በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ነገሮች አልሆን ሲሉኝ የሚሰማኝን የዋጋ ቢስነት ስሜት መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

ነገሮች አልሆን ሲሉኝ የሚሰማኝን የዋጋ ቢስነት ስሜት መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

 የወጣቶች ጥያቄ . . .

ነገሮች አልሆን ሲሉኝ የሚሰማኝን የዋጋ ቢስነት ስሜት መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

“የፈተና ውጤት ካርዴን ስቀበል ከዚህ ቀደም በወደቅሁባቸው አራት የትምህርት ዓይነቶች አሁንም ውጤት እንዳላመጣሁ ተመለከትሁ። ለማለፍ ጥረት አድርጌ ነበር፤ ግን አሁንም ሳይሳካልኝ ቀረ።”—የ15 ዓመቱ ሎረን

“ነገሮች አልሆን ሲሉኝ የሚሰማኝን የዋጋ ቢስነት ስሜት መቋቋም ትግል ይጠይቃል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመኝ አፍራሽ ነገሮችን ማሰብ ይቀናኛል።”የ19 ዓመቷ ጄሲካ

ነገሮች እንደምንፈልገው ላይሆኑ እንደሚችሉ ማሰቡም እንኳን ደስ የማይል ቢሆንም አልፎ አልፎ ግን ሁላችንም እንደዚህ ያለ ሁኔታ ያጋጥመናል። ፈተና ስትወድቅ፣ አንድ የሚያሳፍር ነገር ሲያጋጥምህ፣ የምታስብለትን ሰው እንዳሳዘንከው ሲሰማህ ወይም በሥነ ምግባር ረገድ ከባድ ስህተት በመፈጸምህ ምክንያት ቅስምህ ይሰበር ይሆናል።

እርግጥ ነው፣ ሰዎች ስንባል ሁላችንም ስህተት እንሠራለን። መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል” ይላል። (ሮሜ 3:23) አንዳንዶቻችን ግን ከደረሰብን ውድቀት ማገገም አስቸጋሪ ይሆንብናል። ጄሰን የተባለ ወጣት ሁኔታውን እንዲህ በማለት ይገልጸዋል:- “ራሴን በጣም እኮንናለሁ። ስህተት ብሠራ ሰዎች ይስቁብኝ ይሆናል፤ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ነገሩን ይረሱታል። እኔ ግን ጉዳዩን ከመርሳት ይልቅ እየመላለስኩ አስበዋለሁ።”

አይብዛ እንጂ ስለሠራነው ስህተት ማሰቡ መጥፎ ላይሆን ይችላል። በተለይ ደግሞ ስለ ጉዳዩ ማሰባችን ለመለወጥ የሚገፋፋን ከሆነ እንዲህ ማድረጋችን ጥሩ ነው። ይሁን እንጂ ሁልጊዜ ስህተታችንን እያሰብን ራሳችንን መውቀስ ጎጂ ከመሆኑም በላይ ያሰብነው ነገር ላይ እንዳንደርስ እንቅፋት ይሆንብናል። ምሳሌ 12:25 (የ1980 ትርጉም) “በአሳብ መጨነቅ ሐዘንን ያመጣብሃል” ይላል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው አፍሮዲጡ የተባለ ሰው ያጋጠመውን እንመልከት። አፍሮዲጡ ሐዋርያው ጳውሎስን እንዲያገለግለው ጉባኤው ወደ ሮም ልኮት ነበር። ይሁን እንጂ አፍሮዲጡ ታመመና የተላከበትን ተግባር መፈጸም ሳይችል ቀረ። እንዲያውም ሐዋርያው ጳውሎስ እሱን መንከባከብ አስፈለገው። ጳውሎስ ይህ ታማኝ ሰው ከመታመሙም በላይ ጭንቀት ላይ እንደወደቀ የሚገልጽ ደብዳቤ ለነበረበት ጉባኤ በመላክ አፍሮዲጡ ወደ ቤቱ እንዲመለስ ዝግጅት አደረገ። አፍሮዲጡ የተጨነቀው በምን ምክንያት ነበር? ሐዋርያው “መታመሙን ስለ ሰማችሁም ተጨንቆአል” በማለት ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 2:25, 26) አፍሮዲጡ እንደታመመና የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣት እንዳልቻለ ሌሎች ማወቃቸውን ሲገነዘብ የዋጋ ቢስነት ስሜት አድሮበት ሊሆን ይችላል። በጭንቀት መዋጡ አያስገርምም!

