በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተቸገሩ ሰዎችን መርዳት የምችለው እንዴት ነው?

የተቸገሩ ሰዎችን መርዳት የምችለው እንዴት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

የተቸገሩ ሰዎችን መርዳት የምችለው እንዴት ነው?

“ትምህርቴን ስጨርስ የኤሌትሪክ ሠራተኛ የመሆን እቅድ አለኝ። የመንግሥት አዳራሾች በሚገነቡበት ጊዜ መርዳት እፈልጋለሁ።”—የ14 ዓመቱ ትሪስታን

“ለአዲሱ የሕትመት መሣሪያ 20 ዶላር መዋጮ አድርጌያለሁ። የኪስ ገንዘቤ ቢሆንም ልሰጣችሁ እፈልጋለሁ።”—የ9 ዓመቷ አቢ

አብዛኞቹ ወጣቶች ራስ ወዳድ እንደሆኑ በሚነገርበት በዚህ ዘመን፣ ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች ከዚህ የተለየ አመለካከት እንዳላቸው አሳይተዋል። የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ብዙ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ሌሎችን ለመርዳት ሲሉ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ገንዘባቸውን መሥዋዕት ያደርጋሉ። (መዝሙር 110:3) አንዳንድ ተጨማሪ ምሳሌዎችን ተመልከት።

በአውስትራሊያ የሚኖረው የሰባት ዓመቱ ጂራ ሴት አያቱ ከሞቱ ከትንሽ ጊዜ በኋላ ከወንድ አያቱ 50 ዶላር በስጦታ ተላከለት። ጂራ ገንዘቡን ምን አደረገው? በቀጣዩ የጉባኤ ስብሰባ ላይ ሁሉንም ገንዘብ መዋጮ ሣጥን ውስጥ ጨመረው። ለምን? “ብዙ መጫወቻዎች አሉኝ፣ ያለችኝ ሴት አያት ግን አንድ ብቻ ነበረች። እርሷ ደግሞ ይሖዋን በጣም ስለምትወደው ይህን ገንዘብ መዋጮ እንዳደርገው ትፈልግ እንደነበር አውቃለሁ” በማለት ለእናቱ ነገራት።

በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው የአምስት ዓመቷ ሐና ፈረስ ትወዳለች። በመሆኑም 75 የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ አንድ የአሻንጉሊት ፈረስ እንዲገዛላት ፈለገች። ወላጆቿም ገንዘብ ማጠራቀም ጠቃሚ መሆኑን ሊያስተምሯት በማሰብ የአሳማ ቅርጽ ባላት ትንሽ ገንዘብ ማጠራቀሚያ ውስጥ እንድታስቀምጠው አልፎ አልፎ ገንዘብ ይሰጧት ጀመር። ብዙም ሳይቆይ ሐና፣ የአሻንጉሊት ፈረሱን ለመግዛት ከሚያስችላት በላይ ገንዘብ አጠራቀመች።

ይሁንና በዚህ ጊዜ አካባቢ፣ ካትሪና የተባለችው አውሎ ነፋስ በዩናይትድ ስቴትስ የባሕር ዳርቻዎች አካባቢ አስከፊ ጉዳት አስከተለች። ሐና በአደጋው የተጠቁት ሰዎች ሁኔታ ስላሳሰባት ያጠራቀመችውን ከ100 በላይ የአሜሪካ ዶላር አንድም ሳታስቀር ሰዎቹን ለመርዳት ልትሰጠው ወሰነች። ሐና ለይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት “ይህን ገንዘብ ልሰጣችሁ የፈለግኩት ይሖዋን ስለምወደውና ሌሎችን መርዳት ስለምፈልግ ነው” በማለት ጽፋለች። በእርግጥ ይሖዋ እንዲህ ዓይነቱን የደግነት ምግባር ይመለከታል? መጽሐፍ ቅዱስ “መልካም ማድረግንና ያላችሁንም ከሌሎች ጋር መካፈልን አትርሱ፤ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኘው እንደዚህ ባለው መሥዋዕት ነውና” ይላል።—ዕብራውያን 13:16

