በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት እንድንጥል የሚያደርጉ ምክንያቶች

2. የጸሐፊዎቹ ግልጽነትና ሐቀኝነት

2. የጸሐፊዎቹ ግልጽነትና ሐቀኝነት

ሐቀኝነት እርስ በርስ ለመተማመን መሠረት ይሆናል። አንድ ሰው ሐቀኛ ነው የሚል ስም ማትረፉ እምነት እንድትጥልበት ሊያደርግህ ይችላል። ሆኖም አንድ ጊዜ ውሸት ብታገኝበት ከዚያ በኋላ እሱን ማመን ልትቸገር ትችላለህ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በቅን ልቦና ተነሳስተው የጻፉ ሐቀኛ ሰዎች ነበሩ። ግልጽነታቸው የጻፏቸው ነገሮች እውነት መሆናቸውን ያሳያል።

ስህተቶቻቸውንና ድክመቶቻቸውን አልደበቁም።

የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ጥፋታቸውንና ድክመታቸውን ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። ሙሴ መጥፎ ውጤት ያስከተለበት አንድ ስህተት እንደሠራ ተናግሯል። (ዘኍልቍ 20:7-13) አሳፍ የክፉዎች የቅንጦት ኑሮ ለጊዜውም ቢሆን አስቀንቶት እንደነበረ ገልጿል። (መዝሙር 73:1-14) ዮናስም አምላክን ሳይታዘዝ ቀርቶ እንደነበረ እንዲሁም አምላክ ንስሐ ለገቡት ኃጢአተኞች ምሕረት ባሳያቸው ጊዜ መጀመሪያ ላይ ከፍቶት እንደነበረ ተናግሯል። (ዮናስ 1:1-3፤ 3:10፤ 4:1-3) ማቴዎስ ኢየሱስ ለጠላቶቹ አልፎ በተሰጠበት ምሽት ትቶት ሸሽቶ እንደነበረ አልደበቀም።—ማቴዎስ 26:56

የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን የጻፉት ሰዎች የራሳቸው ሕዝብ በተደጋጋሚ ጊዜ ማጉረምረሙንና ማመጹን ሳይደብቁ ተናግረዋል። (2 ዜና መዋዕል 36:15, 16) ጸሐፊዎቹ የመሪዎቻቸውን ድክመት እንኳ ከመመዝገብ ወደኋላ አላሉም። (ሕዝቅኤል 34:1-10) በኃላፊነት ቦታ ላይ የነበሩትን ጨምሮ ክርስቲያኖች በግለሰብ ደረጃ የሠሯቸውን ስህተቶች አልፎ ተርፎም በአንደኛው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ጉባኤዎች ያጋጠሟቸውን ከባድ ችግሮች የያዙት የሐዋርያት ደብዳቤዎችም ተመሳሳይ ግልጽነት ተንጸባርቆባቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 1:10-13፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:16-18፤ 4:10

ሐቁን ለመሸፋፈን አልሞከሩም።

የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አንዳንዶች አሳፋሪ እንደሆኑ አድርገው ሊቆጥሯቸው የሚችሏቸውን ነገሮች ለመደበቅ ወይም አሰማምረው ለማቅረብ አልሞከሩም። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በወቅቱ የነበረው ዓለም ለእነሱ አድናቆት እንደሌለው ከዚህ ይልቅ ሞኞችና ወራዳ እንደሆኑ አድርጎ በንቀት እንደሚመለከታቸው በግልጽ ተናግረዋል። (1 ቆሮንቶስ 1:26-29) ጸሐፊዎቹ የኢየሱስ ሐዋርያት “ያልተማሩ ተራ ሰዎች” እንደሆኑ ተደርገው ይታዩ እንደነበረ ገልጸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 4:13

የወንጌል ጸሐፊዎች ኢየሱስ በሰዎች ዘንድ የተለየ ክብር እንዲሰጠው በማሰብ ሐቁን አዛብተው አላቀረቡም። ከዚህ ይልቅ ጥሮ ግሮ በሚያድር ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያለው ቤተሰብ ውስጥ እንደተወለደ፣ በዘመኑ በነበሩት ስመ ጥር ትምህርት ቤቶች ገብቶ እንዳልተማረና ያዳምጡት ከነበሩ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ መልእክቱን እንዳልተቀበሉ በሐቀኝነት ተናግረዋል።—ማቴዎስ 27:25፤ ሉቃስ 2:4-7፤ ዮሐንስ 7:15

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ ሐቀኛ በሆኑ ጸሐፊዎች እንደተጻፈ የሚያረጋግጥ በቂ ማስረጃ ይዟል። ሐቀኝነታቸው እምነት እንድትጥልባቸው አያደርግህም?