በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆችን በአምላክ ተግሣጽ ማሳደግ

ልጆችን በአምላክ ተግሣጽ ማሳደግ

 የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ልጆችን በአምላክ ተግሣጽ ማሳደግ

“ልጆቻችሁ የማይጥሷቸው ሕግጋት ማውጣት የሚቻልበት መንገድ”

“ልጃችሁ በአምስት ዓመቱ ሊያውቃቸው የሚገቡ አምስት ሥርዓቶች”

“ሁሉም ልጆች ሊያዳብሯቸው የሚገቡ አምስት ባሕርያት”

“በጣም ልል እንደሆናችሁ የሚጠቁሙ አምስት ምልክቶች”

“በአንድ ደቂቃ እርማት ሥልጠና መስጠት የሚቻልበት ዘዴ”

ልጆችን ማሠልጠን ቀላል ቢሆን ኖሮ ከላይ እንዳሉት ዓይነት ርዕሶች ይዘው የሚወጡ መጽሔቶች እምብዛም ፈላጊ አይኖራቸውም ነበር። ልጆችን ስለማሠልጠን የሚጻፉት በርካታ መጻሕፍትም መዘጋጀታቸው ይቀር ነበር። ሆኖም ልጆችን ማሳደግ መቼም ቢሆን ቀላል ሥራ ሆኖ አያውቅም። በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት እንኳ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ “ተላላ ልጅ በአባቱ ላይ ሐዘን ያስከትላል፤ ለወለደችውም ምሬት ይሆንባታል” ብሎ ነበር።—ምሳሌ 17:25

ዛሬም በዚህ ጉዳይ ላይ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ምክሮች ቢሰጡም ብዙ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዴት ማሳደግ እንዳለባቸው እርግጠኞች አይደሉም። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ምን እርዳታ ያበረክታል?

የተግሣጽ ትክክለኛ ትርጉም

መጽሐፍ ቅዱስ ተግሣጽ በመስጠት ረገድ ወላጆች ምን ድርሻ እንዳላቸው በግልጽ ይናገራል። ለአብነት ያህል፣ ኤፌሶን 6:4 እንዲህ ይላል:- “አባቶች ሆይ፤ እናንተም ልጆቻችሁን አታስቆጧቸው፤ ነገር ግን በጌታ ምክርና ተግሣጽ አሳድጓቸው።” ይህ ጥቅስ ልጆችን በማሳደጉ በኩል ቅድሚያውን መውሰድ ያለበት አባት እንደሆነ ለይቶ ይጠቅሳል። በእርግጥ እናትም ከባልዋ ጎን ሆና የምትጫወተው ሚና እንደሚኖር ግልጽ ነው።

ዚ ኢንተርፕሬተርስ ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ እንዲህ ይላል:- “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተግሣጽ በአንድ በኩል ከሥልጠና፣ ከመመሪያና ከእውቀት በሌላ በኩል ደግሞ ከወቀሳ፣ ከእርማትና ከቅጣት ጋር የተዛመደ ሲሆን ብዙውን ጊዜ ይህ ቃል የሚሠራበት ልጆችን ከማሠልጠን ጋር በተያያዘ ነው።” በዚህም ምክንያት ተግሣጽ ከእርማት የበለጠ ነገርን ይኸውም ልጆችን ጥሩ አድርጎ ለማሳደግ የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ሥልጠና የሚያካትት ነው። ይሁን እንጂ ወላጆች ልጆቻቸውን ላለማበሳጨት ምን ማድረግ ይችላሉ?

 ስሜታቸውን ተረዱላቸው

አንድን ልጅ ምን ሊያበሳጨው ይችላል? እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ ለማሰብ ሞክሩ። የሥራ ባልደረባችሁ ግልፍተኛና ትዕግሥት የለሽ ነው እንበል። ምንም ብታደርጉ የማይደሰት ከመሆኑም በላይ ከምትናገሩትም ሆነ ከምታደርጉት ከማንኛውም ነገር ላይ እንከን አያጣም። አብዛኛውን ጊዜ ሥራችሁን ያጣጥለዋል እንዲሁም የማትፈለጉ እንደሆናችሁ እንዲሰማችሁ ያደርጋል። እንደዚህ ካለው ሰው ጋር መሥራት የሚያበሳጭና ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም?

