በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት ከመፈጸም መታቀብ የምችለው እንዴት ነው?

ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት ከመፈጸም መታቀብ የምችለው እንዴት ነው?

 የወጣቶች ጥያቄ . . .

ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት ከመፈጸም መታቀብ የምችለው እንዴት ነው?

“ትምህርት ቤት ሳለሁ ከማውቀው ልጅ ጋር በ19 ዓመቴ የጾታ ግንኙነት ፈጸምኩ። ምን ያህል እንዳፈርኩና እንደተጨነቅኩ ልነግራችሁ አልችልም። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዋጋ ቢስነት ይሰማኛል።”—ሌሲ *

መጽሐፍ ቅዱስ “ከዝሙት ሽሹ” ብሎ ያዛል። (1 ቆሮንቶስ 6:18) ይሁን እንጂ፣ በዛሬው ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን ትእዛዝ አክብረው እስከሚያገቡ ድረስ ከጾታ ግንኙነት የሚታቀቡ ወጣቶች ቁጥር ጥቂት ነው። እንደ ሌሲ ያሉ አንዳንድ ወጣቶች ለፍላጎታቸው በመሸነፋቸው ለከፍተኛ ሐዘንና የሕሊና ወቀሳ ተዳርገዋል።

የጾታ ፍላጎትን መቆጣጠር ቀላል እንዳልሆነ እሙን ነው። አዶለሰንት ዲቨሎፕመንት የተባለ የመማሪያ መጽሐፍ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚከሰተው የሆርሞን ለውጥ “የጾታ ፍላጎት እንዲያይል” ማድረጉ እንደማይቀር ጠቅሷል። ፖል እንዲህ ሲል እውነቱን ተናግሯል:- “አንዳንድ ጊዜ የጾታ ግንኙነትን የተመለከቱ ሐሳቦች ያለ ምንም ግልጽ ምክንያት ወደ አእምሮዬ ይመጣሉ።”

ሆኖም የሕፃናት ሕክምና ፕሮፌሰር የሆኑት ሃዋርድ ኩሊን አስተያየታቸውን ሲሰጡ እንዲህ ብለዋል:- “[ጉርምስና] የሚያስከትለውን የጠባይ ለውጥ በሆርሞኖች ብቻ ማሳበብ የችግሩን ክብደት ከልክ በላይ ማቃለል ነው።” ፕሮፌሰሩ ማኅበራዊ ሁኔታዎችም የሚጫወቱት ሚና እንዳለ ገልጸዋል። በእርግጥም ማኅበራዊ ሁኔታዎች በተለይም እኩዮች ከባድ ተጽዕኖ ያደርጋሉ።

ፐትሪሸ ሀርሽ የተባሉ አንዲት ደራሲ ኤ ትራይብ አፓርት በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል:- “ወጣቶች የራሳቸውን ዓለም ፈጥረዋል። . . . ይህ ዓለም የእኩያሞች ስብስብ ብቻ ሳይሆን የራሱ የሆነ የአቋም ደረጃ፣ የሥነ ምግባር መሥፈርትና መመሪያ ያለው ራሱን [ከአዋቂዎች] የነጠለ ኅብረተሰብ ነው።” ነገር ግን በዛሬው ጊዜ የበርካታ ወጣቶች “የሥነ ምግባር መሥፈርትና መመሪያ” በአብዛኛው የጾታ ፍላጎታቸውን እንዲቆጣጠሩ ሳይሆን ስድ እንዲለቁት ያበረታታቸዋል። ስለዚህ ብዙዎች ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነትን እንዲሞክሩ ግፊት ተደርጎባቸው ሊሆን ይችላል።

ክርስቲያን ወጣቶች ግን አምላክ ‘ከሥጋ ሥራዎች’ አንዱ የሆነውን ዝሙትን እንደሚያወግዝ ስለሚያውቁ ከማንኛውም ዓይነት የዝሙት ድርጊት ለመራቅ ጥበብ ያለበት ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። * (ገላትያ 5:19) ታዲያ ከባድ ተጽዕኖዎችን ተጋፍጠህ ንጽሕናህን ጠብቀህ መኖር የምትችለው እንዴት ነው?

