በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆቻችሁን ከጥቃት መጠበቅ የምትችሉት እንዴት ነው?

ልጆቻችሁን ከጥቃት መጠበቅ የምትችሉት እንዴት ነው?

አብዛኞቻችን በልጆች ላይ ስለሚፈጸም የፆታ ጥቃት ብዙ ማሰብ አንፈልግም። ወላጆች ስለዚህ ጉዳይ ማሰቡም እንኳ ይዘገንናቸዋል! ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ ጥቃት የዘመናችን አስፈሪና አሳዛኝ እውነታ ሲሆን በልጆች ላይ የሚያስከትለው መዘዝ ደግሞ እጅግ አስከፊ ሊሆን ይችላል። በዚህ ጉዳይ ላይ መወያየቱ ይህን ያህል አስፈላጊ ነው? ለልጃችሁ ደህንነት ስትሉ ምን ያህል መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ ናችሁ? የፆታ ጥቃትን በተመለከተ እውነታውን ማወቅ የሚዘገንን ቢሆንም የልጆቻችሁን ደህንነት ከመጠበቅ አንጻር ግን ልታደርጉት የምትችሉት ትንሹ ነገር ነው። እንዲህ ዓይነቱ እውቀት በልጆቻችሁ ደህንነት ላይ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል።

የዚህ ወንጀል መስፋፋት ችግሩን ለመጋፈጥ የሚያስችላችሁን ድፍረት እንዲያሳጣችሁ አትፍቀዱ። ብቁ እንዳልሆናችሁ ቢሰማችሁ እንኳ ልጃችሁ የሌለው ጥንካሬ አላችሁ፤ ልጃችሁ እናንተ አሁን ያላችሁን ችሎታና ጥንካሬ ለማዳበር ዓመታት እንዲያውም አሥርተ ዓመታት ሊፈጅበት ይችላል። ዕድሜያችሁ እውቀት፣ ተሞክሮና ጥበብ አጎናጽፏችኋል። ልጃችሁን በመጠበቅ ረገድ እንዲሳካላችሁ ይህን ሀብታችሁን በሥራ ላይ ማዋል አስፈላጊ ነው። እያንዳንዱ ወላጅ ሊወስዳቸው ስለሚችላቸው ሦስት እርምጃዎች እንወያያለን። እነሱም የሚከተሉት ናቸው:- (1) የልጃችሁ ዋና ጠባቂ ሁኑ፣ (2) ለልጃችሁ አስፈላጊውን የፆታ ትምህርት ስጡት፣ (3) ለልጃችሁ መሠረታዊ የመከላከያ ዘዴዎችን አስተምሩት።

የልጃችሁ ዋና ጠባቂ ናችሁ?

ልጆች የፆታ ጥቃት እንዳይደርስባቸው በመከላከል ረገድ ተቀዳሚው ኃላፊነት የሚወድቀው በልጆች ላይ ሳይሆን በወላጆች ላይ ነው። በመሆኑም ስለዚህ ጉዳይ ልጆችን ከማስተማር በፊት ወላጆችን ማስተማር ያስፈልጋል። ወላጅ ከሆንክ በልጆች ላይ ስለሚደርስ የፆታ ጥቃት ማወቅ የሚኖርብህ የተወሰኑ ነገሮች አሉ። በልጆች ላይ የፆታ ጥቃት የሚያደርሱት ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆኑና ይህንንም የሚያደርጉት እንዴት እንደሆነ ማወቅ ያስፈልግሃል። ብዙ ጊዜ ወላጆች ልጆችን ስለሚያስነውሩ ሰዎች ሲያስቡ ወደ አእምሯቸው የሚመጡት በሰዋራ ቦታ አድፍጠው በመጠበቅ ልጆችን ጠልፈው የሚደፍሩ የማያውቋቸው ሰዎች ናቸው። እንዲህ የሚያደርጉ አረመኔ ሰዎች መኖራቸው አይካድም። እንደነዚህ ስላሉት ሰዎች ዘወትር በዜና እንሰማለን። ይሁን እንጂ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ እንደነዚህ ዓይነቶቹ ወንጀለኞች ቁጥራቸው በጣም ጥቂት ነው። በልጆች ላይ ከሚፈጸመው የፆታ ጥቃት ውስጥ 90 በመቶ የሚሆነው የሚፈጸመው ልጁ አስቀድሞ በሚያውቀውና በሚያምነው ሰው ነው።

