በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የበሽታ ምልክቶችን ማስታገሥ ብቻ ፈውስ አያመጣም፤ የበሽታውን መንስኤ አውቆ ማከም ያስፈልጋል

ተፈታታኙ ነገር

የችግሮቹን መንስኤ ማወቅ

የችግሮቹን መንስኤ ማወቅ

የሰው ልጅ፣ ሰላማዊና ከስጋት ነፃ የሆነ ሕይወት እንዳንመራ እንቅፋት የሆኑብንን በርካታ ችግሮች መፍታት ይችላል ብለህ ታምናለህ? ለችግሮቻችን ሁነኛ መፍትሔ ለማምጣት ከተፈለገ የችግሮቹን መንስኤ ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል።

ይህን በምሳሌ ለማስረዳት፣ ቶም የተባለ ሰው ያጋጠመውን ሁኔታ እንመልከት። ቶም በጠና ታምሞ የነበረ ሲሆን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሕይወቱ አለፈ። ቶምን ለሞት ያደረሰው ነገር ምንድን ነው? ቶም በታከመበት ሆስፒታል ውስጥ የሚሠራ አንድ ሐኪም “የሕመሙ ምልክቶች በታዩበት ወቅት መንስኤውን ለማወቅ ጥረት ያደረገ ሰው አልነበረም” በማለት ጽፏል። ቶም ወደዚህ ሆስፒታል ከመምጣቱ በፊት ያከሙት ሰዎች የበሽታው መንስኤ ምን እንደሆነ ሳይታወቅ፣ እንዲሁ ሕመሙን የሚያስታግሥ መድኃኒት ሳይሰጡት አልቀሩም።

በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎች የዓለምን ችግሮች ለመፍታት ተመሳሳይ አካሄድ እየተከተሉ ይሆን? ለምሳሌ ያህል፣ መንግሥታት ወንጀልን ለመከላከል ሲሉ ሕግ ያወጣሉ እንዲሁም ለክትትል የሚረዱ የቪዲዮ መሣሪያዎችን ይተክላሉ፤ አልፎ ተርፎም የፖሊስ ኃይላቸውን ያጠናክራሉ። እነዚህ እርምጃዎች በተወሰነ ደረጃ ውጤታማ ቢሆኑም የችግሩን መንስኤ የሚያስወግዱ አይደሉም። ደግሞም አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች አንድ ነገር እንዲያደርጉ የሚያነሳሳቸው በውስጣቸው ያለው ዝንባሌ፣ አስተሳሰብና ፍላጎት ነው።

በደቡብ አሜሪካ በምትገኝ የኢኮኖሚ ቀውስ በገጠማት አገር ውስጥ የሚኖር ዳንኤል የተባለ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “በአንድ ወቅት ጥሩ ኑሮ እንኖር ነበር። የጦር መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች ሊዘርፉን ይችላሉ የሚል ስጋትም አልነበረንም። አሁን ግን ከስጋት ነፃ የሆነ አንድም ከተማ ወይም መንደር የለም። በኢኮኖሚ ቀውሱ ሳቢያ የሰዎች እውነተኛ ማንነት በግልጽ ታይቷል፤ ሰዎች ስግብግቦች እና ለሌሎች ሕይወትም ሆነ ንብረት አክብሮት የሌላቸው ሆነዋል።”

በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ባለው ጦርነት የተነሳ መኖሪያውን ትቶ የተሰደደው ኢላያስ * ከጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ተወልጄ ባደግኩበት ከተማ የነበሩ ብዙ ወጣቶች በጦርነቱ እንዲካፈሉና እንደ ጀግኖች እንዲቆጠሩ ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም የፖለቲካውና የሃይማኖቱ ሥርዓት ግፊት ያሳድርባቸው ነበር። በተቃራኒው ጎራ ያሉትም ተመሳሳይ ግፊት ይደረግባቸው ነበር! ይህም በሰብዓዊ መሪዎች ላይ መታመን ምን ያህል ከንቱ እንደሆነ እንድገነዘብ አድርጎኛል።”

መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በተመለከተ እንዲህ ይላል፦

  • “የሰው የልብ ዝንባሌ ከልጅነቱ ጀምሮ መጥፎ ነው።”—ዘፍጥረት 8:21

  • “ልብ ከምንም ነገር በላይ ከዳተኛ ነው፤ ማንኛውንም ነገር ከማድረግ አይመለስም። ማንስ ሊያውቀው ይችላል?”—ኤርምያስ 17:9

  • “ከልብ ክፉ ሐሳብ፣ ግድያ፣ . . . የፆታ ብልግና፣ ሌብነት፣ በሐሰት መመሥከርና ስድብ ይወጣሉ።”—ማቴዎስ 15:19

የሰው ልጅ በውስጡ ያሉትን መጥፎ ባሕርያት ለማስወገድ ያደረገው ጥረት አልተሳካም። እንዲያውም ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው የሰዎች ክፋት እየተባባሰ ያለ ይመስላል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) የሚያስገርመው ደግሞ ይህ የሆነው ሰዎች ከፍተኛ እውቀት ባካበቱበትና ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ከሌሎች ጋር የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ የሚቻልባቸው ብዙ መንገዶች ባሉበት በዛሬው ጊዜ መሆኑ ነው! ታዲያ ዓለማችንን ከስጋት ነፃ ማድረግ ያልቻልነው ለምንድን ነው? ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር ስለሆነ ነው? ወይስ ጨርሶ የማይቻል ነገር ስለሆነ ነው?

