በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሕይወትህ በቁጥሮች ስሌት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባልን?

ሕይወትህ በቁጥሮች ስሌት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባልን?

ሕይወትህ በቁጥሮች ስሌት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባልን?

በቁጥሮች ላይ የተመሠረተ የአውደ ነገሥት ትንበያ በሳይንስና በተጨባጭ ሁኔታዎች ቢመዘን ፈተናውን ያልፍ ይሆን? በቁጥሮች አማካኝነት የወደፊት ዕጣችንን ማወቅ እንችላለን? የወደፊት ሕይወትህስ በአውደ ነገሥት ስሌትና ትንበያ ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታልን?

አውደ ነገሥት ገላጮች መፍትሔ ያጡለት አንዱ ትልቁ ችግር የተለያዩ ኅብረተሰቦች የተለያዩ የቀን መቁጠሪያዎች መጠቀማቸው ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው የሚኖረው የቻይናውያን የቀን አቆጣጠር በሚሠራበት አካባቢ ቢሆንስ? በመግቢያው ርዕሳችን ላይ የተጠቀሰውን መስከረም 11, 2001 እንውሰድ። በቻይናውያን የቀን አቆጣጠር መሠረት ይህ ቀን የዋለው በ78ኛው ክፍለ ዘመን፣ በ18ኛው ዓመት፣ ሰባተኛው ወር 24ኛ ቀን ላይ ነው። ይኸው ዕለት በኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር መስከረም 1, 1994 ላይ ውሏል። በሙስሊሞች አቆጣጠር 2ኛ ጁማዳ 22, 1422 ነው። በዕብራውያን አቆጣጠር ኤሉል 23, 5761 ነበር። ታዲያ በእነዚህ ሁሉ የተለያዩ አቆጣጠሮች የተገለጸ ዕለት ቁጥር እንዴት ልዩ የሆነ ትርጉም ሊኖረው ይችላል? ሌላው ነገር ደግሞ ስሞች በተለያዩ ቋንቋዎች በተለያዩ ሆሄያት የሚጻፉ መሆናቸው ነው። ለምሳሌ በአውደ ነገሥት ስሌት መሠረት ጆን በሚለው የእንግሊዝኛ ስም ውስጥ ላሉት ሆሄያት የሚሰጠው ቁጥር 2 ነው። ይኸው ስም በስፓንኛ ሲጻፍ ግን ሁዋን ስለሚባል የሚሰጠው ቁጥር 1 ነው።

የጽንፈ ዓለማችን ብዙ ገጽታዎች በአኃዛዊ ቀመር ሊገለጹ ይችላሉ ብሎ ማሰብ አንድ ነገር ነው። እነዚህ ቀመሮች ሙከራ ሊደረግባቸውና ትክክለኛነታቸውም ሊረጋገጥ ይችላል። የግል ስምህ ከተወለድክበት ቀን ጋር እንዲገጣጠም አስቀድሞ የተወሰነና ከተለየ ቁጥር ጋር እንዲተሳሰር የተደረገ በመሆኑ የወደፊት ዕጣህን ማወቅ ትችላለህ ማለት ግን ፈጽሞ የተለየ ነገር ነው።

በዚህ ረገድ የምንደርስበት መደምደሚያ ግልጽ ነው። የአውደ ነገሥት ስሌት እንደየቀን አቆጣጠሩና እንደየቋንቋው የተለያየ ውጤት የሚሰጥ መሆኑ እየታወቀ የሚሰጠው ትንበያ ትክክል ነው ብሎ ማመን ሞኝነት ነው።

“ጊዜና አጋጣሚ”

አንዳንዶች የአውደ ነገሥት ትንበያን የሚከታተሉት በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ነገሮች አስቀድመው ማወቅ ስለሚፈልጉ ነው። ይሁን እንጂ የሰው ልጅ በሕይወቱ ውስጥ የሚያጋጥሙትን ነገሮች አንድ በአንድ አስቀድሞ ማወቅ እንደማይቻል መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። ‘ሩጫ ለፈጣኖች፣ ሰልፍም ለኃያላን፣ እንጀራም ለጠቢባን፣ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፣ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል’ ይላል። (መክብብ 9:11) አዎን፣ ብዙ ነገሮች የሚሆኑት በድንገትና ሳይጠበቁ ነው። በእነዚህ ድንገተኛ ክስተቶች ምክንያት በልደት ቀንና ለመጠሪያ ስም በሚሰጥ የቁጥር ስሌት ላይ ተመስርቶ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ ነገሮችን መተንበይ የማይቻል ነገር ነው።