ተግባቢ የሆነ ጎረቤታችሁ፣ የልጃችሁ አስተማሪ፣ የጤና ባለሙያ፣ የስፖርት አሠልጣኝ ወይም ዘመድ ልጃችሁን በፆታ ይመኘዋል ብላችሁ ማሰብ እንደማትፈልጉ እሙን ነው። ደግሞም፣ አብዛኞቹ ሰዎች እንዲህ አያደርጉም። በዙሪያችሁ ያሉትን ሰዎች ሁሉ መጠራጠር አያስፈልጋችሁም። ያም ቢሆን ግን ልጆችን በፆታ የሚያስነውር ሰው ስለሚጠቀምባቸው ዘዴዎች በማወቅ ልጃችሁን ከጥቃት መጠበቅ ትችላላችሁ።—በገጽ 6 ላይ ያለውን  ሣጥን ተመልከት።

ወላጆች እነዚህን ዘዴዎች ማወቃችሁ ለልጃችሁ ዋና ጠባቂ እንድትሆኑ ያዘጋጃችኋል። ለምሳሌ ያህል፣ ከአዋቂዎች ይበልጥ ልጆችን የሚወድ የሚመስል ሰው ልጃችሁን ነጥሎ ልዩ ትኩረት ቢሰጠውና ስጦታ ቢያመጣለት ወይም እናንተ በማትኖሩባቸው ወቅቶች በተደጋጋሚ ጊዜያት ልጃችሁን ለመጠበቅ ፈቃደኛ መሆኑን ቢገልጽ አሊያም ለብቻው ሽርሽር ይዞት ለመሄድ ቢጠይቃችሁ ምን ታደርጋላችሁ? ግለሰቡ ልጆችን የሚያስነውር ሰው መሆን አለበት ብላችሁ ትደመድማላችሁ? በፍጹም። እንደዚህ ዓይነት ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አትቸኩሉ። ግለሰቡ ይህን የሚያደርገው በቅንነት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ሁኔታ ጥንቃቄ እንድታደርጉ ሊያነቃችሁ ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ “ተላላ ሰው ሁሉን ያምናል፤ አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል” ይላል።—ምሳሌ 14:15

ለማመን የሚከብድ ደግነት መደለያ ሊሆን እንደሚችል አስታውሱ። ሰው በሌለበት ወቅት ከልጃችሁ ጋር መሆን የሚፈልግን ማንኛውንም ሰው በጥንቃቄ ተከታተሉት። የልጃችሁን ሁኔታ ለማየት በማንኛውም ጊዜ ብቅ ልትሉ እንደምትችሉ ለዚህ ሰው ንገሩት። ሜሊሳና ብራድ የተባሉ ወጣት ባልና ሚስት ሦስት ወንዶች ልጆች ያሏቸው ሲሆን ልጃቸው ከትልቅ ሰው ጋር ብቻውን እንዲቆይ በማድረግ በኩል በጣም ጠንቃቆች ናቸው። አንዱ ልጅ ቤት ውስጥ ሙዚቃ በሚማርበት ጊዜ ሜሊሳ ለአስተማሪው “እዚህ እስካለህ ድረስ ብቅ እያልኩ አያችኋለሁ” አለችው። እንዲህ ዓይነቱ ጥንቃቄ ከመጠን ያለፈ ይመስል ይሆናል፤ ይሁን እንጂ እነዚህ ወላጆች ኋላ ከማዘን ከወዲሁ መጠንቀቅን ይመርጣሉ።

