በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የገበሬዎች አለኝታ የሆኑት ፍየሎች በሴርታው

የገበሬዎች አለኝታ የሆኑት ፍየሎች በሴርታው

 የገበሬዎች አለኝታ የሆኑት ፍየሎች በሴርታው

በብራዚል የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

በብራዚል ሰሜን ምሥራቃዊ ክፍል 1,100,000 ካሬ ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው የሴርታው * ከፊል በረሃማ አካባቢ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ፍየሎች ይኖራሉ። ለዘጠኝ ወራት በሚዘልቀው የበጋው ወቅት ደመና የሚባል ነገር በማይታይበት በዚህ አካባቢ ወበቁ ጨርቅ የሚያስጥል ሲሆን መሬቱም በፀሐይ ክርር ብሎ ከመድረቁ የተነሳ እንደ ዓለት ይደድራል። ወንዞች ይደርቃሉ፣ ዛፎች ቅጠላቸው ረግፎ መለመላቸው ይቀራል፤ በአካባቢው የሚነፍሰው ደረቅ ነፋስም እንደ እሳት ይጋረፋል። የርቢ እንስሳት የሚላስ የሚቀመስ ሣር ቅጠል ፍለጋ ወዲያና ወዲህ ሲባዝኑ ይውላሉ።

የብራዚል ፍየሎች ግን የአየሩ ሁኔታ ደረቅ መሆኑ ያን ያህል የሚያስቸግራቸው አይመስልም። ድርቁ በሚከፋበት ወቅት የከብትና የበግ መንጋዎች ቁጥራቸው እየቀነሰ ሲሄድ የፍየሎቹ ግን ይጨምራል። እነዚህ ፍየሎች ድርቁን መቋቋም የሚችሉት እንዴት ነው?

ለችግር ጊዜ የተፈጠረ አፍ

በሴርታው የሚኖሩ በርካታ ሰዎች እንደሚሉት ከሆነ ፍየሎች ቦት ጫማን፣ ኮርቻንና ልብስን ጨምሮ ማንኛውንም ነገር ይበላሉ። በሰሜን ምሥራቅ ብራዚል፣ ሶብራል ከተማ ውስጥ በሚገኘው ብሔራዊ የፍየሎች ምርምር ማዕከል የሚሠሩት ፕሮፌሰር ዠዋው አምብሮሲዮ ፍየሎች በቀላሉ የሚፈጩ የማይመስሉ ከ60 የሚበልጡ ዕጽዋትን ሥራሥር፣ የደረቁ ቅጠሎችና ቅርፊት እየተመገቡ በሕይወት መቆየት እንደሚችሉ ተናግረዋል። እንደ ቀንድ ከብት ያሉት ሌሎች የርቢ እንስሳት ግን ከሣር ውጪ ምንም ነገር አይበሉም ለማለት ይቻላል።

ፍየሎች የተገኘውን ሳያማርጡ መብላታቸው የጠቀማቸው ሲሆን የአፋቸው አፈጣጠርም ቢሆን ለዚህ የተመቸ ነው። አምብሮሲዮ ከብቶች ምግባቸውን ወደ አፋቸው የሚያስገቡት በምላሳቸው እርዳታ በመሆኑ አንድን ቅጠል ወይም የተክል ቅርፊት ነጥለው መብላት እንደማይችሉ ይናገራሉ። ፍየሎች ግን አነስተኛ መጠን ያለውን አፋቸውን፣ እንደፈለጉ የሚያንቀሳቅሱትን ከንፈራቸውንና የሰላ ጥርሳቸውን በመጠቀም በንጥረ ነገሮች የበለጸገውን የተክሎች ክፍል መቀነጣጠብ ይችላሉ። ይህ ምግብ እንደልብ በማይገኝበት አካባቢ አድኖ ለመብላት ያላቸው ችሎታ የአትክልት ፀር የሚል ስም አትርፎላቸዋል። አምብሮሲዮ ግን እንዲህ ይላሉ:- “ለዚህ ተወቃሹ ፍየሎቹን በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንዲኖሩ ያስገደዳቸው ሰው ነው። ፍየሎቹ በሕይወት ለመቆየት ጥረት እያደረጉ ነው።”