በተመሳሳይም አንድ ልጅ ወላጆቹ ሁልጊዜ የሚጨቀጭቁትና የቁጣ ውርጅብኝ የሚያዘንቡበት ከሆነ እንደዚህ ሊሰማው ይችላል። ልጆች በየጊዜው እርማት እንደሚያስፈልጋቸው የማይካድ ከመሆኑም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ወላጆች እንዲህ ያለ እርማት እንዲሰጡ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። ይሁን እንጂ አንድን ልጅ ደግነትና ፍቅር በጎደለው መንገድ በመገሠጽ ማበሳጨት ስሜታዊ፣ መንፈሳዊና አልፎ ተርፎም አካላዊ ጉዳት ሊያስከትልበት ይችላል።

ልጆቻችሁ የእናንተ ትኩረት ያሻቸዋል

ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ ሊመድቡ ይገባል። ዘዳግም 6:7 የአምላክን ሕግጋት “ለልጆችህም አስጠናቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር” በማለት አባቶችን ያዝዛቸዋል። ልጆች በተፈጥሯቸው ወላጆቻቸው በጥልቅ እንደሚያስቡላቸው ማወቅ ይፈልጋሉ። ከልጆቻችሁ ጋር በየዕለቱ ረጋ ያለ ውይይት ብታደርጉ ስሜታቸውን ለመረዳት ትችላላችሁ። እንዲህ ማድረጋችሁ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በቀላሉ በልባቸው ውስጥ ለመቅረጽ ስለሚያስችላችሁ ‘እግዚአብሔርን እንዲፈሩና ትእዛዛቱን እንዲጠብቁ’ ይገፋፋቸዋል። (መክብብ 12:13) ይህ የአምላካዊ ተግሣጽ አንዱ ገጽታ ነው።

ልጆችን ማሳደግ ቤት ከመሥራት ጋር ቢነጻጸር ተግሣጽ ከግንባታ መሣሪያዎቹ አንዱ ይሆናል። ወላጆች በተገቢው መንገድ ከተጠቀሙበት ልጆቻቸው አስፈላጊ የሆኑ ባሕርያትን እንዲያዳብሩ ሊረዷቸውና በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ፈታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት ሊያስታጥቋቸው ይችላሉ። ምሳሌ 23:24, 25 እንዲህ ያለው ሥልጠና የሚያስገኘውን ፍሬ ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “የጻድቅ ሰው አባት እጅግ ደስ ይለዋል፤ ጠቢብ ልጅ ያለውም በእርሱ ሐሤት ያደርጋል። አባት እናትህ ደስ ይበላቸው፤ ወላጅ እናትህም ሐሤት ታድርግ።”

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

‘በጌታ ምክር’

ኤፌሶን 6:4 ልጆችን ‘በጌታ ምክር’ ስለማሳደግ ይናገራል። ‘ምክር’ ተብሎ የተተረጎመውን የግሪክኛ ቃል አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች “እውቀት” እና “ማሳሰቢያ” ብለው ተርጉመውታል። እነዚህ ቃላት ቤተሰቦች መጽሐፍ ቅዱስ ከማንበብ ወይም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተብሎ ከተዘጋጀ ጽሑፍ ላይ እንዲሁ በዘልማድ አንድ ክፍል ከመሸፈን በተጨማሪ ሊያደርጉት የሚገባ ነገር እንዳለ ያሳያሉ። ወላጆች ልጆቻቸው የአምላክ ቃል እንዲገባቸውና የመታዘዝን አስፈላጊነት እንዲገነዘቡ እንዲሁም ይሖዋ እንደሚወዳቸውና ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው እንዲያውቁ ሊረዷቸው ይገባል።

ይህንን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ጁዲ አምላካዊ መመሪያዎችን ለልጆቿ አዘውትራ ከመንገር በተጨማሪ ልታደርገው የሚገባ ነገር እንዳለ ተገነዘበች። “አንድን ነገር አሁንም አሁንም በተመሳሳይ መንገድ እየደጋገምኩ ስነግራቸው ደስ እንደማይላቸው ተመለከትኩ። ስለዚህ የተለያዩ የማስተማሪያ መንገዶችን መጠቀም ጀመርኩ። ከእነዚህ አንዱ ለልጆቼ የሚያስፈልጋቸውን ምክሮች ለየት ባለ መንገድ የሚያቀርቡ በንቁ! መጽሔት ላይ የወጡ ርዕሶችን መፈለግ ነበር። በዚህ መንገድ ልጆቼ ሳይበሳጩ አስፈላጊውን ማሳሰቢያ እንዴት ልሰጣቸው እንደምችል ተምሬያለሁ።”

ቤተሰቡ የተለያዩ ችግሮችን ያሳለፈው አንጂሎ ሴቶች ልጆቹን በአምላክ ቃል ላይ ማሰላሰልን እንዴት እንዳስተማራቸው ሲናገር እንዲህ ይላል:- “አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አብረን ካነበብን በኋላ አንዳንድ ሐሳቦችን እመርጥና ከልጆቼ ሁኔታ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ አብራራላቸው ነበር። ከጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን በግላቸው በሚያነቡበት ወቅት በሕይወታቸው ውስጥ እንዴት ሊሠሩበት እንደሚችሉ በጥልቅ ሲያሰላስሉ መመልከት ችያለሁ።”