ልጃችሁ የሚያከናውናቸውን ተግባራት፣ ጓደኞቹ እነማን እንደሆኑ እንዲሁም የትምህርት ቤት ሥራዎቹን በንቃት ተከታተሉ። በትምህርት ቤት ሊደረግ የታሰበ የሽርሽር ፕሮግራም ካለ ዝርዝር ጉዳዮችን ጠይቁ። ከፆታ ጥቃት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ዙሪያ 33 ዓመታት በሥራ ዓለም ያሳለፉ አንድ የአእምሮ ሕክምና ባለሙያ፣ ወላጆች ቀላል የሆነ ጥንቃቄ ቢያደርጉ ኖሮ ሊያስቀሯቸው ይችሉ የነበሩ በርካታ ጥቃቶች እንዳጋጠሟቸው ገልጸዋል። እኚህ ባለሙያ፣ ልጆችን በፆታ በማስነወር ወንጀል የተፈረደበት አንድ ሰው “ወላጆች ቃል በቃል ልጆቻቸውን ይሰጡናል ማለት ይቻላል። . . . ለእኔ ነገሮችን ቀላል አድርገውልኛል” ማለቱን ተናግረዋል። አብዛኞቹ አስነዋሪዎች በቀላሉ ሊያጠምዷቸው የሚችሏቸውን ልጆች እንደሚመርጡ አስታውሱ። ወላጆች የልጆቻቸውን እንቅስቃሴ በንቃት የሚከታተሉ ከሆነ ልጆቹ የፆታ ጥቃት በሚፈጽሙ ሰዎች ወጥመድ ውስጥ በቀላሉ አይወድቁም።

የልጃችሁ ዋና ጠባቂ የምትሆኑበት ሌላው መንገድ ጥሩ አዳማጭ መሆን ነው። ልጆች አብዛኛውን ጊዜ የፆታ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው አይናገሩም፤ ጉዳዩ የሚያሳፍራቸው ከመሆኑም በላይ ሰዎች ምን ይላሉ የሚለው ያስጨንቃቸዋል። ስለዚህ ጥቃቅን ፍንጮችንም ሳይቀር በጥንቃቄ አዳምጡ። * ልጃችሁ ጥያቄ የሚፈጥርባችሁ አንድ ነገር ከተናገረ በረጋ መንፈስ ጥያቄዎች በመጠየቅ ስለ ጉዳዩ ይበልጥ እንዲነግራችሁ አበረታቱት። * ሞግዚቱ ወይም እናንተ በማትኖሩበት ወቅት የሚጠብቀው ሰው ሌላ ጊዜ እንዲመጣ እንደማይፈልግ ከተናገረ ምክንያቱን ጠይቁት። አንድ ትልቅ ሰው ከእሱ ጋር አስቂኝ ጨዋታ እንደሚጫወት ከነገራችሁ “ምን ዓይነት ጨዋታ ነው? ምን ያደርጋል?” ብላችሁ ጠይቁት። አንድ ሰው እንደኮረኮረው ከነገራችሁ “ምንህን ኮረኮረህ?” ብላችሁ ጠይቁት። ልጁ የሚሰጠውን መልስ ለማጣጣል አትቸኩሉ። ልጆችን የሚያስነውሩ ሰዎች ለልጁ ማንም እንደማያምነው ይነግሩታል፤ የሚያሳዝነው ደግሞ ብዙውን ጊዜ ይህ እውነት ይሆናል። አንድ ልጅ የፆታ ጥቃት ደርሶበት ከሆነ ወላጆቹ የሚናገረውን ማመናቸውና ልጁን በደግነት መርዳታቸው ከደረሰበት ጉዳት እንዲያገግም የሚረዳው አንድ ትልቅ እርምጃ ነው።