ፍየል ማርባት ያዋጣል

የሴርታው ገበሬዎች ለሕይወት የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት ድርቅን መቋቋም የሚችሉት የአካባቢው ፍየሎች ትልቅ እገዛ ያደርጋሉ ቢባል ማጋነን አይሆንም። ብዙ ቤተሰቦች ፕሮቲን በዋነኝነት የሚያገኙት ከፍየሎች ነው። የበሬ ሥጋ ዋጋው ሊወደድ ስለሚችል የተጠበሰ ወይም የተቀቀለ የፍየል ሥጋ እንዲሁም ቡሻዳ (በደቃቁ የተከተፈ ጨጓራና ሩዝ የተጠቀጠቀበት የፍየል አንጀት) በአካባቢው  የተለመዱ ምግቦች ናቸው። ከዚህም በላይ የፍየል ሌጦ ለቆዳ ፋብሪካዎች ተሽጦ ተጨማሪ ገቢ ያስገኛል። በመሆኑም በችግር ጊዜ ፍየሎችን በቀላሉ ሸጦ ለመድኃኒት ወይም ለሌሎች አስፈላጊ ነገሮች መግዣ የሚሆን ገንዘብ ማግኘት ይቻላል።

ፍየሎች የሚመረጡበት ሌላው ምክንያት ደግሞ ላይ ታች ብለው ራሳቸውን መመገብ የሚችሉ በመሆኑ ነው። ቀን ላይ ትናንሽ መንጎች ካቲንጋ ተብለው በሚጠሩት ያልታጠሩ እሾሃማ ቁጥቋጦዎች መሃል ሲግጡ ይውላሉ። ሲመሽ ፍየሎቹ የጌታቸውን ድምፅ ለይተው ስለሚያውቁ ሲጠራቸው ወደየበረታቸው ይመለሳሉ። አብዛኛውን ጊዜ ገበሬው የመራቢያቸው ወቅት እስኪደርስ ድረስ ለፍየሎቹ እምብዛም ትኩረት አይሰጥም። በመራቢያቸው ወራት ግን ለእርድ የሚሆኑትን ፍየሎች ይመርጣል፣ የታመሙትን ያክማል እንዲሁም በግልገሎቹ ላይ ባለቤታቸውን ለመለየት የሚያስችል ምልክት ያደርግባቸዋል። ፍየል ማርባት በጣም ቀላል በመሆኑ የከተማ ነዋሪዎች እንኳን በጓሯቸው ጥቂት ፍየሎች ያረባሉ። ወይም ደግሞ የአካባቢው ሕግ የሚከለክል ቢሆንም በከተማው ውስጥ እየተዘዋወሩ እንዲመገቡ ይለቋቸዋል። በዚህም የተነሳ በከተማይቱ አደባባይ ሣር ቅጠል የምትቃርም ፍየል መመልከት የተለመደ ነው።

ለብዙ መቶ ዓመታት እንደታየው በተለይ በአነስተኛ ግብርና ለሚተዳደሩ ገበሬዎች ፍየል ማርባት ያዋጣል። ስምንት ፍየሎች ለማርባት የሚያስፈልገው ቦታና ጉልበት አንዲት ላም ለማርባት ከሚጠይቀው አይበልጥም። ከዚህም በላይ አንድ ገበሬ አምስት ላሞች ቢኖሩትና አንዷ ብትሞትበት ከመንጋው ውስጥ 20 በመቶ የሚሆነውን አጣ ማለት ነው። ይሁን እንጂ አምስት ላሞች ለማርባት በሚያስፈልገው ቦታና ጉልበት 40 ፍየሎችን ማርባት ይችላል። ስለዚህ በአምስት ላሞች ፋንታ አርባ ፍየሎች ያሉት ገበሬ አንዷ ብትሞትበት ከመንጋው ውስጥ የሚያጣው 2.5 በመቶውን ብቻ ይሆናል። ከዚህ አኳያ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የብራዚል ቤተሰቦች ፍየሎችን በድርቅ ሳቢያ አዝመራው ቢበላሽ ለችግር ቀን መውጫ እንደሚሆኑ አድርገው ቢመለከቷቸው አያስገርምም።

ታታሪነትን ያበረታታሉ

በባሂያ ግዛት በሺዎች የሚቆጠሩ ፍየሎችን ያቀፉ ትላልቅ መንጋዎች ይገኛሉ። ከባሂያ ግዛት ዋና ከተማ 800 ኪሎ ሜትር ያህል ወደ መሃል አገር ገባ ብላ በምትገኘው በኡኣ የፍየሎቹ ቁጥር ከነዋሪዎቹ በአምስት እጥፍ ይበልጣል። መላው ኅብረተሰብ ለማለት ይቻላል የሚተዳደረው ፍየሎችን በማርባት ወይም ከዚያ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን በመሥራት ነው። እንዲያውም የአካባቢው ነዋሪዎች “በኡኣ ሰዎች ፍየል ያረባሉ ከማለት ፍየሎች ሰዎችን ይንከባከባሉ ማለት ይቀላል” እያሉ ይቀልዳሉ።

