በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአሁኑ ጊዜ ያሉ ችግሮች የተሟላ መፍትሔ የሚያገኙት እንዴት ነው?

በአምላክ መንግሥት ግዛት ውስጥ “ሰላም ይበዛል”

በአምላክ መንግሥት ግዛት ውስጥ “ሰላም ይበዛል”

ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የኖረው የአምላክ መንግሥት፣ ይኸውም በአምላክ የተቋቋመው ዓለም አቀፍ መስተዳድር በቅርቡ በምድር ላይ ሰላምና ስምምነት እንዲሰፍን ያደርጋል። በመዝሙር 72:7 ላይ ቃል እንደተገባው በዚያን ወቅት “ሰላም ይበዛል።” ይሁን እንጂ የአምላክ መንግሥት መላዋን ምድር መግዛት የሚጀምረው መቼ ነው? የሚገዛውስ እንዴት ነው? አንተስ የአምላክ መንግሥት የሚያመጣቸውን በረከቶች ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

የአምላክ መንግሥት የሚመጣው መቼ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ መንግሥት በቅርቡ እንደሚመጣ የሚጠቁሙ በርካታ አስደናቂ ክንውኖችን ተንብዮአል። ዓለም አቀፍ ጦርነት፣ ረሃብ፣ በሽታ እና በርካታ የምድር ነውጦች እንዲሁም ክፋት እየበዛ መሄዱ የመጨረሻው ዘመን “ምልክት” ገጽታዎች ናቸው።—ማቴዎስ 24:3, 7, 12፤ ሉቃስ 21:11፤ ራእይ 6:2-8

ሌላው ትንቢት ደግሞ እንዲህ ይላል፦ “በመጨረሻዎቹ ቀናት ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን [ይመጣል]። ምክንያቱም ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ . . . ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ታማኝ ያልሆኑ፣ ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው፣ ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ፣ ስም አጥፊዎች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ፣ . . . በኩራት የተወጠሩ፣ ከአምላክ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:1-4) በየትኛውም ዘመን ቢሆን እነዚህን ባሕርያት የሚያንጸባርቁ አንዳንድ ሰዎች ነበሩ። በአሁኑ ጊዜ ግን እንዲህ ያሉትን ባሕርያት የሚያሳዩት አብዛኞቹ ሰዎች ናቸው።

እነዚህ ትንቢቶች መፈጸም የጀመሩት በ1914 ነው። በእርግጥም የታሪክ ምሁራን እና የፖለቲካ ሰዎች፣ ዓለም ከዚያ ዓመት ጀምሮ ምን ያህል እንደተለወጠ ደጋግመው ተናግረዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ፒተር ሙንክ የተባሉ አንድ ዴንማርካዊ የታሪክ ምሁር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “በ1914 ጦርነት በፈነዳ ጊዜ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ተከፈተ። ብሩህ የነበረው የእድገት ዘመን አክትሞ . . . የመከራ፣ የሽብርና የስጋት ዘመን ተተካ።”

በሌላ በኩል ሲታይ ግን ይህ ተስፋ የሚፈነጥቅ ነው። እነዚህ መጥፎ ነገሮች መከሰታቸው የአምላክ መንግሥት መላዋን ምድር የሚገዛበት ጊዜ እንደቀረበ ይጠቁማል። ይህ በእርግጥም ምሥራች ነው! ኢየሱስ ስለ ፍጻሜው ዘመን ሲናገር “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” ብሏል።—ማቴዎስ 24:14

ይህ ምሥራች የይሖዋ ምሥክሮች መልእክት ዋና ጭብጥ ነው። እንዲያውም የዋናው መጽሔታቸው ርዕስ የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ የሚል ነው። ይህ መጽሔት የአምላክ መንግሥት ለሰው ዘርና ለምድር የሚያመጣቸውን ግሩም በረከቶች አዘውትሮ ይገልጻል።

የአምላክ መንግሥት መላዋን ምድር መግዛት የሚጀምረው እንዴት ነው?

