የአልኮል መጠጥ መጠጣት ስህተት ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
የአልኮል መጠጥ መጠጣት ስህተት ነው?
“የወይን ጠጅ ፌዘኛ፣ ብርቱ መጠጥም ጠበኛ ያደርጋል፤ በእነዚህ የሳተ ሁሉ ጠቢብ አይደለም።” በምሳሌ 20:1 ላይ የሚገኘው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የአልኮል መጠጥ መጠጣት ስህተት እንደሆነ ያመለክታል? አንዳንዶች እንደዚያ ብለው ያስባሉ። እንዲያውም የአልኮል መጠጥን ያላግባብ መጠጣት መጥፎ መዘዝ እንዳስከተለ የሚያሳዩ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን እንደ ተጨማሪ ማስረጃ አድርገው ይጠቅሳሉ።—ዘፍጥረት 9:20-25
እርግጥ ነው፣ የአልኮል መጠጥ ከመጠን በላይ መጠጣት ከባድ መዘዝ ያስከትላል። ከችግሮቹ መካከል የተለያዩ የጉበት በሽታዎች፣ አሳዛኝ አደጋዎች፣ የገንዘብ ችግር፣ የቤተሰብ አባላት ላይ በደል ማድረስ እንዲሁም በጽንስ ላይ የሚደርስ ጉዳት ይገኙበታል። ምናልባትም በሚያስከትላቸው በእነዚህ መዘዞች ምክንያት ሳይሆን አይቀርም “ብዙ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች የአልኮል መጠጥ መጠጣት ሥነ ምግባር የጎደለው ተግባር እንደሆነ ያስተምራሉ” ሲል ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ ዘግቧል። ታዲያ የአልኮል መጠጥ መጠጣት ሥነ ምግባር የጎደለው ተግባር ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ማንኛውንም ዓይነት የአልኮል መጠጥ በትንሹም እንኳ ቢሆን መጠጣትን ይከለክላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ የአልኮል መጠጥ ከልክ በላይ መጠጣት የሚያስከትለውን መጥፎ ውጤት በመግለጽ ያስጠነቅቃል። ኤፌሶን 5:18 “በወይን ጠጅ አትስከሩ፤ ይህ ብክነት ነውና” በማለት ይመክራል። እንዲሁም ምሳሌ 23:20, 21 “ብዙ የወይን ጠጅ ከሚጠጡ፣ ሥጋ ከሚሰለቅጡ ጋር አትወዳጅ፤ ሰካራሞችና ሆዳሞች ድኾች ይሆናሉና” በማለት ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። ኢሳይያስ 5:11 ደግሞ “የሚያሰክር መጠጥ ፍለጋ ማልደው ለሚነሡ፣ እስኪያነዳቸውም ወይን በመጠጣት ሌሊቱን ለሚያነጉ ወዮላቸው!” በማለት ይናገራል።
መጽሐፍ ቅዱስ የአልኮል መጠጥ በልክ መጠጣት ስለሚያስገኘው ደስታና ጥቅምም ይናገራል። ለምሳሌ ያህል መዝሙር 104:15 የአምላክ ስጦታ ከሆኑት ነገሮች አንዱ የሆነው ‘ወይን የሰውን ልብ ደስ እንደሚያሰኝ’ ይናገራል። እንዲሁም መክብብ 9:7 መልካም ሥራ የሚያስገኘውን ሽልማት በመጥቀስ “ሂድ፤ ምግብህን በደስታ ብላ፤ ወይንህንም ልብህ ደስ ብሎት ጠጣ” ይላል። ጳውሎስ ወይን ጠጅ መድኃኒትነት እንዳለው ስለሚያውቅ ለጢሞቴዎስ “ለሆድህና ደጋግሞ ለሚነሣብህ ሕመም፣ ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣበት እንጂ ከእንግዲህ ውሃ ብቻ አትጠጣ” በማለት መክሮታል። (1 ጢሞቴዎስ 5:) የአልኮል መጠጥ በሥቃይ ሥር ያሉ ሰዎች ችግራቸውን እንዲቋቋሙ በመርዳት ረገድ ያለው ኃይል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሶ ይገኛል።— 23ምሳሌ 31:6, 7
ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ የአልኮል መጠጥ መጠጣትን አይከለክልም። ይሁን እንጂ ከልክ በላይ መጠጣትን እንዲሁም ሰካራምነትን ያወግዛል። ስለዚህ ጳውሎስ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች፣ የጉባኤ አገልጋዮች እንዲሁም አረጋውያን ሴቶች “ለብዙ ወይን ጠጅ” እንዳይጎመጁ መክሯቸዋል፤ እንዲሁም ለጢሞቴዎስ “ጥቂት የወይን ጠጅ” ብቻ እንዲጠጣ መክሮታል። (1 ጢሞቴዎስ 3:2, 3, 8፤ ቲቶ 2:2, 3) “ሰካራሞች . . . የእግዚአብሔርን መንግሥት” እንደማይወርሱ ለሁሉም ክርስቲያኖች ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10
መጽሐፍ ቅዱስ ሰካራምነትን ከሆዳምነት ጋር አያይዞ የሚገልጸው መሆኑ ትኩረት የሚስብ ከመሆኑም በላይ ሁለቱም መወገድ የሚገባቸው ነገሮች መሆናቸውን ይናገራል። (ምሳሌ 23:21) ይህን ምክር ምንም የአልኮል መጠጥ አለመቅመስን እንደሚያመለክት አድርገን ከወሰድነው በልክ መመገብም ስህተት ነው ወደሚል መደምደሚያ አያደርሰንም? ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ስህተት እንደሆነ የሚናገረው ስካርን ወይም ሆዳምነትን እንጂ በልክ መብላትን ወይም መጠጣትን አይደለም።
ኢየሱስ ምን አድርጓል?
ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ክርስቶስ ‘የእርሱን ፈለግ እንድንከተል ምሳሌ’ እንደተወልን ከተናገረ በኋላ “እርሱ ኀጢአት አላደረገም” ብሏል። (1 ጴጥሮስ 2:21, 22) ታዲያ ኢየሱስ ለአልኮል መጠጦች የነበረው አመለካከት ምን ዓይነት ነበር? እርሱ ካከናወናቸው ተአምራት መካከል የመጀመሪያው ውኃን ወደ ወይን ጠጅ መቀየር ነበር። ኢየሱስ የቀየረው የወይን ጠጅ ምን ዓይነት ነበር? “የድግሱ ኀላፊ” በተአምራዊ ሁኔታ የተለወጠውን ይህን የወይን ጠጅ በሚመለከት ለሙሽራው “ሰው ሁሉ በመጀመሪያ የሚያቀርበው ጥሩውን የወይን ጠጅ ነው፤ እንግዶቹም ብዙ ከጠጡ በኋላ መናኛውን የወይን ጠጅ ያቀርባል፤ አንተ ግን ጥሩውን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቈይተሃል” የሚል አስተያየት ሰጥቶ ነበር።—ዮሐንስ 2:9, 10
የማለፍ በዓል በሚከበርበት ዕለት የወይን ጠጅ መጠጣት የተለመደ ነገር የነበረ ሲሆን ኢየሱስም የጌታ እራትን ባቋቋመበት ምሽት ወይን ተጠቅሟል። በዋንጫ የተቀዳውን ወይን ለደቀ መዛሙርቱ በመስጠት “ሁላችሁም ከዚህ ጠጡ” ብሏቸዋል። ኢየሱስ በቅርቡ እንደሚሞት ስለሚያውቅ “እላችኋለሁ፤ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር በአዲስ መልክ እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ፣ ከእንግዲህ ከዚህ የወይን ፍሬ አልጠጣም” አላቸው። (ማቴዎስ 26:27, 29) አዎን፣ ኢየሱስ ወይን ጠጅ እንደሚጠጣ ሰዎች ያውቁ ነበር።—ሉቃስ 7:34
እኛስ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
መጽሐፍ ቅዱስ የአልኮል መጠጥ መጠጣትን ባይከለክልም የግድ መጠጣት ይኖርብናል ማለት ግን አይደለም። ከመጠጣት እንድንቆጠብ የሚያደርጉን ብዙ ምክንያቶች አሉ። ለምሳሌ ከዚህ ቀደም የአልኮል ሱሰኛ የነበረ ሰው ትንሽም እንኳ ቢሆን መጠጣቱ የሚያስከትልበትን ችግር ያውቀዋል። አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት ለጽንሱ ደኅንነት ስትል ከመጠጣት ትቆጠብ ይሆናል። እንዲሁም መኪና የሚያሽከረክር ሰው የአልኮል መጠጥ የማሰብ እንዲሁም አጥርቶ የማየት ችሎታን እንደሚያዛባ አውቆ የራሱንም ሆነ የሌሎችን ሕይወት አደጋ ላይ ላለመጣል ሲል ከመጠጣት ይቆጠባል።
በተጨማሪም ክርስቲያኖች የአልኮል መጠጥ መጠጣትን ሕሊናው የማይቀበልን ሰው እንዳያሰናክሉ ይጠነቀቃሉ። (ሮሜ 14:21) ስለዚህ አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት በመስክ አገልግሎት የሚካፈሉ ከሆነ የአልኮል መጠጥ አለመጠጣታቸው የጥበብ እርምጃ ነው። አምላክ ለጥንት እስራኤላውያን በሰጠው ሕግ ላይ ካህናት በቤተ መቅደሱ በሚያገለግሉበት ወቅት “የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ” እንዳይጠጡ መታዘዛቸው ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ነው። (ዘሌዋውያን 10:9) እንዲሁም የአልኮል መጠጦችን መጠጣት በተከለከለባቸው ወይም የዕድሜ ገደብ በተጣለባቸው አገሮች የሚኖሩ ክርስቲያኖች ሕጉን ስለሚታዘዙ ከመጠጣት ይቆጠባሉ።—ሮሜ 13:1
የአልኮል መጠጥ ለመጠጣት ወይም ላለመጠጣት አሊያም መጠኑን መወሰን ለግለሰቡ የተተዉ ናቸው። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ልከኛ እንድንሆን ይመክረናል። እንዲህ ይላል:- “ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ፣ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት።”—1 ቆሮንቶስ 10:31
ይህን አስተውለኸዋል?
▪ የአልኮል መጠጥን አስመልክቶ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምን ማስጠንቀቂያ ሰፍሮ ይገኛል?—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10
▪ ኢየሱስ የአልኮል መጠጥ ይጠጣ ነበር?—ሉቃስ 7:34
▪ እውነተኛ ክርስቲያኖች በምግብም ሆነ በመጠጥ ልማዳቸው ረገድ እንደ መመሪያ ሆኖ የሚያገለግላቸው ነገር ምንድን ነው?—1 ቆሮንቶስ 10:31