የልጃችሁ ዋና ጠባቂ ሁኑ

ለልጃችሁ አስፈላጊውን የፆታ ትምህርት ስጡት

በልጆች ላይ የሚፈጸምን የፆታ ጥቃት አስመልክቶ የተዘጋጀ አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ ልጆችን በማስነወር ወንጀል የተፈረደበት አንድ ሰው “ስለ ፆታ ምንም የማያውቅ ልጅ በቀላሉ ሰለባዬ ይሆናል” ብሎ መናገሩን ጠቅሷል። እነዚህ የሚዘገንኑ ቃላት ለወላጆች ጠቃሚ ማሳሰቢያ ይዘዋል። ስለ ፆታ ምንም የማያውቁ ልጆች በሚያስነውሩ ሰዎች በቀላሉ ይታለላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እውቀትና ጥበብ “ንግግራቸው ጠማማ ከሆነ ሰዎች” ሊጠብቀን እንደሚችል ይናገራል። (ምሳሌ 2:10-12) እናንተስ ልጃችሁ እንዲህ ማድረግ እንዲችል አይደል የምትመኙት? እንግዲያስ ልጃችሁን ከጥቃት ለመጠበቅ ልትወስዱት የሚገባው ሁለተኛ እርምጃ ይህን አስፈላጊ ርዕሰ ጉዳይ በሚመለከት ለልጁ ትምህርት ከመስጠት ወደኋላ አለማለት ነው።

ይሁንና ይህን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? ጥቂት የማይባሉ ወላጆች ስለ ፆታ ጉዳይ አንስተው ከልጆች ጋር መወያየት ያሳፍራቸዋል። ልጃችሁ ደግሞ ይህ ርዕስ ከእናንተ የበለጠ ሊያሳፍረው ስለሚችል ይህን ጉዳይ ላያነሳላችሁ ይችላል። ስለዚህ እናንተ ቀዳሚ ሁኑ። ሜሊሳ እንዲህ ትላለች:- “[ለልጆቻችን] እያንዳንዱን የአካል ክፍል ስም መንገር የጀመርነው ገና ከትንሽነታቸው ጀምሮ ነው። የትኛውንም የአካላቸውን ክፍል በተመለከተ የሚያስቅም ሆነ የሚያሳፍር ነገር እንደሌለ ለማሳየት ስንል ስሙን በሕፃናት አጠራር ሳንቀይር ትክክለኛ መጠሪያውን እንነግራቸው ነበር።” ከዚያ በኋላ ስለ ፆታ ጥቃት ማስተማር ቀላል ይሆናል። ብዙ ወላጆች፣ ሰው እንዳያይብን የምንሸፍናቸው የሰውነታችን ክፍሎች ከሌሎቹ የተለዩ ስለሆኑ ማንም ሊያያቸው ወይም ሊነካቸው እንደማይገባ ለልጆቻቸው ይነግሯቸዋል።

በፊተኛው ርዕሰ ትምህርት ላይ የተጠቀሰችው ሄዘር እንደሚከተለው ትላለች:- “ስኮትና እኔ ለወንድ ልጃችን ቁላውን ማንም ሊያይበት ወይም ሊነካበት እንደማይገባና መጫወቻ እንዳልሆነ ነግረነዋል። እማማም ሆነች አባባ ሌላው ቀርቶ ሐኪሙም እንኳ ቢሆን ማንም ሰው በብልቱ ሊጫወት እንደማይገባ ነገርነው። ወደ ሐኪም ስንወስደው ጤንነቱን ልናስመረምረው እንደሆነና ሐኪሙም ብልቱን የሚነካው ሊመረምረው ብቻ እንደሆነ አስረዳዋለሁ።” ሁለቱም ወላጆች በየጊዜው ከልጃቸው ጋር እንዲህ ያለ ውይይት የሚያደርጉ ሲሆን ማንም ሰው ትክክል ባልሆነ ወይም በሚያሳፍረው መንገድ ቢደባብሰው ምንጊዜም ቢሆን ለእነሱ እንዲነግራቸው ያደፋፍሩታል። ልጆችን በመንከባከብና የፆታ ጥቃትን በመከላከል መስክ የተሰማሩ ባለሙያዎች፣ ሁሉም ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር እንደዚህ ዓይነት ውይይት እንዲያደርጉ ሐሳብ ያቀርባሉ።

