በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የቬኒስ ካናል “ጥቁር ዳክዬ”

የቬኒስ ካናል “ጥቁር ዳክዬ”

 የቬኒስ ካናል “ጥቁር ዳክዬ”

ጣሊያን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

በወረዙ ግምቦች አጠገብ እያለፈች፣ በድልድዮች ሥር እየተሹለከለከች፣ የረቀቀ ዲዛይን ያላቸውን መስኮቶችና በአበቦች የተሞሉ ሰገነቶችን እያማተረች በአንድ ሐይቅ ላይ ወዲያ ወዲህ ትመላለሳለች። መልኳ ጥቁር ሲሆን የምታምር ናት፤ በምትሄድበት ጊዜ ምንም ድምፅ አታሰማም። ከሩቅ ላያት ትልቅ ጥቁር ዳክዬ ትመስላለች። አካሏ ከእንጨት፣ ልስላሴም ሆነ ላባ የሌለው አንገቷ ደግሞ ከብረት የተሠራ ቢሆንም በጣሊያኗ የቬኒስ ከተማ ካናሎች ላይ ስትጓዝ ከዳክዬ የማይተናነስ ግርማ ሞገስ አላት። ይህ ሁሉ የተባለላት አንዳንዶች በዓለም ላይ ተወዳዳሪ እንደሌላት የሚናገሩላት ጎንዶላ ተብላ የምትጠራ ጀልባ ነች። ለመሆኑ ሰዎች በጎንዶላ መጠቀም የጀመሩት ከመቼ ጀምሮ ነው? ጎንዶላ ይህን ያህል ታዋቂ የሆነችው ለምንድን ነው? ከሌሎች ጀልባዎች የተለየች የሚያደርጋትስ ምንድን ነው?

የጎንዶላ አመጣጥ

የመጀመሪያዋ ጎንዶላ የተሠራችበትን ጊዜ በትክክል ማወቅ ባይቻልም አንዳንዶች በ11ኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ እንደሆነ ይናገራሉ። ለመጀመሪያ ጊዜ በሥዕል የተሳለችው ደግሞ በ15ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ነበር። ሆኖም ከሌሎች ጀልባዎች ሁሉ የተለየችና ዝነኛ እንድትሆን የሚያደርጋትን ልዩ መልክ የያዘችው በ17ኛውና በ18ኛው መቶ ዘመን ነው። ጎንዶላ ቀደም ሲል ጠፍጣፋ ወለል የነበራት ቢሆንም ይዘቷ ተለውጦ  ሾጣጣ ቅርጽና የብረት አንገት የኖራት በዚህ ጊዜ ነበር።

ይህች ጀልባ ጎንዶላ የሚለውን ስም እንዴት እንዳገኘች ማወቅም ቢሆን አስቸጋሪ ነው። አንዳንዶች “ጎንዶላ” የሚለው ቃል የመጣው ቀደም ሲል የትንሽ ጀልባ መጠሪያ ከነበረው ክዌምቡላ ከሚለው የላቲን ቃል ወይም ደግሞ “ዛጎል” የሚል ትርጉም ካለው ኮንኩላ ከሚለው ቃል እንደሆነ ይናገራሉ።

በቬኒስ ብቻ የምትገኝ ጀልባ

በእርግጠኝነት ልንናገር የምንችለው ነገር ቢኖር በዚህች ጀልባና በቬኒስ መካከል ጠንካራ ትስስር ያለ መሆኑን ነው። እንዲያውም ጎንዶላ የከተማዋ ዋነኛ ምልክት ሳትሆን አትቀርም። ጎንዶላ ያለችባቸውን የቬኒስን ፎቶግራፎች በሙሉ መመልከት ትችላለህ።

