በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሀብታሞችና በድሆች መካከል ያለው ሰፊ የኑሮ ልዩነት

በሀብታሞችና በድሆች መካከል ያለው ሰፊ የኑሮ ልዩነት

በሀብታሞችና በድሆች መካከል ያለው ሰፊ የኑሮ ልዩነት

የትኛውም ዓይነት ስያሜ ይሰጣቸው፣ በኢንዱስትሪውና በኢኮኖሚው መስክ በልጽገው ከፍተኛ የእድገት ደረጃ ላይ የደረሱ አገሮች የተደላደለ ሕይወት ይመራሉ። ከዚህ በተቃራኒ በአነስተኛ የኢንዱስትሪ እድገት ሳቢያ ኢኮኖሚያቸው ያልዳበረ አገሮች ደግሞ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ስለሆነም እነዚህ ሁለት ቡድኖች በተለያዩ ዓለማት እንደሚኖሩ ያህል ነው።

እውነት ነው፣ እነዚህ የኑሮ ልዩነቶች በአንድ አገር ውስጥም ሊገኙ ይችላሉ። ቀደም ባለው ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱትን በአንጻራዊ መልኩ ባለጸጋ የሆኑ አገሮችን አስብ። በእነዚህ አገሮች ውስጥ ሀብታሞችም ሆኑ ድሆች ይኖራሉ። ለአብነት ያህል በዩናይትድ ስቴትስ ከአገሪቱ ጠቅላላ ገቢ 30 በመቶ የሚሆነው 10 በመቶ ብቻ ወደሆኑት ሀብታም ቤተሰቦች ኪስ የሚገባ ሲሆን ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው 20 በመቶ የሆኑት ቤተሰቦች ደግሞ ከጠቅላላው ገቢ 5 በመቶ ያህሉን ብቻ ያገኛሉ። አንተ በምትኖርበት አገር መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ከሆነ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ አሊያም ተመሳሳይ ነገር ይኖር ይሆናል። ሆኖም በርካታ ዜጎቻቸው በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ መንግሥታት እንኳ በሀብታሞችና በድሆች መካከል የሚታየውን የኢኮኖሚ ልዩነት ማስተካከል አልቻሉም።

የትኛውም ቢሆን እንከን የለሽ አይደለም

የትኛውም ዓለም ቢሆን እኔ ያለሁበት ሁኔታ ሙሉ በሙሉ የተሻለ ነው ብሎ አፉን ሞልቶ መናገር አይችልም። በድሃ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ያሉባቸውን ግልጽ ችግሮች እስቲ ተመልከት። የሕክምና ተቋማት ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው። በዚሁ ገጽ ላይ ባለው ሣጥን ውስጥ በተዘረዘሩት 9 ሀብታም አገሮች 1 ሐኪም ከ242 እስከ 539 ለሚደርሱ ዜጎች ይደርሳል፤ በአንጻሩ ግን በ18ቱ ድሃ አገሮች ውስጥ አንድ ሐኪም የሚደርሰው ከ3,707 እስከ 49,118 ለሚሆኑ ዜጎች ነው። በሀብታም አገሮች ውስጥ የሰዎች አማካይ ዕድሜ 73 እና ከዚያ በላይ ሆኖ እያለ በድሃ አገሮች ውስጥ ከ50 በታች የሆነበትን ምክንያት መረዳት አያዳግትም።

የኢኮኖሚ አቅማቸው ውስን በሆኑ አገራት ውስጥ የመማር እድልም እጅግ ጠባብ ነው፤ አብዛኛውን ጊዜ ልጆችን ለዕድሜ ልክ ድህነት የሚዳርጋቸው ይህ ነው። ማንበብና መጻፍ የሚችሉ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ መሆን ምን ያህል የትምህርት እጥረት እንዳለ ያመላክታል። በሌላ በኩል ከዘጠኙ ሀብታም አገራት መካከል ሰባቱ 100 በመቶ (ሁለቱ ደግሞ 96ና 97 በመቶ) የተማረ የሰው ኃይል ሲኖራቸው በ18ቱ ድሃ አገሮች ግን ቁጥሩ ከፍተኛው 81 ዝቅተኛው 16 በመቶ ነው። ከእነዚህ አገሮች ውስጥ አሥሩ ከ50 በመቶ በታች ናቸው።

በበለጸጉት አገራት የሚኖሩ ሰዎችም ቢሆኑ የተወሰኑ ችግሮች አሉባቸው። በድሃ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በምግብ እጦት ሲሰቃዩ በበለጸጉት አገሮች ውስጥ ያሉት ደግሞ ከልክ በላይ መመገብ በሚያመጣው ችግር ሳቢያ ሕይወታቸውን ያጣሉ። ፉድ ፋይት የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው “በአሁኑ ጊዜ ከምግብ ጋር በተያያዘ ያለው ትልቁ ችግር የተመጣጠነ ምግብ እጦት ሳይሆን ከልክ በላይ መብላትና መጠጣት ነው።” ዚ አትላንቲክ መንዝሊ የተሰኘው መጽሔትም እንዲሁ እንደሚከተለው ሲል ዘግቧል:- “ዘጠኝ ሚሊዮን የሚያህሉ አሜሪካውያን ‘ከልክ ባለፈ ውፍረት ሳቢያ ለአደጋ ተጋልጠዋል’ ማለትም ከተገቢው ክብደት በላይ 45 ኪሎ ግራም ወይም የበለጠ የጨመሩ ሲሆን በአገሪቱ ውስጥ ከዚህ ችግር ጋር በተያያዘ በዓመት 300,000 የሚያህሉ ሰዎች ያለ ዕድሜያቸው ይቀጫሉ።” ይኸው መጽሔት በመቀጠል “ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከመጠን በላይ መወፈር፣ ከረሃብና ከሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ይበልጥ የዓለማችን አሳሳቢ የጤና ችግር ሊሆን ይችላል” ሲል አስተያየቱን ሰንዝሯል። *