ጥበበኛ ጓደኞችን አፍራ

ደስ የሚለው ነገር ግን ማኅበራዊ ሁኔታዎች መጥፎ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩብህ ሁሉ ጥሩ ጓደኞችም በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብህ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስም የሚለው ይህንኑ ነው:-  “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል።” (ምሳሌ 13:20፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33) የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ዘገባ እንደሚያሳየው “ከወላጆቻቸው፣ ከሚያስቡላቸው ሌሎች አዋቂዎችና ከእኩዮቻቸው ጋር ጥሩ ቅርርብ ያላቸው” እንዲሁም “የአቋም ደረጃና ገደብ የተበጀላቸው በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች . . . የጾታ ግንኙነት መፈጸም የመጀመር አጋጣሚያቸው ዝቅተኛ ነው።”

በተለይ ከወላጆችህ ጋር ጥሩ ቅርርብ መፍጠርህ ልዩ እርካታ ያስገኝልሃል። ጆሴፍ “ወላጆቼ በእርግጥም የጾታ ግንኙነትን እንድሞክር ይደረግብኝ የነበረውን ግፊት እንድቋቋም ረድተውኛል” በማለት ይናገራል። እውነት ነው፣ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆች በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ የአቋም ደረጃና ገደብ ሊያወጡልህ ይችላሉ። (ኤፌሶን 6:2, 3) ንጽሕናህን ጠብቀህ ለመኖር በምታደርገው ትግል እንድታሸንፍ ሊደግፉህ ይችላሉ።

የጾታ ጉዳዮችን አንስቶ ከእነርሱ ጋር መነጋገር መጀመሪያ ላይ ሊያሳፍር ይችላል። ነገር ግን ምን እንደሚሰማህ በደንብ ማወቃቸውን ስታይ ትደነቃለህ። እነርሱም በአንድ ወቅት ወጣቶች እንደነበሩ አስታውስ። ሶንያ ወጣቶችን እንዲህ ስትል ትመክራለች:- “ወላጆቻችሁን ቀርባችሁ አማክሩ፤ ስለ ጾታ ጉዳይ አንስታችሁ ለመነጋገር አትፈሩ።”

ወላጆችህ የመጽሐፍ ቅዱስን የአቋም ደረጃ የማይከተሉ ቢሆንስ? ለእነርሱ መስጠት የሚገባህን ክብር ሳትቀንስ ከቤተሰብህ ውጪ ካሉ ሰዎች መመሪያ መጠየቅ ሊያስፈልግህ ይችላል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ፖል እንዲህ ሲል ገልጿል:- “የጾታ ጉዳይን በተመለከተ ከተጋቡ ጎልማሳ ክርስቲያኖች ትልቅ እርዳታ አግኝቻለሁ።” የማታምን እናት ያለቻት ኬንጂ የምትባል ወጣት በተመሳሳይ የሚከተለውን ብላለች:- “ምክር ለማግኘት በመንፈሳዊ ሊያበረታቱኝ ወደሚችሉ የጎለመሱ ክርስቲያኖች እሄዳለሁ።” ነገር ግን የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች:- “ከእኔ ጋር የሚመሳሰል ሃይማኖታዊ እምነት ቢኖራቸውም እንኳን ጠንካራ የሥነ ምግባር አቋም የሌላቸውን ሰዎች አላማክርም።”

አንዳንድ ጊዜ በጉባኤው ውስጥ ያለህን ቅርርብ በተመለከተ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልግህ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ በርካታ ሰዎችን በሚያቅፍ አንድ ቡድን ውስጥ ብዙውን ጊዜ የሚያስከብር ጠባይ የሌላቸው ጥቂት ሰዎች እንደማይጠፉ ያስታውሰናል። (2 ጢሞቴዎስ 2:20) በጉባኤህ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ወጣቶች ‘ግብዞች’ እንደሆኑ ብታውቅ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? (መዝሙር 26:4) ከእንደነዚህ ዓይነቶቹ ጋር የተቀራረበ ወዳጅነት ከመመሥረት ተቆጠብ፤ እንዲሁም በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆነህ ለመቆየት ባደረግከው ቁርጥ ውሳኔ ሊደግፉህ የሚችሉ ጓደኞች ፈልግ።

