በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 4

ኃላፊነት የሚሰማው መሆን

ኃላፊነት የሚሰማው መሆን

ኃላፊነት የሚሰማው መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች እምነት የሚጣልባቸው ናቸው። የተሰጣቸውን ሥራ በጥሩ ሁኔታና በተመደበላቸው ጊዜ ውስጥ ሠርተው ያጠናቅቃሉ።

ሕፃናትም እንኳ አቅማቸው ውስን ቢሆንም ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ መሠልጠን ይችላሉ። ፓረንቲንግ ዊዝአውት ቦርደርስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ሕፃን አሥራ አምስት ወር ሲሞላው፣ አድርግ የተባለውን ነገር ማድረግ የሚጀምር ሲሆን አሥራ ስምንት ወር ሲሞላው ደግሞ ሌሎች የሚያደርጉትን ነገር እያየ ማድረግ ይጀምራል።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “በብዙ ባሕሎች ወላጆች ልጆቻቸው በተለይ ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት ዕድሜ ላይ ሲደርሱ አንዳንድ የቤት ውስጥ ሥራዎችን በመሥራት እንዲያግዟቸው ያደርጋሉ፤ በዚህ ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆችም እንኳ ብዙ የቤት ውስጥ ሥራዎችን አብረው በመሥራት ወላጆቻቸውን ማገዝ ይችላሉ።”

ኃላፊነት የሚሰማው ሰው መሆን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

በርካታ ወጣቶች ራሳቸውን ችለው ከቤት ከወጡ በኋላ ኑሮ ስለሚከብዳቸው ወደ እናታቸውና ወደ አባታቸው ይመለሳሉ። ይህ የሚሆንበት አንዱ ምክንያት ልጆቹ ስለ ገንዘብ አያያዝ፣ ስለ ቤት አያያዝ ወይም የዕለት ተዕለት ኃላፊነቶችን መወጣት ስለሚቻልበት መንገድ ምንም ሥልጠና ስላላገኙ ነው።

ስለዚህ ልጆቻችሁ አዋቂ ሲሆኑ ለሚጠብቃቸው ኃላፊነት ከወዲሁ ብታሠለጥኗቸው ጥሩ ነው። ሃው ቱ ሬይዝ አን አዳልት የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል፦ “ከቤት የሚወጡበት ዕድሜ ላይ እስኪደርሱ ድረስ በጫንቃችሁ ላይ ተሸክማችሁ ካቆያችኋቸው በኋላ ልክ አሥራ ስምንት ዓመት ሲሞላቸው ወደ ውጭው ዓለም አውጥታችሁ ልትጥሏቸው እንደማትፈልጉ የተረጋገጠ ነው።”

ልጆች ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ ማስተማር የሚቻለው እንዴት ነው?

የቤት ውስጥ ሥራ ስጧቸው።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “በትጋት ያከናወኑት ነገር ሁሉ ጥቅም ያስገኛል።”—ምሳሌ 14:23

ትናንሽ ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር አብረው መሥራት ያስደስታቸዋል። እንግዲያው ለልጆቻችሁ የቤት ውስጥ ሥራዎችን በመስጠት ልጆች ያላቸውን ይህን ተፈጥሯዊ ፍላጎት በሚገባ ተጠቀሙበት።

አንዳንድ ወላጆች ግን እንዲህ ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። ልጆቹ በትምህርት ቤት በየቀኑ ብዙ የቤት ሥራ ስለሚሰጣቸው ሌላ ሸክም ሊጨምሩባቸው አይፈልጉም።

ይሁን እንጂ ቤት ውስጥ የሚሠሩ ልጆች፣ የተሰጣቸውን ሥራ መቀበልንና ሠርቶ ማጠናቀቅን ስለሚማሩ በትምህርት ቤትም ስኬታማ የመሆን አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው። ከዚህም በላይ ፓረንቲንግ ዊዝአውት ቦርደርስ የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚገልጸው “ልጆቻችን ገና ትናንሾች እያሉ የሚኖራቸውን የመርዳት ጉጉት ችላ የምንለው ከሆነ ልጆቹ ሌሎችን ማገዝ አስፈላጊ እንዳልሆነ ሊጀምሩ ይችላሉ። . . . በተጨማሪም ሁሌም ሌሎች እንዲያደርጉላቸው መጠበቅ ይጀምራሉ።”

መጽሐፉ ላይ የተጠቀሰው ሐሳብ እንደሚያመለክተው ልጆች የቤት ውስጥ ሥራዎችን መሥራታቸው ተቀባይ ከመሆን ይልቅ ሰጪ፣ ተረጂ ከመሆን ይልቅ ሌሎችን የሚረዱ እንዲሆኑ ያሠለጥናቸዋል። የቤት ውስጥ ሥራዎች፣ ልጆች በቤተሰቡ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዳላቸውና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ኃላፊነት እንዳለባቸው እንዲገነዘቡ ይረዳሉ።

ልጆቻችሁ ላጠፉት ጥፋት ኃላፊነት እንዲወስዱ አድርጉ።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የኋላ ኋላ ጥበበኛ እንድትሆን ምክርን ስማ፤ ተግሣጽንም ተቀበል።”—ምሳሌ 19:20

ልጃችሁ ጥፋት ቢያጠፋ፣ ለምሳሌ ሳያስበው የሌላን ሰው ንብረት ቢያበላሽ ጥፋቱን ልትሸፋፍኑለት አትሞክሩ። ከዚህ ይልቅ ይቅርታ እንዲጠይቅ አልፎ ተርፎም የማካካሻ እርምጃ እንዲወስድ አድርጉ። ልጆች ድርጊታቸው ያስከተለውን መዘዝ እንዲቀበሉ ማድረግ ስህተት አይደለም።

ልጆች ጥፋታቸውን አምነው የሚቀበሉና ለድርጊታቸው ኃላፊነት የሚወስዱ ከሆነ የሚከተሉትን ነገሮች ይማራሉ፦

  • ሐቀኛ መሆንን

  • ጥፋትን በሌሎች ላይ ከማላከክ መቆጠብን

  • ሰበብ አስባብ ከመደርደር መራቅን

  • አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ይቅርታ መጠየቅን