በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ስለ ደም ያለውን አመለካከት ተቀበልኩ

አምላክ ስለ ደም ያለውን አመለካከት ተቀበልኩ

 አምላክ ስለ ደም ያለውን አመለካከት ተቀበልኩ

አንድ ሐኪም እንደተናገረው

በሆስፒታሉ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ሆኜ በሞተ ሰው አካል ላይ የተደረገውን ምርመራ ውጤት ሪፖርት ለሐኪሞች እያቀረብኩ ነበር። የሞተው ሰው አደገኛ እብጠት ነበረበት፤ “ይህ በሽተኛ ለሞት የበቃው ከፍተኛ መጠን ያለው ደም ስለተሰጠው በደረሰበት ቀይ የደም ሴሎች መፈረካከስና ኩላሊቱ በድንገት መሥራት በማቆሙ ምክንያት ነው” አልኩኝ።

አንድ ፕሮፌሰር ከመቀመጫቸው በመነሳት “ለሰውየው የሰጣችሁት የደም ዓይነት የተሳሳተ ነው ማለትህ ነው?” ብለው በንዴት ጮኹብኝ። እኔም “እንዲህ ማለቴ አይደለም” ብዬ መለስኩ። ከዚያም የሟቹን ኩላሊት ቁራጭ በስላይድ ፊልም እያሳየሁ “በኩላሊቱ ውስጥ በርካታ ቀይ የደም ሴሎች ተፈረካክሰው እናያለን። በመሆኑም ኩላሊቱ በድንገት መሥራት ያቆመው በዚህ ምክንያት ነው ብለን መደምደም እንችላለን” በማለት አክዬ ተናገርኩ። * በአዳራሹ ውስጥ ውጥረት ነገሠ፤ እኔም በፍርሃት አፌ ደረቀ። ምንም እንኳ እኔ ወጣት ዶክተር እርሳቸው ደግሞ ፕሮፌሰር ቢሆኑም በዚህ ጉዳይ ላይ አቋሜን ልለውጥ እንደማልችል ተሰምቶኝ ነበር።

ይህ ሁኔታ ባጋጠመኝ ወቅት የይሖዋ ምሥክር አልነበርኩም። የተወለድኩት በ1943 ሴንዳይ በምትባል አንዲት የጃፓን ሰሜናዊ ከተማ ነው። አባቴ ፓቶሎጂስትና የአእምሮ ሐኪም ስለነበር እኔም ሕክምና ለማጥናት ወሰንኩ። በ1970 በሕክምና ትምህርት ቤት የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ሳለሁ ማሱኮ የተባለች ወጣት አገባሁ።

 በፓቶሎጂ መስክ ተሰማራሁ

እኔ ትምህርቴን እስክጨርስ ድረስ ማሱኮ እየሠራች ቤተሰቡን ትደግፍ ነበር። የሕክምና መስክ ስሜቴን ማረከው። የሰው አካል ያለው ድንቅ አሠራር አስደመመኝ! ያም ሆኖ ስለ ፈጣሪ መኖር አስቤ አላውቅም ነበር። የሕክምና ምርምር ለሕይወቴ ትርጉም ይሰጠዋል ብዬ አሰብኩ። ስለሆነም ሐኪም ከሆንኩ በኋላ በፓቶሎጂ፣ ማለትም የበሽታዎች ዓይነተኛ ጠባይ፣ መንስኤና የሚያስከትሉት ችግር በሚጠናበት መስክ ትምህርቴን ለመቀጠል ወሰንኩ።

በካንሰር በሞቱ በሽተኞች አስከሬን ላይ ምርመራ በማካሂድበት ወቅት ደም መስጠት ውጤታማ መሆኑን እጠራጠር ጀመር። ከፍተኛ እድገት ያለው ካንሰር ያለባቸው በሽተኞች ደም ስለሚፈሳቸው የደም ማነስ ሊኖርባቸው ይችላል። ኬሞቴራፒ የሚባለው ሕክምና የደም ማነስን ስለሚያባብስ ሐኪሞች ብዙውን ጊዜ ለበሽተኛው ደም እንዲሰጠው ያዛሉ። ሆኖም ደም መስጠት ካንሰሩ እንዲሰራጭ ሊያደርገው እንደሚችል መጠራጠር ጀመርኩ። ያም ሆነ ይህ፣ ዛሬ ደም መውሰድ የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም እንደሚያዳክምና ይህም እብጠቱ እንደገና እንዲያድግ ሊያደርገው እንዲሁም የካንሰር በሽተኞችን በሕይወት የመትረፍ አጋጣሚ ሊቀንሰው እንደሚችል ታውቋል። *