ታዲያ ነገሮች አልሆን ሲሉን ሊሰማን የሚችለውን የዋጋ ቢስነት ስሜት ማስቀረት የሚቻልበት መንገድ ይኖር ይሆን?

አቅምህን እወቅ

ውጤታማ አለመሆን የሚያስከትለውን የስሜት ጉዳት መቀነስ የሚቻልበት አንዱ መንገድ ሊደረስበት የሚችልና አቅምህን ያገናዘበ ግብ ማውጣት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “በትሑት ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች” ይላል። (ምሳሌ 11:2፤ 16:18) ትሑት ሰው አቅሙን ያውቃል። አንዳንድ ጊዜ ችሎታህን ለማሻሻል ስትል ከበድ ያለ ነገርም ቢሆን ለማከናወን መሞከር ጥሩ መሆኑ አይካድም። ይሁን እንጂ ግቦችህ ከእውነታው የራቁ መሆን የለባቸውም። በሒሳብ በጣም ጎበዝ ላትሆን ወይም የተዋጣልህ ሯጭ ለመሆን የሚያበቃ የሰውነት አቋምና ቅልጥፍና ላይኖርህ ይችላል። ሚካኤል የተባለ የ20 ዓመት ወጣት እንደሚከተለው በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል:- “በስፖርት ጥሩ ችሎታ እንደሌለኝ አውቃለሁ። ስለዚህ  በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ብካፈልም የማልችለውን ነገር እችላለሁ ብዬ ራሴን ለውድቀት አላመቻችም።” አክሎም “የምታወጣው ግብ አቅምህን ያመዛዘነ ይሁን” ብሏል።

ስፒና ባይፊዳ በተባለ የአከርካሪ ሕመምና ሴሬብራል ፓልሲ ተብሎ በሚጠራው በአእምሮ መጎዳት ሳቢያ በሚከሰት የጤና መታወክ የምትሠቃየው የ14 ዓመቷ ኢቮን ስለ ሁኔታዋ ምን እንደሚሰማት እንመልከት። “እንደሌሎች ልጆች መራመድ፣ መደነስ ወይም መሮጥ አልችልም” ትላለች ኢቮን። “ሌሎች ሊያደርጉት የሚችሉትን ነገር ማድረግ አለመቻሌ ያበሳጨኛል። ብዙ ሰዎች ይህን አይረዱልኝም። ያም ሆኖ እንዲህ ያለውን ስሜት ተቋቁሜው እኖራለሁ።” ኢቮን ያሰቡት ስላልተሳካላቸው የዋጋ ቢስነት ስሜት ላደረባቸው ሰዎች የሚከተለውን ምክር ትለግሳለች:- “ጥረት ማድረጋችሁን አታቋርጡ። አለመታከት በጥረታችሁ ግፉበት። ሳይሳካላችሁ ቢቀር ወይም አጥጋቢ ውጤት ባታገኙ ተስፋ አትቁረጡ። የምትችሉትን ሁሉ ማድረጋችሁን ቀጥሉ።”