ይህችን ጀልባ ከከተማዋ ጋር የሚያስተሳስራት ሌላም ነገር አለ። አገር ጎብኚዎችን በካናሉ ላይ የሚያጓጉዝ ሮቤርቶ የተባለ አንድ ጀልባ ቀዛፊ “ቬኒስን ማወቅ የሚቻልበት ፍጹም ልዩ የሆነው መንገድ” ጎንዶላን መጠቀም እንደሆነ ይናገራል። ይህ ሰው “የምትመለከቱት በጣም የተለመዱ ነገሮችን ብቻ ሳይሆን የቬኒስን ጓዳ ጎድጓዳ ሁሉ ነው” በማለት ተናግሯል። ዮሃን ቮልፍጋንግ ፎን ጎተ የተባሉ እውቅ ጀርመናዊ ጸሐፊ በዚህች ጀልባ ተሳፍረው በተጓዙበት ወቅት “ማንኛውም የቬኒስ ተወላጅ በጎንዶላ ላይ ደገፍ ብሎ መጓዝ ሲጀምር የሚሰማው ዓይነት ስሜት ይኸውም የአድሪያቲክ ባሕር ጌታ” የሆኑ ያህል እንደተሰማቸው ተናግረዋል። ቀደም ብሎ የተጠቀሰው ሮቤርቶም “ጎንዶላ የምትሄደው በቀስታ መሆኑ ራሱ ከቬኒስ የአየር ሁኔታ ጋር ይስማማል። የስፖንጅ ትራሶች ባሉት መቀመጫ ላይ ሆናችሁ በቀስታ ስትንዠዋዠዉ ዓለምን እንደጨበጣችሁ ሆኖ ይሰማችኋል” ብሏል።

ጎንዶላን ልዩ የሚያደርጓት ነገሮች

ጎንዶላን ልብ ብላችሁ ስትመለከቷት በስተቀኟ በኩል የተገጠመ አንድ መቅዘፊያ ብቻ ያላት በመሆኗ ቀጥ ብላ መሄድ መቻሏ ያስገርማችሁ ይሆናል። በአንድ መቅዘፊያ የምትቀዝፍ ጀልባ በተደጋጋሚ አቅጣጫዋን ካላስተካከለች በስተቀር ወደ አንድ አቅጣጫ እያደላች በመሄድ ክብ እንደምትሠራ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ይህ ዓይነቱ ሁኔታ በጎንዶላ ላይ አይታይም። ለምን? ታዋቂ በሆኑ ቀደምት ጀልባዎች ላይ ጥናት ያካሄዱ ጂልቤርቶ ፔንዞ የተባሉ ሰው እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “ጀልባዋን ራስም ሆነ እጅና እግር ከሌለው የሰው አካል ጋር ብናመሳስላትና ከሥሯ የሚገኘውን የደጋን ቅርጽ ያለው ወጥ እንጨት የአከርካሪ አጥንት፣ ፍርግርጓን ደግሞ የጎድን አጥንቶች ብንላቸው ጎንዶላ ስኮሊዮሲስ የተባለ ከባድ የአከርካሪ ችግር አለባት ብለን መናገር እንችላለን” ብለዋል። በሌላ አነጋገር የጀልባዋ የቀኝ ክፍል ከግራው በ24 ሴንቲ ሜትር ስለሚያንስ ጎንና ጎኗ ተመጣጣኝ አይደለም። በመሆኑም ጎንዶላ የምትንሳፈፈው ከግራ ወደ ቀኝ ትንሽ ዘንበል ብላ ነው። ወደ አንድ ጎን ማጋደሏ በአንድ መቅዘፊያ ብቻ የምትነዳ መሆኗ የሚያስከትለውን ችግር እንዲሁም በስተግራ በኩል ሆኖ የሚቀዝፈውን ሰው ክብደት ስለሚያካክሰው ቀጥ ብላ እንድትሄድ ያስችላታል።