በ1975 በዚህ ርዕስ መጀመሪያ ላይ የጠቀስኩት ጉዳይ አጋጠመኝ። ይህ ጉዳይ የሚመለከተው ፕሮፌሰሩን ሲሆን እርሳቸው በደም ምርምር ስፔሻሊስት ነበሩ። ስለዚህ በሽተኛው ለሞት የበቃው ደም ስለተሰጠው ነው ብዬ ስናገር መናደዳቸው አያስገርምም! ይሁን እንጂ ማስረጃዬን ማቅረብ ስቀጥል ቀስ በቀስ ንዴታቸው በረደላቸው።

በሽታም ሆነ ሞት አይኖሩም

ባለቤቴ ከአንዲት በዕድሜ የገፉ የይሖዋ ምሥክር ጋር የተገናኘችው በዚሁ ጊዜ ነበር። የይሖዋ ምሥክሯ “ይሖዋ” የሚለውን ቃል ይጠቀሙ ስለነበር ባለቤቴ “ይሖዋ” ማለት ምን ማለት እንደሆነ ጠየቀች። ምሥክሯም “ይሖዋ የእውነተኛው አምላክ ስም ነው” ብለው መለሱላት። ማሱኮ ከልጅነቷ ጀምሮ መጽሐፍ ቅዱስ ታነብ የነበረ ቢሆንም እሷ የምትጠቀምበት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የአምላክን ስም “ጌታ” በሚለው አጠራር ተክቶታል። አሁን አምላክ መጠሪያ ስም ያለው አንድ አካል እንደሆነ አወቀች።

ማሱኮ ወዲያውኑ ከአረጋዊቷ ምሥክር ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። ከሌሊቱ 7:00 ገደማ ከሆስፒታል ወደ ቤት ስመጣ ባለቤቴ በስሜት ተውጣ “መጽሐፍ ቅዱስ በሽታና ሞት እንደሚወገዱ ይናገራል!” አለችኝ። እኔም “እንዲህ ከሆነ ግሩም ነው!” አልኳት። ቀጥላም “አዲሱ ዓለም በቅርቡ ስለሚመጣ ጊዜህን እንድታጠፋ አልፈልግም” አለችኝ። እኔም የሕክምና ሥራህን ተው ማለቷ ስለመሰለኝ ተናደድኩ፤ በመካከላችንም ውጥረት ነገሠ።

ይሁን እንጂ ባለቤቴ የእኔን ፍላጎት ለማነሳሳት ከመሞከር አልተቆጠበችም ነበር። አምላክ እንዲረዳት በመጸለይ ተስማሚ የሆኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥቅሶችን እየፈለገች ታሳየኝ ነበር። በተለይ ልቤን የነኩት የመክብብ 2:22, 23 ቃላት ነበሩ። “ከፀሐይ በታች በደከመበት ድካም ሁሉና በልቡ አሳብ የሰው ጥቅም ምንድር ነው? . . . ልቡም በሌሊት አይተኛም፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።” ይህ ጥቅስ በእኔ ላይ በትክክል ተፈጻሚነት ነበረው፤ ምክንያቱም ሕይወቴን ለሕክምና ሳይንስ በማዋል ቀን ከሌት ብደክምም እውነተኛ እርካታ አላገኘሁም ነበር።

በሐምሌ ወር 1975፣ አንድ እሁድ ቀን ጧት ማሱኮ ወደ ይሖዋ ምሥክሮች የመሰብሰቢያ አዳራሽ ልትሄድ ስትወጣ በድንገት እኔም ለመሄድ ወሰንኩ። ባለቤቴ በመሰብሰቢያ አዳራሹ ስታገኘኝ በጣም ገረማት። ምሥክሮቹም የሞቀ አቀባበል አደረጉልኝ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሁልጊዜ እሁድ  እሁድ ስብሰባ ላይ እገኝ ጀመር። ከአንድ ወር ገደማ በኋላ አንድ የይሖዋ ምሥክር መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናኝ ጀመር። ባለቤቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ከተገናኘች ከሦስት ወር በኋላ ተጠመቀች።