የመራቢያው ወራት ከጀመረ ከአምስት ወራት ገደማ በኋላ ማለትም በግንቦት አካባቢ ግልገሎች መወለድ ይጀምራሉ። እረኞቹ ከሌሊቱ አሥር ሰዓት ጀምረው እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ድረስ ፍየሎችን ማሰባሰብ፣ ውኃ ማጠጣት እንዲሁም የጠፉና በአደገኛ ሁኔታ ላይ ያሉ ግልገሎችን መርዳት የመሳሰሉ ሥራዎችን በትጋት ይሠራሉ። በሥራቸው የተካኑት እነዚህ እረኞች አዲስ የሚወለዱት ግልገሎች ከልክ በላይ ጠብተው ለሞት እንዳይዳረጉ በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ እንስት ፍየሎችን እያሰሩ ያልባሉ። ከዚህም በላይ ጉዳት የደረሰባቸውን እንዲሁም በቆዳ ላይ ትናንሽ ቀዳዳዎችን በመፍጠር የሌጦው ዋጋ እንዲቀንስ በሚያደርገው ቦትፍላይ የተባለ በሽታ የተጠቁትን ፍየሎች ያክማሉ።

 እረኞቹ ፍየሎቹን የሚንከባከቡት በፍቅር ተነሳስተው ቢሆንም ምንም ጥቅም አያገኙም ማለት ግን አይደለም። ታታሪ እረኞች በኡኣ እና በአካባቢው ባሉ ገጠሮች ከጥንት ጀምሮ ይሠራበት በነበረው ኳርቴሳውን (አንድ አራተኛ) ተብሎ የሚጠራ የክፍያ ዘዴ አማካኝነት የድካማቸውን ዋጋ ያገኛሉ። በመራቢያው ወራት ከሚወለዱት የፍየል ግልገሎች ከአራቱ አንዱ አንዳንዴም የመንጋው ባለቤት ለጋስ ከሆነ ከሦስቱ አንዱ ይሰጣቸዋል። ለእያንዳንዱ ግልገል ቁጥር ይሰጠውና ቁጥሩ የተጻፈበት ወረቀት በኩባያ ውስጥ ተደርጎ ዕጣ ይወጣል። ዕጣው በአንካሳም ሆነ በጤነኛ፣ በከሲታም ሆነ በሰባ ግልገል ላይ ሊወጣ ስለሚችል እረኞቹ መንጋውን የሚንከባከቡት እንደራሳቸው ንብረት አድርገው ነው።

የአካባቢውን ዝርያዎች ምርታማነት ማሳደግ

የብራዚል ፍየሎች በ15ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ ከአውሮፓ የፈለሱት ሰፋሪዎች ካመጧቸው ዝርያዎች የተገኙ ናቸው። ይሁን እንጂ በአጠቃላይ ሲታዩ በክብደትም ሆነ በሚሰጡት የወተት መጠን ከአውሮፓውያን አቻዎቻቸው ያንሳሉ።

ለምሳሌ ያህል ካኒንዳ ተብላ የምትጠራው የብራዚል ዝርያ በቀን ከአንድ ሊትር ያነሰ ወተት የምትሰጥ ሲሆን በአውሮፓ የምትገኘውና የቅርብ ዝርያዋ የሆነችው የብሪታንያዋ አልፓይን ፍየል ግን በቀን ከሦስት ሊትር ተኩል በላይ ወተት ትሰጣለች። ለብዙ አሥርተ ዓመታት በርካታ ገበሬዎችና የእርሻ ባለሞያዎች ድርቅን መቋቋም የሚችሉትን የአካባቢውን ዝርያዎች ምርታማ ከሆኑት የውጪ ዝርያዎች ጋር ለማዳቀል ሲጥሩ ቆይተዋል። ምኞታቸው ከተሳካ በብዙዎች ዘንድ “የድሃ ላም” በመባል የሚታወቁት ፍየሎች ለሴርታው ገበሬዎች ትልቅ የገቢ ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ።

የአካባቢውን ፍየሎች ከውጪ ዝርያዎች ጋር ማዳቀል የእንስሳቱን ክብደትና የሚሰጡትን የወተት መጠን ለማሳደግ የሚያስችል አቋራጭ ዘዴ ነው። በብራዚል ሰሜን ምሥራቃዊ ክፍል በምትገኘው የፓራይባ ግዛት የሚገኝ አንድ የእርሻ ምርምር ተቋም የአካባቢውን ፍየሎች ከጣሊያን፣ ከጀርመንና ከእንግሊዝ ዝርያዎች ጋር በማዳቀል አመርቂ ውጤት አግኝቷል። በዚህም የተነሳ ድርቅን መቋቋም የሚችሉና ብዙ ወተት የሚሰጡ ትላልቅ ፍየሎች ለማርባት ተችሏል። ከዚያ በፊት በቀን ከአንድ ሊትር ያነሰ ወተት ብቻ ይሰጡ የነበሩት የፍየል ዝርያዎች አሁን ከሁለት ተኩል እስከ ሦስት ተኩል ሊትር ወተት ይሰጣሉ።