የዚህ ጥያቄ መልስ የሚከተሉትን አራት ወሳኝ እውነታዎች ያካተተ ነው፦

  1. የአምላክ መንግሥት ለውጥ የሚያመጣው በዚህ ዓለም ፖለቲካዊ መሪዎች ተጠቅሞ አይደለም።

  2. የዓለም ፖለቲካዊ መሪዎች ሥልጣናቸውን ላለመልቀቅ ሲሉ የአምላክን መንግሥት አገዛዝ በመቃወም ከንቱ ሙከራ ያደርጋሉ።—መዝሙር 2:2-9

  3. የአምላክ መንግሥት፣ የሰውን ዘር ሲገዙ የነበሩ ፖለቲካዊ መንግሥታትን ያጠፋቸዋል። (ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 19:17-21) ይህ የመጨረሻ ዓለም አቀፍ ጦርነት አርማጌዶን ተብሎ ይጠራል።—ራእይ 16:14, 16

  4. ለአምላክ መንግሥት በፈቃደኝነት የሚገዙ ሰዎች ሁሉ ከአርማጌዶን ጥፋት ተርፈው ሰላማዊ ወደሆነ አዲስ ዓለም ይገባሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ሰዎች “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ብሎ የሚጠራቸው ሲሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሊሆኑ ይችላሉ።—ራእይ 7:9, 10, 13, 14

የአምላክ መንግሥት የሚያመጣቸውን በረከቶች ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

የአምላክ መንግሥት ዜጋ ለመሆን የመጀመሪያው እርምጃ ትምህርት መቅሰም ነው። ኢየሱስ ለአምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ አለባቸው” ብሏል።—ዮሐንስ 17:3

ሰዎች ስለ ይሖዋ አምላክ ትክክለኛ እውቀት ሲቀስሙ በርካታ ጥቅሞች ያገኛሉ። ከእነዚህ ጥቅሞች መካከል ሁለቱን እንመልከት፦ አንደኛ፣ በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ያዳብራሉ። በጠንካራ ማስረጃ ላይ የተመሠረተው ይህ እምነት ደግሞ የአምላክ መንግሥት እውን እንደሆነና ምድርን የሚገዛበት ጊዜ እንደቀረበ እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል። (ዕብራውያን 11:1) ሁለተኛ፣ ለአምላክና ለሰዎች ያላቸው ፍቅር ያድጋል። ለአምላክ ያላቸው ፍቅር እሱን ከልባቸው እንዲታዘዙት ይገፋፋቸዋል። ለሰዎች ያላቸው ፍቅር ደግሞ ወርቃማው ሕግ ተብሎ የሚጠራውን ኢየሱስ የተናገረውን መመሪያ በሥራ ላይ እንዲያውሉ ያነሳሳቸዋል። ወርቃማው ሕግ “ልክ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ እንደምትፈልጉት ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው” ይላል።—ሉቃስ 6:31

ፈጣሪያችን አፍቃሪ አባት እንደመሆኑ መጠን የተሻለ ሕይወት ስንመራ ሲያይ ይደሰታል። አምላክ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ‘እውነተኛው ሕይወት’ በማለት የሚጠራውን ሕይወት እንድናገኝ ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 6:19) በአሁኑ ጊዜ የምንኖረው ሕይወት ‘እውነተኛው ሕይወት’ አይደለም። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት በመከራና በችግር የተሞላ ነው። ‘እውነተኛው ሕይወት’ ምን ሊመስል እንደሚችል ፍንጭ ለማግኘት፣ የአምላክ መንግሥት ለዜጎቹ ከሚያደርጋቸው ግሩም ነገሮች መካከል ጥቂቶቹን ተመልከት።

በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ሰዎች ከስጋት ነፃ ሆነው ይኖራሉ፤ የተትረፈረፈ ምግብም ይኖራቸዋል