አምላክ ስለ ደም ያለውን አመለካከት መቀበል

ብዙም ሳይቆይ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ‘ከደም እንዲርቁ’ እንደሚያዝዝ ተማርኩ። (የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29፤ ዘፍጥረት 9:4) ደም መስጠት ውጤታማ ስለመሆኑ ጥርጣሬ ስለነበረኝ አምላክ ስለ ደም ያለውን አመለካከት ለመቀበል ምንም አልከበደኝም። * ‘ፈጣሪ ካለና እሱም እንዲህ ብሎ ከተናገረ ትክክል መሆን አለበት’ ብዬ አሰብኩ።

በተጨማሪም የበሽታና የሞት መንስኤ የአዳም ኃጢአት መሆኑን ተማርኩ። (ሮሜ 5:12) በወቅቱ፣ የደም ቅዳ ቧንቧዎችን ግድግዳ በማደንደን የደም ዝውውር ችግር እንዲፈጠር በሚያደርግ አርተሪኦስክሌሮሲስ የተባለ በሽታ ላይ ጥናት እያካሄድኩ ነበር። እያረጀን ስንሄድ የደም ቅዳ ቧንቧችን እየጠነከረና እየጠበበ ሄዶ የልብ በሽታ፣ ወደ አእምሯችን ደም የሚያደርሱት ባንቧዎች መታወክ እና የኩላሊት በሽታ ያስከትላል። የዚህ መንስኤ የወረስነው አለፍጽምና መሆኑ አሳማኝ ምክንያት ሆኖ ታየኝ። ከዚያ በኋላ ለሕክምና የነበረኝ ቅንዓት መቀዝቀዝ ጀመረ። በሽታና ሞትን ሊያስወግድ የሚችለው ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው!

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴን ከጀመርኩ ከሰባት ወር በኋላ መጋቢት 1976 በዩኒቨርሲቲው ሆስፒታል መማሬን አቆምኩ። እንደገና ሐኪም ሆኜ መሥራት አልችልም ብዬ ፈርቼ ነበር። ሆኖም በሌላ ሆስፒታል ሥራ አገኘሁ። በግንቦት ወር 1976 ተጠመቅሁ። ሕይወቴን የምጠቀምበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ማለትም አቅኚ ሆኜ ማገልገል እንደሆነ ወስኜ ስለነበር ሐምሌ 1977 በዚህ አገልግሎት መካፈል ጀመርኩ።

አምላክ ስለ ደም ያለውን አመለካከት ደግፎ መቆም

በኅዳር 1979 እኔና ማሱኮ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት በቺባ ግዛት ወደሚገኝ ጉባኤ ተዛወርን። እዚያም በአንድ ሆስፒታል በቀን ውስጥ ለተወሰነ ሰዓት የምሠራው ሥራ አገኘሁ። ሥራ በጀመርኩበት ቀን የቀዶ ሕክምና ዶክተሮች ከበው “የይሖዋ ምሥክር እንደመሆንህ መጠን ደም መውሰድ የሚያስፈልገው በሽተኛ ቢመጣ ምን ታደርጋለህ?” እያሉ በጥያቄ አዋከቡኝ።

እኔም አምላክ ስለ ደም ያለውን አቋም እንደምከተል በአክብሮት ገለጽኩላቸው። ደም መውሰድን የሚተኩ አማራጭ ሕክምናዎች እንዳሉና ታካሚዎቼን ለመርዳት የተቻለኝን ሁሉ እንደማደርግ አስረዳሁ። ከአንድ ሰዓት ውይይት በኋላ ዋናው የቀዶ ሕክምና ዶክተር “አቋምህ ገብቶኛል። ሆኖም ብዙ ደም የፈሰሰው በሽተኛ ቢመጣ እኛ የሚያስፈልገውን እናደርጋለን” ብሎ መልስ ሰጠ። ይህ ሐኪም የሚታወቀው በአስቸጋሪ ጠባዩ ቢሆንም ከዚያ ውይይት በኋላ ጥሩ ግንኙነት የመሠረትን ሲሆን ምንጊዜም እምነቴን ያከብርልኝ ነበር።