ጎጂ ፕሮፓጋንዳ አትስማ

በተጨማሪም በመጻሕፍት፣ በመጽሔቶች፣ በሙዚቃ ፊልሞች፣ በቪዲዮ ጨዋታዎች፣ በፊልሞችና በኢንተርኔት አማካኝነት ከሚሰራጩና እንደ አሸን ከፈሉ የብልግና ሥዕሎችና ንግግሮች ራስህን ለመጠበቅ ብርቱ ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል። መገናኛ ብዙኃን ከጋብቻ በፊት የሚደረግ የጾታ ግንኙነት አስደሳችና ምንም አደጋ የማያስከትል እንደሆነ አስመስለው ያቀርባሉ። ይህ ምን ውጤት አምጥቷል? ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኬንጂ እንዲህ ስትል እውነቱን ተናግራለች:- “የጾታ ግንኙነትን በግልጽ የሚያሳዩና ግብረሰዶምን በረቀቀ መንገድ የሚያቀርቡ ተከታታይ ፊልሞችን እመለከት ነበር። በመሆኑም ይሖዋ እነዚህን ነገሮች ምን ያህል አክብዶ እንደሚመለከታቸው መዘንጋት ጀመርኩ።”

በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፉ መዝናኛዎች ከጋብቻ በፊት የሚደረግ የጾታ ግንኙነት የሚያስከትላቸውን መጥፎ ውጤቶች ማለትም ያልተፈለገ እርግዝናን፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻን እና በጾታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችን በዘዴ መሸፋፈናቸው እውነት ነው። ስለሆነም ‘ክፉውን መልካም፣ መልካሙን ክፉ በሚሉ’ ሰዎች አትታለል።—ኢሳይያስ 5:20

የምሳሌ 14:15ን ቃላት አስታውስ:- “ተላላ ሰው ሁሉን ያምናል፤ አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል።” በምታነብበት ጊዜ፣ የኢንተርኔት ገጾችን ስታስስ ወይም ቴሌቪዥን ስታይ የጾታ ስሜትን የሚቀሰቅሱ ነገሮች ካጋጠሙህ ፈጣን  እርምጃ ውሰድ! መጽሐፉን ክደን፣ ኮምፒውተርህን አጥፋው ወይም የቴሌቪዥኑን ጣቢያ ቀይር አሊያም አጥፋው! ከዚያም አሳብህ ጠቃሚ በሆነ በሌላ ነገር ላይ እንዲያተኩር አድርግ። (ፊልጵስዩስ 4:8) እንዲህ በማድረግ መጥፎ ምኞቶች ከማደጋቸው በፊት በአጭሩ ልትቀጫቸው ትችላለህ።—ያዕቆብ 1:14, 15

አቋምህን እንድታላላ ከሚያደርጉ ሁኔታዎች ተጠንቀቅ

ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠርክ መጫወት ጀምረሃል? ከሆነ ልዩ ጥንቃቄ ልታደርግ ይገባሃል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ያስጠነቅቀናል:- “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነው፤ ፈውስም የለውም።” (ኤርምያስ 17:9) የፍቅር መግለጫዎች ወደ ጾታ ብልግና የማምራታቸው አጋጣሚ ሰፊ ነው። ስለዚህ አንድ ሰው አብሯችሁ እንዲሆን በማድረግ ወይም በቡድን ሆኖ ጊዜ በማሳለፍ ተገቢውን ጥንቃቄ አድርግ። ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ብቻችሁን አትሁኑ።

ምናልባት ለመጋባት የተጫጫችሁ ከሆናችሁ አካላዊ የፍቅር መግለጫዎች ምንም ስህተት እንደሌላቸው ይሰማችሁ ይሆናል። ሆኖም የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ያጠናቀረው ዘገባ እንዲህ ሲል ያስጠነቅቃል:- “ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት ማድረግ ክልክል በሆነባቸው አካባቢዎች እንኳን ሳይቀር የጋብቻው ጊዜ እየቀረበ ሲመጣ የጾታ ግንኙነት የማድረጉ አጋጣሚ በብዙ ሴቶች ላይ ሲከሰት ይታያል።” * ስለዚህ ለፍቅር መግለጫዎች ገደብ በማበጀት ከቅስም ስብራት ራሳችሁን ጠብቁ።

ነገሩ የሚያሳዝን ቢሆንም በርካታ ወጣቶች በተለይም ወጣት ልጃገረዶች ተገድደው ወሲብ ይፈጽማሉ። አንድ ጥናት እንደሚያሳየው:- “በዩናይትድ ስቴትስ ከ15 ዓመታቸው በፊት የጾታ ግንኙነት ከፈጸሙት ልጃገረዶች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት ይህን ያደረጉት ያለ ፈቃዳቸው ነው።” ብዙ ጊዜ ወንጀለኞች ሰለባዎቻቸውን ለማጥቃት ጉልበት ይጠቀማሉ። (መክብብ 4:1) ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ የንጉሥ ዳዊት ልጅ አምኖን የአባቱን ልጅ ትዕማርን እንደ “ወደዳት” እና አታልሎ አስገድዶ እንደደፈራት ይናገራል።—2 ሳሙኤል 13:1, 10-16