ከዚህም በላይ አላግባብ ራስህን ከሌሎች ጋር በማወዳደር ራስህን አታሠቃይ። አንድሩ የሚባለው የ15 ዓመት ወጣት “የእያንዳንዱ ሰው ጥንካሬና ችሎታ ስለሚለያይ ራሴን ከሌላ ሰው ጋር ከማወዳደር እቆጠባለሁ” ብሏል። የአንድሩ አስተያየት በገላትያ 6:4 ላይ ከሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ጋር ይስማማል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “እያንዳንዱ የራሱን ተግባር ይመርምር፤ ከዚያም በኋላ፣ ከሌላ ሰው ጋር ራሱን ሳያወዳድር፣ ስለ ራሱ የሚመካበትን ያገኛል።”

ሌሎች ከአቅምህ በላይ ሲጠብቁብህ

ይሁንና አንዳንድ ጊዜ ወላጆች፣ መምህራን ወይም ሌሎች ሰዎች ከአቅምህ በላይ የሆነ ነገር እንድታደርግ ጫና ያደርጉብሃል። ምንም ያህል ጥረት ብታደርግ የልባቸውን ልታደርስ እንደማትችል ትገነዘብ ይሆናል። ይባስ ብሎም ጫና ያደረጉብህ ሰዎች በውጤትህ አለመደሰታቸውን በሚያናድዱ አልፎ ተርፎም ተስፋ በሚያስቆርጡ ቃላት ይገልጹ ይሆናል። (ኢዮብ 19:2) ወላጆችህም ሆኑ ሌሎች ሰዎች ሆን ብለው ሊጎዱህ እየሞከሩ እንዳልሆነ ትገነዘብ ይሆናል። ጄሲካ እንደተናገረችው “አብዛኛውን ጊዜ የሚናገሩት ነገር ምን ያህል እንደጎዳህ እንኳ አያውቁ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ የችግሩ መንስኤ አለመግባባታችሁ ሊሆን ይችላል።”

በሌላ በኩል ደግሞ ምናልባት አንተ ያላስተዋልከው ችሎታ እንዳለህ ተመልክተው ይሆን? ለምሳሌ ችሎታህን አሳንሰህ በመመልከት የአቅምህን ያህል ጥረት አታደርግ ይሆናል። የሚሰጡህን ሐሳብ ችላ ከማለት ይልቅ ‘ምክራቸውን በማድመጥ ጥበበኛ ብትሆን’ ትጠቀማለህ። (ምሳሌ 8:33) ሚካኤል እንዲህ ይላል:- “ጥቅሙ ለራስህ ነው። የበለጠ እንድትሠራ የሚፈልጉት ራስህን እንድታሻሽል ነው። እንድታከናውነው የሚጠብቁብህን ነገር ልትወጣው እንደሚገባ ፈተና አድርገህ ተመልከተው።”

ይሁን እንጂ ወላጆችህም ሆኑ ሌሎች ሰዎች የሚጠብቁብህ ነገር ከአቅምህ በላይ እንደሆነና ለውድቀት እያመቻቹህ እንደሆነ ቢሰማህስ? እንግዲያውስ አክብሮት በተሞላበት መንገድና በግልጽ ብታነጋግራቸውና እንዴት እንደሚሰማህ እንዲያውቁት ብታደርግ ጥሩ ነው። አንድ ላይ ሆናችሁ አቅምህን ያገናዘበ ግብ ልታወጡ ትችሉ ይሆናል።

በመንፈሳዊ ሕይወትህ “ውጤት አልባ” መሆን

በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ያሉ ወጣቶች የአምላክ አገልጋዮች መሆናቸው የሚያስከትልባቸውን ኃላፊነት የመወጣት ከበድ ያለ ሥራ አለባቸው። (2 ጢሞቴዎስ 4:5) ወጣት ክርስቲያን ከሆንክ አንዳንድ ጊዜ ብቃት እንደሌለህ ወይም በስብሰባዎች ላይ ጥሩ ሐሳብ እንደማትሰጥ ይሰማህ ይሆናል። አሊያም ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሌሎች ለማብራራት ትቸገር ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ ጄሲካ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኝን አንዲት ወጣት መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠናት ነበር። ለተወሰነ ጊዜ ያህል የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዋ ጥሩ እድገት አደረገች። በመሃሉ ግን በድንገት ተነስታ አምላክን ማገልገል አልፈልግም ብላ ወሰነች። ጄሲካ “ጥሩ አስተማሪ እንዳልሆንኩ ተሰማኝ” በማለት ትናገራለች።