ባለጸጋ በሆኑ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ እንዳላቸው አሌ የሚባል አይደለም፤ ሆኖም እነዚህ ሰዎች ትልቅ ግምት የሚሰጡት እርስ በርስ ላላቸው ግንኙነት ሳይሆን ለቁሳዊ ሀብታቸው ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ቁሳዊ ሀብት የማካበት ጉዳይን እንጂ ሕይወትን አይደለም። በዚህም ምክንያት አንድን ሰው ባለው እውቀት፣ ጥበብ፣ ችሎታና ጥሩ ባሕርይ ሳይሆን በያዘው የሥራ ዓይነት፣ በሚከፈለው ደሞዝ መጠን ወይም ባካበተው ንብረት መለካት ይቀናቸዋል።

በጀርመን የሚታተመው ፎከስ የተባለ ሳምንታዊ መጽሔት ደስታ የሚያስገኘው ቀላል ሕይወት መምራት መሆኑን ጠበቅ አድርጎ ሲገልጽ “ትንሽ ብትቀንስ ምን ይመስልሃል?” የሚል ርዕስ ያለው ጽሑፍ አውጥቶ ነበር። ጽሑፉ እንደሚከተለው ይላል:- “በርካታ የምዕራቡ ዓለም ዜጎች ከፍተኛ የብልጽግና ደረጃ ላይ ቢደርሱም ከዓመታት በፊት የነበራቸው ደስታ አሁን አይታይባቸውም። . . . ቁሳዊ ሀብት የሚያሳድድ ማንኛውም ሰው መጨረሻ ላይ ደስታ ማጣቱ የማይቀር ነው።”

ሁለቱን ዓለማት በሀብት ማመጣጠን ይቻል ይሆን?

አዎን፣ እውነታው እንደሚያሳየው የሀብታሞቹም ሆነ የድሆቹ ዓለም የራሱ የሆነ መልካም ጎን ቢኖረውም የዚያኑ ያህል መጥፎ ገጽታም አለው። በድሆቹ ዓለም ያለው ድህነት ከመጠን ያለፈ ሲሆን በሀብታሞቹ ዓለም የሚታየው ቅምጥልነት ደግሞ ከሚገባው በላይ ነው። እነዚህ ሁለት ዓለማት አንዳቸው ከሌላው መማር ቢችሉ ኖሮ ምን ያህል በተጠቀሙ ነበር! ይሁንና ሁለቱን ዓለማት በሀብት ማመጣጠን ይቻላል ብሎ ማሰብ ከተጨባጭ እውነታ ማፈንገጥ ይሆን?

እንደዚያ ማድረጉ ተገቢ ቢሆንም ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ከታየ በሰው ልጆች ችሎታ በጭራሽ ሊሞከር እንደማይችል ይሰማህ ይሆናል። የተሰማህ ስሜት እውነታነት እንዳለው ታሪክ ማረጋገጫ ይሆንሃል። ሆኖም ሁኔታው ፈጽሞ ተስፋ ቢስ አይደለም። የችግሩን ዓይነተኛ መፍትሔ ምናልባት ዘንግተኸው ይሆናል። መፍትሔው ምን ይሆን?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 የኅዳር 8, 2004 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ከገጽ 3-12 ያለውን ተመልከት።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከመጠን በላይ መወፈር፣ ከረሃብና ከሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ይበልጥ የዓለማችን አሳሳቢ የጤና ችግር ሊሆን ይችላል።”—ዚ አትላንቲክ መንዝሊ

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ግራፍ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

አገሮቹ የተዘረዘሩት በእንግሊዝኛ ፊደል ቅደም ተከተል ነው

እጅግ ሀብታም የሆኑ ዘጠኝ አገሮች

የወንዶች አማካይ የሕይወት ዘመን (ዕድሜ) ማንበብና መጻፍ የሚችሉ (%)

ቤልጅየም

75.1 100

ካናዳ

76.4 96.6

ዴንማርክ

74.9 100

አይስላንድ

78.4 100

ጃፓን

78.4 100

ሉክሰምበርግ

74.9 100

ኖርዌይ

76.5 100

ስዊዘርላንድ

77.7 100

ዩናይትድ ስቴትስ

74.4 95.5

በጣም ድሃ የሆኑ አሥራ ስምንት አገሮች

የወንዶች አማካይ የሕይወት ዘመን (ዕድሜ) ማንበብና መጻፍ የሚችሉ (%)

ቤኒን

50.4 37.5

ቡርኪና ፋሶ

43 23

ቡሩንዲ

42.5 48.1

ቻድ

47 53.6

ኮንጎ ሪፑብሊክ

49 80.7

ኢትዮጵያ

47.3 38.7

ጊኒ ቢሳው

45.1 36.8

ማዳጋስካር

53.8 80.2

ማላዊ

37.6 60.3

ማሊ

44.7 40.3

ሞዛምቢክ

38.9 43.8

ኒጀር

42.3 15.7

ናይጄርያ

50.9 64.1

ሩዋንዳ

45.3 67

ሴራሊዮን

40.3 36.3

ታንዛንያ

43.3 75.2

የመን

59.2 46.4

ዛምቢያ

35.3 78

[ምንጭ]

ምንጭ:- 2005 ብሪታኒካ ቡክ ኦቭ ዘ ይር

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

© Mark Henley/Panos Pictures