እንዲህ ሲባል ግን በግዳጅ የሚፈጸም የጾታ ግንኙነትን መከላከል አይቻልም ማለት አይደለም። አደገኛ ሁኔታዎችን በንቃት በመከታተል፣ አቋምህን እንድታላላ ከሚያደርጉህ ሁኔታዎች በመራቅና አስጊ ሁኔታ ሲፈጠር ፈጣን እርምጃ በመውሰድ ራስህን ለመጠበቅ ብዙ ማድረግ ትችላለህ። *

“ያልተከፋፈለ ልብ” ይኑርህ

እስከ አሁን የተወያየንባቸው ሐሳቦች ንጽሕናህን ጠብቀህ ለመኖር በምታደርገው ትግል ድጋፍ እንደሚሰጡህ ተስፋ እናደርጋለን። ውሎ አድሮ ግን በልብህ ውስጥ ያለው ነገር ምን እንደሆነ ባሕርይህ ይገልጸዋል። ኢየሱስ “ዝሙት . . . ከልብ ይመነጫል” ብሏል። (ማቴዎስ 15:19) ስለዚህ በዚህ አንገብጋቢ ጉዳይ ላይ ‘ሁለት ልብ’ (ልዝብ አቋም) ወይም “መንታ ልብ” የመያዝን (ግብዝ የመሆንን) ዝንባሌ መቋቋም አለብህ።—መዝሙር 12:2፤ 119:113

ያደረግከው ቁርጥ ውሳኔ እየተዳከመ እንዳለ ወይም ልብህ እንደተከፈለ ከተሰማህ ልክ ዳዊት እንደለመነው “ስምህን እፈራ ዘንድ፣ ያልተከፋፈለ ልብ ስጠኝ” ብለህ ጸልይ። (መዝሙር 86:11) ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በማጥናትና የተማርከውንም በሥራ ላይ በማዋል ከጸሎትህ ጋር በሚስማማ መንገድ ተመላለስ። (ያዕቆብ 1:22) ሊዲያ እንዲህ ብላለች:- “ሁልጊዜ ‘ማንም አመንዝራ ወይም ርኩስ በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት የለውም’ የሚለውን ጥቅስ ማስታወሴ በጾታ ፍላጎት እንዳልሸነፍ ይገፋፋኛል።”—ኤፌሶን 5:5

ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት ከማድረግ መታቀብ ቀላል ላይሆን ይችላል። በይሖዋ እርዳታ ግን ንጽሕናህን ጠብቀህ መቆየትና ራስህንም ሆነ ሌሎችን ከከባድ ችግርና ሥቃይ መጠበቅ ትችላለህ።—ምሳሌ 5:8-12

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 ስሞቹ ተቀይረዋል

^ አን.8 በነሐሴ 2004 ንቁ! መጽሔት እትም ላይ የወጣውን “የወጣቶች ጥያቄ . . . ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት መፈጸም ምን ስህተት አለው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.21 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የሚለውን መጽሐፍ ገጽ 29 ተመልከት።

^ አን.23 ይህን ጉዳይ በተመለከተ በሚያዝያ 1996 እና በሐምሌ 2004 ንቁ! መጽሔት እትሞች ላይ “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .” በሚለው ዓምድ ሥር በወጡት “ሌሎች በጾታ ስሜት እንዳይዳፈሩኝ ራሴን መጠበቅ የምችለው እንዴት ነው?” እና “ጓደኛዬ የሚፈጽምብኝን አግባብ ያልሆነ ድርጊት ማስተው የምችለው እንዴት ነው?” በሚሉት ርዕሶች ላይ ሐሳቦች ተሰጥተዋል።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የልብህን አውጥተህ ከወላጆችህ ጋር መነጋገርህ ንጽሕናህን ጠብቀህ ለመኖር ይረዳሃል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥሩ ባሕርይ ካላቸው ጋር በቡድን ሆኖ ተቀጣጥሮ መጫወት ጥበቃ ሊሆን ይችላል