ብዙዎች ይህን ርዕስ በተመለከተ ልጆቻቸውን ለማስተማር ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ * (እንግሊዝኛ) የተሰኘው መጽሐፍ ጠቃሚ እርዳታ እንደሚያበረክት ተረድተዋል። “ኢየሱስ ጥበቃ ያገኘው እንዴት ነው?” የሚል ርዕስ ያለው ምዕራፍ 32 ስለ ፆታ ጥቃት እንዲሁም ልጆች ራሳቸውን ከዚህ ዓይነቱ ጥቃት መጠበቃቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የሚገልጽ ቀጥተኛ ሆኖም የሚያበረታታ ሐሳብ ይዟል። ሜሊሳ “መጽሐፉ ለልጆቻችን በግል የነገርናቸውን ነገር ለማጠናከር የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ ሰጥቶናል” በማለት ተናግራለች።

ባለንበት ዓለም ውስጥ አንዳንድ ሰዎች ልጆችን ትክክል ባልሆነ መንገድ መደባበስ ወይም ልጆቹ እንዲደባብሷቸው ማድረግ እንደሚፈልጉ ልጆች ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። እነዚህ ማስጠንቀቂያዎች ልጆች በፍርሃት እንዲርዱ ወይም አዋቂዎችን በሙሉ እንዲጠራጠሩ ሊያደርጓቸው አይገባም። “እንዲህ ዓይነት ትምህርት የሚሰጣቸው ራሳቸውን ከጥቃት መጠበቅ እንዲችሉ ለመርዳት ነው” በማለት ሄዘር ትናገራለች። “ይህ ትምህርት ደግሞ ከፆታ ጥቃት ጋር ምንም ግንኙነት ከሌላቸው ሌሎች ብዙ ትምህርቶች መካከል አንዱ ነው። ለልጃችን እንዲህ ዓይነቱን ትምህርት መስጠታችን ፈጽሞ እንዲፈራ አላደረገውም” ስትል አክላ ተናግራለች።

ለልጃችሁ የምትሰጡት ሥልጠና ስለ ታዛዥነት ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረው መርዳትንም ሊጨምር ይገባል። ለልጅ ታዛዥነትን ማስተማር አስፈላጊ ቢሆንም ይህን ማድረግ ቀላል አይደለም። (ቈላስይስ 3:20) ይሁን እንጂ ወላጆች ስለ ታዛዥነት ሲያስተምሩ ሚዛናቸውን ሊስቱ ይችላሉ። አንድ ልጅ ሁኔታው ምንም ይሁን ምን ማንኛውንም ትልቅ ሰው ሁልጊዜ መታዘዝ እንዳለበት ከተማረ ለጥቃት የተጋለጠ ነው። ልጆችን የሚያስነውሩ ሰዎች ከመጠን በላይ ታዛዥ የሆኑ ልጆችን ለይተው ለማወቅ ብዙ ጊዜ አይወስድባቸውም። ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች ታዛዥነት ገደብ እንዳለው ለልጆቻቸው ያስተምሯቸዋል። ለክርስቲያኖች ይህን ማስተማር እምብዛም አስቸጋሪ አይሆንም። ወላጆች እንዲህ ብለው ሊነግሯቸው ይችላሉ:- “አንድ ሰው፣ ይሖዋ አምላክ መጥፎ ነው የሚለውን ነገር እንድታደርግ ቢነግርህ ያለህን ልታደርግ አይገባም። እማማና አባባም እንኳ ቢሆኑ ይሖዋ መጥፎ ነው የሚለውን ነገር አድርግ ሊሉህ አይገባም። ስለዚህ አንድ ሰው መጥፎ ነገር እንድታደርግ ሊያስገድድህ ከሞከረ ምንጊዜም ለእማማ ወይም ለአባባ መናገር አለብህ።”

