በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሕይወት—በእንክብካቤ መያዝ የሚገባው ስጦታ

ሕይወት—በእንክብካቤ መያዝ የሚገባው ስጦታ

ይሖዋ አምላክ ለሰብዓዊው ቤተሰብ ልጅ የመውለድን ልዩ መብት ማደሉ ይህ ነው የማይባል ውድ ስጦታ ነው! በአምላክ ዓላማ መሠረት አንድ ድንቡሽቡሽ ያለ ሕፃን በጉጉት ሲጠባበቁት በነበሩትና የትዳራቸው ጥምረት ፍሬ የሆነውን እምቦቀቅላ ተንከባክበው ለመያዝ ተዘጋጅተው በሚጠብቁት የሚዋደዱ ባልና ሚስት እቅፍ ውስጥ ይገባል። ልጁ ወደ ገሃዱ ዓለም ብቅ ሲል ቤተሰቡ ደስታ በደስታ ይሆናል።

ይሁን እንጂ አዳምና ሔዋን የሠሩት ኃጢአት በሰብዓዊው ዘር ውስጥ ለሚወለዱት ሕፃናት አሳዛኝ ውጤቶችን አምጥቶባቸዋል። የመጀመሪያዋ እናታችን በሠራችው ኃጢአት የተነሣ ልጆችን በጭንቅና በሥቃይ እንድትወልድ ተረገመች። ሕፃኑ ብቅ የሚልበት በኃጢአት የተሞላ ዓለም ደግሞ ልጅ ማሳደግን አዳጋች አድርጎታል። በመሆኑም ውጥንቅጡ በወጣው በዛሬው ዓለም ውስጥ ብዙውን ጊዜ አንድ ልጅ ሲፀነስ ሰዎች አለመደሰታቸው የሚያስደንቅ አይደለም። ሆኖም ፈጣሪ ስላልተወለደው ሕፃን ያለው አመለካከት ምንድን ነው? አመለካከቱ እየተለወጡ ካሉት የሥነ ምግባር ሁኔታዎች ጋር አብሮ ተለውጧልን? በፍጹም አልተለወጠም። ገና ስላልተወለዱት የዚህ ዓለም ልጆች ያለው አመለካከትና ለእነርሱ ያለው አሳቢነት እንዳለ ነው።

በእናት ማኅፀን ውስጥ አንድ ልዩ ሰብዓዊ ግለሰብ እንደሚያድግ ቅዱሳን ጽሑፎች ቁልጭ አድርገው ይገልጻሉ። ሕይወት የሚጀምረው ከፅንስ ነው። ሕፃኑ ወደ ዓለም ብቅ ሲል ሰው የሚያየው አምላክ አስቀድሞ ያየውን ልጅ ነው። ሕዝቅኤል ‘እያንዳንዱ ማኅፀንን የሚከፍት ልጅ’ ሲል ተናግሯል። (ሕዝቅኤል 20:​26) ኢዮብ “የእናቴ ማኅፀን ደጅ” በማለት ገልጿል። ጭንጋፍ የሆኑትንም ልጆች ‘ብርሃን ያላዩ ሕፃናት’ ሲል ጠርቷቸዋል።​—ኢዮብ 3:​10, 16

ይሖዋ አምላክ በማኅፀን ውስጥ በማደግ ላይ ላለ ለጋ ሕይወት ያለውን ርኅራኄ ልብ በል። ኤርምያስን “በሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፣ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ” ብሎታል። (ኤርምያስ 1:​5) ዳዊት እንዲህ ብሏል:- “እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፣ አካሌም በምድር ታች በተሠራ ጊዜ፣ አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም። ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ።” (መዝሙር 139:​15, 16) ኢዮብ “እኔን በማኅፀን የፈጠረ” ከዚያም “በማኅፀን ውስጥ የሠራን” ሲል አምላክን ጠርቶታል።​—ኢዮብ 31:⁠15

ይሁን እንጂ አምላክ ልጅ ሳትፈልግ ስለፀነሰችና በዚህም ሳቢያ ሆድ ስለባሳት ሴት ያለው ስሜት ምንድን ነው? ፈጣሪ ከባድ የሆኑትን የወላጅ ኃላፊነቶች ከማንም ሰው የበለጠ ያውቃል። አንዲት የፀነሰች እናት በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የምትገኝ ብትሆንም እንኳ የአምላክን ሥርዓቶች ለማክበር ስትል ልጅዋን ላለማስወረድ ከመረጠች ውሳኔዋን አይባርክላትምን? አንድ ወላጅ ደስተኛ ልጅ ማሳደግ እንዲችል የአምላክን እርዳታ ለማግኘት መጸለይ ይችላል፤ ይኖርበታልም። አምላክ በቃሉ ገጾች ላይ ልጆችን ለማሳደግ የሚረዳ ከሁሉ የተሻለ ምክር ሰጥቷል። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በቤተሰብ ኑሮ ውስጥ መተግበር በረከቶችን ያስገኛል። አምላክን የሚፈሩ ልጆችን ማሳደግ የሚያስገኘው ደስታና ካሳ ልጆችን ለማሳደግ ከተከፈለው ማንኛውም ዓይነት መሥዋዕትነት ሚዛን የሚደፋ መሆኑን ማንኛውም በልጆቹ የሚኮራ ወላጅ ሊመሠክር ይችላል።

