በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የገናን በዓል የሚመለከቱ አንዳንድ እውነታዎች

የገናን በዓል የሚመለከቱ አንዳንድ እውነታዎች

 የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

የገናን በዓል የሚመለከቱ አንዳንድ እውነታዎች

በዓለም ዙሪያ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በየዓመቱ የገናን በዓል ለማክበር ሽር ጉድ ይላሉ። ምናልባት አንተም ይህን በዓል ለማክበር በጉጉት ከሚጠባበቁት ሰዎች አንዱ ልትሆን ትችላለህ። በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ ታዋቂ ሃይማኖታዊ በዓል የመካፈል ልማድ አይኖርህ ይሆናል። በዚያም ሆነ በዚህ የገና በዓል በሚያሳድረው ተጽዕኖ መነካትህ አይቀርም። ይህ በዓል ክርስቲያን ባልሆኑት አገሮች እንኳ ሳይቀር የንግዱንም ሆነ የመዝናኛውን ዓለም በመቆጣጠር ላይ ይገኛል።

ስለ ገና በዓል ምን የምታውቀው ነገር አለ? የክርስቶስን የልደት በዓል ማክበር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ አለው? በየዓመቱ በታኅሣሥ ወር መጨረሻ ላይ የሚከበረው ይህ በዓል ከየት የመነጨ ነው?

የገና በዓል ታገደ

በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ጥቂት ምርምር ብታደርግ የገና በዓል ከእውነተኛው የክርስትና እምነት የመነጨ እንዳልሆነ ትገነዘባለህ። በተለያዩ ሃይማኖቶች ውስጥ ያሉ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን በዚህ ይስማማሉ። በመሆኑም በ1647 በእንግሊዝ የክሮምዌል ፓርላማ የገና በዓል የሚከበርበት እለት የሱባዔ ቀን እንዲሆን መወሰኑና በ1652 ደግሞ እስከ ጭራሹ ገና እንዳይከበር እገዳ መጣሉ አያስገርምም። ከ1644 እስከ 1656 ባለው ጊዜ ውስጥ በየዓመቱ ታኅሣሥ 25 ላይ ሆነ ተብሎ የፓርላማ ስብሰባ ይደረግ ነበር። ታሪክ ጸሐፊዋ ፔኒ ኤል ሬስታድ እንደተናገሩት “ስለ ክርስቶስ ልደት የሚሰብኩ ቄሶች ሊታሰሩ እንደሚችሉ ያውቁ ነበር። የቤተ ክርስቲያኑን ንብረት የሚንከባከቡት ሰዎች አብያተ ክርስቲያኖቻቸውን ለገና በዓል ካስጌጡ መቀጫ እንዲከፍሉ ይደረጉ ነበር። እንደማንኛውም የሥራ ቀን ሁሉ በገና በዓል ዕለትም ሱቆች ክፍት እንዲሆኑ በሕግ ተደንግጎ ነበር።” እንደዚህ ዓይነት ከባድ እርምጃ የተወሰደው ለምን ነበር? ፒዩረተን ተብለው የሚጠሩት የፕሮቴስታንት የተሃድሶ አራማጆች ቤተ ክርስቲያን በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የማይገኙ ወጎችን መፍጠር የለባትም የሚል እምነት ነበራቸው። የገናን በዓል በማውገዝ ይሰብኩ እንዲሁም ጽሑፎችን ያሰራጩ ነበር።

በሰሜን አሜሪካም ተመሳሳይ አመለካከት ሰፍኖ ነበር። ከ1659 እስከ 1681 ባለው ጊዜ ውስጥ በማሳቹሴትስ ቤይ የገና በዓል እንዳይከበር ታግዶ ነበር። * በወቅቱ በወጣው ሕግ መሠረት በማንኛውም ዓይነት መልኩ ገናን ማክበር የተከለከለ ሲሆን ይህንን ሕግ የጣሱ ሰዎችም ይቀጡ ነበር። የገናን በዓል የተቃወሙት በኒው ኢንግላንድ የሚገኙት የፕሮቴስታንት የተሃድሶ አራማጆች ብቻ አልነበሩም፤ በመካከለኛው የአሜሪካ ግዛት የነበሩ አንዳንድ ቡድኖችም ተመሳሳይ አመለካከት ነበራቸው። በፔንሲልቬንያ ኩዌከርስ ተብሎ የሚጠራው ሃይማኖት አባላት ገናን በተመለከተ የፕሮቴስታንት የተሃድሶ አራማጆች ዓይነት ግትር አቋም ነበራቸው። አንድ ምንጭ እንዲህ ይላል:- “አሜሪካውያን ወዲያው ነጻነታቸውን እንዳገኙ ራስዋ የኩዌከር ሃይማኖት ተከታይ የሆነችው ኤሊዛቤት ደሪንከር የፊላደልፊያን ነዋሪዎች ‘[ገና] የሚከበርበትን እለት እንደ ማንኛውም አዘቦት ቀን የሚመለከቱት’ የኩዌከር ሃይማኖት ተከታዮች፣ በሃይማኖታዊ ምክንያት ገናን የሚያከብሩ ሰዎች እና ቀኑን ‘በዓመፅና በብኩንነት የሚያሳልፉ’ ሰዎች በማለት በሦስት ቡድኖች ከፈለቻቸው።”

