በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአንባቢዎቻችን

ከአንባቢዎቻችን

 ከአንባቢዎቻችን

ሥርዓተ ፀሐይ ሥነ ፈለክን በተመለከተ ያለኝ እውቀት እጅግ ውስን ቢሆንም “የሥርዓተ ፀሐይን ምስጢር የፈታ ሰው” የሚለውን ርዕስ በጣም ወድጄዋለሁ። (ግንቦት 2005) የፕላኔቶችን እንቅስቃሴ ሕግ ያገኘው ኬፕለር ታላቅ ሥራ አከናውኗል። ከሁሉ በላይ ግን እነዚህን ሕግጋት የፈጠረው ይሖዋ ያለውን ጥበብ ሳስብ በአድናቆት እሞላለሁ።

ኤም. ዋይ.፣ ጃፓን

ሥነ ፈለክ ከምወዳቸው በርካታ መስኮች ውስጥ አንዱ ነው። ዮሐንስ ኬፕለር ሁልጊዜ ተረጋግቶና ተመችቶት የሚኖር ሰው እንዳልነበረ ማንበቤ በጣም አስገርሞኛል። በአዲሱ ዓለም ከይሖዋ በምናገኘው መመሪያ እየታገዝሁ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የሚገኙትን እስከ አሁን ድረስ ያልታወቁ ጋላክሲዎች ከዚህ የቀድሞ ሊቅ ጋር ሆኜ የማጠናበት አጋጣሚ ይኖረኝ ይሆናል። እባካችሁ እነዚህን የመሳሰሉ ማራኪ ርዕሶችን ማውጣታችሁን ቀጥሉ!

ዜድ. ኤም.፣ ጀርመን

ሁሉም ሰዎች የይሖዋን አስደናቂ ፍጥረታት ለመረዳት እንዲችሉ፣ በጣም ከባድ የሆነውን ርዕስ ሊገባ በሚችል መልኩ ስላስቀመጣችሁት አመሰግናችኋለሁ። የኬፕለርን ግኝት በተመለከተ እንዲሁም ከሐሰት ሃይማኖት ለመለየት ስላደረገው ቁርጥ ውሳኔ ሳነብ በጣም ተበረታትቻለሁ! ወደፊትም ይህን የመሰለ ወቅታዊ ርዕሶችን የያዘ መጽሔት እንደምታዘጋጁ እርግጠኛ ነኝ።

ኤስ.ኤም.ቸ.፣ ብሪታንያ

ቲማቲም የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ስሆን “ቲማቲም—ሁለገብ የሆነ ‘አትክልት’” በሚል ርዕስ የወጣውን ሐሳብ ወድጄዋለሁ። (ግንቦት 2005) ይሖዋ የተለያዩ ጣፋጭ አትክልቶችን በመፍጠሩ በጣም አመሰግነዋለሁ። መስመር ያላቸው የቲማቲም ዓይነቶች እንዳሉ ሳውቅ በጣም ተገረምኩ! እንደዚህ የመሰሉ ደስ የሚያሰኙ ርዕሶች ስለምታወጡ አመሰግናችኋለሁ።

ኤም. ኤፍ.፣ ላትቪያ

የወጣቶች ጥያቄ . . . ከመጥፎ ልጆች ጋር የገጠምኩት ምን ነክቶኝ ነው? (ነሐሴ 2005) በዚህ ርዕስ ሥር የቀረበው ነጥብ በሁለት ሐሳብ እየዋለልኩ መቀጠል እንደማልችል እንድገነዘብ አድርጎኛል። ከመጥፎ ጓደኞች ለመራቅ ያደረግኩትን ቁርጥ ውሳኔ አጠናክሮልኛል። አሁን በጉባኤያችን ከሚገኙ በርካታ ወጣቶችና አረጋውያን ጋር የጠበቀ ጓደኝነት ለመመሥረት ችያለሁ፤ ይህም ይሖዋን የሚወዱና ከሕይወት መንገድ እንዳልወጣ የሚያበረታቱኝ የሚወዱኝ ሰዎች እንዳሉ እንዲሰማኝ አድርጎኛል።

ኤም. ዲ.፣ ሜክሲኮ

ያወጣሁት ግብ ላይ ለመድረስ በቁርጠኝነት መታገል (መስከረም 2005) የማርታን ተሞክሮ በማነብበት ጊዜ እንባዬ ይፈስ ነበር። እኔም እንደ ማርታ በሚጥል በሽታ እሠቃያለሁ። የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆኜ ላለፉት አሥር ዓመታት ያገለገልኩ ሲሆን በተለይ ሰውነቴን እያንዘፈዘፈኝ በምወድቅበት ጊዜ ሁኔታዎች በጣም አስቸጋሪ ይሆኑብኝ ነበር። የማርታ ተሞክሮ ተስፋ እንዳልቆርጥ ያደረግሁትን ውሳኔ አጠናክሮልኛል። እንዲሁም በእጅጉ አጽናንቶኛል።

ዋይ. ኤስ.፣ ፖላንድ

እኔም የማርታ ዓይነት ችግር ስላለብኝ እየታገልኩ ነው። የማርታን ተሞክሮ ሳነብ የምመገባቸውን የምግብ ዓይነቶች በተመለከተ ጥንቃቄ ማድረግ ጀመርኩ። ይህ የሚጥል በሽታ ከአሥር ዓመት በላይ ይሖዋን በበለጠ እንዳላገለግለው አድርጎኛል። ሆኖም ከሦስት ዓመት በፊት የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆኜ ለማገልገል የወሰንኩ ሲሆን በዚህም ምንም አልቆጭም። ይህን የመሰለ አበረታች ተሞክሮ ስለምታቀርቡ ይሖዋ አብዝቶ ይባርካችሁ!

ቢ.ኬ.ኬ.፣ ብራዚል

ከማርታ ተሞክሮ በጣም ያበረታታኝ ነገር ተስፋ አለመቁረጧ ነው። ምንም እንኳ ሕመሟ አገልግሎቷን እንድታቆም ቢያደርጋትም ሚዛናዊ አመለካከት መያዟና ይሖዋ በሙሉ ልብ በሚቀርብ አገልግሎት እንደሚደሰት የነበራት እምነት እጅግ አበረታቶኛል።

ኤስ. ኤች.፣ ጃፓን

ከማርታ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ስላጋጠመኝ የአቅም ገደብ እንዳለብኝ መገንዘብ አስፈልጎኛል። ልክ እንደ ማርታ እኔም የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆኜ ማገልገል ችያለሁ። ስለዚህ ተሞክሮዋ በጣም አበረታቶኛል።

ኤፍ. ጂ.፣ ስዊዘርላንድ