ሌላ ምሳሌ እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ ለጋስ መሆንን ሲያበረታታ ‘እንጀራህን በውኃ ፊት ላይ ጣለው፣ ከብዙ ቀን በኋላ ታገኘዋለህና። ለሰባት ደግሞም ለስምንት እድል ፈንታን ክፈል፣ በምድር ላይ የሚሆነውን ክፉ ነገር ምን እንደ ሆነ አታውቅምና’ ይላል። (መክብብ 11:1, 2) አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ክፉ ነገር እንደሚመጣ አስቀድመው አያውቁም፣ ሊያውቁም አይችሉም። በዚህም የተነሣ የሂሣብ ፕሮፌሰር የሆኑት አንደርዉድ ዱድሊ መጽሐፍ ገላጮች “በድንገት የሚከሰቱ ነገሮችን ግምት ውስጥ አያስገቡም። አንድ ወጥ ሥርዓት፣ እቅድና አካሄድ ሳይከተሉ በዘፈቀደ የሚከሰቱ ነገሮች በርካታ ናቸው” ብለዋል።

መጽሐፍ ገላጮች አንዳንድ ጊዜ የሚተነብዩአቸው ነገሮች በትክክል ሊፈጸሙ ይችሉ ይሆናል። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? አንዳንድ ጊዜ ይህ የሚሆነው እንዲሁ እንደ አጋጣሚ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም የመጽሐፍ ገላጮች አነጋገር ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ የተለያየ ትርጉም ሊሰጠው ይችላል። ይሁን እንጂ ከዚህም የበለጠ አሳሳቢ ነገር አለ።

ጥንቆላ ነውን?

መጽሐፍ ቅዱስ በቁጥሮች ላይ የተመሠረተን የአውደ ነገሥት ትንበያ በስም አይጠቅስም። ይሁን እንጂ ሐማ የተባለ አንድ አማሌቃዊ ሰው በአምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በፋርስ ግዛት ይኖሩ የነበሩትን አይሁዳውያን ለማጥፋት ስለጠነሰሰው ሴራ ይነግረናል። ታሪኩ ‘ቀኑንና ወሩን ለመለየት ፉር የተባለ ዕጣ ሐማ ባለበት ጣሉ፤ ዕጣውም አዳር በተባለው በዐሥራ ሁለተኛው ወር ላይ ወደቀ’ ይላል።—አስቴር 3:7 አ.መ.ት

በጥንት ዘመን ለአንድ አከራካሪ ጉዳይ እልባት ለመስጠት ዕጣ ይጣል ነበር። * (ምሳሌ 18:18) ሐማ ግን ዕጣ ያስጣለው ለመጠንቆል ሲል ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ጥንቆላን ያወግዛል። ዘዳግም 18:10-12 “ምዋርተኛም፣ ሞራ ገላጭም፣ አስማተኛም፣ መተተኛም፣ በድግምት የሚጠነቁልም፣ መናፍስትንም የሚጠራ፣ ጠንቋይም፣ . . . በአንተ ዘንድ አይገኝ። ይህንም የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው” ይላል።

መጽሐፍ ቅዱስ ጥንቆላንና አስማት የማድረግን ኃይል የሚያዛምደው ከመናፍስታዊ ድርጊት ጋር ነው። ክፉ መናፍስት አንዳንድ ሁኔታዎች እነርሱ በሚፈልጉት መንገድ እንዲፈጸሙ ሊያደርጉ ይችላሉ። ያም ሆነ ይህ አንድ የተረጋገጠ ነገር አለ:- ማንኛውም ከመናፍስት ጋር ግንኙነት ያለው ድርጊት በአምላክ የተወገዘ ከመሆኑም በላይ አንድን ሰው በክፉ መናፍስት ቁጥጥር ሥር እንዲወድቅ ሊያደርግ ይችላል።—1 ሳሙኤል 15:23፤ ኤፌሶን 6:12

አውደ ነገሥት መግለጥ ምንም ዓይነት ሳይንሳዊ ድጋፍ የለውም። በምክንያታዊ አስተሳሰብ ሲለካም ሚዛን አይደፋም። ከሁሉ በላይ ደግሞ ከጥንቆላ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር ይጋጫል። በዚህ የተነሣ አውደ ነገሥት ሕይወትህን ለመምራትም ሆነ ስለወደፊት ዕጣህ ለማወቅ ጠቃሚ መመሪያ የምታገኝበት መሣሪያ አይደለም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.12 ዕጣ በሚጣልበት ጊዜ እንደ ጠጠር ወይም እንደ ቁርጥራጭ እንጨት ያለ ትናንሽ ነገር በታጠፈ ጨርቅ ወይም በሌላ ዕቃ ውስጥ ይደረጋል። ከዚያም ይነቀነቅና ይጣላል። በዚህ መንገድ ዕጣው የወጣለት ይመረጣል።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የቀን አቆጣጠሮች የተለያዩ መሆናቸው በአውደ ነገሥት ትንበያ ላይ ትልቅ እንቅፋት ይፈጥራል

በጎርጎሳውያን አቆጣጠር መስከረም 11, 2001

በቻይናውያን አቆጣጠር የ78ኛው ክፍለ ዘመን የ18ኛው ዓመት 7ኛ ወር 24ኛ ቀን

በኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር መስከረም 1, 1994

በሙስሊሞች አቆጣጠር 2ኛ ጁማዳ 22, 1422

በዕብራውያን አቆጣጠር 23 ኤሉል 5761

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ኮከብ ቆጠራ የሚሰጠው መግለጫና ትንበያ አስተማማኝ ነው?

