በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሙታንን ልትረዳቸው ትችላለህ?

ሙታንን ልትረዳቸው ትችላለህ?

 የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ሙታንን ልትረዳቸው ትችላለህ?

“ቤተ ክርስቲያን ከጥንትም ጀምሮ . . . [ለሙታን] ፍትሃት ስታደርግ ቆይታለች፤ . . . በዚህ መንገድ የነጹት [ሙታን] አምላክን የማየት አስደሳች አጋጣሚ ያገኛሉ።” —“ካቴኪዝም ኦቭ ዘ ካቶሊክ ቸርች”

ማንኛውም የሰው ዘር ሙታን የሚገኙበት ሁኔታ ያሳስበዋል። ምናልባት አንተም የምትወደውን ሰው በሞት በማጣትህ ሐዘንና የከንቱነት ስሜት ተሰምቶህ ይሆናል። ‘በሞት የተለዩን ሰዎች ሕያው ሆነው ይቀጥሉ ይሆን? እየተሠቃዩ ናቸው ወይስ በሰላም እየኖሩ? እነርሱን መርዳት እችላለሁ?’ በማለት ትጠይቅ ይሆናል።

አብዛኞቹ የሃይማኖት ሰዎች ሙታንን መርዳት እንደሚችሉ ይሰማቸዋል። ለምሳሌ ሂንዱዎች የሚወዱትን ሰው አስከሬን በጋንጀስ ወንዝ ዳርቻ አቃጥለው አመዱን በውኃው ላይ መበተናቸው የሞተውን ሰው ነፍስ ዘላለማዊ ደስታ እንዲያገኝ ሊረዳ እንደሚችል ያምናሉ። በሩቅ ምሥራቅ አገሮች ቡድሂስቶች በወረቀት የተሠሩ የመኪና፣ የቤት፣ የልብስና የገንዘብ ምስሎችን ማቃጠላቸው የሞቱት ሰዎች በሌላኛው ዓለም ሲኖሩ በእነዚህ ንብረቶች መጠቀም እንዲችሉ እንደሚረዳቸው ያምናሉ። በአፍሪካ ደግሞ ሙታንን ይጠቅማል በሚል በመቃብሩ አጠገብ የአልኮል መጠጦችን ያፈሳሉ።

የካቶሊክ እምነት፣ አንድ ሰው “የማይሰረይ ኃጢአት” ሠርቶ ሳይናዘዝ ከሞተ የአምላክን ሞገስ ማግኘት እንደማይችል ያስተምራል። እንዲህ ያሉ ሙታን የሚገኙበት ሁኔታ “‘ገሃነም’ ተብሎ ይጠራል።” በሌላው በኩል ደግሞ የአምላክን ሞገስ ያገኘ ሰው፣ ፍጹም እስኪሆን ድረስ በደንብ ከነጻ በኋላ በሰማይ ከአምላክ ጋር “ከሁሉ የላቀ ፍጹም ደስታ” እንደሚያገኝ ተስፋ ማድረግ ይችላል ብሎ ያስተምራል። ይህ ሂደት መንጽሔ ውስጥ ገብቶ “በሚያነጻ እሳት” ማለፍን የሚጠይቅ ሲሆን ይህ ደግሞ ይቅር ሊባሉ ለሚችሉ ስህተቶች የሚሰጥ ቅጣት ነው። ሆኖም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን  ለሞተው ሰው የምታደርገው ፍትሃት ማለትም ሰውየውን ለማማለድ የሚደረገው ጸሎት እንዲሁም ግለሰቡን ለመጥቀም ተብሎ የሚቀርበው ቁርባን የሞተውን ሰው በመንጽሔ እያለ ሊረዳው ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያለው አገልግሎት እንዲከናወን ገንዘብ የሚከፍሉት የሞተው ሰው ጓደኞችና ዘመዶች ናቸው።

የምትወዳቸው ሰዎች ሊደርስባቸው የሚችለውን ማንኛውንም ዓይነት ሥቃይ ለማቅለል የምትችለውን ሁሉ ለማድረግ መፈለግህ ያለ ነገር ነው። ይሁንና የሞቱትን መርዳት ቢቻል ኖሮ እንዴት ልንረዳቸው እንደምንችል አምላክ በግልጽ ያሳውቀን አልነበረም? መጽሐፍ ቅዱስ ሙታንን ስለ መርዳት ምን እንደሚያስተምር እስቲ እንመልከት።

