስፔን
ማድሪድ
አልባራሲን
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
1. ቦይ
[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
2. ብሉ ሀውስ
3. ሁሊያኔታ ሀውስ
4. የብረት መከላከያ
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
© Ioseba Egibar/age fotostock