ጄሲካ እንዲህ ያለውን ስሜት መቋቋም የቻለችው እንዴት ነበር? በመጀመሪያ፣ ተማሪዋ ሳትቀበል የቀረችው እሷን ሳይሆን አምላክን መሆኑን መገንዘብ ነበረባት። ከዚህም በላይ  በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰውን በርካታ ጉድለቶች የነበሩትን ጴጥሮስ የተባለ አምላክን የሚፈራ ሰው ማስታወሷም ጠቅሟታል። እንዲህ ብላለች:- “ጴጥሮስ ድክመቶቹን እንዳሸነፈና [ከአምላክ] መንግሥት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በማከናወን ረገድ ይሖዋ በብዙ መንገዶች እንደተጠቀመበት መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል።” (ሉቃስ 22:31-34, 60-62) እርግጥ ነው፣ የማስተማር ችሎታህ መሻሻል የሚያስፈልገው ከሆነ በዚህ አቅጣጫ ትጋት የታከለበት ጥረት ማድረግ ያስፈልግህ ይሆናል። (1 ጢሞቴዎስ 4:13) በጉባኤው ውስጥ ሊያስተምሩህና ሊያሠለጥኑህ የሚችሉ የጎለመሱ ክርስቲያኖች ከሚያደርጉልህ እርዳታ ተጠቀም።

በተለይ ተፈታታኝ የሚሆንብህ ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው አገልግሎት ሊሆን ይችላል። ጄሰን “የቤቱ ባለቤት ካልተቀበለኝ ስኬታማ እንዳልሆንኩ ይሰማኝ ነበር” በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል። ታዲያ ይህን ስሜት እንዴት ተቋቋመው? ‘ሰዎቹ አልተቀበሉኝም ማለት ውጤታማ አልሆንኩም ማለት እንዳልሆነ ማስታወስ ነበረብኝ’ ብሏል። በእርግጥም፣ አምላክ እንዲያከናውን ያዘዘውን ነገር ማለትም የስብከቱን ሥራ በመፈጸም ረገድ ተሳክቶለታል! ደግሞም ተቀባይነት ማጣት ደስ የማይል ቢሆንም የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት የማይቀበሉት ሁሉም ሰዎች እንዳልሆኑ አስታውስ። “የሚያዳምጥ ሰው ሳገኝ” ይላል ጄሰን “መስበክ ማንኛውም ጥረት ሊደረግለት እንደሚገባ ያስገነዝበኛል።”