ሕፃኑ የተወለደው ሴቲቱን አስገድዶ በመድፈር ወይም ከአንድ የሥጋ ዘመድ ጋር በተፈጸመ የጾታ ግንኙነት ከሆነ ይሖዋ ጉዳዩን ለየት ባለ መንገድ ይመለከተዋልን? በእናቲቱ ላይ የተፈጸመው ድርጊት ወንጀል ቢሆንም እንኳ ሕፃኑ ተጠያቂ ሊሆን አይችልም። ሕይወቱን መቅጨት ዓመፅን በዓመፅ ለመከላከል መሞከር ካልሆነ በስተቀር የሚፈይደው ነገር የለም። ይሖዋ የእንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ሰለባ የሆኑ ሰዎች በስሜታቸው ላይ የደረሰውን የዕድሜ ልክ ሰቀቀን እንደሚገነዘብና እናቲቱና ልጅዋ ችግሩ ያስከተለውን መዘዝ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መቋቋም እንዲችሉ ሊረዳቸው እንደሚችል ጥርጥር የለውም።

አንድ ዶክተር ለአንዲት ነፍሰ ጡር ልጁ እስከ መጨረሻው ወር ድረስ በማኅፀንዋ ከቆየ ሕይወቷን አደጋ ላይ ሊጥለው እንደሚችል ከነገራትስ ምን ማድረግ ይቻላል? ዶክተር አለን ጉትማቸር እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “በዛሬው ጊዜ የትኛዋም ታካሚ እንደ ካንሰር ወይም ሉኬሚያ ባሉ ገዳይ በሽታዎች የምትሠቃይ ካልሆነች በስተቀር ልጅዋን በደህና ትገላገላለች ማለት ይቻላል። እነዚህን የመሳሰሉ በሽታዎች ካሉባትም ፅንሱን ማስወረድ ሕይወቷን ሊያራዝምላት ቀርቶ ከሞት የመትረፏ አጋጣሚ በጣም የመነመነ ነው።” ዘ ኢንሳይክሎፔድያ አሜሪካና እንዲህ በማለት ገልጿል:- “አብዛኛዎቹ ሴቶች ከባድ የሕክምና ችግሮች ቢያጋጥሟቸውም እንኳ በደህና መገላገል የሚችሉ በመሆኑ የእናቶችን ጤንነት ለመጠበቅ ሲባል ውርጃን መፍቀድ እምብዛም አስፈላጊ አይደለም። አብዛኛዎቹ ውርጃዎች የሚፈጸሙት ልጅ ላለመውለድ ሲባል ነው።” ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ከስንት አንዴ ቢከሰቱ ነው። ይህ ሁኔታ በምጥ ወቅት ላይ ከተከሰተ ግን ወላጆቹ የግድ ከእናቲቱና ከልጁ ሕይወት አንዱን መምረጥ አለባቸው። ይህ የራሳቸው ውሳኔ ነው።

የሕይወት ፈጣሪ ልጅ የመውለድ ችሎታችንን እንዴት ልንጠቀምበት እንደሚገባ ግልጽ መመሪያዎችን ማስቀመጡ ሊያስደንቀን ይገባልን? አንድ ሰው በእንክብካቤ ሊይዘው የማይችለውን ሕይወት ወደ ሕልውና ማምጣቱ በአምላክ ዘንድ ሕይወትን የማጥፋት ያህል ኃጢአት ነው።

ነገሩ እስከ ሥርዓቱ ፍጻሜ ድረስ አወዛጋቢ መሆኑ አይቀርም። ሆኖም የሕይወት ፈጣሪ ለሆነው ለይሖዋ አምላክና የእሱን ሕግጋት እጅግ ለሚያከብሩት ሰዎች ጉዳዩ ምንም የሚያጠያይቅ አይደለም። ሕይወት ገና ከጅምሩ በጥንቃቄና በልዩ እንክብካቤ ሊያዝ የሚገባው ውድ ስጦታ ነው።

ሸክሙን የሚጋራ አባት ከሌለ ልጁን ማሳደግ ቀላል አይሆንም። ይሁን እንጂ ከሰማያዊ አባታችን ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረት አንዲት እናት ልጅን ለማሳደግ የሚያስፈልገውን የሞራልና የስሜት ብርታት፣ ድጋፍና መመሪያ እንድታገኝ ያስችላታል። የነጠላ ወላጆችን ሸክም ለማቅለል የክርስቲያን ጉባኤንም አዘጋጅቷል።