የስኩዊድ ምንቃር
ንድፍ አውጪ አለው?
የስኩዊድ ምንቃር
▪ የስኩዊድ ምንቃር ለሳይንስ ሊቃውንት እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል። ሊቃውንቱ እንደሚከተሉት ያሉትን ጥያቄዎች ያነሳሉ፦ ‘እንደዚህ ያለ እጅግ ጠንካራ ነገር አጥንት በሌለው ፍጥረት ላይ እንዴት ሊጣበቅ ቻለ? ይህ ጠንካራ ነገር ለስላሳ ከሆነው የስኩዊዱ አካል ጋር በመፋተግ ይህን እንስሳ የማይጎዳው ለምንድን ነው?’
እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ የስኩዊድ ምንቃር ወደ ጫፉ ላይ ጠንካራ ሲሆን ከወደ ሥሩ ግን ለስለስ ያለ ነው። ካቲን ከተባለ እንደ ጥፍር ያለ ጠንካራ ንጥረ ነገር፣ ከውኃና ከፕሮቲን የተሠራው የስኩዊድ ምንቃር ለስላሳ ከሆነው የታችኛው ክፍል አንስቶ ጠንካራ እስከሆነው ክፍል ድረስ ቀስ በቀስ እየጠጠረ ስለሚሄድ ስኩዊዱ ምንቃሩን ምንም ጉዳት ሳያደርስበት እንደፈለገ ሊጠቀምበት ይችላል።
የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ፍራንክ ዞክ በስኩዊድ ምንቃር ላይ ጥናት ማካሄድ “ለተለያዩ ሥራዎች የሚያገለግሉ ነገሮችን እርስ በርስ እንዲጣበቁ ከማድረግ ጋር በተያያዘ፣ ንድፍ አውጪዎች ባላቸው አስተሳሰብ ላይ ከፍተኛ ለውጥ” እንደሚያመጣ ገልጸዋል። ጥናቱ ከፍተኛ ለውጥ ያስገኛል ተብሎ ከታሰበባቸው መስኮች ውስጥ አንዱ ሰው ሠራሽ እጆችንና እግሮችን ከመሥራት ጋር የተያያዘ ነው። በዚያው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተመራማሪ የሆኑት አሊ መዘሬስ “[የስኩዊድን] ምንቃር አሠራር በመከተል በአንድ ወገን እንደ ለስላሳ አጥንት (cartilage) በቀላሉ መተጣጠፍ የሚችል በሌላው ወገን ደግሞ እጅግ ጠንካራ የሆነና በእንቅስቃሴ ጊዜ የሚፈጠረውን ሰበቃ መቋቋም የሚችል ሰው ሠራሽ እጅና እግር” መሥራት እንደሚቻል ያስባሉ።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? ከታችኛው ክፍል አንስቶ እስከ ጫፉ ድረስ ቀስ በቀስ እየጠጠረ የሚሄደው የስኩዊድ ምንቃር የተገኘው እንዲሁ በአጋጣሚ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
© Richard Herrmann/SeaPics.com
© Bob Cranston/SeaPics.com