በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 2

ትሕትና

ትሕትና

ትሕትና ምንድን ነው?

ትሑት ሰዎች ለሌሎች አክብሮት አላቸው። ትዕቢተኞች አይደሉም፤ እንዲሁም ሰዎች ለየት ባለ መንገድ እንዲይዟቸው አይጠብቁም። ከዚህ ይልቅ ለሌሎች ልባዊ አሳቢነት የሚያሳዩ ከመሆኑም ሌላ ከእነሱ ለመማር ፈቃደኞች ናቸው።

አንዳንድ ጊዜ ትሕትና የድክመት ምልክት ተደርጎ ይታያል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ትሕትና የጥንካሬ መገለጫ ነው። ትሑት ሰዎች ደካማ ጎናቸውን ያውቃሉ፤ እንዲሁም የአቅም ገደብ እንዳለባቸው አምነው ይቀበላሉ።

ትሕትና አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

 • ትሕትና ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት ለመመሥረት ይረዳል። ዘ ናርሲሲዝም ኤፒደሚክ የተባለው መጽሐፍ “በጥቅሉ ሲታይ ትሑት ሰዎች በቀላሉ ከሌሎች ጋር ወዳጅነት መመሥረት ይችላሉ” በማለት ገልጿል። አክሎም እንዲህ ያሉ ሰዎች “ከሌሎች ጋር መነጋገርና መግባባት አይከብዳቸውም” ብሏል።

 • ትሕትና ለልጃችሁ የወደፊት ሕይወት ጠቃሚ ነው። ልጃችሁ ትሕትናን ማዳበሩ ለአሁኑም ሆነ ለወደፊት ሕይወቱ ይጠቅመዋል። ለምሳሌ ወደፊት ሥራ ለመቀጠር ሲሞክር ይህ ባሕርይ በጣም ይረዳዋል። ዶክተር ሌነርድ ሳክስ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ስለ ደካማ ጎኗ የማታውቅና ለራሷ የተጋነነ አመለካከት ያላት ወጣት በሥራ ቃለ መጠይቆች ላይ ጥሩ ውጤት የማግኘት አጋጣሚዋ ጠባብ ነው።” አክለውም “ቀጣሪዋ ምን እንደሚፈልግ የማወቅ ልባዊ ፍላጎት ያላት ወጣት ግን ሥራውን የማግኘት አጋጣሚዋ ሰፊ ነው” ብለዋል። *

ልጆች ትሑት እንዲሆኑ ማስተማር የሚቻለው እንዴት ነው?

ልጃችሁ ለራሱ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረው እርዱት።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “አንድ ሰው ምንም ሳይሆን ራሱን ከፍ አድርጎ የሚመለከት ከሆነ ራሱን እያታለለ ነው።”—ገላትያ 6:3

 • ከእውነታው የራቁ ሐሳቦችን ከመናገር ተቆጠቡ። “ያሰብከው ሁሉ ይሳካልሃል” ወይም “መሆን የምትፈልገውን ሁሉ ከመሆን የሚያግድህ ምንም ነገር የለም” እንደሚሉት ያሉ አነጋገሮች የሚያበረታቱ ይመስሉ ይሆናል፤ ብዙውን ጊዜ ግን በገሃዱ ዓለም ውስጥ ያለው ሁኔታ ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። ልጃችሁ ይበልጥ ስኬታማ የሚሆነው ሊደረስባቸው የሚችሉ ግቦች ካሉትና እነዚህ ግቦች ላይ ለመድረስ ጠንክሮ የሚሠራ ከሆነ ነው።

 • ያደረገውን ነገር ለይታችሁ በመጥቀስ አመስግኑት። ልጃችሁን እንዲሁ በደፈናው “ጎበዝ” ማለታችሁ ልጁ ትሕትና እንዲያዳብር አይረዳውም። ስለዚህ ያደነቃችሁለትን ነገር ለይታችሁ ጥቀሱለት።