በዚያው በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር ቴፈኒ የተባለች አንዲት ወጣት፣ ፍሎሪዳ በ2004 በሁለት አውሎ ነፋሶች ከተመታች በኋላ እንደሚከተለው ስትል ለይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ጽፋ ነበር:- “እኔና ወንድሜ ቲመቲ 110 የአሜሪካ ዶላር መዋጮ ማድረግ እንፈልጋለን። ቤታችን ያን ያህል ጉዳት አልደረሰበትም፤ ሆኖም አውሎ ነፋሱ ሌሎች ቤቶችን እንዴት እንዳደረጋቸው ተመልክተናል። በመሆኑም ሌሎችን መርዳት ስለፈለግን ገንዘብ ማጠራቀም ጀመርን። ቲመቲ ሰዎች ግድግዳ ሲያፈርሱ በመርዳት 10 ዶላር ሲያገኝ እኔ ደግሞ 100 ዶላር አጠራቀምኩ።” ቴፈኒ የ13 ዓመት ልጅ ስትሆን ወንድሟ ቲመቲ ደግሞ ገና 7 ዓመቱ ነው! ከራሳችን ይልቅ የሌሎችን ፍላጎት ማስቀደማችን ምን ያስገኝልናል? ምሳሌ 11:25 “ሌሎችን የሚያረካም ራሱ ይረካል” ይላል።

ዕድሜያቸው ከ4 እስከ 15 የሚሆኑ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚኖሩ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች፣ በአፍሪካ ያሉት የእምነት ባልንጀሮቻቸው የመንግሥት አዳራሾች እንደሚያስፈልጓቸው ይሰማሉ። በመሆኑም አንድ ነገር ማድረግ እንዳለባቸው ተሰማቸው። እነዚህ ወጣቶች እንዲህ ብለዋል:- “ያገለገሉ ዕቃዎች ደጃፋችን ላይ በሚሸጡበት ወቅት ብስኩቶችንና ኬኮችን በመሸጥ 106.54 የአሜሪካ ዶላር አገኘን። ገንዘቡ በአፍሪካ ውስጥ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚማሩባቸውን መሰብሰቢያ አዳራሾች ለመሥራት እንደሚውል ለገበያተኞቹ እንነግራቸው ነበር። ብዙ ሰዎች ጥሩ ምላሽ ሰጥተውናል። ብስኩቶቹንና ኬኮቹን ለመሸጥ ዘጠኝ ሰዓት የፈጀብን ቢሆንም ይህን ያደረግነው ለይሖዋ በመሆኑ አንቆጭም!”

አንተም ሌሎችን መርዳት ትችላለህ

ቀደም ሲል ተሞክሯቸው የተገለጸው ወጣቶች “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” የሚሉትን የኢየሱስን ቃላት እውነተኝነት ተገንዝበዋል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) አንተም ከመስጠት የሚገኘውን ደስታ መቅመስ ትችላለህ። መስጠት የምትችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

በእምነት ባልንጀሮችህ ላይ አንድ ዓይነት ችግር እንደደረሰ ሰምተህ ታውቃለህ? ለምሳሌ ያህል በተፈጥሮ አደጋ እንደተጠቁ የሚገልጽ ሪፖርት ሰምተሃል? ቤት ንብረትህን ማጣት ወይም የምትወደውን ሰው በሞት መነጠቅ ምን ሊመስል እንደሚችል አስብ። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች ‘ሌሎችን የሚጠቅመውንም እንጂ፣ ራሳቸውን የሚጠቅመውን ብቻ መመልከት’ እንደሌለባቸው ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 2:4) የምትኖረው የተፈጥሮ አደጋው ከደረሰበት አካባቢ ርቀህ ቢሆንም እንኳ የይሖዋ ምሥክሮች ሌሎችን ለመርዳት የሚያደርጉትን ጥረት ለማገዝ የገንዘብ መዋጮ ማድረግ ትችላለህ። *

ችግር የደረሰባቸውን ሰዎች መርዳት የምትችልባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የይሖዋ ምሥክር ከሆንክ በጉባኤህ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ለምን መለስ ብለህ አትቃኝም? እርዳታ የሚሹ አረጋውያን ወይም ሌሎች ወንድሞች አሉ? የቤት ውስጥ ሥራዎችን በማከናወን ልትረዳቸው ትችላለህ? ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች እንደሚከተለው በማለት ጽፎላቸዋል:- “እርስ በርሳችሁ በወንድማማች መዋደድ አጥብቃችሁ ተዋደዱ፤ አንዱ ሌላውን ከራሱ በማስበለጥ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ።” (ሮሜ 12:10) እርዳታ የሚያስፈልገው ሰው እንዳለ ካስተዋልክ ለመርዳት ራስህን አቅርብ። ዝቅተኛ የተባሉ ሥራዎችን ለመሥራትም ቢሆን ፈቃደኛ ሁን። እንዲሁም ሌሎችን መርዳት ይሖዋን ከማገልገል ጋር በጥብቅ የተዛመደ መሆኑን አትዘንጋ። መጽሐፍ ቅዱስ “ለድኻ የሚራራ ለእግዚአብሔር ያበድራል፤ ስላደረገውም ተግባር ዋጋ ይከፍለዋል” በማለት ይገልጻል።—ምሳሌ 19:17