ለደም ያለኝ አክብሮት ተፈተነ

በቺባ ስናገለግል በጃፓን፣ ኤቢና ውስጥ አዲስ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እየተሠራ ነበር። ቤቴል ተብሎ በሚጠራው በዚህ ሕንፃ ግንባታ ለመካፈል የመጡትን ፈቃደኛ ሠራተኞች ጤንነት ለመንከባከብ እኔና ባለቤቴ በሳምንት አንድ ቀን ወደዚያ እንሄድ ነበር። ከጥቂት ወራት በኋላ በኤቢና ቤቴል በሙሉ ጊዜ እንድናገለግል ተጠራን። በመሆኑም መጋቢት 1981፣ ለ500 ፈቃደኛ ሠራተኞች ጊዜያዊ መኖሪያነት በተዘጋጀው ሕንፃ ውስጥ መኖር ጀመርን። ጧት ጧት የግንባታ ሥፍራውን መታጠቢያና መጸዳጃ ቤት በማጽዳት ከረዳሁ በኋላ ከሰዓት በኋላ የሕክምና ምርመራ አካሂድ ነበር።

ከታካሚዎቼ አንዷ በ1949 ሚስዮናዊ ሆና ከአውስትራሊያ ወደ ጃፓን የመጣችው ኢልማ ኢዛሎብ ነበረች። ሉኪሚያ የተባለው በሽታ ስለነበረባት ከጥቂት ወራት በላይ በሕይወት እንደማትቀጥል ሐኪሟ ነግሯት ነበር። ኢልማ ሕይወቷን ለማራዘም ደም መውሰድ አልፈለገችም፤ እስከ ሕይወቷ ፍጻሜ በቤቴል ለመቆየት መረጠች። በዚያ ጊዜ ቀይ የደም ሴሎች እንዲባዙ የሚያደርጉ እንደ ኤሪትሮፖይቲን ያሉ መድኃኒቶች ገና በሥራ ላይ አልዋሉም ነበር።  ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ የሄሞግሎቢኗ መጠን ወደ 3 እና 4 ግራም ይወርድ ነበር! (የጤነኛ ሰው ሄሞግሎቢን ከ12 እስከ 15 ነው።) የሆነ ሆኖ እሷን ለማከም የተቻለኝን ሁሉ አድርጌያለሁ። ኢልማ በጥር ወር 1988 እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ በአምላክ ቃል ላይ የማይናወጥ እምነት በማሳየት ቀጥላለች። ይህም ሐኪሟ ከጥቂት ወራት በላይ በሕይወት አትቆዪም ካላት በኋላ ለሰባት ዓመታት ኖራለች ማለት ነው!

በጃፓን የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በሠራሁባቸው ዓመታት በርካታ ፈቃደኛ ሠራተኞች ቀዶ ሕክምና አስፈልጓቸው ነበር። በአካባቢው በሚገኙ ሆስፒታሎች የሚሠሩ ሐኪሞች ያለ ደም ቀዶ ሕክምና ለማድረግ በመተባበራቸው ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። በተደጋጋሚ ጊዜያት ቀዶ ሕክምናው ወደሚካሄድበት ክፍል ገብቼ እንድመለከትና አንዳንዴም በቀዶ ሕክምናው እንድረዳ ተጋብዣለሁ። የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ደም ያላቸውን አቋም የሚያከብሩ ሐኪሞችን ላመሰግን እወዳለሁ። እንደዚህ ካሉት ሐኪሞች ጋር አብሬ መሥራቴ ስለእምነቴ ለመናገር ብዙ አጋጣሚዎችን ከፍቶልኛል። በቅርቡ ከእነዚያ ሐኪሞች አንዱ የተጠመቀ የይሖዋ ምሥክር ሆኗል።

ሐኪሞች የይሖዋ ምሥክሮችን ያለ ደም ለማከም ያደረጉት ጥረት ለሕክምናው መስክ የጎላ አስተዋጽኦ ማድረጉ ያስደስታል። ያለ ደም የተደረጉ ቀዶ ሕክምናዎች ደም አለመውሰድ ጠቃሚ ለመሆኑ ማስረጃ ናቸው። ደም ሳይወስዱ ቀዶ ሕክምና የተደረገላቸው በሽተኞች ደም ከወሰዱት ይልቅ ቶሎ እንደሚያገግሙና ከቀዶ ሕክምናው በኋላ የሚደርስ ችግርም እንደሚቀንስ ጥናቶች ያሳያሉ።