 • በማኅበራዊ ድረ ገጽ አጠቃቀሙ ላይ ገደብ አበጁ። ብዙውን ጊዜ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ሰዎች ስለ ተሰጥኦዎቻቸውና ስላከናወኗቸው ነገሮች ለሌሎች እንዲያሳውቁና ወደ ራሳቸው ትኩረት እንዲስቡ ያደርጋሉ፤ ይህ ደግሞ የትሕትና ፍጹም ተቃራኒ ነው።

 • ለጥፋቱ ቶሎ ይቅርታ እንዲጠይቅ አድርጉ። ልጃችሁ ጥፋቱ ምን እንደሆነ እንዲገባውና ጥፋቱን አምኖ እንዲቀበል እርዱት።

ልጃችሁ አድናቂ እንዲሆን አበረታቱት።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “አመስጋኝ መሆናችሁን አሳዩ።”—ቆላስይስ 3:15

 • ተፈጥሮን ማድነቅ። ልጆች ለተፈጥሮ አድናቆት ሊኖራቸውና ሕልውናችን ምን ያህል በዚያ ላይ የተመካ እንደሆነ ሊገነዘቡ ይገባል። በሕይወት ለመኖር የምንተነፍሰው አየር፣ የምንጠጣው ውኃና የምንበላው ምግብ ያስፈልገናል። እነዚህን ነገሮች እንደ ምሳሌ አድርጋችሁ በመጠቀም ልጃችሁ በተፈጥሮ ላይ ለሚታዩት አስገራሚ ነገሮች አድናቆት እንዲያዳብር እርዱት።

 • ሰዎችን ማድነቅ። ልጃችሁ ሁሉም ሰው በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ከእሱ እንደሚበልጥ እንዲሁም ሌሎች ባላቸው ሙያና ችሎታ ከመቅናት ይልቅ ከእነሱ ለመማር ጥረት ማድረግ እንዳለበት እንዲገነዘብ እርዱት።

 • አድናቆትን መግለጽ። ልጃችሁ እንዲሁ ለአፉ ብቻ ሳይሆን ከልቡ አድናቆቱን እንዲገልጽ አበረታቱት። አድናቂነት፣ ትሕትና የሚገነባበት አንዱ ጥሬ ዕቃ እንደሆነ ይነገራል።

ለሌሎች መልካም ማድረግ ጠቃሚ ነገር እንደሆነ ለልጃችሁ አስተምሩት።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ . . . ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።”—ፊልጵስዩስ 2:3, 4

 • ልጃችሁ የቤት ውስጥ ሥራዎችን እንዲሠራ አድርጉ። ልጃችሁ የቤት ውስጥ ሥራዎችን እንዳይሠራ ማድረግ ‘ይህ ሥራ ለአንተ አይመጥንም!’ የሚል መልእክት ሊያስተላልፍ ይችላል። የቤት ውስጥ ኃላፊነቶችን መወጣት ከጨዋታ በፊት መቅደም አለበት። ልጃችሁ የቤት ውስጥ ሥራዎችን መሥራቱ ሌሎችን እንዴት እንደሚጠቅም እንዲሁም ይህን በማድረጉ ሌሎች ምን ያህል እንደሚያደንቁትና እንደሚያከብሩት ግለጹለት።

 • ለሌሎች መልካም ማድረግ ትልቅ መብት እንደሆነ በሚገባ አስረዱት። ሌሎችን የሚጠቅሙ ተግባሮችን ማከናወን ልጆች ብስለት እንዲያዳብሩ የሚረዳ ወሳኝ መንገድ ነው። በመሆኑም ልጃችሁ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው እነማን እንደሆኑ ለማስተዋል ጥረት እንዲያደርግ አበረታቱት። እነሱን ለመርዳት ምን ማድረግ እንደሚችል ተወያዩ። ደግሞም እንዲህ ያሉ ነገሮችን ሲያከናውን አመስግኑት እንዲሁም አስፈላጊውን ድጋፍ አድርጉለት።

^ አን.8 ዘ ኮላፕስ ኦቭ ፓረንቲንግ ከተባለው መጽሐፍ ላይ የተወሰደ።