በሶብራል የሚገኘው የምርምር ማዕከልም ተግባራዊ ለማድረግ ብዙ ወጪ የማይጠይቅና ከላይ ከተጠቀሰው የማይተናነስ ውጤት ያለው ዘዴ አግኝቷል። ተመራማሪዎቹ ፍየሎች የተወሰኑ ቅጠላ ቅጠሎችን መርጠው እንደሚመገቡ አስተዋሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ቅጠሎች የሚገኙት ዛፎቹ እድገታቸውን አቁመው ቅጠላቸውን በሚያረግፉበት ወቅት ብቻ ነበር። እናም እነዚህ ቅጠሎች በብዛት እንዲያድጉ በአንዳንድ ዛፎች ላይ ከተወሰነ ከፍታ በላይ ያሉት ቅርንጫፎች በሙሉ እንዲገረዙ ተደረገ። በዚህም የተነሳ ዛፎቹ ፍየሎቹ ሊደርሱበት በሚችሉበት ከፍታ ላይ ቅርንጫፎች አወጡ። ይህ ምን ውጤት አስገኘ? በእነዚህ አካባቢዎች የሚሰማሩት ፍየሎች ክብደታቸው በአራት እጥፍ ሊጨምር ችሏል።

እነዚህ እድገቶች ቢኖሩም ትናንሽ መንጋዎች ያሏቸው ገበሬዎች ሳይንሳዊ ምርምር መፍትሔ ሊያስገኝለት የማይችል አንድ ሌላ ችግር አለባቸው። አንድ ገበሬ ይህን ችግር ሲናገር “ሰዎች ከሚያረቧቸው ፍየሎች ጋር በጣም ይላመዱና ልክ እንደ ቤት እንስሳት ይመለከቷቸዋል። ስለዚህ እነርሱን ማረድ ፈተና ይሆንባቸዋል” ብሏል። የፍየሎቹ ባለቤቶች ተንከባክበው ካሳደጓቸው ፍየሎች መለየት በጣም ይከብዳቸዋል። ለፍየሎቹ እድሜ መርዘም አስተዋጽኦ ያደረገው ሌላው ምክንያት ይህ ሳይሆን ይቀራል?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 የሰሜን አፍሪካን በረሃና የሣር ምድር ስላስታወሳቸው ለቦታው ዴዘርታው ወይም ትልቅ በረሃ የሚል መጠሪያ የሰጡት የፖርቱጋል ሰፋሪዎች ሳይሆኑ አይቀሩም።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ስለ ፍየል ወተት የሚናፈሰው ወሬና ሐቁ ምን ይመስላል?

ብዙዎች የፍየል ወተት ከተጠጣ በኋላ በቀላሉ እንደማይፈጭ ይናገራሉ፤ ሌሎች ደግሞ ይከረፋል ይላሉ። ይሁን እንጂ ይህን የተሳሳተ ወሬ አትመን። የላም ወተት አልፈጭ ካለህ ሐኪምህ በአማራጭ እንድትጠጣ የሚመክርህ የፍየል ወተትን ነው። በፕሮቲንና በቅባት የበለጸገ ቢሆንም በውስጡ ያሉት ንጥረ ነገሮች መጠናቸው ትናንሽ ከመሆኑም በላይ በቀላሉ የሚፈጩ ናቸው። ስለ ጠረኑስ ምን ለማለት ይቻላል?

ሚያስገርመው የፍየል ወተት ጠረን አልባ ነው። ወተቱ የሚሰነፍጥ ወይም የሚከረፋ ሽታ ካለው ፍየሏ ከአውራ ፍየል ጋር የነበረች በመሆኗ ወይም በንጽሕና ባለመታለቧ የተነሳ ሊሆን ይችላል። ከአውራው ፍየል ቀንድ በስተ ጀርባ የሚገኙት ዕጢዎች እንስቷን ፍየል የሚስብ ሆርሞን ያመነጫሉ። ይህ ሆርሞን አውራው ፍየል የነካው ማንኛውም ነገር መጥፎ ጠረን እንዲኖረው ያደርጋል።

[ምንጭ]

CNPC–Centro Nacional de Pesquisa de Caprinos (Sobral, CE, Brasil)

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

“ሴርታው”

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፍየሎች አመቺ ቅርጽ ያለውን አፋቸውን በመጠቀም ከዕጽዋት ላይ ምርጥ ምርጡን ክፍል እየመረጡ መቀነጣጠብ ይችላሉ

[ምንጭ]

Dr. João Ambrósio–EMBRAPA (CNPC)

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ካርታ:- Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.; ፍየሎች:- CNPC–Centro Nacional de Pesquisa de Caprinos (Sobral, CE, Brasil)