ከታላቁ ሐኪም መማሬን መቀጠል

በሕክምናው መስክ በቅርብ የተደረጉትን መሻሻልና ለውጥ ለመከታተል እሞክራለሁ። ሆኖም ከታላቁ ሐኪም ከይሖዋ መማሬን እቀጥላለሁ። ይሖዋ የሚያየው እንዲሁ ላይ ላዩን ሳይሆን ሁለመናችንን ነው። (1 ሳሙኤል 16:7) ሐኪም እንደመሆኔ መጠን እኔም የእያንዳንዱን በሽተኛ አጠቃላይ ማንነት ለመመልከት እሞክራለሁ እንጂ በሕመሙ ወይም በሕመሟ ላይ ብቻ አላተኩርም። ይህም ለበሽተኛው የተሻለ ሕክምና ለመስጠት አስችሎኛል።

አሁንም በቤቴል በማገልገል ላይ ነኝ። እስካሁንም ድረስ ከፍተኛ ደስታ የሚሰጠኝ ሌሎች ስለ ይሖዋ እንዲማሩ መርዳት ሲሆን ይህም እርሱ ስለ ደም ያለውን አመለካከት ማሳወቅንም ይጨምራል። ታላቁ ሐኪም ይሖዋ አምላክ ማንኛውንም ዓይነት በሽታና ሞትን በቅርቡ ወደ ፍጻሜ እንዲያመጣው ጸሎቴ ነው።—ያሱሺ አይዛዋ እንደተናገረው

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 በዶክተር ዴኒዝ ሃርሜኒንግ የተዘጋጀው ሞደርን ብለድ ባንኪንግ ኤንድ ትራንስፊውዥን ፕራክቲስስ (ዘመናዊው የደም ባንክና ደም የመስጠት ልማድ) የተሰኘው የመማሪያ መጽሐፍ እንደሚለው “ደም በመውሰዱ ወይም በእርግዝና ምክንያት አሊያም ከሌላ ሰው የተወሰደ አካል ስለተተካለት ቀድሞውንም ሰውነቱ የተቆጣ በሽተኛ . . . ደም ከተሰጠው፣ ከጊዜ በኋላም ቢሆን የቀይ የደም ሴል መፈረካከስ ሊያጋጥመው ይችላል።” እንዲህ ባለው ሁኔታ ሰውነት የተሰጠውን ደም እንዳይቀበል የሚያደርገውን ፀረ እንግዳ አካል (አንቲቦዲ) “ደም ከመሰጠቱ በፊት በሚደረጉት የታወቁ የምርመራ ዘዴዎች ለይቶ ማወቅ አይቻልም።” ዳይሌይስ ኖትስ ኦን ብለድ የተሰኘው ጽሑፍ እንደሚገልጸው የቀይ የደም ሴሎች መፈረካከስ “ከበሽተኛው ደም ጋር የማይስማማ አነስተኛ መጠን ያለው . . . ደም ቢሰጠው እንኳን ሊያጋጥም ይችላል። ኩላሊት ሥራውን ሲያቆም በደም ውስጥ ያለውን ቆሻሻ ማስወገድ ስለማይችል በሽተኛው ቀስ በቀስ ይመረዛል።”

^ አን.8ጆርናል ኦቭ ክሊኒካል ኦንኮሎጂ በነሐሴ 1988 እትሙ ላይ የሚከተለውን ብሏል:- “በቀዶ ሕክምና ወቅት ደም ያልተሰጣቸው የካንሰር ሕመምተኞች ደም ከተሰጣቸው የተሻለ የማገገም አጋጣሚ አላቸው።”

^ አን.16 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ደም የሚያስተምረውን በሚመለከት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ደም ሕይወትህን ሊያድን የሚችለው እንዴት ነው? የተሰኘውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ ብሮሹር ተመልከት።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ደም መውሰድን የሚተኩ አማራጭ ሕክምናዎች እንዳሉና ታካሚዎቼን ለመርዳት የተቻለኝን ሁሉ እንደማደርግ አስረዳሁ”

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ያለ ደም የተደረጉ ቀዶ ሕክምናዎች ደም አለመውሰድ ጠቃሚ ለመሆኑ ማስረጃ ናቸው”

[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ከላይ:- መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር ሳቀርብ

በስተቀኝ:- በአሁኑ ጊዜ ከባለቤቴ ከማሱኮ ጋር