ከባድ ስህተቶች

ከባድ ስህተት፣ አልፎ ተርፎም ከባድ ኃጢአት ብትሠራስ? አና የምትባለው የ19 ዓመት ልጃገረድ እንዲህ ያለ ስህተት ሠርታ ነበር። * “ጉባኤው፣ ቤተሰቦቼና በተለይም ደግሞ ይሖዋ እንደጠበቁኝ ሆኜ ሳልገኝ ቀረሁ” በማለት ተናግራለች። ከዚህ ሁኔታ ለማገገም ንስሐ መግባትና በጉባኤው ውስጥ ያሉ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ሰዎችን እርዳታ መሻት ያስፈልግሃል። (ያዕቆብ 5:14-16) አና አንድ ሽማግሌ የተናገራቸው ቃላት እንዳጽናኗት ታስታውሳለች:- “ንጉሥ ዳዊት ብዙ ስህተቶች የፈጸመ ቢሆንም ይሖዋ ይቅር ሊለው ፈቃደኛ እንደነበረና ዳዊትም ወደ ቀድሞ ሁኔታው እንደተመለሰ ሽማግሌው ነገረኝ። ይህ እኔም [በመንፈሳዊ እንዳገግም] ረድቶኛል።” (2 ሳሙኤል 12:9, 13፤ መዝሙር 32:5) አንተም ብትሆን ራስህን በመንፈሳዊ ለማጠናከር የምትችለውን ያህል ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል። አና “የመዝሙርን መጽሐፍ ደጋግሜ አነበዋለሁ። እንዲሁም የሚያበረታቱ ጥቅሶችን በማስታወሻ ደብተሬ ላይ አሠፍራቸዋለሁ” ብላለች። ከባድ ኃጢአት የሠራ ሰውም እንኳን ቢሆን ከጊዜ በኋላ ወደ ቀድሞ መንፈሳዊ አቋሙ ሊመለስ ይችላል። ምሳሌ 24:16 “ጻድቅ ሰባት ጊዜ እንኳ ቢወድቅ ይነሣልና” ይላል።

ከውድቀት ማገገም

በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ አነስተኛ በሚመስሉ ጉዳዮችም እንኳ ነገሮች እንዳሰብከው ሳይሆኑ ሲቀሩ ስሜትህ ሊጎዳ እንደሚችል አይካድም። ታዲያ ይህ ሁኔታ ያስከተለብህን የዋጋ ቢስነት ስሜት ማሸነፍ የምትችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ እውነታውን በመቀበል ስህተትህን ተጋፈጠው። ሚካኤል እንደሚከተለው በማለት ይመክራል:- “በሁሉም ነገር ስኬታማ እንዳልሆንክ አድርገህ ከማሰብ ይልቅ መሥራት ያልቻልከው የትኛውን ሥራ እንደሆነና ለምን እንዳቃተህ ለይተህ እወቅ። እንዲህ ማድረግህ በሚቀጥለው ጊዜ በተሻለ መንገድ ለመሥራት ያስችልሃል።”

በተጨማሪም ስለ ራስህ ከሚገባ በላይ ከማሰብ ተቆጠብ። “ለመሣቅም ጊዜ አለው፤” ይህ ደግሞ በራስህ ስህተት መሣቅንም ሊጨምር ይችላል! (መክብብ 3:4) የተስፋ መቁረጥ ስሜት ካደረብህ እንደ ትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ ወይም ስፖርት ባሉ በጥሩ ሁኔታ ልታከናውናቸው የምትችላቸው ነገሮች ላይ አተኩር። እምነትህን ለሌሎች እንደመናገር ባሉት ‘መልካም ሥራዎች’ መካፈል በሥራህ ይበልጥ እንድትደሰት ሊረዳህ ይችላል።—1 ጢሞቴዎስ 6:18

በመጨረሻም “እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ” እንደሆነና “ሁልጊዜ በደልን አይከታተልም” እንደተባለለት አስታውስ። (መዝሙር 103:8, 9) ጄሲካ እንዲህ ትላለች:- “ይበልጥ ወደ ይሖዋ አምላክ እየቀረብኩ ስሄድ በሚያጋጥመኝ ችግር ሁሉ ድጋፍና እርዳታው እንደማይለየኝ ያለኝ እምነት ይጨምራል።” አዎን፣ በአንዳንድ ጉዳዮች ባይሳካልህም የሰማዩ አባትህ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከትህ ማወቁ ያጽናናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.23 ስሟ ተቀይሯል።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከአቅምህ በላይ እንደሚጠበቅብህ ከተሰማህ አክብሮት በተሞላበት መንገድ የሚሰማህን ተናገር

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥሩ አድርገህ የምትሠራቸውን ነገሮች ማከናወን የዋጋ ቢስነትን ስሜት ሊያስወግድልህ ይችላል