የካልቪን አመለካከት አራማጅ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ ሄንሪ ዋርድ ቢቸር የተባሉ ታዋቂ አሜሪካዊ ሰባኪ 30 ዓመት እስኪሆናቸው ድረስ ስለ ገና በዓል ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበረም። በ1874 ቢቸር “ገና ለእኔ ያልተለመደ በዓል ነበር” ሲሉ ጽፈዋል።

የቀድሞዎቹ የባብቲስትና የኮንግርጌሽናሊስት አብያተ ክርስቲያናትም የክርስቶስን ልደት ለማክበር  መሠረት የሚሆን ምንም ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ አላገኙም ነበር። አንድ ምንጭ በኒው ፖርት [ሮድ ደሴት] የሚገኘው የባብቲስት ቤተ ክርስቲያን ገናን ለመጀመሪያ ጊዜ ያከበረው በታኅሣሥ 25, 1772 እንደሆነ ይገልጻል። ይህም የመጀመሪያው የባብቲስት ቤተ ክርስቲያን በኒው ኢንግላንድ ከተቋቋመ 130 ዓመታት ገደማ በኋላ ማለት ነው።

የገና በዓል አመጣጥ

ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔዲያ እንደሚከተለው በማለት ይገልጻል:- “ክርስቶስ የተወለደበት ቀን አይታወቅም። ወንጌሎች ቀኑንም ሆነ ወሩን አይገልጹም። . . . ኤች ኡዝነር ባቀረቡትና . . . ዛሬ ባሉ በርካታ ምሁራን ዘንድ ተቀባይነት ባገኘው መላ ምት መሠረት የክርስቶስ ልደት የክረምቱ ማብቂያ በሚውልበት ቀን (በጁሊያን የቀን መቁጠሪያ መሠረት ታኅሣሥ 25፣ በኢትዮጵያውያን የቀን መቁጠሪያ መሠረት ታኅሣሥ 29) ላይ እንዲሆን የተወሰነው በዚህ ቀን ፀሐይ ወደ ሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ መመለስ ስትጀምር ሚትራ የተባለችው አምላክ አረማዊ አምላኪዎች ዲይስ ናታሊስ ሶሊስ ኢንዊክቲ (የማትበገረዋ ፀሐይ የልደት ቀን) የተባለውን በዓል ያከብሩ ስለነበረ ነው። ታኅሣሥ 25, 274 እዘአ ኦሪሊየን የተባለው የሮማ ንጉሠ ነገሥት የፀሐይን አምላክ የሮም ግዛት ዋና ጠባቂ ብሎ የሰየመው ሲሆን በካምፐስ ማርቲየስ ቤተ መቅደስ ሠርቶለታል። የገና በዓል አከባበር የመጣው የፀሐይ አምልኮ በሮማ በገነነበት ወቅት ላይ ነው።”

የማክሊንቶክና ስትሮንግስ ሳይክሎፔዲያ እንዲህ ይላል:- “ገና መለኮታዊ ድጋፍ የሌለውና [በአዲስ ኪዳን] ውስጥ የማይገኝ በዓል ነው። ክርስቶስ የተወለደበትን ቀን ከ[አዲስ ኪዳንም] ሆነ ከሌላ ከየትኛውም ምንጭ ማረጋገጥ አይቻልም።”

‘ከንቱ ማታለያ’

ከላይ ከቀረቡት ነጥቦች አንጻር እውነተኛ ክርስቲያኖች በገና በዓል በሚደረጉት ልማዶች መካፈል ይኖርባቸዋልን? አምላክ ለእሱ የሚቀርበው አምልኮ እሱን ከማያመልኩ ሰዎች ሃይማኖታዊ እምነቶችና ልማዶች ጋር መቀላቀሉ ያስደስተዋልን? ሐዋርያው ጳውሎስ በቆላስይስ 2:8 ላይ እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል:- “እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፣ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ።”

ሐዋርያው እንደሚከተለው በማለትም ጽፏል:- “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስስ ከቤልሆር [ሰይጣን] ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው?”—2 ቆሮንቶስ 6:14, 15

የይሖዋ ምሥክሮች ይህንን የማያሻማ መረጃ ስለሚያውቁ የገናን በዓል አያከብሩም። ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር በሚስማማ መልኩ ራሳቸውን ‘በዓለም ከሚገኝ እድፍ በመጠበቅ ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ ለእግዚአብሔር’ ለማቅረብ ይጥራሉ።—ያዕቆብ 1:27

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 ማሳቹሴትስ ቤይ የእንግሊዝ የፕሮቴስታንት ተሃድሶ አራማጆች በ1628 ያቋቋሙት ግዛት ሲሆን በኒው ኢንግላንድ ከተቆረቆሩት የመጀመሪያ ግዛቶች ሁሉ ሰፊና በጣም ስኬታማ ግዛት ነው።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በ1652 የእንግሊዝ ፓርላማ ገና እንዳይከበር አግዶ ነበር

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ገና ለእኔ ያልተለመደ በዓል ነበር”—አሜሪካዊው ቄስ ሄንሪ ዋርድ ቢቸር

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሚትራስ እና የፀሐይ አምላክ አማኞች የሆኑ አረማውያን (በውቅር ምስሉ ላይ የሚታዩት) ታኅሣሥ 25ን ያከብሩ ነበር

[ምንጭ]

Musée du Louvre, Paris