በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሐሳብ ልውውጥ ለምድራችን የሕይወት ሰንሰለት የግድ አስፈላጊ ነው

የሐሳብ ልውውጥ ለምድራችን የሕይወት ሰንሰለት የግድ አስፈላጊ ነው

 የሐሳብ ልውውጥ ለምድራችን የሕይወት ሰንሰለት የግድ አስፈላጊ ነው

ጁሊ ሕፃን ሳለች ወላጆቿ የመጀመሪያዋን ቃል የምታወጣበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቁ ነበር። የጁሊ እናት “‘እማዬ’፣ ‘አባዬ’ የሚሉት ቃላት ከአንድ ሕፃን አፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲወጡ እንደመስማት ወላጅን የሚያስደስት ነገር የለም” ብላለች። “ጁሊ ለመጀመሪያ ጊዜ ‘እማዬ’ ብላ ስትጠራኝ በትናንሽ እጆቿ እቅፍ አድርጋ ‘እናቴ አንቺ ነሽ። እውድሻለሁ፣ ላነጋግርሽም እፈልጋለሁ’ የምትለኝ ያህል ነበር። ያን ልዩ ጊዜ ፈጽሞ አልረሳውም” ትላለች። በእርግጥም ሐሳብ ለሐሳብ የመለዋወጥ ችሎታ ውድ ስጦታ ነው!

እርግጥ ነው፣ ሐሳባቸውን የመግለጽ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ብቻ አይደሉም። እንስሳትም በደመ ነፍስ ቢሆንም አስደናቂ የሆኑ የመነጋገሪያ ዘዴዎች አሏቸው። ለምሳሌ ያህል በረዷማ በሆነው በአንታርክቲካ የሚኖሩ ፔንግዊን የተባሉ የአእዋፍ ዝርያዎች ተጓዳኞቻቸውን የሚያሽኮረምሙበት የክረምቱ ወራት ከመግባቱ በፊት እርስ በርሳቸው ይጯጯሃሉ። ይህን የሚያደርጉት ግን ለጨዋታ ብለው አይደለም። ወደፊት ለሚቀፈቀፈው ጫጩት ሕልውና የግድ አስፈላጊ የሆነ ሥርዓት ነው። እንዴት?

እንስቷ ፔንግዊን የጣለችውን እንቁላል ወንዱ ፔንግዊን በመታቀፊያ ከረጢቱ ውስጥ አቆይቶ እንዲቀፈቅፈው ከሰጠችው በኋላ ምግቧን ለመፈለግ ወደ ባሕሩ ታመራለች። ከስልሳ አምስት ቀናት በኋላ በበረዶ ላይ በደረቷ እየተሳበች 150 ኪሎ ሜትር የሚያክል ርቀት ተጉዛ ትመጣለች። የነበረችበትን ቦታ አውቃ መመለሷ ራሱ ትልቅ ተአምር ቢሆንም ተጓዳኟን ፔንግዊንና የተቀፈቀፈችውን ጫጩት በአሥር ሺህ ከሚቆጠሩት የሚጯጯሁ ፔንግዊኖች እንዴት ለይታ ማወቅ ትችላለች? አንዳቸው ሌላውን በሚያሽኮረምሙበት ጊዜ ያሰሙ የነበረውን ዜማ በሚገባ ስለሚያስታውሱ ለወራት ተለያይተው ከቆዩ በኋላ እንኳን ለመገናኘት ይችላሉ።

እንስሳት የሚነጋገሩት አስደናቂ በሆኑት የተለያዩ የድምፅ ዓይነቶች ብቻ ሳይሆን በአካላዊ እንቅስቃሴ፣ ዓይን በሚስቡ ቀለሞች፣ አንጸባራቂ በሆኑ መብራቶችና ረቂቅ በሆኑ ጠረኖች አማካኝነትም መልእክት ይለዋወጣሉ። ለማመን የሚያዳግት ቢሆንም እንኳ (ወደፊት እንደምንመለከተው) እጽዋትም ጭምር እርስ በርሳቸውና ከአንዳንድ እንስሳት ጋር መነጋገር ይችላሉ። አዎን፣ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ እርስ በርሱ ለሚደጋገፈውና በጣም ውስብስብ ለሆነው የምድራችን የሕይወት ሰንሰለት በእርግጥ አስፈላጊ ነው።

በዙሪያችን ባለው ዓለም ስለሚገኙ አንዳንድ የሐሳብ መለዋወጫ ዘዴዎች ይበልጥ ለማወቅ ትፈልጋለህ? ሐሳብ ለሐሳብ ለመለዋወጥ ችሎታህ ያለህን አድናቆት ከፍ ለማድረግና ይህንንም ችሎታህን ለማሻሻል ትፈልጋለህ? የሚቀጥሉት ርዕሶች በዚህ በኩል ሊረዱህ ይችላሉ።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንስት ፔንግዊን ተጓዳኟን ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?