“አንዳንድ ጊዜ ተጫዋች ትሆናለህ። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ዝምተኛና ቁጥብ ትሆናለህ። እንግዳ ከሆኑ ሰዎች ጋር ቶሎ መቀራረብ ጥሩ መስሎ አይታይህም። የራስህ የሆነ አስተሳሰብ ያለህና በቂ ማስረጃ ካልቀረበልህ ቶሎ ብለህ ነገሮችን የማታምን ሰው ነህ። የተለያዩ ነገሮችን መቅመስና መሞከር ያስደስትሃል። በማያፈናፍኑ ሕጎችና ደንቦች ታፍነህ ስትያዝ ግን ትበሳጫለህ። ብዙ የመሥራትና የማደግ እቅምና ችሎታ እያለህ በሚገባ አልተጠቀምክበትም። በችሎታህና በአሠራርህ ቅር የመሰኘት አዝማሚያ ይታይብሃል።”

ይህ መግለጫ አንተን በትክክል የሚገልጽ እንደሆነ ይሰማሃል? እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ለመግለጫው ከልክ ያለፈ ትርጉም ሰጥተሃል ማለት ነው። ምክንያቱም በዚህ መግለጫ ውስጥ የተጠቀሰው አብዛኛው ነገር ከብዙዎቹ ሰዎች ሁኔታ ጋር የሚስማማ ነው። በዚህ የተነሣ አንባቢዎች ከእነሱ ሁኔታ ጋር የማይሄደውን መግለጫ ችላ ብለው በማለፍ ከእነሱ ባሕርይ ጋር በሚመሳሰሉት መግለጫዎች ላይ ሲያተኩሩ ይስተዋላል። ዋይ ዱ ባስስ ካም ኢን ስሪስ—ዘ ሂድን ማቲማቲክስ ኦቭ ኤቭሪዴይ ላይፍ የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው “ተመራማሪዎች በሆሮስኮፕ ቻርት ላይ የሚገኘው የኮከቦች ስም ባይኖር ሰዎች የትኛው አንቀጽ ስለ እነርሱ እንደሚናገር ለመለየት እንደማይችሉ፣ የኮከቦቹ ስም በሚኖርበት ጊዜ ግን በኮከባቸው ሥር የተሰጠው መግለጫ ስለ እነርሱ በትክክል ይናገራል ብለው እንደሚያምኑ ደርሰውበታል።”

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ምሳሌያዊ ቁጥሮች

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ቁጥሮች ምሳሌያዊ ትርጉም አላቸው። ትርጉማቸው ግን በተጠቀሱበት ጥቅስ ዙሪያ ባለው ሐሳብ ብቻ የተወሰነ ነው። ለምሳሌ፣ አራት ቁጥር ሙሉ ወይም አጠቃላይ የሆነን ነገር ለማመልከት ተሠርቶበታል። ይህ ሐሳብ “አራቱ የምድር ማዕዘኖች” እና “አራቱም የሰማይ ነፋሳት” በሚሉት ሐረጎች ተገልጿል። (ኢሳይያስ 11:12፤ ዳንኤል 8:8) ስድስት ቁጥር ፍጹም አለመሆንን የሚያመለክትበት ጊዜ አለ። የራእይ መጽሐፍ ለሰይጣን ምድራዊ የፖለቲካ ድርጅት የሰጠው ቁጥር “የሰው ቁጥር” ሲሆን ቁጥሩም 666 ነው። (ራእይ 13:18) እዚህ ላይ ስድስት ቁጥር ሦስት ጊዜ ተደጋግሞ መጠቀሱ ይህ አውሬያዊ ድርጅት በጣም ፍጽምና የጎደለው መሆኑን ያመለክታል። ሰባት ቁጥር በምሳሌያዊ መንገድ ሲሠራበት ምልዓትን ያመለክታል። (ዘሌዋውያን 4:6፤ ዕብራውያን 9:24-26) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት እነዚህና ሌሎች ምሳሌያዊ ትርጉም ያላቸው ቁጥሮች የተለየ ትርጉም የሚያሰጣቸው የተጠቀሱበት ትንቢታዊ ሐሳብ ነው።

ቅዱሳን ጽሑፎች ለአንዳንድ ቁጥሮች የተለየ ትርጉም ይስጡ እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የአንዳንድ ቃሎችን ሆሄያት ከቁጥሮች ጋር አቀናጅተን ምሥጢራዊ እውነቶች ለመፍታት እንድንሞክር አያበረታታንም።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሃማ የዘር ማጥፋት ሴራውን የሚያካሂድበትን ቀን የመረጠው በጥንቆላ ተጠቅሞ ነበር