በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወደ ላይ ተመሙ!

ወደ ላይ ተመሙ!

 ወደ ላይ ተመሙ!

በቀዝቃዛው የመከር ወቅት አመሻሹ ላይ ነው። እረጭ ብሎ የነበረው አካባቢ በኅብረት የሚጓዙ ዝይዎች ባሰሙት ጫጫታ ደፈረሰ። በድንገትም 20 የሚያክሉት ከበላዬ በትልቁ የV-ቅርጽ ሠርተው በጣም በሚያምር ሁኔታ ክንፎቻቸውን እያማቱ ሲበሩ ተመለከትሁ። ከመካከላቸው አንደኛው ማራኪ በሆነ መንገድ ወደ ግራ ገንጠል ብሎ ከታጠፈ በኋላ ከቡድኑ ኋላ መብረር ጀመረ። አስደናቂው ትርዒት ትኩረቴን ሳበው። ዝይዎች የV-ቅርጽ ሠርተው የሚበሩት ለምንድን ነው? ወዴትስ ነው የሚሄዱት?

ዝይ ከውኃ ላይ ወፎች አንዱ ሲሆን ከዳክዬ ጋር በጣም ይመሳሰላል። በዓለም ዙሪያ 40 የሚደርሱ ዝርያዎች ሲኖሩት በአብዛኛው በእስያ፣ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል በጣም ታዋቂ የሆነው ዝርያ ረጅም ጥቁር አንገት ያለውና በጉሮሮው ዙሪያ ነጭ ምልክት ያለበት የካናዳው ዝይ ነው። ከዚህ የዝይ ዝርያ ውስጥ ትልቁ እስከ 8 ኪሎ ግራም የሚመዝን ሲሆን የክንፉ ርዝመት ከጫፍ እስከ ጫፍ 2 ሜትር ይደርሳል። የካናዳው ዝይ የበጋውን ጊዜ የሚያሳልፈው ወደ ሰሜን ርቆ በመሄድ በአላስካ ግዛትና በሰሜን ካናዳ ነው፤ ከዚያም የክረምቱን ጊዜ በሜክሲኮ ለማሳለፍ ወደ ደቡብ ይፈልሳል።

ዝይዎች የሚፈልሱበት ወቅት ለሕይወታቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ወደ ሰሜን ቶሎ ቢመለሱ ውኃው ገና በረዶ ስለሚሆን የሚመገቧቸውን ዕፅዋት ማግኘት አይችሉም። ስለዚህም የካናዳ ዝይዎች ወደ ሰሜን የሚመለሱት  አየሩ እየሞቀ ሲሄድ ነው። ዝይዎች መስፈሪያ ቦታቸው ሲደርሱ ጥንድ ጥንድ በመሆን ለመራባት የሚያመቻቸውን አካባቢ መርጠው ጎጆ ይቀልሳሉ።

ዝይዎች የV-ቅርጽ ሠርተው መብረራቸው እርስ በርስ እንዲተያዩ ከማድረጉም በተጨማሪ ከፊት ያለው ወፍ አቅጣጫውን፣ ፍጥነቱን ወይም ከፍታውን ሲቀይር ወዲያው ለማየትና እርሱን ለመከተል ያስችላቸዋል። በተጨማሪም አንዳንድ ምሑራን እንደሚያምኑት ከሆነ ከፊት ለፊት የሚበሩት ወፎች አየሩን እየሰነጠቁ መሄዳቸው ከኋላ ላሉት በረራቸውን ቀላል ያደርግላቸዋል። ያም ሆነ ይህ ፍልሰቱ ብዙ ቤተሰቦችን የሚያካትት ሲሆን ትላልቅ የሆኑት እየተፈራረቁ የመሪነቱን ቦታ ይይዛሉ።

አብዛኛውን ጊዜ የካናዳ ዝይ ጎጆውን ለመቀየስ በየዓመቱ አንድ ዓይነት አካባቢ ይመርጣል። ጎጆውንም ለመሥራት እንደ ጭራሮ፣ ሣር እና የእንጨት ሽበትን የመሳሰሉ ቀላል ነገሮችን ይጠቀማል። ዝይ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ የሚኖረው ከአንድ ተጓዳኝ ጋር ብቻ ነው። ከጥንዶቹ አንዱ በሞት ቢለይ በሕይወት የቀረው ዝይ ሌላ ተጓዳኝ ይይዛል። አብዛኛውን ጊዜ ግን ብቻውን ይኖራል።

ሴቷ ዝይ ከአራት እስከ ስምንት እንቁላሎች ትጥልና በ28 ቀናት ውስጥ ትፈለፍላቸዋለች። የዝይ ወላጆች የማይበገሩ ተከላካዮች ናቸው። በእነርሱ ወይም በጫጩቶቻቸው ላይ ጥቃት ከተሰነዘረባቸው ጥንዶቹ በጣም ይቆጣሉ። ወደ እነርሱ የቀረበን ጠላት በክንፎቻቸው ኃይለኛ ጥፊ ያቀምሱታል።

የዝይ ጫጩቶች ድምፅ ማሰማት የሚጀምሩት ገና እንቁላል ውስጥ እያሉ ነው። የሚያሰሙት ድምፅ እንደተደሰቱ ወይም ችግር እንደገጠማቸው የሚገልጽ ነው። ትልልቆቹ ዝይዎች እርስ በርስም ሆነ ከጫጩቶቻቸው ጋር የተለያዩ ድምፆችን በማውጣት ይግባባሉ። ተመራማሪዎች የካናዳ ዝይዎች የሚግባቡባቸውን 13 የሚያህሉ ድምፆች መለየት ችለዋል።

እውነትም ዝይዎች በተፈጥሯቸው “እጅግ ጠቢባን” መሆናቸውን ያረጋግጣሉ። (ምሳሌ 30:​24) እርግጥ ነው፣ ዝይዎችን በተመለከተ ምስጋና የሚገባው አእዋፍን ጨምሮ ሁሉን የፈጠረው ይሖዋ አምላክ ነው።​—⁠መዝሙር 104:​24

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ይህን ያውቁ ኖሯል?

● ወላጆቹ ዝይዎች ጫጩቶቹ እንደተፈለፈሉ ልጆቻቸውን ይዘው ለዘለቄታው ጎጆውን ለቀው ይሄዳሉ። አብዛኛውን ጊዜ ቤተሰቦች አይነጣጠሉም።

● ጥቁር ራስ ያላቸው ዝይዎች 8, 900 ሜትር ከፍታ ያለውን የኤቨረስት ተራራ አቋርጠው እንደሚፈልሱ ይነገራል።

● አንዳንድ የዝይ ዝርያዎች 1, 600 ኪሎ ሜትር ያለ እረፍት መብረር ይችላሉ።

● የV-ቅርጽ ሠርተው የሚበሩ ዝይዎች በተመሳሳይ ፍጥነት ብቻውን ከሚበር ዝይ ጋር ሲነጻጸሩ፣ በኅብረት የሚበሩት ክንፋቸውን ቶሎ ቶሎ ስለማያርገበግቡ የልባቸው ምት አነስተኛ ይሆናል።

[ምንጭ]

ከላይ በስተ ግራ:- U.S. Fish & Wildlife Service, Washington, D.C./Duane C. Anderson

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

የሚበሩ ዝይዎች:- © Tom Brakefield/CORBIS