ጨርሶ የማይቻል ነገር ለማድረግ እየሞከርን ነው?

ሰዎች ያሏቸውን መጥፎ ባሕርያት በሆነ ተአምር ማስወገድ ብንችል እንኳ ዓለማችንን ከስጋት ነፃ ማድረግ አንችልም። ለምን? ምክንያቱም ይህ ከሰው አቅም በላይ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው መንገድ በራሱ እጅ [አይደለም]። . . . አካሄዱን እንኳ በራሱ አቃንቶ መምራት አይችልም” ሲል በግልጽ ይናገራል። (ኤርምያስ 10:23) በእርግጥም ራሳችንን የመምራት ችሎታ አልተሰጠንም። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ በውኃ ውስጥ አሊያም በጠፈር ላይ እንድንኖር እንዳልተፈጠርን ሁሉ ሰዎችን እንድንገዛ ተደርገንም አልተፈጠርንም!

በውኃ ውስጥ እንድንኖር እንዳልተፈጠርን ሁሉ ሰዎችን እንድንገዛ ተደርገንም አልተፈጠርንም

በአጠቃላይ ሲታይ ሰዎች እንዴት መኖር ወይም በየትኞቹ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መመራት እንዳለባቸው ሌሎች ሰዎች ሲነግሯቸው ደስ አይላቸውም። በተጨማሪም ፅንስ ከማቋረጥ፣ ልጆቻቸውን ከመቅጣት ወይም እንዲህ ካሉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ምን ሊያደርጉ እንደሚገባ ሌሎች እንዲወስኑላቸው አይፈልጉም። እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ብዙውን ጊዜ በሰዎች መካከል ውዝግብ ይፈጥራሉ። ስለሆነም ትሕትና የሚጠይቅ ቢሆንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ የተሻለ እንደሆነ ምንም አያጠያይቅም። ሰው፣ ሰውን የመግዛት ችሎታውም ሆነ መብቱ የለውም። ታዲያ በዚህ ረገድ እርዳታ ማግኘት የምንችለው ከየት ነው?

ከሁሉ የተሻለ እርዳታ ማግኘት የምንችለው ከአምላክ ነው፤ ምክንያቱም የፈጠረን እሱ ነው! ደግሞም አንዳንዶች እንደሚያስቡት፣ አምላክ እኛን አልረሳንም። እንደ እውነቱ ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጥበብ ያዘለ ሐሳብ አምላክ እንደሚያስብልን በግልጽ ያሳያል። ይህን በዓይነቱ ልዩ የሆነ መጽሐፍ ስናጠና ስለ ራሳችን የተሻለ ግንዛቤ ይኖረናል። እንዲሁም የሰው ዘር ታሪክ እጅግ አሳዛኝ የሆነው ለምን እንደሆነ መረዳት እንችላለን። አንድ ጀርመናዊ ፈላስፋ በአንድ ወቅት እንደገለጹት ‘ሰዎችም ሆኑ መንግሥታት ከታሪክ ፈጽሞ ሊማሩ’ ያልቻሉት ለምን እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጥበብ ይጠብቀናል!

በአንድ ወቅት ኢየሱስ “ጥበብ ጻድቅ መሆኗ በልጆቿ ሁሉ [ወይም “በውጤቷ፣”] ተረጋግጧል” ብሎ ነበር። (ሉቃስ 7:35 ግርጌ) ጥበብ ከሚንጸባረቅባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች አንዱ በኢሳይያስ 2:22 ላይ የሚገኘው ነው፤ ጥቅሱ “ለራሳችሁ ስትሉ፣ ከአፍንጫው እንደሚወጣ እስትንፋስ በሆነ ሰው አትታመኑ” ይላል። ይህ ጥሩ ምክር ከሐሰት ተስፋዎችና ሊፈጸሙ የማይችሉ ነገሮችን በጉጉት ከመጠበቅ ያድነናል። በዓመፅ ስትታመስ በነበረች አንዲት የሰሜን አሜሪካ ከተማ የሚኖረው ኬነት እንዲህ ብሏል፦ “የተለያዩ የፖለቲካ ሰዎች ሥልጣን በያዙ ቁጥር ሁኔታዎችን እንደሚያስተካክሉ ቃል ይገባሉ፤ ሆኖም የገቡትን ቃል መጠበቅ አይችሉም። ይህም፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር ምንጊዜም ትክክልና ጥበብ ያዘለ እንደሆነ ያረጋግጣል።”

ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዳንኤል የሚከተለውን ጽፏል፦ “በየዕለቱ የሚፈጸመው ነገር ሰዎች በጥሩ ሁኔታ ማስተዳደር እንደማይችሉ ይበልጥ እንዳምን ያደርገኛል። . . . ባንክ ውስጥ ገንዘብ ማጠራቀማችሁ ወይም ራሳችሁን ለመደገፍ የሚያስችል የገቢ ምንጭ ያላችሁ መሆኑ ከስጋት ነፃ የሆነ ሕይወት እንደምትመሩ ዋስትና አይሆንም። ሰዎች፣ ነገሮች እንዳሰቧቸው ባለመሆናቸው ለብስጭት ሲዳረጉ ተመልክቻለሁ።”

መጽሐፍ ቅዱስ ሊፈጸሙ የማይችሉ ነገሮችን ተስፋ ከማድረግ እንድንጠበቅ የሚረዳን ከመሆኑም ሌላ እውነተኛ ተስፋም ይሰጠናል። የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ያብራራል።

^ ስሙ ተቀይሯል።