በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሊጠፉ የተቃረቡ ዝርያዎች የሚኖሩበት የመጨረሻው መጠጊያ

ሊጠፉ የተቃረቡ ዝርያዎች የሚኖሩበት የመጨረሻው መጠጊያ

ሊጠፉ የተቃረቡ ዝርያዎች የሚኖሩበት የመጨረሻው መጠጊያ

ስፔን የሚገኘው የንቁ! ጸሐፊ እንዳዘጋጀው

በመላው ዓለም በዕፅዋትና በእንስሳት ላይ የተደቀነው የመጥፋት አደጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ዝርያዎች እንደሚጠፉ ይገምታሉ። ደግነቱ፣ አንዳንድ የተራራ ሰንሰለቶች ቀደም ሲል ሰፊ በሆነ ክልል ውስጥ በብዛት ይገኙ ለነበሩ ዕፅዋትና እንስሳት መጠለያ እየሆኑ ነው። ይሁን እንጂ በእነዚህ ተራራማ ክልሎችም እንኳ ሳይቀር የአካባቢ መበከልና ሰዎች የሚያደርሱት ጉዳት አስጊ ሁኔታ ፈጥሯል። ይህ ሁኔታ በፕላኔታችን ላይ ሕዝብ ከሚበዛባቸው አህጉሮች አንዱ የሆነውን የአውሮፓን ያህል በግልጽ የሚታይበት ቦታ አይኖር ይሆናል።

ፈረንሳይን ከስፔን በሚለየው ፒረኒዝ በሚባለው የተራራ ሰንሰለት ላይ የሚገኙ በርካታ ብሔራዊ ፓርኮች ለአካባቢው ዕፅዋትና እንስሳት መጠጊያ ሆነው እያገለገሉ ናቸው። ጥበቃ ወደሚደረግላቸው ወደ እነዚህ አካባቢዎች የሚመጡ ጎብኚዎች ጥፋት ለተጋረጠባቸው ብዙ ዝርያዎች የመጨረሻ መጠጊያ የሆነውን ቦታ ለማየት ዕድል ያገኛሉ። እስቲ እነዚህ ፓርኮች ምን ጥቅም እንደሚሰጡ በአጭሩ እንመልከት።

የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው ዝርያዎች

አበቦች፦ እጅግ ውብ ከሆኑት የዱር አበቦች አንዳንዶቹ የሚበቅሉት ከ1,500 ሜትር በላይ ከፍታ ባላቸው ቦታዎች ነው። ደማቅ ሰማያዊ ቀለም ያላቸው ስኖው ጀንሸን እና ትራምፔት ጀንሸን (1) የሚባሉት የሚያምሩ አበቦች፣ ዛፎች የማይበቅሉበትን የላይኛውን የተራራ ክፍል ያስውቡታል። ወደታች ደግሞ ቢች ተብለው ከሚጠሩት ዛፎች መካከል ለመጥፋት የተቃረበው ሌዲስ ስሊፐር (2) የተባለው የኦርኪድ አበባ ዝርያ በብዛት ይታያል። ተፈጥሮን የሚያደንቁ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይህን ደን በየዓመቱ ይጎበኙታል። ስለዚህም የደን ጠባቂዎች እነዚህ ውድ አበቦች እንዳይበላሹ ወይም እንዳይነቀሉ በቀን ውስጥ ለ14 ሰዓት ያህል ይጠብቃሉ።

ቢራቢሮዎች፦ ብዙ ዓይነት የዱር አበቦች የሚገኙባቸውና የሰው እጅ ያላበላሻቸው በተራራው ላይ የሚገኙ መስኮች በቀለማት ላሸበረቁት ቢራቢሮዎች መጠጊያ ሆነውላቸዋል። በክንፎቹ ላይ ደማቅ ቀይ ነጠብጣብ ያሉት አፖሎ (3) የሚባለው ትልቅ ቢራቢሮ በኮሸሽላዎች መካከል ብር ብር ይላል። ትንንሾቹን አበቦች ደግሞ ሊካኤኒዴ ከሚባለው የቢራቢሮ ዝርያ የሚመደቡት ሰማያዊ ቢራቢሮዎችና ቀይ ቡኒ ቀለም ያላቸው ቢራቢሮዎች (4) ያለማቋረጥ ይጎበኟቸዋል። በተጨማሪም ፔይንትድ ሌዲ እና ቶርቶይዝሼል የሚባሉት ቢራቢሮዎች በሸንተረሮቹ ላይ ውር ውር ሲሉ ይታያሉ።

እንስሳት፦ ከአውሮፓ ትልልቅ አጥቢ እንስሳት መካከል ብዙዎቹ በአንድ ወቅት በተለያዩ የአህጉሩ ክፍሎች ይፈነጩ ነበር። ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ በብዛት ከመታደናቸው የተነሳ ለመጥፋት ተቃርበዋል። በአሁኑ ጊዜ ተኩላ፣ ድብ፣ ሊንክስ (5) የሚባለው የድመት ዝርያ፣ ባይሰን የሚባለው የጎሽ ዝርያ፣ ቻሚ ተብሎ የሚጠራው የአጋዘን ዝርያና አይቤክስ የሚባለው የተራራ ፍየል (6) የሚገኙት በጥቂት ተራራማ ቦታዎች ወይም ወደ ሰሜን ዋልታ አካባቢ ብቻ ነው። በፒረኒዝ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙት ግርማ ሞገስ ያላቸው የዱር እንስሳት በአንድ ወቅት በእነዚህ ተራሮች ላይ በብዛት ይገኙ እንደነበረ ማስረጃ ይሆናሉ። ጥሩ አስተሳሰብ ያላቸው አንዳንድ ጎብኚዎች ‘የቀሩት ጥቂት እንስሳት የወደፊት ዕጣ ምን ይሆን’ የሚለው ነገር ያሳስባቸዋል።

“የተራራ ጫፎች” ባለቤት የሆነው ፈጣሪ በተራሮች ላይ የሚኖሩት የዱር እንስሳት ደህንነት እንደሚያሳስበው እርግጠኞች እንድንሆን የሚያደርግ በቂ ምክንያት አለን። (መዝሙር 95:4) ይሖዋ አምላክ ከመዝሙራት በአንዱ ውስጥ “የዱር አራዊት ሁሉ፣ በሺ ተራራዎች ላይ ያለውም እንስሳ የእኔ ነውና። በየተራራው ያለውን ወፍ ሁሉ ዐውቃለሁ” ብሎ ተናግሯል። (መዝሙር 50:10, 11) ይሖዋ ለምድርና በላይዋ ላለው ፍጥረት የሚያስብ መሆኑ፣ በተራሮች ላይ የሚገኙት እንስሳት እንዲጠፉ ፈጽሞ እንደማይፈቅድ ለማመን የሚያስችል በቂ ማስረጃ ይሆነናል።

[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

1 ትራምፔት ጀንሸን

2 ሌዲስ ስሊፐር ኦርኪድ

3 አፖሎ ቢራቢሮ

4 ቀይ ቡኒ ቀለም ያለው ቢራቢሮ

5 ሊንክስ

6 የተራራ ፍየል

[ምንጭ]

La Cuniacha