ይህችን “ዳክዬ” ከሌሎች ልዩ የሚያደርጋት አንደኛው ገጽታ አንገቷ ነው። ጀልባዋ ብረት ከሆነው ጀርባዋ በተጨማሪ ከብረት የተሠራው ብቸኛው ነገር አንገቷ ነው።  ደራሲው ጃንፍራንኮ ሙኔሮቶ አንገቷ “በጣም አስገራሚና ልዩ” ከመሆኑ የተነሳ “ለመጀመሪያ ጊዜ ከሚያያት ሰው አእምሮ አይጠፋም” በማለት ጽፈዋል። አንገቷ ብረት መሆኑ ቀደም ባሉት ጊዜያት ከበስተኋላ ሆኖ ጀልባዋን የሚቀዝፈውን ሰው ክብደት ለማካካስ ይረዳ ነበር፤ አሁን ግን ከጌጥነት ያለፈ ጥቅም የለውም። ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ወግ እንደሚለው ከሆነ አንገቷ ላይ በፊት በኩል ያሉት ስድስት ነገሮች የከተማዋን ስድስት ክፍለ ከተማዎች የሚያመለክቱ ሲሆን የኋለኛው ደግሞ ጁዴካ ተብላ የምትጠራውን የቬኒስ ደሴት ያመለክታል። ኤስ (S) የሚመስለው የአንገቷ ቅርጽ ታላቁ የቬኒስ ካናል ያለውን ቅርጽ እንደሚያመለክት ይነገራል።

ጎንዶላን የተለየች የሚያደርጋት ሌላው ነገር ደግሞ ጥቁር መልክ ያለው “ላባዋ” ነው። ጎንዶላዎች ጥቁር የሆኑበትን ምክንያት በሚመለከት የማይነገር ታሪክ የለም። ከእነዚህ ታሪኮች መካከል አንዱ እንደሚለው ከሆነ በ16ኛውና በ17ኛው መቶ ዘመን ጎንዶላዎች ትኩረት እንዲስቡ ብሎም ምቾት እንዲኖራቸው ለማድረግ ሲባል ቀለማቸው ከመብረቅረቁም በላይ ፈር እየለቀቁ መጡ። በዚህም የተነሳ የቬኒስ ምክር ቤት ልከኝነትን ለማበረታታት ሲል እንዲህ በሚያደርጉት ላይ የገንዘብ ቅጣት ለመጫን ተገዶ ነበር። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ጀልባዎቻቸውን ማስጌጥ ከመተው ይልቅ ቅጣት መክፈሉን መረጡ። በመሆኑም አንድ ዳኛ ሁሉም ጎንዶላዎች ጥቁር ቀለም እንዲቀቡ የሚያስገድድ ደንብ ደነገጉ። አንዳንዶች ደግሞ ጥቁር ቀለም ብላክ ዴዝ ተብሎ በተሰመየው በሽታ ምክንያት ለሞቱት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሐዘንን ለመግለጽ የሚያገለግል ምልክት እንደሆነ ይናገራሉ። ከዚህም በላይ ጎንዶላዎች ጥቁር ቀለም የሚቀቡት የቬኒስ ወይዛዝርት ነጭ የፊት ቆዳ ጎልቶ እንዲታይ ለማድረግ እንደሆነ የሚናገሩም አሉ። ይሁን እንጂ፣ ትክክለኛው ምክንያት ያን ያህል የተወሳሰበ አይደለም፤ ጥንት ጎንዶላዎች መልካቸው ጥቁር ሊሆን የቻለው ውኃ እንዳይገባባቸው ለመከላከል ሲባል ሙጫ ይቀቡ ስለነበረ ነው።

በጥቁሯ ዳክዬ ጀልባ ላይ ተፈናጠህ ፀጥ እረጭ ባለው ውኃ ላይ በዝግታ ስትጓዝ ከቆየህ በኋላ ጉዞህን ወደጀመርክበት በካናሉ ዳር ወደተሠራ መቆሚያ ትመለሳለህ። ጎንዶላዋን ከርቀት በዓይንህ ስትከተላት ‘ዳክዬዋ ድንገት ረዥሙን አንገቷን ዞር አድርጋ የተበታተነ ላባዋን ታስተካክል ይሆን?’ ብለህ ለአንድ አፍታ ታስብ ይሆናል።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሁለቱ የጎንዶላ ጎኖች አወቃቀር ተመጣጣኝ አይደለም

[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጎንዶላን ልዩ የሚያደርጋት የብረት አንገት

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቬኒስ ካናል ላይ ጎንዶላን የሚቀዝፈው ሮቤርቶ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

© Medioimages