በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 1

ራስን መግዛት

ራስን መግዛት

ራስን መግዛት ምንድን ነው?

ራስን መግዛት የሚከተሉትን ነገሮች የማድረግ ችሎታን ያካትታል፦

  • የፈለጉትን ነገር እስኪያገኙ ድረስ በትዕግሥት የመጠበቅ

  • ውስጣዊ ግፊቶችን የመግታት

  • አንድን ሥራ ባይወዱትም እንኳ አጠናቆ የመሥራት

  • ከራስ ይልቅ ሌሎችን የማስቀደም

ራስን መግዛት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ራሳቸውን መግዛት የሚችሉ ልጆች፣ ጊዜያዊ ደስታ የሚያስገኙላቸው ቢመስሉም እንኳ አጓጊ ሁኔታዎችን ተቋቁመው ማለፍ ይችላሉ። በአንጻሩ ደግሞ ራሳቸውን መግዛት የሚያቅታቸው ልጆች

  • ብስጩ የመሆን

  • በመንፈስ ጭንቀት የመያዝ

  • የሲጋራ፣ የዕፅ ወይም የአልኮል መጠጥ ሱሰኛ የመሆን እንዲሁም

  • መጥፎ የአመጋገብ ልማድ የመከተል አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው።

አንድ ጥናት እንዳረጋገጠው ራሳቸውን የሚገዙ ልጆች አዋቂ ከሆኑ በኋላ ለጤና ችግሮች የመጋለጥ፣ ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ውጥረት ውስጥ የመግባትና ሕግ ጥሰው ችግር ላይ የመውደቅ አጋጣሚያቸው አነስተኛ ነው። የፔንስልቬንያ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት አንጄላ ደክዎርዝ ከዚህ ጥናት በመነሳት “ራስን መግዛት መቼም ቢሆን ‘በዛ’ ሊባል የሚችል ባሕርይ አይደለም” የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።

ልጆች ራሳቸውን የሚገዙ እንዲሆኑ ማስተማር የሚቻለው እንዴት ነው?

‘አይሆንም’ ማለትን ልመዱ፤ ደግሞም በአቋማችሁ ጽኑ።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ቃላችሁ ‘አዎ’ ከሆነ አዎ ይሁን፤ ‘አይደለም’ ከሆነ አይደለም ይሁን።”—ማቴዎስ 5:37

ትናንሽ ልጆች አንድ ነገር ሲከለከሉ በመነጫነጭ ወይም በማልቀስ የወላጆቻቸውን ሐሳብ ለማስቀየር ይሞክሩ ይሆናል፤ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ እንዲህ የሚያደርጉት በሰው ፊት ሊሆን ይችላል። ወላጆች በዚህ የሚሸነፉ ከሆነ ልጁ መነጫነጭ ወይም ማልቀስ የወላጆችን አቋም ለማስቀየር የሚያስችል ውጤታማ ዘዴ እንደሆነ ሊሰማው ይችላል።

በሌላ በኩል ግን ወላጆች ‘አይሆንም’ ካሉ በኋላ በአቋማቸው የሚጸኑ ከሆነ ልጁ አንድ መሠረታዊ የሕይወት እውነታ ማለትም የፈለጉትን ነገር ሁልጊዜ ማግኘት እንደማይቻል ይማራል። “የሚገርመው፣ ይህን ሐቅ የተገነዘቡ ሰዎች በጣም ደስተኞች እንደሆኑ መመልከት ተችሏል” በማለት ዶክተር ዴቪድ ዎልሽ ጽፈዋል። አክለውም “ዓለም ሁልጊዜ እነሱ የፈለጉትን ነገር በብር ሳህን ላይ አድርጎ እንደሚያቀርብላቸው ለልጆቻችን ማስተማራችን አይጠቅማቸውም” ብለዋል። *

ልጃችሁ ‘አይሆንም’ መባልን ከወዲሁ ከተማረ ወደፊት አንዳንድ ፈተናዎች ሲቀርቡለት ለምሳሌ ዕፅ እንዲወስድ፣ ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት እንዲፈጽም ወይም ሌሎች መጥፎ ነገሮች እንዲያደርግ ሲፈተን ‘አይሆንም’ ማለት ቀላል ይሆንለታል።

ልጃችሁ ድርጊቱ፣ ጥሩም ሆነ መጥፎ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል እንዲገነዘብ እርዱት።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል።”—ገላትያ 6:7

ልጃችሁ ማንኛውም ድርጊት የሆነ ውጤት እንደሚያስከትልና ራስን አለመግዛትም መጥፎ መዘዝ ማስከተሉ እንደማይቀር ሊገነዘብ ይገባል። ለምሳሌ ያህል፣ በሚበሳጭበት ጊዜ መቆጣት የሚቀናው ከሆነ ሌሎች ሊርቁት ይችላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የሚያበሳጭ ነገር ሲያጋጥመው ራሱን የሚገዛ ከሆነ ወይም ሌላ ሰው ሲናገር ጣልቃ ገብቶ ከመናገር ይልቅ በትዕግሥት የሚጠብቅ ከሆነ ሰዎች ይቀርቡታል። ልጃችሁ ራሱን ለመግታት ጥረት ማድረጉ ብዙ ጥቅም ሊያስገኝለት እንደሚችል እንዲገነዘብ እርዱት።

ልጃችሁ ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑት ነገሮች ቅድሚያ መስጠትን እንዲማር እርዱት።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።”—ፊልጵስዩስ 1:10

ራስን መግዛት መጥፎ ነገር ከማድረግ መቆጠብን ብቻ ሳይሆን እምብዛም የማያስደስቱ አስፈላጊ ነገሮችን ማድረግንም ይጨምራል። ልጃችሁ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን መለየትን እንዲሁም እነዚያን ነገሮች ማድረግን መማር ይኖርበታል። በመሆኑም አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች በቅድሚያ እንዲሠራ አድርጉ። ለምሳሌ ያህል፣ ወደ ጨዋታ ከመሄዱ በፊት የቤት ሥራውን ሠርቶ እንዲጨርስ ንገሩት።

ጥሩ አርዓያ ሁኑ።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እኔ እንዳደረግኩላችሁ እናንተም እንደዚሁ እንድታደርጉ አርዓያ ሆኜላችኋለሁ።”—ዮሐንስ 13:15

ደስ የማይል ወይም የሚያበሳጭ ሁኔታ ሲያጋጥማችሁ የምትሰጡትን ምላሽ ልጃችሁ መመልከቱ አይቀርም። ስለዚህ ራስን መግዛት የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝ አርዓያ በመሆን አሳዩት። ለምሳሌ ያህል፣ ልጃችሁ ትዕግሥታችሁን የሚፈታተን ነገር በሚያደርግበት ጊዜ በቁጣ ቱግ ትላላችሁ ወይስ ጉዳዩን በረጋ መንፈስ ለመያዝ ጥረት ታደርጋላችሁ?

^ አን.20 ኖ፦ ዋይ ኪድስ ኦቭ ኦል ኤጅስ ኒድ ቱ ሂር ኢት ኤንድ ዌይስ ፓረንትስ ካን ሴይ ኢት ከተባለው መጽሐፍ ላይ የተወሰደ።