ሙታን ያሉበት ሁኔታ

ከላይ ያየናቸው ልማዶች በሙሉ የሰው ነፍስ አትሞትም በሚለው እምነት ላይ የተመሠረቱ ናቸው። በዚህ እምነት መሠረት አንድ ሰው ሥጋዊ አካሉ ከሞተ በኋላ በውስጡ የነበረችው ነፍስ በሕይወት መኖሯን ትቀጥላለች። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብሎ ያስተምራል? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይናገራል:- “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁምና፤ መታሰቢያቸው ይረሳል፤ ምንም ዋጋ የላቸውም። ፍቅራቸው፣ ጥላቻቸው፣ ቅናታቸውም ከጠፋ ቈይቶአል፤ ከፀሓይ በታች በሚሆነው ነገር ሁሉ፣ ፈጽሞ ዕጣ ፈንታ አይኖራቸውም። እጅህ የሚያገኘውን ሥራ ሁሉ በሙሉ ኀይልህ ሥራው፤ ልትሄድበት ባለው መቃብር [“ሲኦል፣” የግርጌ ማስታወሻ] ውስጥ መሥራትም ሆነ ማቀድ፣ ዕውቀትም ሆነ ጥበብ የለምና።” (መክብብ 9:5, 6, 10) ሲኦል፣ የሰው ልጆችን መቃብር የሚያመለክት የዕብራይስጥ ቃል ነው።

መዝሙራዊው በመንፈስ አነሳሽነት “መንፈሳቸው ትወጣለች፤ ወደ መሬታቸውም ይመለሳሉ፤ ያን ጊዜም ዕቅዳቸው እንዳልነበር ይሆናል” በማለት ሞት በሰው ልጆች ላይ የሚያስከትለውን ውጤት ጽፏል።—መዝሙር 146:4

መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገራቸው ሐሳቦች እምነት የሚጣልባቸውና ምክንያታዊ ናቸው። አንድ አፍቃሪ አባት ልጆቹ በወረሱት የኃጢአት ዝንባሌ ምክንያት እንዲሠቃዩ የሚያደርግ ይመስልሃል? (ዘፍጥረት 8:21) ፈጽሞ እንደማያደርገው የታወቀ ነው። ታዲያ በሰማይ ያለው አባታችን ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነገር እንዴት ሊያደርግ ይችላል? በጥንቷ እስራኤል ይኖሩ የነበሩ አንዳንዶች በዚያን ጊዜ የነበረውን የአረማውያን አምልኮ ሥርዓት በመከተል ልጆቻቸውን በእሳት አቃጥለው ለሐሰት አማልክት መሥዋዕት ባደረጉ ጊዜ፣ ይሖዋ ይህ አስከፊ ድርጊት ‘ያላዘዘውና ከቶም ያላሰበው’ መሆኑን በመግለጽ አውግዟቸዋል።—ኤርምያስ 7:31

የኃጢአት ውጤት ሞት እንጂ ከዚያ በኋላ ባለ ሕይወት መሠቃየት አይደለም። ቅዱሳን ጽሑፎች “የኀጢአት ደመወዝ ሞት ነው” እንዲሁም “የሞተ ከኀጢአት ነጻ ወጥቶአል” በማለት ይናገራሉ።—ሮሜ 5:12፤ 6:7, 23

ሙታን እየተሠቃዩ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ ልክ ከባድ እንቅልፍ ውስጥ እንዳሉ ያህል በመሆናቸው ደስታም ሆነ ሌላ ምንም ነገር አይሰማቸውም። ስለዚህ ሰዎች ሙታንን ለመርዳት የሚያደርጉት ማንኛውም ጥረት ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር እንደሚጋጭ ምንም ጥያቄ የለውም።

ሙታን ምን ተስፋ አላቸው?

እንዲህ ሲባል ግን በሞት ያንቀላፉ የምትወዳቸው ሰዎች ሁሉ ለዘላለም በድን ሆነው ይቀራሉ ማለት አይደለም። ከዚህ በተቃራኒ ብሩህ ተስፋ ይጠብቃቸዋል።

ኢየሱስ የቅርብ ወዳጁን አልዓዛርን ከሞት ከማስነሳቱ በፊት “ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ” በማለት ተናግሮ ነበር። (ዮሐንስ 11:11) በሌላ ወቅት ደግሞ ‘መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ጊዜ እንደሚመጣና ከመቃብር እንደሚወጡ’ ተናግሯል። (ዮሐንስ 5:28, 29) ከሞት የተነሱት ከቀድሞ ኃጢአታቸው ነጻ ስለሚወጡ ከዚህ ቀደም በሕይወት እያሉ በሠሯቸው ነገሮች አይሠቃዩም። ፍጹም በሆነ ሁኔታ ውስጥ የመኖር አጋጣሚ ያገኛሉ። እንዴት ያለ ድንቅ ተስፋ ነው!

ይህ ተስፋ ማራኪ ሆኖ ካገኘኸው እምነት የሚጣልበት መሆኑን ከማረጋገጥ ወደኋላ አትበል። የይሖዋ ምሥክሮች ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው።

ይህን አስተውለኸዋል?

▪ ሙታን የሚያውቁት ነገር አለ?—መዝሙር 146:4፤ መክብብ 9:5, 6, 10

▪ አምላክ የሞቱትን ሰዎች በእሳታማ ሲኦል ውስጥ እንዲሠቃዩ ያደርጋል?—ኤርምያስ 7:31

▪ ሙታን ምን ተስፋ አላቸው?—ዮሐንስ 5:28, 29