እርግጥ ነው፣ ሌሎችን የምትረዳበት ከሁሉ የላቀ መንገድ የአምላክ ቃል ስለሆነው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያወቅኸውን ለእነርሱም በማካፈል ነው። ኢየሱስ “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሏል። (ዮሐንስ 17:3) ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አሁን ሰዎች ሕይወት አድን የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት መስማት ያስፈልጋቸዋል። በመሆኑም ‘የምትደክመው በከንቱ እንዳልሆነ’ በመተማመን አዘውትረህ በስብከቱ ሥራ በቅንዓት መካፈልህን ቀጥል።—1 ቆሮንቶስ 15:58

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “የወጣቶች ጥያቄ . . .” የሚሉትን ተከታታይ ርዕሶች ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.13 አንድ የተወሰነ አካባቢን ለመርዳት ታስበው የሚላኩ የገንዘብ መዋጮዎችን በአመስጋኝነት እንቀበላለን። ይሁንና በአደጋ ጊዜ እርዳታ ማድረግ ሲያስፈልግ ገንዘብ ወጪ የሚደረገው የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያከናውኑትን ሥራ ለማገዝ ከሚውለው ገንዘብ ላይ በመሆኑ መዋጮው ለዓለም አቀፉ ሥራ ተብሎ ቢላክ ይመረጣል።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

የአንተን እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች አሉ?

እነዚህን ሰዎች ለመርዳት ምን ማድረግ ትችላለህ?

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

መልካም ማድረግንና ያላችሁንም ከሌሎች ጋር መካፈልን አትርሱ፤ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኘው እንደዚህ ባለው መሥዋዕት ነውና።ዕብራውያን 13:16

[በገጽ 24 እና 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

መስጠትን መማር ያለብን ለምንድን ነው?

ወላጆቼ ጊዜያቸውንም ሆነ ጉልበታቸውን ይሖዋንና ሰዎችን ለማገልገል ሲጠቀሙበት መመልከቴ እኔም ሕይወቴን በዚሁ መንገድ ለመምራት እንድነሳሳ አድርጎኛል። አባቴ እንዲህ ይለኝ ነበር:- የቱንም ያህል ትንሽ ይሁን ለይሖዋ ብለህ የምትሠራው ነገር ለዘላለም ሲታወስ ይኖራል። ይሖዋ ዘላለማዊ በመሆኑ የሠራኸውን ሥራ ለዘላለም አይረሳውም። ለራስ ብቻ መኖር ግን ከንቱ ነው። ስትሞት የሠራኸው ነገር ሁሉ አብሮህ ይሞታል።’”—የ24 ዓመቱ ኬንታሮ፣ ከጃፓን

እንደ እውነቱ ከሆነ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ የቤት ውስጥ ሥራዎችን በመሥራት አረጋውያንን የማገዝ ፍላጎት አልነበረኝም። ከጓደኞቼ ጋር መዝናናት እፈልግ ነበር። ሆኖም ከአረጋውያኑ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ስጀምር አብሬያቸው መሆኔ ያስደስተኝ ጀመር። እነዚህ ወንድሞች በአንድ ወቅት እንደ እኔ ወጣት የነበሩና አሁንም ከእኔ ጋር ተመሳሳይ ስሜት ያላቸው ሰዎች መሆናቸውን ተገነዘብኩ። ይህ ደግሞ እንድረዳቸው ገፋፋኝ።—የ27 ዓመቱ ጆን፣ ከእንግሊዝ

ልጅ እያለሁ የመንግሥት አዳራሽ በማጽዳትና በሌሎችም እንቅስቃሴዎች እካፈል ነበር። በጉባኤያችን የሚገኙ ወንድሞችን በጉልበት ሥራ መርዳትም ያስደስተኝ ነበር። ሌሎችን ስትረዳ እንዲህ ማድረግህ ምን ያህል እንደሚያስደስታቸው ትመለከታለህ። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ወቅት ከሌሎች ወንድሞች ጋር በመሆን ወደ አንዲት አረጋዊት እህት ቤት ሄድንና የቤቱን ግድግዳ በወረቀት ለጠፍንላቸው። እኚህ እህት እጅግ በጣም ተደሰቱ! ሰውን ስታስደስት አንተም ደስተኛ ትሆናለህ።—የ23 ዓመቱ ኧርማን፣ ከፈረንሳይ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙ ወጣቶች አደጋ የደረሰባቸውን ሰዎች ለመርዳት ሲሉ የገንዘብ መዋጮ ያደርጋሉ