በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ትምህርት 5

የአዋቂዎች መመሪያ አስፈላጊነት

የአዋቂዎች መመሪያ አስፈላጊነት

አዋቂዎች የሚሰጡት መመሪያ ምን ነገሮችን ያጠቃልላል?

ልጆች በሕይወታቸው ውስጥ የአዋቂዎች አመራርና ምክር ያስፈልጋቸዋል። ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን ይህን ሚና ለመጫወት ከሁሉ የተሻለ አጋጣሚ ያላችሁ እናንተ ናችሁ፤ ደግሞም እንዲህ የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎባችኋል። ይሁን እንጂ ሌሎች አዋቂዎችም ለልጆቻችሁ ጥሩ መካሪ ሊሆኑ ይችላሉ።

የአዋቂዎች መመሪያ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

በብዙ አገሮች ውስጥ፣ ልጆች ከአዋቂዎች ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ በጣም አጭር ነው። እስቲ የሚከተሉትን ነጥቦች ተመልከት፦

  • ልጆች አብዛኛውን የቀኑን ክፍለ ጊዜ የሚያሳልፉት በትምህርት ቤት ሲሆን በዚያ ደግሞ የተማሪዎች ቁጥር ከአስተማሪዎችና ከሌሎች አዋቂዎች ቁጥር በእጅጉ ይበልጣል።

  • አንዳንድ ልጆች ሁለቱም ወላጆቻቸው ሥራ ቦታ ስለሚሆኑ ከትምህርት ቤት ሲመለሱ የሚጠብቃቸው ባዶ ቤት ነው።

  • አንድ ጥናት እንዳረጋገጠው፣ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ያሉ ከ8 እስከ 12 ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች በየቀኑ በአማካይ ስድስት ሰዓት ያህሉን ጊዜ የሚያሳልፉት የመዝናኛ ሚዲያ በመጠቀም ነው። *

ሆልድ ኦን ቱ ዩር ኪድስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል፦ “ልጆች መመሪያና ምክር የሚጠይቁት ወይም አርዓያ አድርገው የሚመለከቱት እናቶቻቸውን፣ አባቶቻቸውን፣ አስተማሪዎቻቸውንና ኃላፊነት የሚሰማቸውን ሌሎች አዋቂዎች ሳይሆን . . . የገዛ እኩዮቻቸውን ሆኗል።”

ለልጆች መመሪያ መስጠት የሚቻለው እንዴት ነው?

ከልጆቻችሁ ጋር ጊዜ አሳልፉ።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ልጅን ሊሄድበት በሚገባው መንገድ አሠልጥነው፤ በሚያረጅበት ጊዜም እንኳ ከዚያ ፈቀቅ አይልም።”—ምሳሌ 22:6

ልጆች በተፈጥሯቸው መመሪያ ለማግኘት የሚሞክሩት ከወላጆቻቸው ነው። እንዲያውም ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ልጆች አሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ከደረሱ በኋላም እንኳ ከእኩዮቻቸው ምክር ይልቅ ለወላጆቻቸው ምክር ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ። ዶክተር ሎረንስ ስቲንበርግ ዩ ኤንድ ዩር አዶለሰንት በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ልጆች ጉርምስናን አልፈው የወጣትነት ዕድሜ ላይ ከደረሱ በኋላም እንኳ በባሕርያቸውና በዝንባሌያቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት ወላጆቻቸው ናቸው።” አክለውም “በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻችሁ የምትናገሩትን ነገር የማይቀበሉበት ወይም በሐሳባችሁ የማይስማሙበት ጊዜ ቢኖርም ለእናንተ አመለካከት ከፍ ያለ ግምት ይሰጣሉ፤ እንዲሁም የምትናገሩትን ነገር ያዳምጣሉ” ብለዋል።

ልጆቻችሁ መመሪያ ለማግኘት ወደ እናንተ ዞር የማለት ተፈጥሯዊ ዝንባሌ ስላላቸው ይህን አጋጣሚ በሚገባ ተጠቀሙበት። ከልጆቻችሁ ጋር ጊዜ አሳልፉ፤ እንዲሁም አመለካከታችሁን፣ እሴቶቻችሁንና ተሞክሯችሁን አካፍሏቸው።

 ልጃችሁ አርዓያ የሚሆነው ሰው እንዲያገኝ እርዱት።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ከጥበበኞች ጋር የሚሄድ ጥበበኛ ይሆናል።”—ምሳሌ 13:20

ከምታውቋቸው ሰዎች መካከል በጉርምስና ዕድሜ ላይ ለሚገኝ ልጃችሁ ጥሩ አርዓያ የሚሆን አዋቂ አለ? ታዲያ ይህ ግለሰብ ከልጃችሁ ጋር ጊዜ እንዲያሳልፍ ለምን አታደርጉም? እርግጥ ነው፣ የወላጅነት ኃላፊነታችሁን አሳልፋችሁ ትሰጣላችሁ ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ እምነት የምትጥሉበትና በልጃችሁ ላይ ምንም ጉዳት እንደማያደርስ እርግጠኛ የሆናችሁት ሰው የሚሰጠው ድጋፍ ለልጃችሁ የምትሰጡትን ሥልጠና ለማጎልበት ይረዳችኋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው ጢሞቴዎስ፣ አዋቂ ከሆነ በኋላም እንኳ ከጳውሎስ ጋር ጊዜ በማሳለፉ ብዙ ጥቅም አግኝቷል፤ ጳውሎስም ቢሆን ከጢሞቴዎስ ጋር ወዳጅነት በመመሥረቱ ተጠቅሟል።—ፊልጵስዩስ 2:20, 22

በዛሬው ጊዜ ዘመድ አዝማድ ልክ እንደ ድሮው አንድ አካባቢ ላይ ተሰባስቦ አይኖርም፤ አያቶች፣ አጎቶች፣ አክስቶችና ሌሎች ዘመዶች የሚኖሩት በተለያየ የዓለም ክፍል ውስጥ ሊሆን ይችላል። የእናንተም ቤተሰብ ሁኔታ እንደዚህ ከሆነ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻችሁ ጥሩ አርዓያ ከሚሆኗቸው አዋቂዎች መማር የሚችሉበት አጋጣሚ እንዲያገኙ አድርጉ።

^ አን.9 ጥናቱ እንደሚያሳየው በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች በየቀኑ በአማካይ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ያህል ጊዜ የሚያሳልፉት የመዝናኛ ሚዲያ በመጠቀም ነው። አነስ ያለ ዕድሜ ስላላቸው ልጆችም ሆነ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ስለሚገኙት ወጣቶች የሚገልጸው አኃዛዊ መረጃ፣ ልጆቹ በትምህርት ቤት ሳሉ ወይም የቤት ሥራ ሲሠሩ ኢንተርኔት በመጠቀም የሚያሳልፉትን ጊዜ አይጨምርም።