በመጨረሻም ማንም ሰው ልጃችሁ ምስጢሩን ከእናንተ እንዲደብቅ የመጠየቅ መብት እንደሌለው እንዲያውቅ አድርጉ። ማንም ሰው ልጃችሁ ከእናንተ ምስጢር እንዲደብቅ ቢጠይቀው ልጁ ስለ ሁኔታው ሁልጊዜ ሊነግራችሁ እንደሚገባ አሳውቁት። አስነዋሪው ለልጁ ምንም ነገር ቢነግረው፣ ቢያስፈራራው ወይም ልጁ ራሱ የሠራው መጥፎ ነገር ቢኖርም እንኳ ሁኔታውን ለእናቱ ወይም ለአባቱ መናገሩ ምንጊዜም ቢሆን ተገቢ እንደሆነ ንገሩት። እንዲህ ዓይነቱ መመሪያ ልጃችሁን ሊያስፈራው አይገባም። አብዛኞቹ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ነገር ፈጽሞ እንደማያደርጉ ማለትም መደባበስ የማይገባቸው ቦታ ላይ እንደማይደባብሱት፣ የአምላክን ትእዛዝ እንዲጥስ ወይም ምስጢር እንዲደብቅ እንደማይጠይቁት ንገሩት። ቃጠሎ ቢነሳ በየትኛው መንገድ ማምለጥ እንደምትችሉ እንደምትወያዩ ሁሉ እነዚህን መመሪያዎች የምትሰጡትም ምናልባት ቢያጋጥም ለጥንቃቄ ብላችሁ ነው፤ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ጨርሶ ላያጋጥምም ይችላል።

ለልጃችሁ አስፈላጊውን የፆታ ትምህርት ስጡት

ለልጃችሁ መሠረታዊ የመከላከያ ዘዴዎችን አስተምሩት

በዚህ ርዕስ ውስጥ የምንወያይበት ሦስተኛው እርምጃ፣ እናንተ በሌላችሁበት አንድ ሰው ልጃችሁን በፆታ ሊያስነውረው ቢሞክር ልጁ ሊያደርግ የሚገባውን አንዳንድ ነገሮች ማስተማር ነው። ብዙውን ጊዜ ወላጆች እንዲያደርጉት የሚመከሩት አንዱ ዘዴ በጨዋታ መልክ ማስተማር ነው። ወላጆች “. . . ቢያጋጥምህ ምን ታደርጋለህ?” የሚል ጥያቄ ይጠይቁትና ልጁ መልስ ይሰጣል። እንዲህ ልትሉ ትችላላችሁ:- “አብረን ገበያ ሄደን ብንጠፋፋ ምን ታደርጋለህ? እንዴት አድርገህ ታገኘኛለህ?” ልጁ የሚሰጠው መልስ ከምትጠብቁት የተለየ ሊሆን ይችላል፤ በዚህ ጊዜ “ከዚህ የተሻለ ምን ማድረግ የምትችል ይመስልሃል?” እንደሚለው ያሉ ተጨማሪ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ምን ማድረግ እንዳለበት እንዲያውቅ ልትረዱት ትችላላችሁ።

አንድ ሰው ልጁን ትክክል ባልሆነ መንገድ ሊደባብሰው ከሞከረ ምን ምላሽ ቢሰጥ እንደሚሻል ለማሳየትም ተመሳሳይ በሆኑ ጥያቄዎች ልትጠቀሙ ትችላላችሁ። ልጁ ባቀረባችሁለት ጥያቄ ከተደናገጠ ስለ ሌላ ልጅ የሚገልጽ ታሪክ ልትነግሩት ትችላላችሁ። ለምሳሌ ያህል፣ እንዲህ ልትሉት ትችላላችሁ:- “አንዲት ትንሽ ልጅ ከምትወደው ዘመዷ ጋር ሳለች ዘመዷ መደባበስ የማይገባው ቦታ ላይ ሊደባብሳት ሞከረ። ራሷን ከጥቃት ለመጠበቅ ምን ማድረግ ያለባት ይመስልሃል?”

ለልጃችሁ መሠረታዊ የመከላከያ ዘዴዎችን አስተምሩት

ልጃችሁ ከላይ እንደተጠቀሰው ዓይነት ሁኔታ ቢገጥመው ምን እንዲያደርግ ልታስተምሩት ይገባል? አንድ ደራሲ እንዲህ ብለዋል:- “ኮስተር ብሎ ‘እምቢ’ ወይም ‘እንዲህ አታድርግ! ልቀቀኝ!’ ‘ተው!’ ብሎ መጮኽ ግለሰቡ ከድርጊቱ እንዲቆጠብና እኩይ ተግባሩን በዚህ ልጅ ላይ መፈጸም እንደማይችል እንዲያስብ ሊያደርገው ይችላል።” ልጃችሁ ጮክ ብሎ እምቢታውን ለመግለጽ፣ ከግለሰቡ ለማምለጥና የሆነውን ነገር ለእናንተ ለመናገር ነፃነት እንዲሰማው አጭር ሠርቶ ማሳያ እንዲሠራ በማድረግ አለማምዱት። ልምምዱን በደንብ የተረዳው የሚመስል ልጅ በጥቂት ሳምንታት ወይም ወራት ውስጥ በቀላሉ ሊረሳው ይችላል። ስለዚህ አዘውትራችሁ አለማምዱት።

ልጁን በቅርብ የሚንከባከቡት ሰዎች በሙሉ ይኸውም አባቱ፣ እንጀራ አባቱ ወይም ሌሎች ወንዶች ዘመዶቹ ጭምር በዚህ ውይይት ውስጥ መካተት አለባቸው። ለምን? ምክንያቱም እንዲህ ባለው የማስተማር ሂደት ውስጥ የተካተቱት በሙሉ በልጁ ላይ የፆታ ጥቃት እንደማይፈጽሙበት ቃል እየገቡለት ነው። የሚያሳዝነው አብዛኛውን ጊዜ የፆታ ጥቃት የሚፈጸመው በቤተሰብ ክልል ውስጥ ነው። የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት የፆታ ጥቃት በተስፋፋበት ዓለም ውስጥ ቤተሰባችሁ አስተማማኝ የእረፍት ቦታ እንዲሆን ልታደርጉ የምትችሉት እንዴት እንደሆነ ያብራራል።

^ አን.10 የፆታ ጥቃት የደረሰባቸው ልጆች አፍ አውጥተው ባይናገሩም የደረሰባቸው ችግር እንዳለ የሚጠቁሙ ነገሮች እንደሚያደርጉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ልጅ መኝታው ላይ ሽንቱን እንደ መሽናት፣ ወላጆቹን የሙጥኝ ማለት ወይም ለብቻው መሆንን መፍራት የመሳሰሉ ቀደም ሲል ትቷቸው የነበሩ ልማዶች በድንገት ካገረሹበት ይህ አንድ ከበድ ያለ ነገር እያስጨነቀው መሆኑን የሚያመለክት ፍንጭ ሊሆን ይችላል። እንደነዚህ ያሉት ምልክቶች አንድ ልጅ የፆታ ጥቃት እንደደረሰበት የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች እንደሆኑ ተደርገው መወሰድ የለባቸውም። ልጁን ያስጨነቀው ነገር ምን እንደሆነ አውቃችሁ ልታጽናኑት፣ ልታረጋጉትና ከጥቃት ልትጠብቁት እንድትችሉ ስሜቱን እንዲያወጣው በረጋ መንፈስ አነጋግሩት።

^ አን.10 ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል በዚህ ርዕስ ውስጥ የፆታ ጥቃት የሚያደርሰውም ሆነ የጥቃቱ ሰለባ የሆነው ልጅ ወንዶች እንደሆኑ ተደርገው ተገልጸዋል። መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ግን ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።

^ አን.15 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።